የነፃነት አርበኞቹ የሚያዝያ 27 ጀግኖች

ኢትዮጵያ በታሪኳ የትኛውንም ሀገር በኃይል ወርራ አታውቅም። ነገር ግን በሀገረ መንግሥት ታሪኳ ውስጥ ብዙዎች ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን ለማንበርከክ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። እርሷ ደግሞ ለየትኛውም ባዕድ ወራሪ እጅ ሰጥታ አታውቅም። በተለይም አፍሪካን በቅኝ ግዛት ለመቀራመት አውሮፓውያን ተስማምተው ሲዘምቱ፤ ባርነትን አንቀበልም ባሉ በጀግኖቹ ልጆቿ ነፃነቷን አስከብራ እስከዛሬ ዘልቃለች።

ኢትዮጵያ እንደዋዛ የተፈጠረች ሀገር አይደለችም። የዘመናት ውጣ ውረድን ድል አድርገው በመጡ ሕዝቦች የተገነባች ሀገር ናት፡፡ የኢትዮጵያዊነት እሴት መሠረቱ ጽኑ ነው፡፡ አባቶች ደማቸውን እንደ ጅረት አፍሰው ነገን አስበው በደማቸው ያጸኗት ሀገር ናት፡፡ በተለይ በጣሊያን የወረራ ዘመን ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማዋ ከታጠፈ፣ ሉዓላዊነቷ ከተደፈረ 5 ዓመታት በኋላ ነፃነቷን ያስመለሰችው ከ83 ዓመት በፊት ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ነው፡፡ በዚህ ዘመን ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በአርበኞች ብርታትና መስዋዕትነት የጣሊያን ባንዲራ አውርደው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በታላቁ ቤተ መንግሥት ሰቀሉ።

የሚያዝያ 27 የንጉሠ ነገሥቱ አዲስ አበባ ገብተው ሰንደቅ ዓለማ መስቀል ሌላው ታሪካዊነቱ ከአምስት ዓመታት አስቀድሞ ሚያዝያ 27 ቀን 1928 በዚያው ቀን ወደ ኢትዮጵያ የዘመተው የጣልያኑ ጦር አዛዥ ጄኔራል ባዶሊዩ አዲስ አበባ ገብቶ በታላቁ ቤተ መንግሥት የጣሊያንን ባንዲራ የሰቀለበት ቀን መሆኑ ነው። ጣሊያን ከዓድዋ ሽንፈቷ 40 ዓመታት በኋላ በዘመናዊ የጦር መሣሪያና በወታደራዊ ኃይል ይበልጥ ደርጅታ ኢትዮጵያን ከሦስት አቅጣጫዎች ወረረች። ከዓድዋው ዘመቻ ያልተሻለ የጦር ትጥቅ የነበራት ኢትዮጵያም የጣሊያንን ጦር በፅናት ተዋጋች።

የወቅቱ ኃያላን እንግሊዝና ፈረንሳይ የጦር መሣሪያ በግዢ እንዳታገኝ ለጣሊያን ተደርበው ስላሴሩባት ኢትዮጵያ ብቻዋን ጦርነቱን በመጋፈጧ ድል ማግኘት አልቻለችም።

የየግንባሮቹ የኢትዮጵያ የጦር አዛዦች ብዙዎቹ ሞተው ሠራዊቱም በመርዝ ጋዝና በአውሮፕላን ቦምብ ተደብድቦ ያለቀው አልቆ የቀረው ቀርቶ ጣልያን ጊዜያዊ ድል አግኝታ ዋና ዋና ከተሞችን ቢቆጣጠርም ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በገጠሩ ክፍል እምቢ ለነፃነቴ፣ እምቢ ለሀገሬ ብለው የሽምቅ ውጊያ ጀመሩ።

ንጉሠ ነገሥቱም ስደት ሄደው በጊዜው ለነበረው የመንግሥታቱ ማህበር (ሊግ ኦፍ ኔሽን) አቤቱታ አቀረቡ። የሚሰማቸው ግን አላገኙም። በሌላ በኩል አርበኞች ግን ከቀን ወደ ቀን ድል እየተቀናጁ የጣሊያን ወታደሮችን መፈናፈኛ፤ መግቢያ መውጫ አሳጧቸው። ከጣሊያን ወታደሮች ይማርኳቸው በነበሩ መሣሪያዎች ራሳቸውን እያደራጁ አብዛኛውን የገጠር ክፍል ተቆጣጠሩት።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መቀስቀስ ለኢትዮጵያ ትልቅ ቦታ ነበረው። የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲቀሰቀስ ጣሊያን የናዚ ጀርመን አጋር ሆነች። ያን ጊዜ እንግሊዞች የጣሊያን ጠላት ሆነው ኢትዮጵያን መደገፍ ጀመሩ። ስለዚህም ወታደራዊ ድጋፍ ሰጥተው፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ረዷቸው። በጄኔራል ካኒንግሂም የሚመራው የእንግሊዝ ጦር ከኬንያ ተነስቶ ከደቡብ አቅጣጫ ወደ መሀል ኢትዮጵያ ሲገሰግስ፤ በጄኔራል ፕላት የሚመራው ጦር ከሱዳን ተነስቶ ወደ አሥመራ፤ ከዚያም ከሰሜን አቅጣጫ ወደ መሐል ኢትዮጵያ ተንቀሳቀሰ።

