‹‹አሠሪዎችና ሠራተኞች በውይይት ችግሮቻቸውን ሲፈቱ ሰላሙ የተረጋገጠ ምርታማ ኢንዱስትሪ ይፈጠራል›› – አቶ ካሣሁን ፎሎ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት

በሥሩ 2ሺ303 ተቋማት ወይም ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የተቋቋሙ ሠራተኛ ማህበራትና ወደ አንድ ሚሊየን የሚደርስ አባላት ያለው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) የሠራተኞችን በነፃነት የመደራጀት፣ መብትና ጥቅሞቻቸውም እንዲከበሩላቸው እየሠራ ያለ ተቋም ነው። ይዞ የተነሳቸው ዓላማዎቹን ለማሳካት ምን ያህል ርቀት እንደተጓዘ፣ ስኬቶቹን፣ የኢንዱስትሪው ሰላምና መረጋጋት በምን ሁኔታ ውስጥ እንደሆነ ከኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሣሁን ፎሎ ጋር ያደረግነው ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ፡-

አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ በየዓመቱ እየተከበረ ስላለው ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን (ሜይዴይ) መነሻና ፋይዳው ያስታውሱን?

አቶ ካሣሁን፡- ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀንን ለማክበር መነሻ የሆኑት፤ ከኢንዱስትሪ አብዮት ጀምሮ በሠራተኛ ላይ የሚደርሱ በደሎች፤ ያለረፍት ለረጅም ሰዓት መሥራት፣ የደመወዝ ክፍያ አነስተኛ መሆን፣ የሙያ ደህንነት አለመጠበቅና የዓመት ዓረፍትም አለመኖር ዋነኞቹ ናቸው። ጉዳት ሲደርስባቸውም የጉዳት ካሳ አለማግኘት እና በደል ደርሶባቸውም የሚያሰራቸው ኩባንያ ያለምንም ካሳና ክፍያ ሲያባርራቸው መቆየቱም ሌላኛው ምክንያት ነው።

እንዲህ ያሉ በአሠሪዎች የሚደርሱ በደሎችን ለመቃወም ሠራተኞች እንቅስቃሴ ጀመሩ። እንቅስቃሴው የተጀመረውም በኢንዱስትሪ በበለፀጉ ሀገሮች ሲሆን፤ ፈር ቀዳጆቹ በአሜሪካን ሀገር ውስጥ በሚገኙ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ናቸው። በሂደት ወደ ካናዳ፣ አውሮፓና ሌሎች ሀገሮች እንቅስቃሴው ተዛምቶ የኢንዱስትሪ ሠራተኞች በተለያየ መልኩ ትግላቸውን ሲያካሂዱ ቆዩ።

ሠራተኛ ማህበር የሚመስል ግን ደግሞ እውቅና የሌለው ማህበር አቋቁመውም ነበር። ቆይተው ደግሞ የጋራ የሆነ ህብረት መፍጠር ሞከሩ፤ ሠራተኞች ከሚደርስባቸው ጭቆና ለመውጣት፤ እ.ኤ.አ በ1884 የሥራ ማቆም ርምጃ ወሰዱ። ብዙ ትግልም አደረጉ። ሆኖም ግን የሥራ ማቆም ርምጃው ሕጋዊ የሆነ ሽፋን አልነበረውም። ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ የነበረው፤ የሥራ ማሽኖችንም በመስበር ጭምር ነበር ።

ይወስዱ በነበረው የኃይል ርምጃ፣ ሠራተኞችን አደራጅታችኋል፣ አስተባብራችኋል በሚል ብዙዎች ታሰሩ። በአደባባይ በስቅላት እንዲቀጡ የተወሰነባቸውም ነበሩ። ለመብታቸው ሲታገሉ እንዲህ የተለያየ በደል የደረሰባቸውን ሠራተኞች ለማሰብ እ.ኤ.አ በ1886 ሜይ አንድ ቀን በካናዳና በአፍሪካ ያሉ ሠራተኞች የጋራ ጉባኤ አካሄዱ። ጉባኤው በአደባባይ ላይ የተሰቀሉ ሰዎች እንዲዘከሩ ውሳኔ አሳለፈ። በዓሉ በየዓመቱ ሜይ አንድ ቀን መከበር የጀመረው ግን እኤአ በ1890 ጀምሮ ነው።

