ዜጎችን የቤት ባለቤት ማድረግን ያለመው አዲስ መንገድ

መንግሥት በከተሞች በተለይ በአዲስ አበባ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለመመለስ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት በተመጣጣኝ ክፍያ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያለውን የማህበረሰብ ክፍል ለመድረስ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

የዜጎችን የመኖሪያ ቤቶች ፍላጎት ለመመለስ የተለያዩ ዓይነቶች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን መገንባቱን በማጠናከር፣ በማህበር ተደራጅተው ቤት ለሚያለሙ እንዲሁም የግሉ ዘርፍ በሪል ስቴት ልማት እንዲሰማራ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ሰርቷል፡፡

እንዲያም ሆኖ ግን የቤቶች ልማቱና ፍላጎቱ ሰፊ ክፍተት እየታየበት ይገኛል፡፡ ዜጎች መሠረታዊ ፍላጎት የሆነውን የመኖሪያ ቤት በአቅማቸው ልክ ገዝተው ለመኖር አዳጋች ሆኖባቸዋል። የቤት ባለቤት ለመሆን በአንድ ጊዜ የግዴታ ሚሊዮኖችን ማውጣት አሊያም ከአቅም በላይ ብድር ውስጥ መዘፈቅ ውስጥ መግባት የግድ እስከ መሆን ደርሷል።

በቅርቡ ደግሞ ይህን ችግር በአዲስ አማራጭ ለመፍታት ከግል ባለሀብቶችና ማህበራት ጋር ለመሥራት በሩን ክፍት አድርጓል። በግልና መንግሥት አጋርነት የቤቶች ልማት ሥራው ተጀምሯል፡፡ አካሄዱ በፍጥነትና በዝቅተኛ ወጪ የመኖሪያ ቤት ችግርን ማቃለል ያለመ ነው።

ይህንን ተከትሎ በርካታ ባለሀብቶች፣ አልሚዎች፣ ማህበራትና አዳዲስ ሃሳብ ያላቸው ግለሰቦች ዜጎችን የመኖሪያ ቤት ባለቤት ማድረግ የሚያስችሉ ስልቶችን ይዘው እየመጡ ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ኪ ሀውሲንግ ፋይናንስ ሶሉሽን አንዱ ነው። ይህ ድርጅት የማህበረሰቡን የቤት ባለቤት የመሆን ፍላጎት የሚፈታ የፋይናንስ አማራጭ ይፋ አድርጓል። በመጀመሪያው ዙርም ለተመዝጋቢዎቹ በእጣ ቤት አስረክቧል። የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው የስኬት ዓምዱ የድርጅቱ መስራች አባልና ሥራ አስኪያጅ ከሆኑት አቶ ግሩም ይልማ ጋር ባደረገው ቆይታ፣ አቶ ግሩም ‹‹ኪ ሀውሲንግ›› በተሰኘው ኩባንያቸው አዲስ መንገድ ያሉትን የቤቶች ልማት ይዘው መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ ግሩም ይልማ ተወልደው ያደጉት በኢትዮጵያ ቢሆንም ለ32 ዓመታት በውጭ ሀገር ኖረዋል። ለ20 ዓመት በእንግሊዝ ለንደን በቀሪዎቹ ዓመታት ደግሞ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት ኑሯቸውን አድርገው ነበር። የአርክቴክቸር፣ የግራፊክስ ዲዛይንና ኮንስትራክሽን ትምህርቶችን ተከታትለዋል።

ይሁን እንጂ ተቀጥሮ ከመሥራት ይልቅ የሥራ ፈጣሪነት (Entrepreneur) ዝንባሌ አድሮባቸው ወደ ንግዱ ዓለም ተቀላቀለዋል። የኩነት ዝግጅት (Event Organizing)፣ ሬስቶራንት፣ የኦላይን ቲሸርት ብራንድ (T- Shirt e-commerce)፣ ከቻይና ወደ አሜሪካ እቃ እያስመጡ ከመሸጥ ጀምሮ በነበሩባቸው ሀገራት በርከት ባሉ የንግድ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ሰርተዋል።