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሚመራውና የአርበኞችና የእንግሊዝ አማካሪዎች የሚገኙበት ጌዲዮን ተብሎ የተሰየመው ጦር ከሱዳን ተነስቶ በኦሜድላ አልፎ በጐጃም በኩል ወደ መሐል ሀገር ገሠገሠ። በመካከለኛ ኢትዮጵያ አርበኞች በጣሊያን ወታደሮች ላይ ጥቃታቸውን አፋፋሙ። ጣሊያኖች ክፉኛ ተሸነፉ። በየቦታው ድል የመሆናቸው ዜና ናኘ። ዘመቻው ከተጀመረ ሁለት ወራት ሳይሞላው፤ ጣሊያኖች አዲስ አበባን ለቀው ፈረጠጡ። መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም የጄኔራል ካኒንግሃም ጦር አዲስ አበባን ተቆጣጠረ። እንግሊዞች ኢትዮጵያውያን አርበኞች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ስላልፈለጉ ቀዳማዊ ኃይል ሥላሴን በደብረ ማርቆስ ለአንድ ወር ያህል እንዲቆዩ አደረጓቸው።

ይሁንና በአዲስ አበባ በአርበኞች ተፅዕኖና ቅሬታ የተነሳ አርበኞች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ፈቀዱ። አፄ ኃይለ ሥላሴም ወደ አዲስ አበባ እንዲጓዙ ፈቀዱ። ንጉሠ ነገሥቱም አዲስ አበባ በታላቁ ቤተ መንግሥት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሰቀሉ። አጼ ኃይለሥላሴ አዲስ አበባ ገብተው የሚከተለውን ንግግር አድርገው ነበር።

‹‹ይህ የምትሰሙት ድምጽ የኔ የንጉሳችሁ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ነው። አባቶቻችን ደማቸውን አፍሰው አጥንታቸውን ከስክሰው በነፃነት ያቆዩልን ሀገራችንን ወደ ከፍተኛው የሥልጣኔ ደረጃ ለማራመድ የምንደክምበት ጊዜ ከጥንት ጀምሮ ስለሆነ ዳግመኛ ጠላታችን ኢጣሊያ ይህንን እይታ ወሰናችንን ጥሳ የግፍ ጦርነት እንዳደረገችብን ሁላችሁም የምታውቁት ነው።

እኛም በተቻለን ከተከላከልን በኋላ ርዳታ ለመጠየቅ ወደ መንግሥታት ማህበር ወደ ወዳጆቻችን መንግሥታቶች መጣን፤ እዚህ ስንነጋገር በቆየንበት ጊዜ የኢትዮጵያ አርበኞች ሰይፋችሁን ሳትከቱ ፊታችሁን ሳትመልሱ ሰንደቅ አላማችሁን ሳታጥፉ ለባዕድ አንገዛም በማለት በመሳሪያ ብዛት ከሚበልጣችሁ ጨካኝ ጠላት ጋር የባሕርይ የሆነውን ጀግንነታችሁን መሣሪያ አድርጋችሁ በኢትዮጵያ አምላክ ብቻ ተማምናችሁ በጀግንነት ቀንና ሌሊት በዱር በገደል ስትጋደሉ ቆይታችሁ ይኸው አሁን እንደምታዩት የማያቋርጥ የአምስት ዓመት ትግላችሁ የድካማችሁንና የመስዋዕታችሁን ፍሬ ለማየት እንድትበቁ አደረጋችሁ።

የሀገሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ! ዛሬ ኢትዮጵያ እጆቹዋን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታ እልል እያለች ምስጋናዋን የምታቀርብበት ደስታዋንም ለልጆቹዋ የምትገልጽበት ቀን ነው። የኢትዮጵያ ልጆች ከባድ የመከራ ቀንበርና ከዘለዓለም ባርነት ነፃ የወጡበት ቀንና እኛም አምስት ዓመት ሙሉ ተለይተነው ከነበረው ከምንወደውና ከምንናፍቀው ሕዝባችን ጋር ለመቀላቀል የበቃንበት ቀን ስለሆነ ይህ ቀን የተከበረና የተቀደሰ በየዓመቱም ታላቁ የኢትዮጵያ በዓል የሚውልበት ነው። በዚህም ቀን ለሚዎዷት ለሀገራቸው ነፃነት ለንጉሠ ነገሥታቸውና ለሰንደቅ አላማቸወ ክብር አባቶቻቸው የተላለፈውን ጥብቅ አደራ አናስወስድም በማለት መስዋዕት ሆነው ደማቸውን ያፈሰሱትን አጥንታቸውን የከሰከሱትን ጀግኖቻችንን እናስታውሳለን። ለዚህም ለጀግኖቻችን የኢትዮጵያ ታሪክ ምስክር ይሆናል።›› አሉ፡፡

ንጉሡ ጨምረውም ‹‹ባለፈው አምስት ዓመታት ውስጥ በዝርዝር ተነግረውና ተቆጥረው የማያልቁ ያገኘናቸው መከራና ስቃይ ትምህርት ሆነውን ሠራተኛነት፣ አንድነት፣ ህብረትና ፍቅር በልባችሁ ተጽፈው ለምናስበው ለኢትዮጵያ ጉዳይ ረዳቶች ለመሆን ዋና ትምህርት የሚሰጣችሁ ነው። በአዲሷ ኢትዮጵያ ከእንግዲህ ወዲያ የማትነጣጠሉ በሕግ ፊት ትክክልና ነፃነት ያላችሁ ሕዝቦች እንድትሆኑ እንፈልጋለን። ሀገር የሚለማበትን ሕዝብ የሚበለጽግበትን እርሻ፣ ንግድ፣ ትምህርትና ጥበብ የሚሰፋበትን የሕዝባችን ሕይወቱና ሀብቱ የሚጠበቅበትን የሀገር አስተዳደርም በአዲሱ ስልጣኔ ተለውጦ ፍጹም የሚሆንበትን ይህን ለመሰለው ለምንደክምበት ሥራ አብሮ ደካሚ መሆን አለባችሁ» ብለው ነበር።

ይሄ የኢትዮጵያውያን የድል ብስራት የሆነው የአርበኞች ቀን ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት ነው። በዚህ ጦርነት ውስጥ ምላጭ ስቦ ጥይት ከተኮሰው አርበኛ በተጨማሪ በየቤቱ ሆኖ በተለያየ መልክ በውጊያው የተሳተፈው ሰው ቀላል አልነበረም። በትግሉ ጊዜ የአርበኞች ዋናው ችግር ቀለብ ነበር። ቀለባቸውን የሚያገኙትም ከአርሶ አደሩ ቤት ነው። ይሄ ነገር የሚሆነው ታዲያ በግድም በውድም ነበር። በተለይም ከጠላት ጋር የሚያብሩ ሰዎችን ደግሞ እህላቸው እንዲዘረፍና ለሠራዊቱ ቀለብ እንዲሆን ተደርጓል።

ሠራዊቱ ‹‹ደረቅ ጦር›› እና ‹‹መደዴ ጦር›› ተብሎ ለሁለት ተከፍሎም ነበር። ደረቅ ጦር የተባለው ሙሉ በሙሉ ውጊያ ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤ ‹‹መደዴ ጦር›› የተባለው ደግሞ እንደሁኔታው የእርሻ ሥራ ላይ እንዲሰማራ ይደረጋል። ነገሩ ሲከፋ ግን አርበኞች ፍራፍሬ፣ ቅጠላቅጠልና የዱር አውሬ ሁሉ እየበሉ ተዋግተዋል። እናቶች ከሠራዊቱ ጋር አብረው በመዝመት ምግብና ውሃ ከማቀበል በተጨማሪ ባህላዊ ሕክምና እየሰጡ ሠራዊቱን ታድገዋል። የወደቀውን በማንሳት የቆሰለውን በመጠገን ተሳትፈዋል። ይህ የአርበኞች ቀን የሁሉም ኢትዮጵያዊ የተጋድሎ ድል ነው ማለት ይቻላል።

በእዚህ የአርበኞች የድል በዓል ላይ የሲልቪያ ፓንክረስት አስተዋፅዖም ሊጠቀስ ይገባል። ሲልቪያ ፓንክረስት እንግሊዛዊት ናት። የኢትዮጵያ በፋሽስቶች መወረር ያንገበገባት ሴት ናት። ከኢትዮጵያ ንጉሠ ጎን በመቆም የኢትዮጵያ አርበኛ ሆነች። New Times and Ethiopian News የተሰኘ ጋዜጣ ማሳተም ጀመረች።