የበዓሉ ዓላማም፤ ለሠራተኞች መብት ሲታገሉ መስዋዕት የሆኑ ሰማዕታትን ማሰብና ለወደፊቱ ደግሞ የትግል ቃል ኪዳንን ለማደስ ነው። በተጨማሪም በዓሉ በየዓመቱ ሲከብር ሠራተኞች ያሉባቸው ችግሮች ጎልተው እንዲወጡ ይደረጋል። በዓሉ መከበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ሀገራት በተለያዩ መሪ ሃሳቦች ሲከበር ቆይተዋል። የዓለም የሠራተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲከበር ዘንድሮ ለ135ኛ ጊዜ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ49ኛ ጊዜ ነው።

የበዓል አከባበርም እንደየሀገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ ይለያያል። አንዳንድ ሀገራት በፌስቲቫል ደረጃ በማዘጋጀት ሳምንቱን በሙሉ በተለያየ ዝግጅት ያከብራሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ባላቸው ወቅታዊ ችግር ላይ አደባባይ ወጥተው ተቃውሞ ያሰማሉ። ቀኑን ምክንያት በማድረግ በአዳራሽ ውይይት በማካሄድ የሚያከብሩም አሉ።

የሜይዴይ መከበር ፋይዳውን ስናነሳ ደግሞ፤ የሠራተኞች እንቅስቃሴ ሲጀመር፤ ተቃውሟቸውን የሚያሰሙት አደባባይ በመወጣት ነበር። ዛሬ ስለዓለም ሥራ ድርጅት የምናወሳው፣ አሰሪ፣ ሠራተኛና መንግሥት በጋራ ሆነው ማህበራዊ ምክክሮሽ ደረጃ ላይ መድረስ የቻለው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በነበረው ትግል ነው። ትግሉ ገፍቶ በዓለም አቀፍ ደረጃም የመሰባሰብ ሁኔታ መጣ። በጣሊያን በፈረንሳይ፣ በእንግሊዝ፣ በጀርመን በሁሉም ሀገራት ትግሎች ነበሩ።

በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት እ.ኤ.አ. በ1919 ትኩረት የተሰጠው፣ የሠራተኞች ጉዳይ በሰላማዊ ሁኔታ ካልተፈታ በየትኛውም ዓለም ሰላም ሊኖር አይችልም ተብሎ ነበር። ከዚሁ ጎን ሊግ ኦፍኔሽን ተቋቁሞ ነበር። የማቋቋሙ ሃሳብ የተነሳው ከአሜሪካን ነው። የአሠሪ፣ የሠራተኛና የመንግሥት ግንኙነት የሚመራ አንድ ዓለም አቀፍ ተቋም መኖር እንዳለበትም በሊግ ኦፍኔሽን ውይይት ተደረገበት።

እ.ኤ.አ. በ1919 በተባበሩት መንግሥታት ሥር ሆኖ የሚሠራ የዓለም የሥራ ፓርላማ ተቋቋመ። በዓመት አንድ ጊዜ አሰሪ፣ ሠራተኛና መንግሥት በየሀገራቱ የሚወያዩበት እንዲሆን ለማስቻል ነው። ይህ ድርጅትም እንዲፈጠር ያስቻለው ሠራተኞች ያደረጉት ትግል ነው።

ወደ ዘንድሮ ሜይዴይ አከባበር ለመመለስ፤ በተለይም የኢትዮጵያን ጉዳይ ስናነሳ ኢንዱስትሪው ወደኋላ ቀርቶ የጀመርን ቢሆንም፤ በሌሎቹ ሀገሮች የደረሱት ጭቆናዎች በሀገራችንም ደርሷል። በሀገራችን ኢንዱስትሪዎች ማቆጥቆጥ የጀመሩት ኢትዮጵያን በኃይል የወረረው ፋሽስት ጣሊያን ከሀገር ከወጣ በኋላ ነው። አብዛኞቹም ፋብሪካዎች በንጉሣውያን ቤተሰቦች የተያዙ ናቸው።

በዚህ ምክንያትም በሠራተኞች ላይ ከፍተኛ ጭቆና ይደርስ ነበር። ጭቆናው እንዲባባስ ያደረገው ደግሞ በወቅቱ የባሪያ ሽያጭ የነበረበት የፊውዶ ቡሩዣ ሥርዓት ስለነበረ ነው። ይህ ሥርዓት ቢለወጥም ኢንዱስትሪው ውስጥ የነበረው የአሽከርና ሎሌ ዓይነት እንጂ የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት አልነበረም። በወቅቱ ሠራተኛ ማህበር ማቋቋም ወንጀል ነበር። ይህን ችግር ለማስወገድ የኢትዮጵያ ሠራተኞች አማራጭ ያደረጉት በየፋብሪካው ውስጥ እድር ማቋቋም ነበር። ቆይተው ደግሞ ሀገር አቀፍ የሠራተኞች መረዳጃ እድር ብለው ከፍ አደረጉት።

