የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት በአንድ ቻይና መርህ እይታ

ሕዝባዊት ሪፐብሊክ ቻይና በዓለም ደረጃ ተፅኖ መፍጠር በሚያስችል አቅም እየመጣች ያለች ሀገር ናት። ከአርባ ዓመታት በፊት ከድህነት ለመውጣት ስትፍጨረጨር የነበረች ይህች ሀገር ፣ አሁን ላይ በስኬት የምትጠቀስና ብዙ ነገር ሞልቶ የተትረፈረፈባት ሀገር ሆናለች። ድህነትን በመቅረፍ ረገድ ያሳየችው ስኬት፣ በዓለም ዙሪያ እስካሁን ድረስ ከድህነት ጋር እየታገሉ ላሉ ሀገራት ጥሩ ትምህርት መሆን የቻለ ነው። ሀገሪቱ በኢኮኖሚ አቅሟ እያደገች በመጣች መጠን በዓለም ዙሪያ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም በዚያው ልክ እያደገ ይገኛል። በተለይ ታዳጊ ሀገራት ከቻይና ጋር መልካም ወዳጅነት መመስረትን እንደ መልካም አጋጣሚ አድርገው እየወሰዱት ይገኛሉ።

ቻይና ከየትኛውም ሀገር ጋር በምታደርገው ግንኙነት የአንድ ቻይና መርህ እንደ ቅድመ ሁኔታ ታስቀምጣለች ። ይህ መርህ የደሴት ግዛት የሆነችው ታይዋን ከታሪካዊም ሆነ ሕጋዊ መከራከሪያ አኳያ የዋናው ቻይና አካል መሆኗን የሚያመላክት ነው። ከዚህ የተነሳ ሁሉም ሀገር ይህንን እውነታ ተቀብሎ እውቅና እንዲሰጥ የቻይና ፍላጎት ነው። በተለይ የሕዝባዊት ሪፐብሊክ ቻይና ከተቋቋመበት እ.አ.አ. ከ1949 ወዲህ ይህ መርህ በቻይና በኩል ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል።

ነገር ግን በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ወቅት በሀገራት መካከል ከነበረው ርዕዮተ-ዓለማዊ ፉክክር እና አሁን ደግሞ እያደገ ከመጣው ጂኦፖለቲካዊ ፉክክር የተነሳ በአንድ ቻይና መርህ ዙሪያ የተለያዩ ሀገራት የተለያዩ አቋሞችን ሲያንፀባርቁ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ከ1971 (እ.አ.አ) ወዲህ የአንድ ቻይና መርህን ተቀብላ ለቤጂንግ መንግሥት እውቅና ሰጥታለች። ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላም በዚሁ የአንድ ቻይና መርህ መሠረት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማጠናከር ችለዋል።

ከ1991 (እ.አ.አ) ወዲህ የነበረው አስር ዓመት ለሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነቱ መደላደል የተፈጠረባቸው ናቸው። ከአዲሱ የፈረንጆች ሚሊኒየም ጀምሮ ባሉት ዓመታትም ሀገራቱ በፖለቲካዊና፤ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጠንካራ ግንኙነት መመስረት የቻሉበት ነው። በዚህም ኢትዮጵያ የእድገት ፖሊሲ ቀርፃ መንቀሳቀስ ስትጀምር ቻይና ሁነኛ አጋር ለመሆን ችላለች።

በሀገራቱ መካከል በዚህ ደረጃ የሚገለጽ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት መመሥረት የተቻለው በአንድ ቻይና መርህ ላይ ኢትዮጵያ ጠንካራ አቋም መያዝ በመቻሏ ነው። የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ አካሄድ በቅርበት ለሚመለከት ፣ በአንድ ቻይና መርህ ጉዳይ ዙሪያ ብዙ መልእክቶች ያሉት ነው። የዚህ አጭር ፅሁፍ ዓላማም ኢትጵያጵያ በቻይና ጉዳይ ለያዘችው የአንድ ቻይና መርህ አስረጅ ሊሆኑ የሚችሉ ሶስት ጉዳዮችን ማቅረብ ነው።

