ኢትዮጵያ ለዘመናት ስትፈተንባቸው ከቆየችባቸው የልማት ማነቆዎች ውስጥ የፕሮጀክቶች መጓተት አንዱና ዋነኛው ነው። ሀገሪቱ በፕሮጀክቶች መጓተት የምትታወቅና በርካታ የሕዝብ ሀብትም ለኪሳራ ሲዳረግባት የቆየች ሀገር ነች።
ይህ ደግሞ ከዝቅተኛ የስራ ባህልና ከፕሮጀክቶች የሥራ አመራር ክህሎት ማጣት ጋር የሚያያዝ ነው። በዋነኝነት የሥራ ባህላችን ዝቅተኛ መሆን የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ዓመታት እንዲፈጁና እንደሀገር የኢኮኖሚ ኪሳራ እንዲደርስብን ምክንያት ሆኗል። በተለይም ከመሠረተ ልማት ግንባታ ጋር በተያያዘ ብዙ መገለጫዎች ያሉት ነው። በደካማ የሥራ ባህልና በፕሮጀክቶች የአመራር ጥበብ ማነስ የተነሳ ተጀምረው የተጓተቱና ጭራሹንም መጨረስ ያልቻልናቸው ፕሮጀክቶች ተቆጥረው የሚያልቁ አይደሉም።
ተጀምረው ከተረሱት ውስጥ የስኳር ፋብሪካዎች፤ የማዳበርያ ፋብሪካ፤ የግብርና ማቀነባበሪያዎችና የመሳሰሉት እስካሁንም ተጀምረው የቀሩ ናቸው። በደካማ የሥራ ባህል የተነሳ በጾም በጸሎት የሚያልቁ ፕሮጀክቶችን ስናይ ደግሞ እንደሀገር የት እንደነበርን በቀላሉ መገንዘብ ያስችለናል። አብነት እንዲሆነን ጥቂቶቹን እንመልከት።
ቀደም ባለው ጊዜ አንድ ባለ 12 ወለል ህንጻ ለማጠናቀቅ እስከ 15 ዓመታ ይወስድ እንደነበረ የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ። ለአብነት መሃል ፒያሳ ላይ የሚገኘው በተለምዶ አራዳ ህንጻ ተብሎ የሚታወቀው ባለ 12 ወለል ህንጻ ከ15 ዓመታት በላይ ወስዷል። በደርግ ጊዜ ተጀምሮ በኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት የተጠናቀቀ ዓመታትን የፈጀ ህንጻ ነው።
የመንገድ ፕሮጀክቶችም ቢሆኑ አንዱ መገለጫቸው ከተያዘላቸው ጊዜ በላይ መፍጀታቸው ነው። ለአብነትም ከአቡነ ጴጥሮስ እስከ አስኮ ያለው መንገድ በሁለት ዓመታት ውስጥ ይጠናቃል ተብሎ ከአምስት ዓመታት በላይ መውሰዱ የሚታወቅ ነው።
በተመሳሳይም የኮተቤ አራራት መንገድ በግንባታ መዘግየት ብዙዎችን ሲያማርር ቆይቷል። መንገዱ በሁለት ዓመታት ውስጥ ይጠናቃቃል ቢባልም ከሰባት ዓመታት በላይ በመዘግየቱ መንግሥትን ለበርካታ ወጪ ህብረተሰቡን ደግሞ ለቅሬታ ዳርጓል።
በተጨማሪም በ2009ዓ.ም የተጀመረውም የቃሊቲ ማሳለጫ በሁለት አመት ተኩል ይጠናቀቃል ቢባልም አምስት አመታትን ወስዷል።
ከመንገድ ፕሮጀክቶች ወጣ ስንልም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመማርያና አስተዳደር ህንጻዎች በርካታ አመታትን በመፍጀት በፕሮጀክት መዘግየት የሚጠቀሱ ናቸው። በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚካሄዱ ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ ገደብ ውስጥ ባለመጠናቀቃቸው በመማር ማስተማሩ ሂደት ጥላ ከማጥላታቸውም በላይ ዩኒቨርሲቲውን ለተጨማሪ ወጪ የዳረጉ ናቸው።
ሌላው በግንባታ መዘግየት ተጠቃሽ የሆነው የጳውሎስ ሆስፒታል ማስፋፍያ ግንባታ ነው። ይህ ማስፋፍያ ግንባታ ከተጀመረ 10 ዓመታትን ሊያስቆጥር ጥቂት ጊዜያት ብቻ ይቀራሉ። የግንባታው መጓተትም ሆስፒታሉ ያለበትን የህክምና መስጫ ክፍሎች እጥረት ከማባባሱም ባሻገር ሆስፒታሉን ከፍተኛ ለሆነ ወጪ መዳረጉን የተወካዮች ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ማንሳቱ የሚታወስ ነው።