እድሩን የሚመራም መረጡ። ውይይት ሲያደርጉም ያነሱ የነበረው የሥራ ሰዓት መቀነስ እንዳለበት፣ በሌሎች ሀገሮች እንደተደረገው ሁሉ በነፃ የመደራጀት መብታቸው እንዲጠበቅ፣ የሙያ ደህንነታቸውና ጤንነታቸው መጠበቅ እንዳለበት፣ ደመወዛቸው እንዲስተካከል ነው። እነዚህን መብቶቻቸውን እያነሱ የሚወያዩትም በየቤተክርስቲያኑ ውስጥ እና በግለሰቦች ቤት ውስጥ በመገናኘት ነበር።

መረዳጃ እድሩ እያስተባበረ ውስጥ ለውስጥ ትግል ማድረጉ ተጠናክሮ ወደ ሥራ ማቆም ርምጃ ተሸጋገሩ። በ1954 ዓ.ም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ ይቋቋም የሚል ሃሳብ ተነሳ። ይሁን እንጂ የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ የሌላት ሀገር እንዴት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጽሕፈት ቤት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ይቋቋማል? የተሻልን እኛ ነን የሚል ከተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ተቋውሞ ተነሳ። በወቅቱ ኢትዮጵያን ይመሩ የነበሩት ንጉሥ አፄ ኃይለሥላሴ አሠሪና ሠራተኛ ጉዳይን የሚመራ ደንብ በ1954ዓ.ም እንዲወጣ አደረጉ።

ደንቡ ግን ዝርዝር አልነበረም። ደንቡን መሠረት አድርጎ በ1955ዓም ሀገር አቀፍ የሠራተኞች ማህበር እንዲቋቋም ተደረገ። እድሩን ሲመሩ የነበሩት ማህበሩንም እንዲመሩ ተደረገ። መሪዎቹም በዓለም አቀፍ ሠራተኞች ኮንፈዴሬሽን ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስልጠና ተሰጣቸው። ወደ 29 የሚሆኑ ማህበራት የነበሩ ሲሆን፤ የራሳቸውን ምርጫ በማድረግም ከሚያዝያ አንድ ቀን 1955 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማህበር (ኢሠአማ) መሠረቱ።

ሠራተኞቹ ማህበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ወታደራዊ የደርግ አገዛዝ ሥልጣኑን እስኪረከብ ድረስ ከፍተኛ ትግል ሲያደረጉ ነበር። ከሠራዊቱና ከተማሪዎች ቀጥሎ የሠራተኛው ትግል በሶስተኛ ደረጃ የሚገኝ ነበር። በአስመራ፣ በድሬዳዋ፣ በአጠቃላይ ኢንዱስትሪዎች ባሉባቸው ሁሉ በተከታታይ የሥራ ማቆም አድማዎች ይደረጉ ነበር። በወቅቱ የሠራተኛውን መብት ለማስከበር እድር እንዲቋቋም ሃሳብ ከማፍለቅ ጀምሮ በመሪነት ጭምር ከፍተኛ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ አቶ አበራ ገሙ የተባሉ ሰው አይዘነጉም።

ማህበሩን እንዲመሩ ከወንጂ ስኳር ፋብሪካ የተመረጡት አቶ አብረሃም መኮንን ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፤ አቶ አበራ ገሙ ደግሞ የማህበሩ የክብር ፕሬዚዳንት ሆነው በማማከር ያግዙ ነበር። ሆኖም ማህበሩ በሚፈለገው ልክ ሥራውን ለመሥራት ባለመቻሉና የመንግሥትንም ድጋፍ ባለማግኘቱ አቶ አበራ ገሙ ያለውን ሁኔታ መቋቋም ባለመቻላቸውና የሚሆነውም ማየት ባለመፈለጋቸው እራሳቸውን ለማጥፋት ችለዋል። ግለሰቡም እየታወሱ ይኖራሉ።

ወታደራዊው ደርግ ሥልጣን ከያዘ በኋላም ቢሆን፤ ምቹ ሁኔታ አልነበረም። ሀገርን የተቆጣጠረው የወታደሩ ክፍል ነበር። የሠራተኛ ማህበሩ የሠራተኛ ፓርቲ ይባል ነበር። በስፋት የፓርቲ ሥራዎች ይከናወኑበት ነበር። ሜይዴይ እስከዚህ ድረስ አልተከበረም። በኢትዮጵያ ሜይዴይ መከበር የጀመረው በ1968 ዓ.ም ነው። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሕዝቡ የሚያከብረው በቀበሌ ታዞ ሰልፍ እየወጣ ነበር። ርእሰ ብሔሩም በስፍራው ተገኝተው ንግግር ያደርጉ ነበር።