  1. ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለተፈጠረው የዓለም ሥርዓትና ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደረግ ያልተቋረጠ ድጋፍ

ኢትዮጵያ ገና የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ሀገራት በመተባበር ደህንነታቸውን ማስጠበቅና ዓለምን ለሰው ልጆች ሁሉ ምቹ መኖሪያ ማድረግ ይቻላል የሚለውን አስተሳሰብ መነሻ በማድረግ የሊግ ኦፍ ኔሽንን ልትቀላቀል ችላለች። በዚህ ወቅት አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ውስጥ ስለነበሩ አፍሪካዊ ትብብርን መመሥረት አስቸጋሪ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ሊጉ ለማቅናት ተገዳለች።

በሊጉ አባል በነበረችበት ወቅትም ወረራ እንዳይፈፀምባትና ደህንነቷ እንዲጠበቅ ማድረግ የምትችለውን ሁሉ ለማድረግና ድምጿን ለማሰማት ችላለች። ሊጉ የተመሠረተው በደህንነት ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመቆም የነበረ ቢሆንም ፣ የትኛውም አባል ሀገር ለኢትዮጵያ ድምፅ ጆሮ ለመስጠት ፈቃደኝ አልሆነም ፤ በዚህም ኢትዮጵያን ከጣልያን ወረራ ሊታደጋት አልቻለም።

እ.አ.አ ከ1939 እስከ 1944 ድረስ ጣልያን ኢትዮጵያን እንደወረረችው ሁሉ፣ ጃፓንም ቻይናን ወርራ ነበር። ሁለቱም ወራሪ ሃይሎች ታዲያ ከ1943 ጀምሮ ሃይላቸው እየከዳቸው ስለመጣ ይዞታቸውን እንዲለቁ እየተገደዱ ነበር። በዚህ ወቅት የቻይና ሪፐብሊክ፣ የአሜሪካ እና የእንግሊዝ መንግሥት መሪዎች በካይሮ ተገናኝተው የጃፓን ወረራ ስለሚቀለበስበትና የቀደሙ የቻይና ግዛቶች ስለሚመለሱበት ሁኔታ መምከር ቻሉ።

በውይይታቸው ማብቂያ ላይ ባወጡት የካይሮ ዲክላራሲዮን መሠረት፣ ጃፓን ከአንደኛው የዓለም ጦርነት መጀመሪያ፣ ከ1914 ጀምሮ የያዘቻቸውን በፓስፊክ ውቅያኖስ የሚገኙ ደሴቶችን እና ከቻይና የሰረቀቻቸውን ሁሉንም ግዛቶች እንደምትነጠቅና ለቻይና ሪፐብሊክ እንዲመለሱ እንደሚደረግ ይደነግጋል።

ይህ ካይሮ ላይ የተደረሰው ስምምነት ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ በኤስያና ፓስፊክ ቀጣና ሊመሠረት ስለታሰበው ሥርዓት እንደ ፍኖተ-ካርታ ሆኖ ያገለገለ ነው። በተለይ ለቻይና ብዙ በጎ እድሎችን የሚያጎናፅፍ ነበር። እነዚህ የሶስት ሀገራት መሪዎች በተመሳሳይ መልኩ በ1945 በድጋሚ ተገናኝተው ጃፓን እጅ ስለምትሰጥበት መንገድ እየተወያዩ ነበር።

በመጨረሻ ላይ ባወጡት ፖትስዳም ዲክላራሲዮን መሠረት ለጃፓን የቀረበላት አማራጭ በሰላም እጅ መስጠት ወይንም የሶስቱ ሀገራት ጥምር ጦር ለሚያደርሰው የመጨረሻ ጥቃት እንድትዘጋጅ ነበር። ከዚህ ጎን ለጎን ቻይናን በተመለከተ በዲክላራሲዮኑ አንቀፅ 8 ላይ ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ የካይሮ ዲክላራሲዮን ላይ የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊ እንደሚደረግ ይደነግጋል።