ግዙፉ የዓባይ ግድብም የፕሮጀክት መጓተት ሰለባ ከሆኑ ፕሮጀክቶች በግንባር ቀደምትነቱ የሚነሳ ነው። የዓባይ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ በአምስት አመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ በዕቅድ ቢያዝም 13 አመታትን አስቆጥሯል።
የዓባይ ግድብ በ 82 ቢሊዮን ብር ወጪ ለመገንባት ውል ቢገባም በነበረው እጅግ ደካማ የፕሮጀክት አስተዳደር ግድቡ ከመጓተትም አልፎ የህልውና አደጋ ገጥሞት ቆይቷል። ግድቡን ከገጠመው መሰናከልና የሞት አደጋ ለማዳን በርካታ ጥረቶች ተደርገው አሁን ከ95 በመቶ በላይ ማድረስ ተችሏል። ሆኖም ቀደም ሲል በተከሰተው የግንባታ መጓተት የግድቡ ግንባታ ከ13 ዓመት በላይ ከመውሰዱም በሻገር የግንባታ ወጪውን ከሶስት እጥፍ በላይ አሳድጎታል።
የኮይሻ ግድብም ቢሆን በአምስት አመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ግንባታው ቢጀመርም ዘንድሮ ስምንተኛ አመቱን ይዟል። ግድቡ በነበረበት ከፍተኛ የፋይናንስ እጥረትና ቀውስ ለወራት ቆሞ የነበረ ሲሆን ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ችግሩ ከመሰረቱ እንዲስተካከል በመደረጉ ግንባታው በመፋጠን ላይ ይገኛል።
እንደ አጠቃላይ ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከለውጡ በፊት በነበረው ብልሹ አሰራር ምክንያት በኢትዮጵያ የተለያዩ 102 ፕሮጀክቶች መጓተታቸው ምክንያትም 42 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ ጠይቀዋል።
የፕሮጀክቶች መጓተት ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ጉዳቶች ያሉት ሲሆን ፕሮጀክቶቹ ከተመደበላቸው በጀት ተጨማሪ ወጪ ይጠይቃሉ፤ በብድር የሚሰሩ ከሆነ ተጨማሪ ወለድ እንዲከፈል ያስገድዳሉ፤ ሌላ ብድር ለማግኘትም መሰናክል ይፈጥራሉ። ፕሮጀክቶቹ በወቅቱ ተጠናቀው ይሰጡት የነበረውን ጥቅምም ያሳጣሉ ።
ቀደም ሲል በነበረው አሰራር አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች የሚዘገዩት በደካማ የስራ ባህል ምክንያት፤ በመንግሥታዊ ውስብስብ ቢሮክራሲያዊ አሰራር፣ቀና ትብብር አለመኖር፣ በፕሮጀክት አስተዳደር ችግርና በዕቅዶች የተፈጻሚነት ጉድለት መሆኑ በጥናት ከተረጋገጠ በኋላ በኢትዮጵያ አዲስ የፕሮጀከት አፈጻጸም መመዝገብ ጀምሯል። አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶችም አስገራሚ በሆነ ፍጥነት ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ መታየታቸው ሀገሪቱ በፕሮጀክቶች መጓተት ስትከፍል የነበረው ኪሳራ ከፍተኛ እንደነበር ለመገንዘብ ያስችላል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጓተቱትም ሆነ አዲስ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ረገድ ብዙ መሻሻሎች ታይተዋል። የግንባታ ሂደት በሪፖርት