ሜይዴይን የምናከብረው ለሠራተኞች መብትና ጥቅም ብለው በመታገላቸው ሥራ እንዲለቁ የተወሰነባቸውን፣ የታሰሩትንና እራሳቸውንም ያጠፉትን በማሰብ፣ ለቀጣይም ቃል ኪዳናችንን በማደስ ነው። ሌሎች ወቅታዊ የሆኑ ጥያቂዎችም በዓሉን መሠረት አድርገው ይነሳሉ።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ አሁንም በኢንዱስትሪው አላደገችም። በኮንፌዴሬሽን ደረጃ የሠራተኛ መብትን ለማስከበር የሚደረገው እንቅስቃሴ ምን ያህል ውጤታማ ነው?

አቶ ካሣሁን፡- መሠረታዊ ማህበራት አሉ። በክፍለ ኢኮኖሚ ደረጃ ደግሞ የተደራጁ ፌዴሬሽኖች አሉ። ከዚያ በኋላ ደግሞ ኮንፌዴሬሽን አለ። ስለዚህ በ1955 ዓ.ም ማህበር ሲቋቋምም ሀገር አቀፍ ነበር። ኢንዱስትሪ ከዘመነ ወይንም ካደገ በኋላ ኮንፌዴሬሽን ይሆናል የሚል አካሄድ የለም። ኮንፌዴሬሽን የሚወክለው ሀገርን ነው። በዓለም ሥራ ድርጅት ለመወከልም ሆነ ከመንግሥት ጋር ለመነጋገር ሀገር አቀፍ ማህበር ያስፈልጋል።

የኮንፌዴሬሽኑ ዋና ተግባር በሀገር አቀፍ በሚወጡ ሕጎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች ላይ ከመንግሥት ጋር ድርድር ያደርጋል። ደንብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ከመቅረቡ በፊት ቅድሚያ የሚነጋገሩት አሠሪ፣ ሠራተኞችና መንግሥት ናቸው። የሶስትዮሽ ምክክር ወይም መድረክ የሚያስፈልገው በጋራ እየተመካከሩ ልዩነቶቻቸውን እያጠበቡ ወደ አንድ እንዲመጡ በማሰብ ነው። የተወሰነ ልዩነት ካላቸው ደግሞ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ተልኮ የሚያስታርቅ ውሳኔ ያሳልፋል። ውሳኔም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኮ ይፀድቃል። ኮንፌዴሬሽን አስፈላጊ የሚሆነው ከዚህ አኳያ ነው።

ታች ያሉት ከአሠሪው ጋር የሚደራደሩት እንደየድርጅታቸው ባህሪና የህብረት ስምምነት ነው። ችግር ሲያጋጥማቸው የሚያግዛቸውና የሚከራከርላቸው ኮንፌዴሬሽኑ ነው። የሕግ ድጋፍም ያደርግላቸዋል። ስልጠና ይሰጣቸዋል። ኮንፌዴሬሽኑ እስከ ዓለም አቀፍ ድረስ የተደራጀ ነው። በአፍሪካ ደረጃ የሠራተኛ ኮንፌዴሬሽን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም የዓለም አቀፍ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን አለ። ኮንፌዴሬሽኑ ግንኙነቱ ዓለም አቀፍ ነው። የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ ሲወጣ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ሁኔታ ብቻ አይደለም፤ ለሠራተኞች የተቀመጡ ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ደረጃዎች አሉ። ሀገራት የሚያወጡት ሕግ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓለም ሥራ ድርጅት ከወጡ ድንጋጌዎች በታች መሆን

የለበትም። በአጠቃላይ የሠራተኛ ጉዳይ ዓለም አቀፍ ባህሪ አለው።

አዲስ ዘመን፡- ኮንፌዴሬሽኑ እስከ አሁን ባከናወናቸው ተግባራት በስኬት የሚያነሳቸውንና ተግዳሮቶችንም ቢያብራሩልን?