ጃፓንም ብዙም ሳትቆይ ስለተሸነፈች ጦርነቱ በአጭር ጊዜ ሊቋጭ ችሏል። ከዚህ የተነሳ ቻይና ነባር ግዛቶቿን ለማስመለስና አዲስ በተመሠረተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል የመሆን እድልን አግኝታለች። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሲመሰረት ኢትዮጵያም አባል በመሆን በንቃት መሳተፍ እንደጀመረች የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ።

ከቻይና ጋር የነበራት ግንኙነትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሳኔዎችንና መርሆዎችን የተከተለ ነበር። እ.አ.አ በ1970 ኢትዮጵያና ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት ከጀመሩበት ጊዜ እና በ1971 የመንግሥታቱ ድርጅት ቻይናን በተመለከተ ሪዞሊሽን 2758ን ካሳለፈ ወዲህ ኢትዮጵያ የአንድ ቻይና መርህን ስትደግፍ ቆይታለች።

የ2758 ውሳኔ ዋና ሃሳብ የሚያተኩረው የሕዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ ሕጋዊው የቻይና ወኪል እንደሆነና ከዚህ በፊት የቻይና ሪፐብሊክ መንግሥት ይጠቀምባቸው የነበሩ መብቶችና ጥቅሞች በሙሉ ለሕዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ መንግሥት እንዲተላለፉ ያስቀምጣል። ኢትዮጵያም ይህንን ውሳኔ በመቀበልና በመተግበር ለመንግሥታቱ ድርጅት ያላትን ታማኝነት እያሳየች ትገኛለች። ለድርጅቱ ውሳኔ ካላት ቁርጠኝነት በተጨማሪ ከቻይና ጋር ለጀመረችው የሁለትዮሽ ግንኙነትም ውሳኔውን መተግበሯ ትልቅ እገዛ አድርጓል።

  1. የቻይና የውስጥ ጉዳይ እስከሆነ ድረስ ለቻይና መተው ያስፈልጋል

ቻይና የጃፓንን ወረራ ለመቀልበስ ስታደርገው የነበረው ጦርነት በ1945 በጃፓን ተሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል። በጊዜው የቻይና መንግሥት ይመራ የነበረው በኮሚንታንግ ፓርቲ አማካይነት ነበር። ይህ ፓርቲ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ በአብዮታዊ ተዋጊዎች የሚደርስበትን ጫና መቋቋም ባይችልም እስከ 1949 ድረስ በሥልጣን ለመቆየት ችሏል።

በ1949 በቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የሚመራው ጦር ቤጂንግን በመቆጣጠር የሕዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ መንግሥትን መሠረተ። የኮሚንታንግ መንግሥት በበኩሉ የቻይና ደሴት ወደሆነችው ወደ ታይዋን በመሸሽ የቻይና ሪፐብሊክ የሚል መንግሥት መስርቶ ሥልጣኑን ሊያስቀጥል ችሏል። ታይዋን ውስጥ የተመሠረተው መንግሥት ዓለምአቀፋዊ እውቅናን ማግኘት የቻለ መንግሥት ስለነበር ለቻይና የተሰጡ መብቶችንና ጥቅሞችን ሁሉ የመጠቀም እድል ነበረው።

ከዚህ የተነሳ የፀጥታው ምክር ቤት መቀመጫን ለመያዝና ለሕዝባዊት የቻይና ሪፐብሊክ እውቅና ካልሰጡ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማድረግ ችሏል። ቤጂንግ ላይ መቀመጫውን ያደረገው የሕዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ መንግሥት በበኩሉ ለታይዋን የተሰጠውን እውቅና የራሱ ለማድረግ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ነበር።

