በዕለተ- ዕሁድ በአንድ ስፍራ የተሰባሰቡት ጎረቤታሞች ከወትሮው በተለየ ጭውውት ይዘዋል። ዛሬን በቀጠሮ ያገናኛቸው ወርሀዊው የዕድር ክፍያ ነው። ይሁን እንጂ ከዚህም የዘለለ ሌላ ምክንያት ይዘዋል። አብዛኞቹ በቅርቡ በግቢያቸው ስለሚከወነው የሰርግ ስነ-ስርአት እየተወያዩ ነው። ጥቂቶቹ ደግሞ እንደጉርብትናቸው መሆን ስለሚገባው ግዴታ ይነጋገራሉ።
ሁሌም ቢሆን በዚህ የጋራ መኖሪያ እንዲህ አይነቱ ልማድ አዲስ አይደለም። በሀዘንና በደስታ በበአላትና በአዘቦት ቀናት ሁሉ ማህበራዊነት በተግባር ሲገለጽ ቆይቷል። አመታትን በአብሮነት የዘለቁት እነዚህ ሰዎች በጉርብትና ለመገናኘት የተለያዩ ምክንያቶች ሰበብ ሆነዋቸዋል።
አብዛኞቹ ቀድሞ በአንድ አካባቢ የነበሩና ሰፈራቸው በመልሶ ማልማት የተነሳ ነዋሪዎች ናቸው። ጥቂቶቹ ደግሞ በተመሳሳይ ከተለያዩ አካባቢዎች መጥተው ጉርብትናውን ተቀላቅለዋል። በቅርቡ የግቢው ነዋሪዎች የሆኑት መምህራንም የዚህ ግቢ አንድ አካል መሆን ከጀመሩ ጊዜያት ተቆጥረዋል። ቤቶቹን በኪራይ የሚጠቀሙ ሌሎችም እንዲሁ በጉርብትናው አብረው ዘልቀዋል፡፡
ይህ አብሮነት እውን መሆን ከጀመረ ወዲህ በግቢው በርካታ ማህበራዊ ጉዳዮች ሲከወኑ ቆይተዋል።እንዲህ እንደአሁኑ ሰርግ በሆነ ጊዜም እንደወዳጅ ዘመድ ሁሉ ደስታን የሚካፈለው አብሮ ነዋሪው ጎረቤት ነው።በችግር በመከራና በሀዘን ጊዜም መተሳሰብ መረዳዳቱ አይቀሬ ይሆናል።
ለጎረቤታሞቹ ዋና ሃሳብ ሆኖ የከረመው የሰርግ ጉዳይ ጊዜው በደረሰ ዕለት የሁሉም ድርሻ በተለየ ተሳትፎ ሲገለጽ ውሏል። ከሰርጉ ዋዜማ ጀምሮ አብሮነት የተስተዋለበት ይህ አጋጣሚ የእምነት ገደብ አልታየበትም። ቋንቋን ከባህል፣ ብሄርን ከማንነት የነጠለ ልዩነትም አልነበረውም ።
መተሳሰብ በመከባበር እየተዋዛ መረዳዳት በአብሮነት በተረጋገጠበት ግቢ ደስታውን የእኩል ለማድረግ ጨዋታና ጭፈራው የጋራ ሆኖ ሰንብቷል። የወላጅነትን ወግ ማዕረግ ያዩት አቶ ሁሴንና እመት ሉባባ ወንድ ልጃቸውን ለመዳር ጥሪውን ካደረሱ ወዲህ ወዳጅ ዘመዱ ከቤታቸው ከቷል። በተለይ ደግሞ ጎረቤቶቻቸው እንደየቅርበታቸው የአቅማቸውን ለማበርከት ከጎናቸው ተሰልፈዋል።
በዚህ የጋራ መኖሪያ ሙስሊም ከክርስቲያኑ ተግባብቶና ተስማምቶ ይኖራል። እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ባለ ጊዜም አንድነትን የሚያጠናክሩ አብሮነትን የሚያጎለብቱ ማህበራዊ ሁነቶች በተግባር ይገለጻሉ። የሁለቱ ሃይማኖት ተከታዮች ገበታ ለየቅል ቢሆንም አንዳቸውን ከአንዳቸው የሚለይ መስተንግዶ ተደርጎ አያውቅም።ሁሌም ሁሉንም በእኩል ለማሳተፍ በየዕምነቱ ተከታዮች እጅ የሚዘጋጅ ማዕድ ይኖራል።
በዚህ ቀን ሙስሊሞች የራሳቸውን ገበታ አዘጋጅተው እንግዶቻቸውን ይሸኛሉ። የሃይማኖቱ ተከታዮች ላልሆኑትም የሚቀርና የሚጎድልባቸው አይኖርም። ልክ እንደሙስሊም ወገኖቻቸው ሁሉ በቤት በጓዳቸው ተገኝተው የራሳቸውን ምግብ ያዘጋጃሉ። በአንድነት ሆነውም በጥሪው የተገኙ ተጋባዦችን በእኩል ቆመው ያስተናግዳሉ።
በዕለቱም የሆነው እንዲህ ነበር። ከማዕድ ቦታው መለየት በቀር አብሮነትን የሚለይ ገጽታ አልተስተዋለም። ሁሉንም በሚያግባባው ሀገርኛ ሙዚቃ አብዛኛው ታዳሚ አንድነቱን በገሃድ አስመስክሯል። ሙሽሮችን ጨምሮ መላው ቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ ደስታውን ባሳየበት ውሎ የግቢው ነዋሪዎች ፍቅርና መተሳሰብ የማይረሳ ሆኖ አልፏል።
«በጀሞ አንድ ህብረት በአንድነት» የጋራ መኖሪያ አንድ መቶ ስምንት አባወራዎችና ቤተሰቦቻቸው ህይወትን በአብሮነት ይጋራሉ። በዚህ ስፍራ የዕምነትና ሃይማኖት፣የቋንቋና ብሄር መለያየት ችግር ሆኖ አያውቅም።ይህ ወንድማማችነት የፈጠረው ስሜትም በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ጭምር እየተገለጸ አመታትን ተሻግሯል።
በዚህ ግቢ ሀዘን በደረሰ ጊዜ ድንኳን ጥሎ፣ እንደራስ አልቅሶና ተደጋግፎ ማለፍ የተለመደ ነው። የቀድሞው ህብረት በአንድነት ማህበር ሊቀመንበር አቶ ሁሴን ሰይድ እንደሚሉትም እንዲህ አይነቱ ልማድ የተጀመረው በአንድ ወቅት በግቢው ባጋጠመ ድንገተኛ ሃዘን ምክንያት ነበር። አቶ ሁሴን ያንን ጊዜ ዛሬም ድረስ በተለየ ያስታውሱታል።
«የዛኔ አብዛኛው ነዋሪ ከነበረበት ተነስቶ ወደአካባቢው የከተመበት ወቅት ነበር። ሁሉም ለስፍራው አዲስና እንግዳ እንደመሆኑም እርስበርስ የመተዋወቅ አጋጣሚው አልዳበረም። በወቅቱ ግቢው እንደአሁኑ የለማና የተመቻቸ ባለመሆኑ የነዋሪውም ቁጥር የበረከተ አልነበረም። አብዛኞቹ ቤታቸውን ከተረከቡ በኋላ ፈጥነው ባለመግባታቸው ግቢው በጭርታ ውሎ በዝምታ ያመሻል። ከቀናት በአንዱ ቀን ግን ዝምታውን ሰብሮ የወጣ ደማቅ ጩኸት ድንገት ተሰማ። በግቢው ይህ አይነቱ አጋጣሚ ሲፈጠር አዲስ ነበርና ሁሉም ተደናግጦ ተሯሯጠ። ከአንድ መኖሪያ ቤት ልቆ የሚሰማው ለቅሶ የቤቱን አባወራ መሞት ያረጋገጠ ነበር። ይህኔ ሁሉም ሃዘኑን እንደራሱ ቆጥሮ አብሮ ተላቀሰ። «አናውቃቸውም፣ አያውቁንም» ሳይልም ከቤት ከጓዳቸው ገብቶ መከራቸውን ተካፈለ ።
ይህ ከሆነ በኋላ ጎረቤቶች ሰብሰብ ብለው በጋራ መከሩ። መኖሪያ ግቢው አዲስ ነውና፣ ዕድርና ማህበር አይታወቅም። ለእንዲህ አይነቱ ክፉ አጋጣሚ የሚሆን ተብሎ የተቀመጠ ጥሪትም የለም። አዎ!እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድና ሃዘንተኞችን በጉርብትና ለማገዝ አንድ መፍትሄ ያሻል። ሰዎቹ ከምክራቸው በኋላ ከኪስ ከጓዳቸው የየራሳቸውን ለማበርከት ተስማሙ። እንደነበረው ወግና ባህልም ቀን ከማታ ከሃዘንተኞቹ ሳይለዩ ሃዘኑን የጋራ አድርገው ሰነበቱ።
ይህ ክፉ አጋጣሚ የፈጠረው መተዋወቅ ግን በዚሁ ብቻ አልተቋጨም። ድንገቴው ሃዘን ያስከተለው ቅርርቦሽ አብሮነትን አጠናክሮ በግቢው የመረዳጃ ዕድር እንዲቋቋም ምክንያት ሆነ። እነሆ! ዛሬ በህብረት በአንድነት የጋራ መኖሪያ የመረዳጃ ዕድር ተመስርቷል። በቂ ወንበሮች፣ ድንኳንና ሌሎችም ዕቃዎች የተሟሉለት ይህ ዕድር ዛሬ ለሃዘን ብቻ ሳይሆን ለሰርግ ለምርቃትና ለሌሎችም ፍላጎቶች ይውላል።
በርካቶች እንደሚስማሙበት በጋራ ቤቶቹ ያለው አኗኗር ስያሜያቸውን የሚመጥን አይደለም። ብዙዎቹ የራሳቸውን ነጻነት በመሻት ግለኝነትን ይመርጣሉ። ሌሎችም ከጎናቸው ያለውን ጎረቤት በወጉ ሊያውቁት አይፈቅዱም። በዚህ ግቢም ቢሆን አልፎ አልፎ ይህ አይነቱ እውነታ ይስተዋላል። አብዛኞች ግን አሁንም ቀድሞ የነበረውን አብሮነት አልተዉትም። የዕድር፣ የዝክርና የማህበር ልምዳቸው ዛሬም ድረስ አብሯቸው ቀጥሏል።
ወይዘሮ ከበቡሽ ደመቀ በግቢው መኖር ከጀመሩ አመታትን አስቆጥረዋል። ቀድሞ የነበሩበት ሰፈር በልማት ምክንያት ሲነሳና ኑሯቸው ወደጋራ መኖሪያ ሲቀየር ተጨንቀውና አስበው እንደነበር አይሸሽጉም። በዚህ ስፍራ ኑሮና ህይወት እንደትናንቱ አይደለም። የጋራ ህንጻው በአንድም ይሁን በሌላ ከብዙሃን የሚያገናኝ በመሆኑ መቻቻልና መተሳሰብ ግድ ይላል። ወይዘሮ ከበቡሽ እንደሚሉትም የሁሉም ሰው ባህርይ እንደመልኩ ይለያያል። አንዱ የሌሎችን ጥቅም ካከበረና መብትን ካልተጋፋ ግን ተስማምቶ መኖሩ ቀላል ይሆናል።
ወይዘሮዋ በግቢው ዝክር ፣ ልደትና ክርስትና ደግሶ የመጠራራትና የመተጋገዝ ልማዱ አሁንም ቢሆን እንዳልቀዘቀዘ ይናገራሉ። የአኗኗር ባህሪው የተመቸ ነው ባይባልም ባለውና በተገኘው አማራጭ ተጠቅሞ ማህበራዊነትን ማስፋት ተችሏል። የትናንቱን ልምዳቸውን ያልተዉ ብዙ ነዋሪዎች ዛሬም ጸበል ጸዲቅ አዘጋጅተው ጎረቤቶቻቸውን ይጠራሉ።
አሁንም በአንዳንድ ነዋሪዎች ዘንድ የእንጨት ሙቀጫ ፣ የድንጋይ ወፍጮና መጅ፣ ብረት ምጣድና ሌሎችም በአግባቡ እንደተያዙ ናቸው። በእነሱ መገልገል የሚሹ ጎረቤቶችም ዕቃዎቹን ተውሰው ሽሮና በርበሬ፣ ያዘጋጃሉ። ብቅል ፈጭተው፣ ጌሾ ይወቅጣሉ። በእንጨት አሻሮ ቆልተውና ቂጣ ጋግረው ጠላ ይጠምቃሉ።
ይህ ሁሉ አብሮነት በሚታይበት ግቢ ለቡሄና ለመስቀል ደመራ ተሰባስቦ መጨፈርና መጫወት የተለመደ ነው። በግቢው የዕምነትና የሃይማኖት ልዩነት ቢኖርም ፈቃደኞች የሆኑ በርካቶች በጨዋታው ለመታደም ዝግጁ ናቸው። ሙስሊሙ በክርስቱያኑ፣ ክርስቲያኑም በሙስሊሙ አውደአመት ተገኝቶ «በእንኳን አደረሳችሁ» ወግ ባህል የመጠያየቁ ልማድም በደስታ ይከወናል።
መምህር ወንደወሰን እሸቱ በእንዲህ አይነቶቹ አጋጣሚዎች ሁሌም ኢትዮጵያዊነትን የሚያንጸባርቁ ባህልና ወጎች እውን ይሆናሉ ባይ ነው። ማህበራዊነት ያለምንም ልዩነት በሚረጋገጥበት እውነትም አንዱ የሌላውን ወዶና አክብሮ የመቻቻል ሂደቱ ይኖራል። በአሁኑ ጊዜ በተለይም በኮንዶኒየም አኗኗር ይህ አይነቱ ወግ እየደበዘዘ ነው። ይሁን እንጂ በተለያዩ ማህበራዊ ግንኙነቶች አብሮነቱን እንደነበረው ማስቀጠል እንደሚቻል ይናገራል።
እንደ ማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው ዶክተር የራስወርቅ አድማሴ አገላለጽ ደግሞ የሰውልጅ በተለያዩ ምክንያቶች አብሮነቱን ያዳብራል። ሰዎች ሰው ለመባል የሚችሉትም በግለኝነት ሳይሆን አብሮ በመኖሩ መስመር ሲያልፉና ሲሳተፉ ነው። የሰው ልጆች ተከባብሮና ተዋዶ በመኖር የጋራ ጥቅማቸውን ያስከብራሉ። እንደሳቸው አባባል ይህ እውነት በሰዎች ተቀራርቦ መኖር ላይ ብቻ አይወሰንም። በተመሳሳይ ሀገርና አህጉሮችም ጭምር ተቻችለው መኖርን ያውቃሉ።
ብዙውን ጊዜ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎች በአንድ መንግስት ጥላ ስር የመኖር አጋጣሚው አላቸው። እንዲህ መሆኑም በፍቅርና በሰላም ተግባብቶ ለመኖር ምክንያት ይፈጥራል። በኑሮ መሀል ልዩነት የሚንጸባረቅ ከሆነ ግን ፉክክርን ለማስከተል ሰበብ ሆኖ ወደግጭት ሊያመራ ይችላል። መቼም ቢሆን በቋንቋ ፣ በሃይማኖት፣ በገቢ መጠን፣ በአካባቢ ልዩነትና በሌላም የተከፋፈሉ ነዋሪዎችን የሚያገናኙ ግዴዎች ይኖራሉ።
በእነዚህ ልዩነቶች መሃል ግን አንድነት የሚፈጠርበት አግባብ አይቀሬ ይሆናል። አንድ ሀገርን የተዋጣለት ነው የሚያስብለውም እነዚህን ልዩነቶች ጭምር አቻችሎ ሲያራምድ ነው። ዶክተር የራስወርቅም የአብሮ መኖርን ጥብቅ ሰንሰለት በተለያዩ ማህበራዊ ትስስሮች መሀል እያስተዋሉት መሆኑን ይናገራሉ። አመታትን በጉርብትና ያሳለፉና አካባቢያቸው በመልሶ ማልማቱ የተነሳ ነዋሪዎች አሁንም ድረስ ዕድራቸውን አላፈረሱም። እንደቀድሞ በተለመደው ስፍራ ባይገናኙም በየወሩ በቤተክርስቲያናት አጸድ ስር ተሰባስበው የሚገባቸውን ግዴታ ይወጣሉ።
አሁን ባለንበት ዘመን ከከተሞች መስፋትና ከህዝብ ቁጥር መብዛት ጋር ተያይዞ የአኗኗር ልምድና ባህርይ ተለውጧል። በተለይም በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ግለኝነት እየተለመደ ነው። ይህ መሆኑም የቀድሞውን አብሮነት ለማሳሳት ስጋት የሚፈጥር ይሆናል።
እንደ ማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አባባል ግን በእንዲህ አይነቶቹ ግቢዎች አኗኗርን መሰረት አድርገው የሚወጡ ህገ ደንቦች ነዋሪውን ለማስተሳሰርና አቻችለው ለማኖር ምክንያት ይሆናሉ። እግረ መንገዱንም ነዋሪዎቹ ለግቢው የሥነሥርዓት ህጎች እንዲገዙና አብሮ የመኖርን ጠቀሜታ እንዲገነቡ ያግዛቸዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 29/2011
መልካምስራ አፈወርቅ