አቶ ካሣሁን፡- የኮንፌዴሬሽኑ ዋና ተግባራት የሠራተኛውን መብትና ጥቅም ማስከበር ነው። በመሆኑም በመጀመሪያ ሠራተኛው ለመብትና ጥቅሙ እንዲታገል በማህበር እንዲደራጅ ማድረግ ሲሆን፤ ለዚህም ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ይሠራል። የሠራተኛው መብትና ጥቅም፤ ያለበትን ችግርም ሆነ ከሠራተኞች፣ ከአሠሪዎችና ከመንግሥት ጋር በድርድር እንዲፈታለት ይደረጋል። በመሠረታዊ ደረጃ ያሉ አመራሮችም ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ያደርጋሉ። ከእነርሱ በላይ ሲሆን ደግሞ በክፍለ ኢኮኖሚ ለተደራጁ ፌዴሬሽኖች ይቀርባል።

እነርሱም ከአቅማቸው በላይ ሲሆን፤ ለኢሠማኮ ወይም ለኮንፌዴሬሽን ያስተላልፋሉ። ኮንፌዴሬሽኑ ደግሞ በድርድር እንዲፈታ ማድረግ ካልቻለ ወደ ሕግ በመውሰድ እስከ ሰበር ሰሚ ድረስ ለሠራተኛው ተከራክሮ መፍትሔ እንዲያገኝ ያደርጋል። የማህበር አባል የሆነ ሰው ነፃ የሕግ አገልግሎት የማግኘት መብት አለው። የኮንፌዴሬሽኑ ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ባሉበት ሁሉ የሕግ ባለሙያዎች ስላሉ የሕግ አገልግሎት ይሰጣል።

የሠራተኛ የመብትና የተለያዩ ጥያቄዎች በአንድ ጊዜ መፍትሔ ተሰጥቷቸው የሚያቆሙ አይደሉም። ለምሳሌ የደመወዝ ጥያቄ አንዴ ተጨምሮ ይበቃል የሚባል አይደለም። ኑሮ ተለዋዋጭ በመሆኑ የደመወዝ ጥያቄ ይቀጥላል። አሠሪው ከሚያገኘው ትርፍም ለሠራተኛው መስጠት ይኖርበታል። በዚህ ላይ ሠራተኛውና አሠሪው መደራደር አለባቸው። ድርድሩ ቀላል አይሆንም። በተለይም አሠሪው ላለመክፈል ብዙ ውጣውረድ ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል። ውል ተፈራርመው እንኳን ተፈፃሚ አያደርጉም። ኮንፌዴሬሽኑ የቆመው ለሠራተኛው በመሆኑ እነዚህን ነገሮች ይከታተላል። እንዲህ ያሉ ነገሮች ማቆሚያ ስለሌላቸው ችግሩ አንዴ ብቻ አይፈታም።

ኮንፌዴሬሽኑ ውጤት ካስመዘገበባቸው አንዱ፤ በግል ድርጅት ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች የሥራ አገልግሎታቸውን ሲጨርሱ ጡረታ የማግኘት መብት አልነበራቸውም። ኮንፌዴሬሽኑ ከብዙ ትግል በኋላ በግል ድርጅት ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች በ2003 ዓ. ም የጡረታ መብታቸው እንዲከበርላቸው ማድረግ ችሏል። ሌላው በ2008 ዓ.ም የሥራ ግብር ተቀንሷል። ይህ ውሳኔ ሲወሰን በደመወዝ ተከፋዩ ላይ የኑሮ ጫና ነበር።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ጥናት ተጠንቶ ለሁሉም ደመወዝ ተካፋይ ሠራተኛ የሥራ ግብር ቅናሽ ሊደረግ ችሏል። የወሊድ ፈቃድም በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥና በግል ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ልዩነት ነበረው። እኩል መሆን አለበት የሚል ጥያቄ አቅርበን ነበር። በተለየ ሕግ ይተዳደሩ የነበሩ የኤጀንሲ ሠራተኞች ጉዳይ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ መታቀፍ አለበት የሚል ጥያቄም በማቅረብ ብዙ ተከራክረናል።

በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ አንድ ሰው በዓመት ዓረፍት የሚሰጠው 14ቀን ብቻ ነበር። በግል ሠራተኞች ግን የተቀመጠው ሰባት ቀን ብቻ የሚል ነበር። እርሱም ቢሆን አሠሪው ሲፈቅድ የሚል ነው። ሠራተኛው በተለያየ ምክንያት አንድ ቀን ከቀረ ሁለት ቀን ካረፈደም ከሥራው ይባረራል፤ የሥራ ስንብት ክፍያም ማግኘት የለበትም የሚሉና ሌሎችም ጫናዎች ነበሩት። እነዚህ ሁሉ ልዩነቶች ነበሩ። በመቀጠል ያደረግነው ልዩነቶቻችን አስመልክቶ ሠራተኛውን የማስተባበር ሥራ ነው የሠራነው። ኮንፌዴሬሽኑ ነገሮች እንዲቀየሩ ሠራተኛውን የማስተባበር እንጂ ሌላ ነገር ማድረግ አይችልም። በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅም ሆነ በሕገ መንግሥቱ በተፈቀደው መሠረት ሕጋዊ መንገድ ተከትሎ ሰላማዊ ሠልፍ በማድረግ፣ ሥራ የማቆም ርምጃ መውሰድ ነው። እነዚህን መብቶቹን የሚጠቀመው ግን የመጨረሻ አማራጭ ላይ ሲደርስ ነው።