ጋዜጣው በየሳምንቱ ለእንግሊዝ ፓርላማ አባላት የሚበተን ነው። ቀሪው ደግሞ ለሌሎች ታላላቅ ሰዎች የሚሰጥ ነው። ጋዜጣው ኢትዮጵያ ውስጥ ፋሽስቶች እየፈፀሙ ስላሉት አሰቃቂ ግፍ የሚገልጽ ነው። እንደ እንግሊዝ ያሉ ታላላቅ መንግሥታት ይህን ግፍ እንዲቃወሙ የሚቀሰቅስ ነው። በመጨረሻም የእንግሊዝ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጎን ቆሞ ፋሽስቶችን እንዲፋለም አደረገች።

አቶ ዘውዴ ረታ ደግሞ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት በሚለው መጽሐፋቸው ስለታሪካዊቷ ሚያዝያ 27 እንዲህ ጽፈዋል፦ ‹‹ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱ በከፍተኛ አጀብ እኩለ ቀን ስድስት ሰዓት ላይ ከታላቁ የዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት አደባባይ ላይ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሰንደቅ ዓላማችንን መልሰው ሰቀሉት፡፡ የክብር ዘብ ተሰልፎ፣ በራስ አበበ አረጋይ የሚመራው አሥር ሺህ አርበኞች ያሉት ጦር ዙሪያውን በሀገር ፍቅርና በብሔራዊ ስሜት እንደቆፈጠነ፣ በሱዳን በኩል የመጣውና በሻለቃ ዊንጌት የሚመራው የጌዲዮን ጦርም ተሰልፎ፣ መድፍ ተደጋግሞ እየተተኮሰ ሰንደቃችን በክብር ከፍ አለ፡፡›› ይላል፡፡

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከስደት መልስ መናገሻ ከተማቸው ሚያዝያ 27 ቀን ገብተው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከማውለብለባቸው አራት ወር በፊት ጥር 12 ቀን ሱዳን ድንበርን ተሻገረው ኢትዮጵያ ገብተው ያውለበለቡት ኦሜድላ ላይ እንደነበር በመፅሐፉ ተጠቅሷል፡፡

ከሰማንያ ስምንት ዓመታት በፊት የተፈጸመው የፋሺስት ጣሊያን ወረራ በኢትዮጵያ ላይ ብዙ መከራዎችን ትቶ ማለፉ አይዘነጋም፡፡ አርበኞች ሀገራዊ ነፃነት ለማስከበር የሕዝቡን ልዕልና ለማስጠበቅ ያደረጉት ተጋድሎ የትየለሌ ነው፡፡ ጣሊያን በዓድዋ ላይ የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል ከ40 ዓመት ቆይታ በኋላ በፋሺስታዊ መንግሥቷ አማካይነት በአምስቱ ዘመን የሠራችው ግፍ ተነግሮ አያልቅም፡፡ ወረራውን በፈጸመች ባመቱ በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በአዲስ አበባና በአካባቢው ከተፈጸመው ግፍ አንስቶ በሁሉም ክፍላተ ሀገር ብዙ ጥፋት ደርሷል፡፡

ከእነዚህም መካከል የመጀመሪያው የፋሺስት ወንጀለኞች የኢትዮጵያን ሠራዊት የፈቱበት በተምቤንና በሐሸንጌ በመርዝ ጋዘ ያደረሱት እልቂት ይጠቀሳል፡፡ ጣልያን ያልጠበቀችውና ዓለም አየዋለሁ ብላ ያላሰበችውን ድል ኢትዮጵያ በዓድዋ ተራሮች መካከል ተቀብላለች። ይህንንም ተከትሎ ሽንፈቷ የቆጫት የምትመስለው ጣልያን ቂም ይዛ ቆይታ፣ ለበቀል ከ40 ዓመታት በኋላ በ1928 ዳግም ኢትዮጵያን ወርራለች። ይህንንም በዘመናዊ የጦር መሣሪያና በወታደራዊ ኃይል ይበልጥ ተደራጅታ ያደረገችው በመሆኑ፣ በዓድዋ ጦርነት ከነበራት ትጥቅ ያልተሻለ ወታደራዊ አቅም ላልገነባችው ኢትዮጵያ እጅግ ከባድ ነበር። ነገር ግን አርበኞቿ በጽናት ከመዋጋት አልተቆጠቡምና ኢትዮጵያ ለማሸነፍ በቃች። ክብር ለሀገራቸው ደግም የማይተካ ውድ ሕይወታቸውን ያለስስት በመስጠት ነፃነቷን ጠብቃ እንድትኖር ለተዋደቁ ኢትዮጵያውያን!

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You