አቶ ግሩም ለውጡን ተከትሎ በተፈጠረው ምቹ አጋጣሚ ወደ ሀገራቸው እንደገቡና ማህበረሰቡን ይጠቅማል ወዳሉት ሥራ መሰማራታቸውን ይናገራሉ። በሂደቱም ዓባይ ቲቪን (የቴሌቭዥን ጣቢያን) በግላቸው መመስረታቸውን ይገልፃሉ። በሚዲያ ሥራ ላይ ብቻ ያልተገደበው የሥራ ፈጠራ ተግባራቸው ወደ ሌሎችም ተግባራት እንዲያተኩሩ ስላስገደዳቸው በሀገሪቱ ቁልፍ ችግር ተደርጎ በሚወሰደው ‹‹የመኖሪያ ቤትን በቀላል ዋጋ የማግኘት ችግር›› ላይ እንዲያተኩሩ አደረጋቸው። በዚህም ከሌሎች አራት ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ኪ-ሀውሲንግ ፋይናንስ ሶሉሽንን መሠረቱ።

‹‹ዋናውን የማህበረሰብ ችግር መፍታት ሲቻል ትልልቅ ኩባንያዎችን መመሥረት ይቻላል›› የሚሉት አቶ ግሩም፣ በዚህ እሳቤ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች የቤት ባለቤት ለመሆን ሲሹ የሚያጋጥማቸውን የገንዘብ እጥረት ሊፈታ የሚችል ስልት (strategy and model) ድርጅታቸው በመፍጠር ወደ ተግባር መግባቱን ይናገራሉ።

ንግድ ማለት የማህበረሰቡን ችግር መፍታት እንደሆነ የሚያምኑት አቶ ግሩም፤ ከመሥራች አባላቱ ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያለው ማህበረሰብ የመኖሪያ ቤት ባለቤት መሆን ያልቻለበትን ምክንያት በቅድሚያ በጥልቀት አስጠንተዋል። በዚህም መሠረታዊ ችግሩ የቤት እጥረት ሳይሆን የገንዘብ ችግር እንደሆነ ማወቅ ችለዋል።

ችግሩን በልዩ አስተሳሰብና መንገድ ለመፍታት በማሰብ የማህበረሰቡን የፋይናንስ ችግር ሊቀርፍ የሚችል ሞዴልም ተፈጠረ። በሀገራችን ባህል የሚታወቀውን እቁብ፣ የኪራይና በሌሎች የዓለም ሀገራት ተግባራዊ የሚደረገውን የባንክ ብድር (mortgage) በአንድ ላይ በማዋሃድ ኪ የቤቶች የጋራ ፈንድ (Key – Common Housing Fund) (KEY – CHF) ሞዴልን ድርጅታቸው መፍጠሩን የሚገልፁት ሥራ አስኪያጁ፤ መርሀ ግብሩ በአነስተኛ መነሻ ክፍያና ለሰላሳ ዓመት በሚቆይ ወርሃዊ መዋጮ የሚተገበር መፍትሔ መፍጠር የቻለ እንደሆነ ያብራራሉ። መነሻ ክፍያውም 83 ሺህ 145 ብር እንደሆነ እና እድለኛው እጣ (ቤት ለመገዛት የሚያስችል እቁብ አሊያም የተጠራቀመ ገንዘብ ልንለው እንችላለን) እስኪወጣለት ድረስ ከሁለት ሺህ ብር ጀምሮ ወርሃዊ ቁጠባ እንደሚያደርግ ይገልፃሉ። በዓመት ሁለት ጊዜ በሚወጣው እጣ እድለኛ የሆነው ሰውም (ልክ እቁብ እንደሚደርሰው) በመረጠው ከተማ ላይ ቤት እንደሚገዛለት ያስረዳሉ።

ድርጅቱ ደመወዝ ወይም አነስተኛ/መካከለኛ ገቢ ኖሮት ነገር ግን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ቤት መግዛት ለማይችል ሰው አማራጭ እንደፈጠረ የሚናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ የኪ ሀውሲንግ ወይም (KEY – CHF) የንግድ ስልት ከግለሰቦች በጣም ትንሽ፣ ከብዙሃኑ ደግሞ ብዙ ማትረፍን በተመሳሳይ የንግድ ፍልስፍናው ያደረገ መሆኑን ያብራራሉ። በዚህ አካሄድ አብዛኛው ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያለው ዜጋ የቤት ባለቤት እንደሚሆን ይገልፃሉ። የባንኮች ፣ ኢንሹራንስ ኩባንያ እና ሌሎች የቴክኖሎጂና የንብረት አስተዳደር ላይ ያሉ አጋሮቻቸው አብረዋቸው እየሰሩ መሆናቸውንም ይገልፃሉ። ድርጅቱ ከቡና ባንክና ከፀሐይ ባንክ ጋር በአጋርነት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