በ2011 ዓ.ም በወጣው የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ የዝቅተኛ ደመወዝ ወለል ከወቅቱ የገበያና ኢኮኖሚ ጋር በማየት በየዓመቱ የሚከለስ የደመወዝ ቦርድ ይቋቋማል የሚል ውሳኔ ላይ መድረስ ተችሏል። ይሁን እንጂ ዝቅተኛ የደመወዝ የወለል መጠን በሕግ ባለመወሰኑ ጥያቄው ቀጥሏል። ኮንፌደሬሽኑ በሕጎች፣ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ይከራከራል፤ ይደራደራል፣ ሠራተኞችንም ያስተባብራል።

አዲስ ዘመን፡- የሠራተኞች የመደራጀት መብትን የሚጥሱ የግል አሠሪ ድርጅቶች ላይ ቅሬታ ይነሳል። ይህን የሚፈጽሙት ዓለም አቀፍ ሕጉን ጠንቅቀው የሚያውቁ የውጭ ኩባንያዎች ጭምር ናቸው። በእናንተ ግምገማ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ ካሣሁን፡- የሠራተኛው ጥያቄ በአንዴ የሚያበቃ አይደለም ያልኩት ለዚህ ነው። እንዲህ ያለው ችግር የሚስተዋለው በውጭም በሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ጭምር ነው። ከተደራጀ ጥቅሙን ይጠይቀኛል ከሚል ነው። ሠራተኛው የሚጠይቀው በአዋጅ የተፈቀደለትን ነው። አንዳንዶቹ ጥያቄዎች ማህበር ኖረም አልኖረም መሟላት ያለባቸው ናቸው። ለምሳሌ የደህንነት መጠበቂያ አልባሳትና ተያያዥ ነገሮች ያስፈልጋሉ። አሠሪዎች ይሄንን እንደ ወጪ ይቆጥሩታል። ካደጉ ሀገራት የመጡት ኩባንያዎችም ቢሆኑ ካልተገደዱ በስተቀር ለማሟላት ፈቃደኛ አይሆኑም። ለምሳሌ፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ሠራተኞች መደራጀት አይችሉም ነበር። እኔም እዛ ግቢ መግባት አልችልም ነበር። ከተለያዩ የመንግሥት ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ከአሠሪዎች ጋር በመወያየት፣ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ተደርጓል።

ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች በማህበር ተደራጅተዋል። ቦሌ ለሚ ውስጥ የሚገኝ አንድ ድርጅት ቀርቶ ነበር። አሁን እነርሱም ፈቃደኛ ሆነዋል። ዱከም ኢንደስትሪ ዞን ውስጥ ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ ኢንደስትሪዎች አሉ። ግን አንድም ሠራተኛ በማህበር አልተደራጀም። ክትትላችንን እንቀጥላለን። እነዚህ ያነሰኋቸው በአንድ አካባቢ ያሉትን ነው። በተለያየ ቦታ ያልተደራጁ አሉ። አዲስ የሚመጣውም ቢሆን በተመሳሳይ ሁኔታ የሚያልፍ ነው። ስለዚህ ሥራው ተጠናክሮ በመዋቅራዊ አካሄድ እንዲፈታ ጥረት ይደረጋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ /ዶክተር/ ጋርም በነፃ የመደራጀትና የመደራደር መብት ላይ ችግሮች መኖራቸውን በተመለከተ ስለ ሠራተኞች ጉዳይ ስንወያይ ነበር። ከተነጋገርንባቸው ችግሮች መካከል በሀገር አቀፍ ደረጃ በተቋቋመ አሠሪና ሠራተኛ አማካሪ ቦርድ ሥራን የተመለከተ ነው። ቦርዱ ከሠራተኛ፣ ከአሠሪና ከመንግሥት የተውጣጡ 15 አባላት የተካተቱበት ነው። በውይይታችን ቦርዱ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ሥራው ተቋርጦ ስለነበር ሥራውን እንዲቀጥል አንስተናል። የሚነሱ ጥያቄዎች ለቦርዱ ቀርበው ውሳኔ ያገኛሉ። ከውይይቱ በኋላ አማካሪ ቦርዱ ሥራውን የቀጠለ ሲሆን፣ የሚመራው በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ነው።