ከዓመታት ጥረት በኋላ የመንግሥታቱ ድርጅት ባሳለፈው ሪዞሊሽን 2758 መሠረት የሕዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ መንግሥት ሕጋዊ እውቅናን ሊያገኝ ችሏል። ከዚህ በኋላ የቤጂንግ መንግሥት ሕጋዊው የቻይና መንግሥት በመሆን ታይዋንን ጨምሮ በመላው ቻይና ላይ ሕጋዊ መንግሥት እንደሆነና በታይዋን ላይም የማይገረሰስ መብት እንዳለው ማረጋገጫን አግኝቷል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ውሳኔን ተከትሎ የሕዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ መንግሥት በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫን ከመውሰዱ በተጨማሪ ሕጋዊ ግንኙነቶችን ከተለያዩ ሀገራት ጋር ማድረግ የሚችልበትን መብት ወስዷል። የቻይና መንግሥት ጥረቱን በመቀጠል ታይዋንን ሙሉ በሙሉ ወደ ቻይና ለማካተት የተለያዩ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

ከሌሎች ሀገራት ጋር በሚያደርገው ግንኙነትም በቅድሚያ የሚነሳው አጀንዳ የአንድ ቻይና መርህ እንዲሆን አድርጓል። በቤጂንግና በታይፔ መካከልም ተከታታይ የሆኑ ፖለቲካዊ ድርድሮችና ውይቶች እየተደረጉ ይገኛል። ከ1971 ጀምሮ እስካሁን ድረስ በሁለቱ መንግሥታት አንዳንዴ በከፍተኛ ፖለቲካዊ አመራሮች መካከል፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ በኤክስፐርቶች መካከል የፖለቲካዊ ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል።

አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ውይይቶች የተራራቁ አቋሞች የሚንፀባረቁባቸው ሲሆኑ በሌላ ጊዜ ደግሞ የተሻለ መቀራረብ ይታይባቸዋል። ይህ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ከታይዋን ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች በሙሉ የቻይና የውስጥ ችግር መሆናቸውን ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያ በአንድ ቻይና መርህ ዙሪያ እንኳን የተለየ አቋም ልታራምድ ቀርቶ በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠትም አይጠበቅባትም።

እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ ለአንድ ቻይና መርህ ያሳየችው ወጥ አቋም ከቻይና ጋር ለምታደርገው ግንኙነት ትልቅ አቅም ሆኖላታል። በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ቅኝት በባህሪው በሌሎች ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ተሞክሮ የለውም። ኢትዮጵያ ከየትኛውም ሀገር ጋር የምታደርገው ግንኙነት በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ አለመግባት ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌ ጭምር ነው።

ይህ ማለት ደግሞ በሕገመንግሥታዊ አግባብ ወደ ሥልጣን የሚመጣ የትኛውም መንግሥት ሕገመንግስቱ ያስቀመጠውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መርሆዎች አክብሮ እንዲሄድ ያስገድደዋል። ከዚህ የተነሳ ወደፊትም ቢሆን ኢትዮጵያ በቻይና የውስጥ ጉዳይ ላይ አትገባም ማለት ይቻላል።

ማንም ሀገር ከሌላ ሀገር ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት ለመመስረት በሚነሳበት ወቅት አጋር ሊሆን የሚፈልገው ሀገር ፍላጎቶቹንና የዚያን ሀገር ስስ ፖለቲካዊ ጉዳዮች በመለየት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንደሚያደርግ ይታወቃል። የጋራ የሆኑ ፍላጎቶችን ከተናጠላዊ ፍላጎቶች መለየትና በጋራ ጉዳዮች ላይ ተባብሮ ለመሥራት መንቀሳቀስም ከዲፕሎማሲ የሚጠበቅ ጥበብ ነው።

ሀገራት በሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ላይ ተናጠላዊ ጉዳዮች ወይም የአንዱ ሀገር የራሱ ብቸኛ ፍላጎት ላይ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ሊያውኩ እንደሚችሉ ስለሚያውቁ ተናጠላዊ ጉዳዮችን ወደ ጎን በማለት የጋራ ጉዳዮች ላይ አተኩረው ይሠራሉ። የኢትዮጵያና የቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነትም የቻይናን ተናጠላዊ ፍላጎት ለቻይና በመተው የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መመሥረቱ ለሁለትዮሽ ግንኙነቱ መጠናከር ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል።