‹‹አንድ መቶ ሺህ ሰው በአስር ዓመት ውስጥ የቤት ባለቤት እናደርጋለን›› የሚሉት አቶ ግሩም፣ ለዚህም የመልካም አፈፃፀም ዋስትና /Performance Bond/ ከቡና ኢንሹራንስ ጋር መገባቱን ይናገራሉ። በዚህ ስልት ቤት ለመግዛት የሚሰባሰበው የማህበረሰብ ክፍል ለገንዘቡ ደህንነት የማይሰጋበት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ያስረዳሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ በዚህም በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት በሚወጡ አራት እጣዎች ከገበያው ላይ ቤት በመግዛት ለእድለኞች ይሰጣሉ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ከቤት አልሚዎች ጋር በሚደረጉ ስምምነቶች፣ ኪ ሀውሲንግ በሚያስቀምጠው ዋጋ እና የጥራት ደረጃ ተሰርቶ በእጣ እንዲረከቡ ይደረጋል፡፡ ድርጅታቸው ከተመሰረተ በወራት ዕድሜ ውስጥ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እጣ አውጪነትና ዝግጅቱ በመገናኛ ብዙሃን በተላለፈ ቀጥታ ሥርጭት ድርጅቱ በመጀመሪያው ዙር ለ58 ሰዎች ቤት አስረክቧል።

ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያለው ማህበረሰብ መሠረታዊ ችግር ገበያ ላይ መኖሪያ ቤት ማጣት ሳይሆን የገንዘብ መሆኑን የጠቀሱት ሥራ አስኪያጅ፣ ይህንን ችግር የሚፈታ የእቁብ ፅንሰ ሃሳብ ከቤት ብድር /Mortgage/ ጋር በማዋሃድ ዜጎች በረጅም ጊዜ ክፍያ ቤት የሚያገኙበትን እድል መፍጠር መቻሉን የድርጅቱ ስኬት መሆኑን ገልጸውታል፡፡

ሥራ አስኪያጁ እንዳብራሩት፤ ድርጅቱ ከተመሠረተ በጥቂት ወራት ውስጥም 17 ሺህ የሚደርሱ ተመዝጋቢዎችን አሰባስቧል፤ በቀጣይ ሶስት ወራት 100 ሺህ ቤት ፈላጊዎችን መዝግቦ በማጠናቀቅ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ሁለተኛ ዙር እጣ ለማውጣት እየሠራ ይገኛል፡፡ ይህን ዕቅድ ለማሳካትም ከማህበራት፣ ከተቋማት እና ከሌሎችም ጋር መኖሪያ ቤት ፈላጊዎችን የማስተባበር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል።

‹‹አዲስ አስተሳሰብ ይዘን ነው የመጣነው›› የሚሉት አቶ ግሩም፤ ይህንን ፅንሰ ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ መሬት ለማውረድ ከመንግሥት ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የመኖሪያ ቤት እጥረት ሀገራዊ ችግር እንደሆነ በማንሳት የግሉ ዘርፍ ችግሩን ለመፍታት ተሳታፊ እንዲሆን በተጋበዘው መሠረት ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያለው የማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንዲሆን ኪ ሃውሲንግ ፋይናንስ ሶሉሽን ኪ የቤቶች የጋራ ፈንድ (Key – CHF) ስልቱን ይዞ መምጣቱንም ያስረዳሉ። በቀጣይ ዓመታት ስለመቶ ሺህ ብቻ ሳይሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ስለማስቻል መነጋገርና ጠንክሮ መሥራት ይገባል ይላሉ።

እሳቸው እንደተናሩት፤ የኪ ሀውሲንግ ፋይናንስ ሶሉሽን ዋና ዓላማ ማህበራዊ ኃላፊነትን (corporate social responsibility) መወጣት ነው፤ የህብረተሰቡን ቁልፍ የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት አዲስ የረጅም ጊዜ ክፍያ አማራጭ ከመፍጠሩም ባሻገር ሌሎች ተመሳሳይ የማህበረሰቡን ችግሮች የሚያቃልሉ የበጎ ፍቃድ ተግባራት ላይም ይሳተፋል።