የ2016 ዓ.ም እቅድ ወጥቶ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ፀድቆ እየተተገበረ ነው። የመደራጀትና መደራደር ነፃነት መብትን የተመለከተ ጉዳይ በስድስት ወር አንዴ ቋሚ የሆነ መድረክ ይካሄዳል። የመደራጀት ምጣኔ ምን ያህል እንዳደገ፣ መደራጀት ለምን አነሰ፣ በኢንዱስትሪ ውስጥ የሚፈጠሩ ግጭቶች የአፈታት ሁኔታ፣ የሚሉ ግምገማዎችን ያደርጋል። አቅጣጫዎችንም ያስቀምጣል። ሁለት ጊዜ መድረኮች ተዘጋጅተዋል።

አዲስ ዘመን፡- አሁን የኢንዱስትሪው ሰላም በምን ሁኔታ ላይ ነው?

አቶ ካሣሁን፡- ኢንዱስትሪው ውስጣዊም ውጫዊም ጫናዎች አሉበት። ውጫዊ ጫናው ድርጅቶች ለኢንዱስትሪው የሚሆን ጥሬ ዕቃ ለመግዛት የውጭ ምንዛሪ የማግኘት ችግር ነው። በዚህ ምክንያትም ሠራተኞች ይቀንሳሉ። አንዳንዶቹ ሠራተኛው ማግኘት የሚገባውን ጥቅማ ጥቅም ይቀንሳሉ። ይሄ መረጋጋትን አይፈጥርም። ሌላው ጫና ደግሞ የፀጥታ መደፍረስ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ሠራተኞች ታግተው ገንዘብ ይጠየቃል። የሚገደሉም አሉ። ለአብነት በሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ሠራተኞች ላይ የደረሰውን ማንሳት ይቻላል። ወንጂና መተሀራ ላይም ሠራተኞች ታግተው ተገድለዋል። ይሄ ሠራተኛው እንዳይረጋጋ እያደረገው ነው። ችግሩ በተለይ በክልሎች ጎልቶ ይስተዋላል።

በውስጥ የሚደርሰው ጫና በነፃ መደራጀትና የመደራደር መብት እንዲሁም አሠሪው የገባውን ቃል አለማክበር ሲሆን፣ በዚህ ሁኔታም ግጭቶች ይፈጠራሉ። በተቻለ መጠን በውስጥ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ጥረት እያደረግን ነው። ውጫዊው ጫና ግን የጋራ የሆነ እንደ ሀገር መፍትሔ የሚፈልግ ጉዳይ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ኮንፌዴሬሽኑ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያለው ግንኙነት እንዴት ይገለጻል?

አቶ ካሣሁን፡- ኮንፌዴሬሽኑ የዓለም ሥራ ድርጅት አባል ነው። ከዚያ ውጭ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በተለያየ መልኩ ግንኙነት ያደርጋል። ለማህበር መሪዎች የምንሰጠውን የተለያየ ሥልጠና ከዓለም አቀፉ በምናገኘው ድጋፍ ነው። የአፍሪካ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ጋር በጋራ ሆነን እንደ ሀገርም፣ እንደ አፍሪካም ስላለው ችግር እንወያያለን። የአፍሪካ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልም ነን።

በምክትል ደረጃም በምክር ቤቱ ሠርተናል። ከኖርዌይ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ጋር በቅርበት እንሠራለን። በሥልጠናና በተለያየ መልኩም እያገዙን ነው። ከአሜሪካን ሌበር ፌዴሬሽን ጋርም በቅርበት እንሠራለን። የዓለም አቀፍ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ኦዲት አባል ሆነን እየሠራን ነው። ኮንፌዴሬሽኑ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በአፍሪካም በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥሩ ቅርበት እንዳለን ይታወቃል።

‹‹በአንዳንድ ሀገር ጥቁርና ነጭ በሚል ክፍፍል ይደረጋል። ኢትዮጵያ ደግሞ የተለያዩ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሀገር ሆና፤ አሁን ደግሞ ሀገሪቷ ውስጥ እየታየ ባለው የፖለቲካ ትኩሣት ኢሠማኮ ተጽእኖ ሳይፈጠርበት እንዴት አንድነቱን አስጠብቆ ሊቆይ ቻለ?›› ተብሎ ጥያቄ ቀርቦልን በተለያዩ ዓለም አቀፍ የጉባኤ መድረኮች ላይ ተሞክሯችንን አካፍለናል። ሠራተኞችን እንዴት እንደምናደራጅም እንዲሁ ልምድ አካፍለናል።