ብቻ ሳይሆን በቦታው በመገኘትም ጭምር ያሉባቸውን ተጨባጭ ችግሮች እንዲቀረፉ በማድረግ እና አዳዲስ ፕሮጀክቶችም በተያዘላቸው ጊዜና በጀት እንዲጠናቀቁ በማድረግ ረገድ አዲስ የፕሮጀክት አጨራረስ ምዕራፍ ላይ መድረስ ተችሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ከመጣ ወዲህ ለዘመናት ሲጓተቱ የነበሩ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለአገልግሎት ከማብቃት ባሻገር የተጀመሩትን በፍጥነት የማስቀጠልና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በሚገርም ፍጥነት ለውጤት ማብቃት ተችሏል። ከዓመታት በፊት ተጀምረው በመጓተት ብሎም በመክሰም ሂደት ውስጥ የነበሩትን የዓባይ እና የኮይሻ ግድቦችን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ ተችሏል። የንግድ ባንክን ህንጻ ከመቆም ታድጎ ለአገልግሎት በቅቷል። የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የኢንሳ መስርያ ቤቶች አምረውና ደምቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል።
በገበታ ለሀገር ከተገነቡት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የወንጪ ደንዲ የኢኮ ቱሪዝም ማዕከል ነው። ይህ ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተጠናቀቁና ኢትዮጵያ ያላትን ፕሮጀክት አፈጻጸም ታሪክ ከፍ ያደረገ ትልቅ ፕሮጀክት ነው።
አዲሱ አመራር ነባር ፕሮጀክቶችን ከማጠናቀቅ አልፎ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በመጨረሽ የብዙዎችን ይሁንታ አግኝቷል። ከእነዚህ ውስጥ ገበታ ለሀገር ተብለው ከተጀመሩና ለመዲናዋ መስህብ ከሆኑት ፕሮጀክቶች ውስጥ የአንድነት፤ የወዳጅነትና የእንጦጦ ፓርኮች ተጠናቀው የአዲስ አበባ ድምቀት ሆነዋል። የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክትም የከተማዋ አንዱ ድምቀት ለመሆን በቅቷል።
በአይነቱ ለኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነውም የሳይንስ ሙዚየምም በአጭር ጊዜ ተገንብቶ የከተማው መስህብ ሆኗል። አሁን ደግሞ ሙሽራዋ አዲስ አበባ በአዳዲስ ፕሮጀክቶች ብቅ ብላለች። አዲስ አበባ የዓለም የዲፕሎማሲ መዲና፣ የአፍሪካ ዋና ከተማ፣ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ እንቅስቃሴ መናኸሪያ እንደ መሆኗ ይህን የሚመጥን ልማት እየተከወነላት ይገኛል። የልማቱ መጠርያም የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ይሰኛል ።
በፍጥነትና ጥራት እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች እጅን አፍ ላይ ለመጫን የሚያስገድዱ ናቸው።
ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ፣ ከአራት ኪሎ እስከ ቦሌ ድልድይ፣ ከቦሌ ድልድይ በመገናኛ ወደ ሲኤምሲ፣ ከቦሌ ተርሚናል ወደ ጎሮ፣ ከሜክሲኮ ወደ ወሎ ሠፈር፣ እንዲሁም ከእንግሊዝ ኤምባሲ ወደ አራት ኪሎ የሚወስዱ ኮሪደሮች መሆናቸው ታውቋል። ስራውም በስድስት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ተነግሯል።