  1. በሁለቱ ሀገራት መካከል የልማት ትብብር እየጨመረ ይገኛል

ኢትዮጵያ በፈጣን እድገት ላይ ያለ ኢኮኖሚ ያላት መሆኑ ከሌላ ሀገር ጋር በምታደርገው ግንኙነት ለልማት ትብብር ቅድሚያ መስጠቷ ተፈጥሯዊ አካሄድ ነው። የልማት ትብብር ሲባል ከእርዳታና ድጋፍ በተጨማሪ ሌሎች ጉዳዮችንም ያካትታል። ለልማት የሚያስፈልገውን ገንዘብ በኢንቨስትመንት መልኩ ወይንም በብድር መልኩ ማግኘት የልማት ትብብር አንዱ አካል ነው።

ከዚህ አኳያ የቻይናና የኢትዮጵያ የሁለትዮሽ የልማት ትብብር ረጅም ርቀት ተጉዟል። በአሁኑ ሰአት ለሥራ እድል ፈጠራ፣ ለከተሜነት እድገት እና የፋይናንስ እጥረትን ለመቅረፍ የሚረዳው ውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በአብዛኛው የሚመጣው ከቻይና ነው። የቻይና ኩባንያዎች አትዮጵያ ውስጥ እንደ መንገድና የባቡር መስመር፣ ሰማይ-ጠቀስ ህንፃዎች፣ የቴሌኮም መሠረተ-ልማት፣ እንዲሁም በሃይል ማመንጫ ግድቦች ግንባታ ላይ በስፋት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚደረገው የንግድ ልውውጥም ከአመት ወደ አመት መጠኑ እየጨመረ ይገኛል። እንደዚህ አይነቱ የልማት ትብብር ግለቱን ጠብቆ እንዲሄድ አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ ለኢትዮጵያ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ለቻይናም ቢሆን የኢትዮጵያ ታዳጊ ኢኮኖሚና ሰፊ የሕዝብ ብዛት ትልቅ የገበያ እድል ይፈጥርላታል።

በርግጥ እንደዚህ አይነት የልማት ትብብር እያደገ የመጣው እ.አ.አ በ2000 የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም (ፎካክ) ከተመሠረተ ወዲህ መሆኑ ይታወቃል። ከፎረሙ ምሥረታ በኋላ ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት በአንድ ቻይና መርህ መሠረት ማጠናከር ጀምራለች። ኢትዮጵያም የፎረሙ አባል እንደ መሆኗ መጠን ከቻይና ጋር ያላትን ግንኑነት ሁለቱንም ሀገራት ሊጠቅም በሚችል መልኩ እያስኬደችው ትገኛለች።

የአንድ ቻይና መርህ ለቻይና የውጭ ግንኙነት የማይነቃነቅ መሠረታዊ መርህ ነው። ይህን መርህ የሚቀበል የትኛውም ሀገር ከቻይና ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ አይቸግረውም። ኢትዮጵያም የቻይናን ፍላጎት መነሻ በማድረግና በየትኛውም ሀገር የውስጥ ጉዳይ ላይ የመግባት ፍላጎት የሌላት መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ከቻይና ጋር በአንድ ቻይና መርህ መሠረት የሁለትዮሽ ግንኙነቷን አጠናክራ እየቀጠለች ትገኛለች። ወደፊትም ቢሆን ሁለቱ ሀገራት በጋራ ጉዳዮች ላይ አተኩረው እስከሠሩ ድረስ ግንኙነታቸውን ከማጠናከር ሊገታቸው የሚችል ነገር አይኖርም ብሎ መደምደም ይቻላል።

ዳርእስከዳር ታዬ (ፒኤችዲ)

አዲስ ዘመን ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You