ሌላው የአፍሪካ ቀንድ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን የሚባል አለ። ከስምንቱ የኢጋድ አባል ሀገራት ጋር የጋራ የሆነ አንድ ኮንፌደሬሽን አለን። ችግሮቻችን ተመሳሳይ በመሆናቸው የሠራተኞች መብትና ጥቅምን ለማስጠበቅ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን መንግሥታትን ማገዝ ስላለብን፣ በተጨማሪም በአፍሪካ ቀንድ የሰዎች ነፃ ዝውውር መኖር አለበት ብለን ስለምናምን፣ መንግሥታት ኢጋድ ያወጣውን ፕሮቶኮል ስምምነት እንዲፈርሙ በጋራ ለመሥራት አንድነታችን አስፈላጊ ነው። ፍላጎታችን የምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ወደ አንድነት እንዲመጣ ነው። ኮንፌዴሬሽናችን፤ የእርስ በእርስ ጦርነት መቆም አለበት፤ ችግሮች መወገድ አለባቸው፤ ሀገሮች በሥጋት የሚተያዩበት ነገር መወገድ አለበት ብሎ የሚያምንና ለችግሮችም መፍትሔ እንዲበጅ የሚሠራ ተቋም ነው። ከኢጋድ ጋርም በቅርበት እየሠራ ይገኛል።

አዲስ ዘመን፡- ኮንፌዴሬሽኑ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ያለው ሚና እንዴት ይገለጻል?

አቶ ካሣሁን፡- ዴሞክራሲ ለሁሉም ነገር መሠረት ነው ብለን እናምናለን። በሠራተኛ ማህበራት ውስጥም የዳበረ ነው። የዴሞክራሲ ሥርዓት ግጭትን ለማስወገድ፣ እድገትን ለማምጣት ይረዳል። እንደሀገርም ባህል መሆን አለበት። ምክንያቱም ችግሮቻችንን በኃይል ሳይሆን፤ በውይይትና በንግግር መፍታት ደረጃ ላይ ለመድረስ ያስችለናል። ኮንፌዴሬሽኑ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዙሪያ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ይሠራል። የሥነ ዜጋ ስልጠናዎችን ይሰጣል። ሀገራዊ ምርጫ ሲካሄድ በታዛቢነት ይሠራል።

አዲስ ዘመን፡- በዓሉን አስመልክቶ መልዕክት ካልዎት ያስተላልፉ?

አቶ ካሣሁን፡- የሠራተኞች በነፃ የመደራጀት መብት ሠራተኛውንና አሠሪውን የጋራ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል። አሠሪዎችና ሠራተኞች በውይይት ችግሮቻችን ሲፈቱ ሰላሙ የተረጋገጠ ምርታማ ኢንደስትሪ ይፈጠራል። ድርጅቱ ከያዘው ሠራተኛ በላይ ተጨማሪ ለመቅጠር ያስችለዋል። ኢንዱስትሪው ሲስፋፋ፣ የሠራተኛውም መብት ከተጠበቀ የአባላቱ ቁጥርም ይጨምራል። ኮንፌዴሬሽኑ ለዚህ መደላድል ለመፍጠር ሪፎርም እየሠራ ነው። ኢንዱስትሪ በሚበዘባቸው አካባቢዎች ቅርንጫፍ በመክፈት ታች ወርደን ለማጠናከር እየሠራን ነው።

በቅድሚያ ለመላው ሠራተኞች እንኳን ለሜይዴይ አደረሳችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ‹‹ለሰላምና ለኑሮ ውድነት መፍትሔ እንሻለን።›› በሚል መሪ ቃል በምናከብረው ሜይዴይ በዓል ላይ ሌሎችም መልስ የሚፈልጉ ጥያቄዎች ይነሳሉ። በተለይ ደግሞ ሰላም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ኢንደስትሪው ምርታማ ሆኖ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ሚና እንዲኖረው ሰላም ያስፈልጋል። ሰላም ለማስፍን መንግሥት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ ቢሆንም፤ የሁሉም አካላት ትብብርና ተሳትፎ መኖር አለበት። ኑሮ ውድነቱም ቢሆን፤ የሚቃለልበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። መንግሥት ለቀረበለት ጥያቄም መልስ እንዲሰጥ እንጠይቃለን።

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።

አቶ ካሣሁን፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You