በአጠቃላይ በአምስት አቅጣጫዎች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ከመሰረቱ የሚቀይር ነው። ከሁሉም የሚያስደስተው ደግሞ ስራውን በታያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማጠናቀቅ የሚደረገው ርብርብ እና ጠንካራ የስራ ባህል አግራሞትን የሚፈጥር መሆኑ ነው።
አጠቃላይ ያለውን እንቅስቃሴ ለተመለከተ የኮሪደር ልማቱ በታሰበለት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ መገመት አያዳግትም። የተሽከርካሪ መሄጃ አስፋልቱን እና የእግረኛ መንገዱን ስፋት ለተመለከተውም ዓለም አቀፍ ደረጃን ባሟላ መልኩ እየተገነባ መሆኑን ያመላክታል።
የኮሪደር ልማቱን ተዘዋውሮ ለመመልከት እድል ላገኘ ሰው የሚያስገርመው ነገር የሰራተኞች የስራ ትጋትና ቅልጥፍና ነው። በዚህ ሁሉ ትጋት ውስጥ ደግሞ ስራው ጥራቱን ጠብቆ መሄዱ የሚያስገርም ነው። የተለያዩ የግንባታ ማሽነሪዎች ሲርመሰመሱ፤ሰራተኞች ደፋ ቀና ሲሉ ፤ከፍተኛ አመራሮች አቧራና ጸሃይ ፤ጨለማና ብርድ ሳይበግራቸው ክትትል ሲያደርጉ ለተመለከተ በሀገራችን አዲስ የስራ ባህል እየተፈጠረ መሆኑን መገንዘብ አያዳግተውም።
ለአብነት ከዓድዋ ሙዚየም እስከ መገናኛ ያለውን መንገድ ብንመለከት ነዋሪዎቹን አሳምኖ ከማንሳትና ቤቶቹን አፍርሶ ለግንባታ ክፍት እስከ ማድረግ የወሰደው ጊዜ ከሁለት ሳምንታት የሚበልጥ አልነበረም። በተለይም ለመንገድና ለሌሎች መሰረተ ልማቶች ግንባታ አመቺ ያልሆኑ ቦታዎችን በፍጥነት አጽድቶ ምቹ ለማድረግና ወደ ግንባታ ለመግባትም የወሰደው ጊዜ በጣት ከሚቆጠሩ ቀናት የዘለለ አይደለም። ከዚህ ቀደም በነበሩ ጊዜያት ነዋሪዎችን አሳምኖ ወደ ተዘገጀላቸው ምትክ ቦታ ለማዘዋወርና ወደ ግንባታ ለመግባት አመታትን ይወስድ እንደነበረ በግልጽ የሚታወቅ ነው።
ዛሬ ግን እነዚህ ሁሉ ግዙፍ ስራዎች በጥቂት ቀናት ውስጥ ተጠናቀው የአስፋልት ማንጠፍ ስራ፤ የእግረኛ መንገድ ንጣፍ፤ የመንገድ ጠርዞችን የማስዋብና የማሳማር ስራዎች እጅግ በፈጠነ መልኩ ሲከናወኑ ማየት የሚያስገርም ነው።
መሽቶ በነጋ ቁጥር ተጀምረው የሚያልቁ ፕሮጀክቶችን የተመለከተ በፕሮጀክቶች መጓተት ሀገሪቱ ምን ያህል ወደኋላ እንደተጎተተች ለመረዳት አያዳግተውም። በፕሮጀክቶች መጓተት ምክንያት ቀደም ሲል ተጀምረው ከንቱ የቀሩት የያዩ ማዳበርያ፣ የስኳር ፋብሪካዎች፣ የመንገድ ፕሮጀክቶች፣ በየቦታ እንደ አሸን ተጥለው የሚገኙ የግንባታ ማስጀመርያ የመሰረት ድንጋዮች ይህችን ሀገር በብዙ ዋጋ እንድትከፍል ያደረጓት ናቸው።
እነዚህ የተጓተቱ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ገንዘብ የባከኑባቸው ከመሆኑም ባሻገር በከፍተኛ መጠን ባለው ወለድ በተገኘ የውጭ ብድር የተጀመሩ በመሆናቸው ሀገሪቱን እስካሁን ከፍላ ላልጨረሰችው ዕዳ ዳርጓታል። ዛሬ ግን እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ተረት ሆነው ፕሮጀክቶችን ጀምሮ ማጠናቃቅ ባህል እየሆነ መጥቷል።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም