የ‹‹ካላዛር›› በሽታን ለማከም ተስፋ የሰጠ ሙከራ

ካላዛር ወይም በሳይንሳዊ ስሙ ‹‹ቪሴራል ሌሽመናይስስ›› ከወባ ቀጥሎ በዓለም ላይ በጥገኛ ተህዋሲያን የሚተላለፍ ገዳይ በሽታ ሲሆን ከወባ በሽታ ጋር ተመሳሳይ ምልክቶች እንደሚስታዋሉበት ይነገራል።የካላዛር በሽታ ትኩሳት፣ የክብደት መቀነስ፣ ከልክ ያለፈ የጣፊያና የጉበት እድገት የሚያስክትል ሲሆን በጊዜው ካልታከመ ለሞት ሊዳርግ ይችላል።በሽታው በአሸዋ ዝንብ ንክሻ የሚተላለፍ ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ፣ ደቡብ እስያና በደቡብ አሜሪካ በሚገኙ 80 ሀገራት ውስጥ ተንሰራፍቷል።በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዚህ በሽታ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር አንድ ቢሊዮን መድረሱንና አብዛኞቹ ህሙማንም በምስራቅ አፍሪካ እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።

የአየር ንብረት ለውጥ የካላዛር በሽታን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት በማወክ በሽታው እስካሁን ወዳልተዳረሰባቸው ቦታዎች እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል።በዓለም ላይ በየአመቱ ከ50 ሺ እስከ 90 ሺ የሚደርሱ ሰዎች በካላዛር የሚያዙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ገሚሱ እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት መሆናቸውንም ነው መረጃዎቹ የሚጠቁሙት።

ካላዛር 46 አይነት የበሽታ ዝርያዎች ያሉት ሲሆን በህክምና እንደሚድን በወቅቱ ህክምና ካላገኘ ደግሞ ለሞት ሊዳርግ እንደሚችል በህክምና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይገለፃል።

በአፍሪካ አሁን እየተሰጠ የሚገኘው የካላዛር ህክምና በሆስፒታል ውስጥ በየቀኑ ለ 17 ቀናት የሚወሰድ ከፍተኛ ህመም የሚፈጥር ክትባት ሲሆን ልብን፣ ጉበትን እና ቆሽትን በመጉዳት ለሕይወት አስጊ የሆኑ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ሊያስከትል እንደሚችል ተገልጿል።ከዚህ አንፃር አዲሱ የካላዛር ህክምና የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና በሽታውን ለማጥፋት ካስቀመጠው አቅጣጫ ጋር የተጣጣመ እንዲሁም በእጅጉ ትኩረት የተነፈገውንና ለማከምም አስቸጋሪ የሆነውን የካላዛር በሽታ ለማዳን በሚደረገው ርብርብ ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት ያግዛል ተብሏል፡፡

በአንፃሩ በኢትዮጵያ በምርምር ላይ የሚገኘው አዲሱ የ “LXE408” በአፍ የሚወሰድ መድሃኒት አሁን ከሚሰጠው ህክምና የበለጠ ፈዋሽና አስተማማኝ እንደሚሆን ይጠበቃል። ፈውስ ትኩረት ለተነፈጉ በሽታዎች ኢኒሺዬቲቭ (DNDi) እና አጋሮቹ ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ፣ አስተማማኝ፣ ለአጠቃቀም ቀላል እና ለህሙማን ምቹ የሆነ በአፍ የሚወሰድ የካላዛር መድሃኒት ለማስገኘት የሚያካሂዱት ምርምር በቅርቡ ወደ ምእራፍ ሁለት የክሊኒካል ሙከራ መሸጋገሩ ይታወሳል።ኢትዮጵያ እንደ አንድ ካላዛር የተንሰራፋበት ሀገር አዳዲሶቹ ኬሚካላዊ ምርምሮች ወደሚካሄዱበት ምእራፍ ሁለት ክሊኒካዊ ሙከራ መግባቷ እንደ ትልቅ እምርታ ተቆጥሯል።

ዶክተር እሌኒ አየለ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የካላዛር በሽታ ጥናትና ህክምና ማዕከል ውስጥ በሚካሄደው በዚህ ክሊኒካል ሙከራ ተባባሪ ተመራማሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፣ ይህ ምርምር ውጤታማና ደህንነቱ የተጠበቀ ህክምና የማስገኘት እድሉ ሰፊ ነው።አሁን ላይ በኢትዮጵያ ያሉት የካላዛር ህክምና አማራጮች ከፍተኛ የሆነ ውስንነት ያለባቸው፣ ጎጂ ክትባትን ግዴታ የሚያደርጉ፣ እጅግ ቀዝቃዛ የህክምና ቁሳቁሶች ጥቅም ላይ የሚውሉባቸው እንዲሁም ህሙማን አገልግሎቶቹን ፍለጋ የረጅም ርቀት ጉዞ የሚጠይቁ እና ለረጅም ጊዜም ሆስፒታል ውስጥ ተኝተው የሚታከሙባቸው ናቸው፡፡

እቅዱ ከሰመረ በምርምር ላይ የሚገኘው ህክምና ፈዋሽ፣ የጎንዮሽ ጉዳቱ አነስተኛ የሆነና ህሙማን በመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ በሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ተቋማት ተደራሽ ይሆናል።ይህም ህክምናው ባስፈለገበት ጊዜ ሁሉ ታካሚዎች በቀላሉ እንዲያገኙትና የበሽታውን ተስፋፊነትና ጉዳት ይቀንሳል። ከምንም በላይ በሽታውን እስከወዲያኛው ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል፡፡

አዲሱ ህክምና በኢትዮጵያ የመድሃኒት ሙከራ መስፈርት መሠረት የሚካሄድ ሲሆን በየቀኑ የሶዲየም ስቲቦግሉኮኔት እና ፓሮሞማይሲን ድብልቅ መርፌዎች ለ17 ቀናት ይሰጣል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከ18 እስከ 44 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 52 ፈቃደኛ ጎልማሶች በጥናቱ ይሳተፋሉ።

በተመሳሳይ የሁለተኛው ምእራፍ የ”LXE408” ክሊኒካዊ ሙከራ በህንድ ሀገር እየተከናወነ ሲሆን በምስራቅ አፍሪካና ደቡብ እስያ የሚገኙ ህሙማን ለዚህ ምርምር የተለያየ ምላሽ እንደሚያሳዩ ይጠበቃል።ይህ የተለያየ ምላሽም ነው ተገቢው ህክምና እንዲገኝ ምርምር ማካሄዱን የግድ ያደረገው፡፡

ፈውስ ትኩረት ለተነፈጉ በሽታዎች ኢኒሺዬቲቭ (DNDi) የካላዛር ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶ/ር ፋቢያና አልቬዝ እንደሚናገሩት በካላዛር ሕክምናዎች ወደ አዲሱ ትውልድ የህክምና አሰጣጥ ሽግግር እየመጣ ነው።በሽታውን በዘላቂነት ከመላው ዓለም በተለይም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ከሆኑት የአፍሪካ ሀገራት ለማስወገድ አዳዲስ ሕክምናዎችን ማግኘት መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ይህ አዲስ ክሊኒካዊ ሙከራም የተሻለ፣ ለታካሚ ተስማሚ፣ ለሁሉም ሰው ተደራሽ የሆኑ ውጤታማ መድሃኒቶችን ለማስገኘት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተስፋ ተጥሎበታል።

ይህ በአፍ የሚወሰድ “LXE408” የተሰኘ ህክምና ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በዓለም አቀፉ መድሃኒት አምራች ኩባንያ በኖቫርቲስ (Novartis) ነው። ከዚያም እ.አ.አ በ2020 መጀመሪያ ላይ ዲኤንዲ እና ኖቫርቲስ እንክብሉን በጋራ ለማበልጸግ የትብብር ስምምነት ፈጽመው በአንድ ማእቀፍ መሥራት ጀመሩ። የቅድመ ክሊኒካዊ ምርምርን እና የመጀመሪያ ደረጃ ጥናትን የማጠናቀቅ ብሎም የኬሚካል ምርትና ቁጥጥር ሥራውን ሃላፊነት ወስዶ እየሠራ የሚገኘው ኖቫርቲስ ሲሆን ምርመሩ ውጤታማ ሆኖ መድሃኒቱ የገበያ ፍቃድ ካገኘ የተጠቃሚውን አቅም ባገናዘበ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለገበያ ያቀርባል።በዋናነትም በሽታው በእጅጉ የተንሰራፋባቸው ሀገራት ተደራሽ ይሆናሉ።

የ“LXE408” ህክምና ግኝት እና ህክምናውን በክሊኒካዊ ምርምር በማዘመን የካላዛር ህሙማንን ለመርዳት የሚደረገው ጥናት በብሪታንያው ግብረሰናይ ድርጅት ዌልካም የገንዘብ ድጋፍ የተካሄደ ነው።በኢትዮጵያ የተካሄደው ክሊኒካዊ ሙከራ ደግሞ የገንዘብ ድጋፉን ያገኘው ከአውሮፓና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ክሊኒካዊ ሙከራዎች ጥምረት (EDCPT) ነው።

በአሁኑ ጊዜ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ወቅት እየጠበቀ እንዳዲስ የሚቀሰቀሰውን የካላዛር በሽታ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ እቅድ ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ይህን እቅድ ለማሳካትና በሽታው ዳግም እንዳይመለስ የሚደረገው ጥረትም የተሻሻሉ ህክምናዎችን በመተግበር ላይ የተመሠረተ ነው።ውጤቱ ያማረ ከሆነ፣ አዲሱ በአፍ የሚወሰድ ህክምና “LXE408” ይህን በሽታ የማስወገድ ጥረት በእጅጉ ያግዛል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የጤና ድርጅት ሳይንቲስትና የካላዛር በሽታ መከላከል ተጠሪ ዶክተር ሳዉራብ ጃይን በበኩላቸው እንደሚሉት ካላዛር ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን በዋናነትም ህጻናትን የሚያጠቃ ለሕይወት አስጊ የሆነ በሽታ ነው።ከዚህ አኳያ ይህን በሽታ ባስቸኳይ ማስወገድ ይገባል።በሽታውን ማስወገድ የበሽታው ተጠቂ የሆኑትን ማህበረሰቦች ከድህነት ለማውጣትም ሁነኛ መንገድ ይሆናል።

እ.ኤ.አ በ2030 የተያዘው አንዱ ዓላማ ለህብረተሰብ ጤና ጠንቅ የሆኑትን ትኩረት የተነፈጉ ሃሩራማ በሽታዎች በዋናነትም ካላዛርን ማስወገድ ነው።በዚህ መሠረት የተሻሻሉ ምርምሮችንና ህክምናዎችን ማካሄድ ከዋና ዋናዎቹ ተግባራት አንዱ ነው።

ለዚህ ጥናት የገንዘብና ተክኒካዊ ድጋፍ የተገኘው ከአውሮፓና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ክሊኒካዊ ሙከራዎች ጥምረት (EDCTP2)፣ ከኖርዌይ የልማት ትብብር ኤጀንሲ፣ የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የጀርመን የትምህርት እና ጥናት ሚኒስቴር፣ ሜዲሲንስ ሳንፍሮንቴርስ ኢንተርናሽናል፣ የስዊዘርላንድ የልማትና ትብብር ኤጀንሲ፣ የብሪታንያ ዓለም አቀፍ ልማት ድርጅት፣ የተለያዩ የግል ፋውንዴሽኖችና ግለሰቦች ይገኙበታል።