በዚህም ለአዲስ አበባ ማኅበራዊ ትረስት ፈንድ 300 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል ሲሉ ጠቅሰው፣ በቅርቡ ለተጀመረው ‹‹ለፅዱ ኢትዮጵያ›› ሀገራዊ ንቅናቄም 100 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል። በጥቅሉ ማህበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ተግባር ድርጅቱ የተመሰረተበት ቁልፍ እሴት (core value) እንደሆነም ይገልፃሉ።

በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ ላለፉት ዓመታት ስኬታማ ጉዞ ያደረጉት አቶ ግሩም፣ ከዚህ በኋላ በሚኖራቸው ጊዜ ከሌሎች አባላት ጋር በመሆን ሀገራቸውን ለማገልገል የሚያስችሉ አዳዲስ ሃሳቦች ላይ ለመሰማራት ወስነው ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ኑራቸውን ማድረጋቸውን ይገልፃሉ። ከማህበረሰቡና ከመንግሥት ጋር በመደጋገፍ ችግር ፈቺ የሥራ ፈጠራዎች ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግም ይገልፃሉ።

የቤት ፈላጊው ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድ መገንዘባቸውን ጠቅሰው፣ በየጊዜው የቤት ፈላጊውን ቁጥር ፍላጎት በሚያሳካ መልኩ ድርጅቱም በረጅም ጊዜ እቅዱ ተጨማሪ ፕሮጀክቶችን የመተግበር ራእይ ሰንቆ ጉዞውን በስኬት መንገድ ላይ መጀመሩን ነግረውናል።

‹‹የራሱን የሥራ ፈጠራ ለመጀመር የሚያስብ አዲሱ ትውልድ መነሻ ሃሳቡ መሆን ያለበት ከማህበረሰቡ ቁልፍ ችግሮች ነው›› የሚሉት አቶ ግሩም፤ እያንዳንዱ ችግር የንግድና የሥራ ፈጠራ ሃሳብ መሆኑን ይገልፃሉ። ወጣቶች በዚህ ላይ አተኩረው በመሠረታዊነት የለዩትን ችግር የሚፈታ መፍትሔ መፍጠር ሲችሉ ስኬታማ ንግድ መመሥረት እንደሚችሉ አመልክተው፣ በዚያ ላይ እንዲያተኩሩ ምክረ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ። ንግድ ሁሉ ለቅንጦት የሚሆኑ ጉዳዮች ላይ ማጠንጠን እንደሌለበትም ተናግረው፣ ወደፊት እንዳንራመድ እንቅፋት የሆኑትን ችግሮች መፍታት ላይም ማተኮር እንዳለበት ያስረዳሉ።

‹‹የትኛውን የማህበረሰብ ችግር መፍታት እችላለሁ?›› የሚለውን ጥያቄ ወጣቶች መመለስ ከቻሉ እና በዚያ ላይ ጊዜና እውቀታቸውን ተጠቅመው ከሰሩ ስኬታማ እንደሚሆኑም ይናገራሉ። በየትኛውም ዓለም ላይ የሚፈጠሩ ታላላቅ ኩባንያዎች መነሻቸውን ያደረጉት ችግር መፍታት ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ እንዲህ ዓይነት ኩባንያዎች ዛሬ ትልቅ ቦታ መድረሳቸውንም ይገልፃሉ። እነዚህን ኩባንያዎችና ተቋማት ወጣቶች በምሳሌነት መውሰድ ይገባቸዋል ይላሉ። በዚህ ላይ ትጋትና ቁርጠኝነትን መጨመር እንደሚያስፈልግም ይገልፃሉ።

‹‹እኛ ልንፈታው የመረጥነው ችግር በጣም ከባዱን ነው›› የሚሉት አቶ ግሩም፤ እስካሁንም ዘላቂ መፍትሔ ያልተበጀለት በክብደቱ ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ። አስፈላጊውን መስዋዕትነት በመክፈል የበኩላቸውን ዐሻራ በመጣል እንደሚያሳኩትና መፈክራቸውንም “ቀላል ነው!” እንዳሉት ገልጸውልናል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You