የኢትዮጵያ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ጉዞ

ዜና ትንታኔ

ባለፉት ስድስት ዓመታት በፖለቲካ ዲፕሎማሲ መስክ በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ከየትኛውም ጊዜ በላይ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ተፈጥሯል፡፡ ግንኙነቶችን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር የሚደረገው ጥረትም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥር 2016 ዓ.ም የታተመው ‹‹ዲፕሎማሲያችን›› ጆርናል እንደሚያመለክተው፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ጉዞ ውጤታማ ሥራ ተሰርቷል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ውጤት ካስመዘገበችባቸው የዲፕሎማሲ ሥራዎች ውስጥ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲም አንዱ ነው። በሁለትዮሽ ግንኙነት ረገድ ከበርካታ ሀገራት ጋር ግንኙነቷን ማጠናከር ተችሏል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በአፍሪካ አንድነትና ኅብረት ምስረታና የሥራ እንቅስቃሴ የተመዘገበው የዲፕሎማሲ ድል ቀጣይነት ለማረጋገጥ አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ ብሪክስን በመቀላቀል ያገኘችው ድል ተጠቃሽ ነው። ድሉ በቀላሉ የተመዘገበ ሳይሆን በሳልና ውጤታማ የዲፕሎማሲ ትግል ተደርጎበት የተገኘ ነው ሲል ሰነዱ ያብራራል።

ኢትዮጵያ ይህን ተቋም የተቀላቀለችው ከአንድ ጎራ ወጥታ ወደ ሌላ ለመቀላቀል ሳይሆን መነሻውም መድረሻውም ብሄራዊ ጥቅም የማረጋገጥ ጉዳይ መሆኑን ጆርናሉ ያስረዳል።

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጉዞ በአፍሪካ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃና በመካከለኛው ምሥራቅ ያላትን ግንኙነት ያጠቃልላል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል፤ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጉዞ ከጥንት ጀምሮ እየተንከባለለ የመጣ ችግር አለበት፡፡ በተለይ ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር በታሪክ፣ በቋንቋ፣ በእምነት፣ በቅርበት፣ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና የንግድ ግንኙነት ቢኖርም ግንኙነቱ በሚፈለገው ልክ ሳያድግ ቆይቷል፡፡ይህም ኢትዮጵያም በርካታ ጫናዎች እንዲደርሱባት ምክንያት ሆኗታል ይላሉ፡፡

የዓባይ ውሃ ጉዳይ ለኢትዮጵያና ለመካከለኛው ምሥራቅ ግንኙነት የትስስር ምንጭ ነው ያሉት አደም፤ ክርስትና፣ እስልምናና አይሁድ ከመካከለኛው ምሥራቅ የመጡ እምነቶች ናቸው፡፡ ይህም ትልቅ ትስስር ፈጥሯል፡፡

ከስድስት ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ሲመጡ እየተንከባለለ የመጣውንና ያልተጠቀምንበትን የመካከለኛው ምሥራቅ ግንኙነት እንዲጠናከር ማድረግ ተችሏል፡፡ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲው ስለመጠናከሩ በመግለጽ፤ ውጤትም ተገኝቶበታል ነው ያሉት፡፡

ባለፉት ስድስት ዓመታት የተጀመረውን ግንኙነት አጠናክሮ ለመቀጠል አረብኛ ቋንቋ የሚችሉ ዲፕሎማቶችን መመደብ አስፈላጊ ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አደም፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት የተመዘገቡ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ውጤቶችን ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ የቱሪዝምና የንግድ ልውውጡ እያደገ መጥቷል፡፡

እንዲሁም ባለፉት ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እያበረከተች ያለው አስተዋጽኦ ቀላል አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ይበልጥ ተሰሚነቷን በማሳደግ የዲፕሎማሲ ጉዞዋን ውጤታማ ለማድረግ ከዲፕሎማት አመዳደብ ጀምሮ ያሏትን ጠንካራ ጎኖች መጠቀም አለባት፡፡ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋን መፈተሽና የውስጥ ሰላም ማስፈን ይገባል ይላሉ፡፡

ባለፉት ስድስት ዓመታት የዲፕሎማሲ ጉዞ ለኢትዮጵያ አልጋ በአልጋ ነው ማለት ባይቻልም በፖለቲካ ዲፕሎማሲው መስክ ተጨባጭ ውጤቶች የተገኙበት ነው፡፡ ከጎረቤት ሀገራት ጀምሮ ቀደም ሲል እምብዛም ጠንካራ ግንኙነት ካልነበራት የላቲን አሜሪካ፣ የካሪቢያን ሀገራት፣ሩቅ ምሥራቅና መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ጋር ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት መፍጠር ተችሏል፡፡ ሚሲዮን በአዲስ አበባ የከፈቱ ሀገራት ቁጥርም እየጨመረ ሲሆን አንድ መቶ 34 መድረሱንም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ የበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መስራችና አባል ብትሆንም ባለፉት ስድስት ዓመታትም ይህን ታሪኳን በማስቀጠል የብሪክስ ጥምረት ሀገራት አባል ሆናለች፡፡ ይህም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ውጤትን ያሳያል፡፡ በተለያዩ ሀገራት በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱና በሚኖሩበት ሀገር ክብራቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ የተሰራው የዲፕሎማሲ ሥራ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከተገኙት የዲፕሎማሲ ውጤቶች መካከል የሚጠቀስ መሆኑን ምሁሩ ይገልጻሉ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብዩ ተድላ በበኩላቸው፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት የተመዘገቡ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ስኬቶችን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት በኢትዮጵያ አዲስ የዲፕሎማሲ ጉዞ ውጤት የተገኘበት ነው፡፡ በተለይ በፖለቲካ ዲፕሎማሲ መስክ ከሀገራት ጋር ጥሩ የሁለትዮሽ ግንኙነት መፍጠር ተችሏል። በርካታ ሀገራት ኤምባሲያቸውን በአዲስ አበባ የከፈቱበትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም የተጠበቀበት ነው፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት ያጋጠሙ ችግሮችንና የውጭ ጫናዎችን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍታት መቻሉንም ያስረዳሉ፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ ማግስት ጀምሮ መሥራታቸውን የገለጹት አቶ ነብዩ፤ በዚህም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር ተችሏል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር አይተኬ ሚና ተጫውታለች፡፡ ኢትዮጵያ ለሰላም የሠራችው ሥራ ዓለም እውቅና የሰጠው ነው፤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኖቤል የሰላም ሽልማት ያሰጠ መሆኑን አውስተዋል፡፡ አሁንም ኢትዮጵያ ባለችበት ቀጣና ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ጠንካራ ሚናዋን በመወጣት ላይ ትገኛለች ይላሉ፡፡

የቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር እንዲጎለብት በፖለቲካ ዲፕሎማሲው ረገድ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ ይህም ኢትዮጵያን የቀጣናው የስህበት ማዕከል ሆና እንድትቀጥል አድርጓታል፡፡ በለውጡ ዓመታት ውስጥ ትልቅ ዲፕሎማሲ ድል ተደርጎ የሚቆጠረው የብሪክስ ጥምረት አባል መሆኗ ነው። ይህ ጥምረት ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ቅቡልነቷን እንደሚያሰፋ አቶ ነብዩ በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

ሞገስ ጸጋዬ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You