በምርምር ላይ ያለው የካላዛር መድሃኒት በአፍ የሚወሰድ ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ በሽታውን ለማጥፋት የተያዘው ግብ እውን እንዲሆን ያግዛል ተብሏል። በሽታው በተለይም ሞቃታማ በሆኑ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ በስፋት እንደመከሰቱ በዚሁ አካባቢ የሚኖሩና በበሽታው ተጠቂ ለሆኑ ዜጎችም ትልቅ እፎይታ ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የካላዛር በሽታ ጥናትና ህክምና ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ሳሙኤል ተሾመ እንደሚገልፁት በኢትዮጵያ የካላዛር በሽታ የመጨመር አዝማሚያ በማሳየቱ ለበሽታው ፈዋሽና አስተማማኝ መድሃኒት ለማግኘት የሚደረገው ምርምር ወደ ምዕራፍ ሁለት መሸጋገሩ ተስፋ የሚሰጥ ነው። ምርምሩ መድሃኒት ሆኖ ለታማሚው ለመድረስ ከዚህ በኋላ ሁለት ደረጃዎችን ማለፍ ይጠበቅበታል።ውጤታማና ደህንነቱ የተጠበቀ ህክምና የማስገኘት እድሉም ሰፊ ስለመሆኑ ተነግሮለታል።

ምርምሩን ኢትዮጵያውያን ከተለያዩ ሀገራት ተመራማሪዎችና የላቦራቶሪ ተቋማት ጋር በጋራ እያከናወኑት ይገኛሉ።በአሁኑ ወቅትም የካላዛር ህክምና ለ17 ቀን በመርፌ የሚሰጥ ሲሆን የተለያዩ የጎንዮሽ ጉዳቶች ይኖሩታል።በኢትዮጵያ የመድሃኒት ሙከራ ምርምር መስፈርት መሠረት እየተካሄደ ያለው አዲሱ የ“LXE408” መድሃኒት በአፍ የሚወሰድ ሲሆን መድሃኒቱ አሁን ከሚሰጠው ህክምና የበለጠ ፈዋሽና አስተማማኝ እንደሚሆን ይጠበቃል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ ያሉት የካላዛር ህክምና አማራጮች ውስንነት አለባቸው።ህሙማን የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ረጅም ርቀት መጓዝና ሆስፒታል ውስጥ ተኝተው መታከም ግዴታ አለባቸው።ይሁንና በምርምር ላይ የሚገኘው ህክምና ፈዋሽ፣ የጎንዮሽ ጉዳቱ አነስተኛ፣ ህሙማን ደግሞ በመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ በሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ተቋማት ህክምናውን በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ የሚያግዝ ነው።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በተስፋፋው ካላዛር በሽታ ከወራት በፊት ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ሲሆን የአካባቢው የጤና ተቋማት ሃላፊዎችና የሕክምና ባለሙያዎች፣ በአካባቢው ከሰባት ወራት በፊት የተከሠተው በሽታ በመስፋፋት ላይ መሆኑን አረጋግጠዋል።ከደቡብ ኦሞ ዞን ብቻ፣ በበሽታው ከተያዙት 150 ሕሙማን 17ቱ በስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ መሞታቸውን፣ የዞኑ ጤና መምሪያ አስታውቋል። በሽታው፥ በኮንሶ፣ በጋሞ እና በጎፋ ዞኖችም መዛመቱን የሆስፒታል ምንጮች አረጋግጠዋል።

በተመሳሳይ በአማራ ክልል ከ1996 ዓ.ም ጀምሮም በተለይም በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከም ወረዳ አካባቢ በሽታው በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያጠቃ ስለነበር ህክምናው በነፃ መሰጠት እንደተጀመረ በአዲስ ዘመን የመጀመሪያ ሆስፒታል የተገኘነው መረጃ ያመላክታል።ከዛም በኋላ በሽታው በዚሁ አካባቢ ጥቂት የማይባሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን እንዳጠቃ ይነገራል።ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ በምርምር ላይ የሚገኘው አዲሱ የ“LXE408” በአፍ የሚወሰድ መድሃኒት ወደ ምእራፍ ሁለት የክሊኒካል ሙከራ መሸጋገሩ በሽታውን ለማከም ለሚደረገው ጥረት ትልቅ ተስፋ ነው።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You