
ዜና ትንታኔ
ውሃ የአንድን ሀገር እድገት እና መጻዒ ዕድል ከሚወስኑ የተፈጥሮ ሀብቶች መካከል ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ የውሃ ሀብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የገጸ ምድር እና የከርሰ ምድር ውሃ እንዳላት ቢነገርም፤ ለዘመናት ይህንን ሀብቷን በወጉ ጥቅም ላይ ሳታውል ቀርታለች ይላሉ እነዚሁ ባለሙያዎች፡፡ ለመሆኑ አሁን ላይ ሀገሪቱ በውሃ ሀብቷ የመጠቀም ሁኔታዋ ምን ይመስላል? የዓባይ ግድብ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ መድረሱ ምን ዓይነት አንድምታ ይኖረዋል? ስንል ለዘርፉ ምሑራን ጥያቄ አቅርበናል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሀብትና ኢንጂነሪንግ አስተዳደር መምህር እንዲሁም የውሃ ሀብት ባለሙያዎች ማኅበር መሥራችና ፕሬዚዳንት አማኑኤል አባተ (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት ‹‹ኢትዮጵያ ከ122 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ በላይ የገጸ ምድር እና በቅርቡ በወጡ ጥናቶችም እስከ 40 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ በላይ የሚገመት የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት አላት፡፡ ከዚህ ውስጥ ለመጠጥ፣ ለሃይድሮ ኤሌክትሪክም ይሁን ለመስኖ ልማት እየተጠቀመች ያለችው ተደማምሮ ከ10 በመቶ አይበልጥም ይላሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ በውሃ ሀብቷ የመጠቀም አቅሟ መሻሻል አሳይቷል፤ ለዚህም የዓባይ ግድብ ግንባታና የመስኖ ልማት ሥራዎች ማሳያ ናቸው›› ብለዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ትልቁ ሀብቷ ውሃ ነው›› የሚሉት አማኑኤል (ዶ/ር)፤ ይህን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥም ይሁን የሰዎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ትችላለች፡፡ የዓባይ ግድብ የኃይል አቅርቦትን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ በመሆኑ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ አስተማማኝ ዋስትና የሚሰጥ ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የውሃን ጥቅም በውል እንዲረዳ እና ለውሃ ዋጋ እንዲሰጥ አዲስ መነቃቃትንም የፈጠረ ነው›› ብለዋል፡፡
ውሃ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ነዳጅ ነው የሚሉት አማኑኤል (ዶ/ር) የዓባይ ግድብም በብዙ ውጣ ውረዶችና ጫናዎች መሐል ለማለፍ የተገደደው በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህርና ተመራማሪ አያኖ ሲርቦ (ዶ/ር)፤ አማኑኤል (ዶ/ር) ያቀረቡትን ሃሳብ የሚጋሩት መሆኑን በአስተያየታቸው አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ጥሩ የውሃ ሀብት አላት ተብሎ ቢታሰብም የውሃ ሀብቷ በአግባቡ ጥቅም ላይ ይዋል ቢባል ግን ካላት የሕዝብ ብዛትና የቆዳ ስፋት አንጻር በቂ ነው የሚባል አይደለም ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ በውሃ የመጠቀም ጅምር ተግባራትን እያከናወነች መሆኑ እንደጥሩ የሚታይ መሆኑን አንስተው፤ በተለይም የዓባይ ግድብ እንደሀገር ሕዝቡ የውሃን ጥቅም ያየበትና ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም የዘመናት ቁጭታቸውን የተወጡበት ትልቅ ድል እንደሆነ አንስተዋል፡፡
የዓባይ ግድብ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል እና ምርቱን ለጎረቤት ሀገራትም በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና በሚደረገው የንግድ ትስስር የኢትዮጵያ በኢነርጂው ዘርፍ የመሪነት ሚና እንድትጫወት የውሃ ሀብቷ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክትላት ይገልጻሉ፡፡
ኢትዮጵያ ከውሃ ሀብቷ ብቻ እስከ 45 ሺህ ሜጋ ዋት የሚገመት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል አቅም እንዳላት እና 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በመስኖ ማልማት የሚያስችል አቅም እንዳላት ጥናቶች ያመላክታሉ ያሉት አያኖ (ዶ/ር)፤ እስከ አሁን ይህንን ሀብት ባለመጠቀሟ የምግብ ዋስትናዋን ማረጋገጥ እንዳልቻለች ጠቅሰዋል፤ አሁን ላይ በውሃ ዘርፍ እየተሠራ ያለው ሥራ ተስፋ ሰጪ መሆኑንና የኢትዮጵያን እድገት የሚያስወንጭፍ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ ሃሳቡ ተስፋ እንደሚስረዱት፤ የዓባይ ግድብ መጠናቀቅ ለቀጣናውና ለመላው አፍሪካ የልማት እንቅሰቃሴም አርዓያነት ያለው ስኬት ተደርጎ ይታያል፡፡ አፍሪካ ከሌሎች አኅጉሮች ወደ ኋላ የምትቀርበት አንዱ ምክንያት የተፈጥሮ ሀብቷን ለማልማት የሚያስችል የገንዘብና የቴክኖሎጂ አቅም በማጣቷ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ይህንን በሚቀለብስ መልኩ በራሷ አቅም የዓባይ ግድብን ገንብታ ለፍጻሜ ማድረሷ ለአፍሪካውያን ትልቅ ልምድ የሚሰጥ ነው፡፡ አፍሪካውያን ገንዘብና የሰው ኃይል አቅማቸውን አስተባብረው ከችግር ካልወጡ በስተቀር ከውጭ የሚወርድላቸው ነገር አለመኖሩን የሚማሩበት ነው ይላሉ፡፡
የኃይል እጥረት የልማት ከፍተኛው ማነቆ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ሃሳቡ፤ የዓባይ ግድብ መጠናቀቅ በተለይም በቀጣናው ያለውን የኃይል እጥረት ሊቀርፍ የሚችል ነው ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ እስከ አሁንም ያላትን ኃይል ለቀጣናው ሀገራት በማካፈል ችግራቸውን እየቀረፈች መሆኑን ጠቅሰው፤ የግድቡ መጠናቀቅ የምታደርገውን የኃይል አቅርቦት በእጥፍ ሊያሳድግላት የሚችል በመሆኑ ለአካባቢው ሀገራት ሁነኛ መፍትሔ በመሆን ያገለግላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የዓባይ ግድብ መጠናቀቅ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚውና ማኅበራዊ ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነ በመጥቀስ ብሔራዊ አንድነትና ኩራትን የሚጨምር እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
አማኑኤል (ዶ/ር) ሀገራት ለውሃ ከሚሰጡት ትልቅ ዋጋ እና ትኩረት አንጻር ኢትዮጵያ ስትታይ ክፍተት እንዳለባት ጠቅሰው፤ በውሃ የመጠቀም ልምዷ እየተሻሻለ ሲመጣ ጠንካራ የውሃ አስተዳደር ተቋም እየፈጠረች መሄድ ይጠበቅባታል ብለዋል፡፡
የውሃ ሀብትን ጥቅም ላይ ለማዋል በዘርፉ ምርምርና ጥናት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ከዚህ አንጻር ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሀብት ኢንስቲትዩት እንደነበረ በማስታወስ፤ ይህ ተቋም ራሱን ችሎ ጠንክሮ መውጣት ሲገባው ጭራሽ ወደ ማዕከልነት እንዲወርድ መደረጉ ተገቢ አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡
በአንጻሩ ግብፅ ከ44ሺህ በላይ በውሃ ዘርፍ የሚሠሩ ምሑራንና ባለሙያዎች እንዳሏት የጠቀሱት አማኑኤል (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ በውሃ ዘርፍ የሚሠሩ ተመራማሪዎች ቁጥር በጣም ኢምንት መሆኑ የውሃ ሀብትን በተለያዩ አማራጮች ለመጠቀም በሚደረገው ጥረት ላይ ክፍተት ስለሚፈጥር ወደፊት ይህን አሠራር ማስተካከል ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
አያኖ (ዶ/ር) በቀጣይም ኢትዮጵያ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድቦችን አብዝታ በመገንባትና የመስኖ ሥራዎችን በማስፋፋት የውሃ ሀብቷን በአግባቡ ጥቅም ላይ አውላ ሕዝቧን ከተረጂነት ማላቀቅ ይጠበቅባታል ይላሉ፡፡ ትልልቅ ወንዞችን ብቻ ሳይሆን ገባር ወንዞችን እና ተፋሰሶችንም በያሉበት አካባቢ ለልማት በማዋል ተጠቃሚነቷን ማረጋገጥ እንደሚኖርባትና የውሃ ሀብትን በዘላቂነት ለማስቀጠልም የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም በራሳችን አቅም ለመገንባት የዓባይ ግድብን የመሠረት ድንጋይ ስናስቀምጥ በዓለም ማኅበረሰብ ዘንድ ይጨርሱታል የሚል እምነት አልነበረም ያሉት አቶ ሃሳቡ፤ ይህን ግዙፍ ፕሮጀክት ማጠናቀቅ መቻላችን ብሔራዊ ኩራትና አንድነትን አጎናጽፎናል፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲዊ ክብደት እንዲጨምር አድርጓል ይላሉ፡፡
በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በዓባይ ግድብ ዙሪያ ከ10 ጊዜ በላይ ስብሰባዎች እንደተደረጉና ጉዳዩ የዓለም ሚዲያዎች መነጋገሪያ እንደነበር አስታውሰው፤ ያን ሁሉ ጫና በመቋቋም የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሳችን ትልቅ ድል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የዓባይ ወንዝ በዓለም ላይ ኢ-ፍትሐዊነት ከነገሠባቸው የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀሞች አንዱ እንደነበር ጠቅሰው፤ ግድቡ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ እንደሆነ እና ትብብር ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ ማሳያ ሆኖ የሚጠቀስ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ የገነባችው ግድብ በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብታቸው ለተነፈገው የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት የመሸጋገሪያ ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል እንደሆነ ጠቅሰው፤ ሌሎችም አርዓያውን እንዲከተሉ የሚያስችል በቀጣይም ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን እንድትጠቀም የሚያነቃቃ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም