ኢትዮጵያ በ2025 የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂን እውን ለማድረግ በርካታ ተግባራት እያከናወነች ትገኛለች። ስትራቴጂውን እውን እንዲሆን ከሚያደርጉ አስቻይ ሁኔታዎች መካከል ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ አንዱ ነው። መታወቂያው አካታች ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ይታመናል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ዲጂታል መታወቂያ ከዜጎች በሚወሰዱ ውስን የባዮሜትሪክስ እና ዲሞግራፊክ መለያዎች አማካኝነት የተረጋገጠ መረጃ ለማቅረብ የሚያስችል ሲሆን፤ የዲጂታል ሥነ ምህዳር ለመፍጠር የላቀ ሀገራዊ ፋይዳ አለው። ለአካታች የማህበራዊ ኢኮኖሚ እድገት፣ ለቢዝነስ ትስስር፣ ለኢ-ጋቨርንመንት አገልግሎት፣ በዳታ የሚመራ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት፣ ለቀልጣፋ ማህበራዊ አገልግሎት፣ ለተሻለ የዜጎች ሕይወት እና የሳይበር ማጭበርበርን ለመከላከል አስተማማኝ ወሳኝ መሆኑ ይገለጻል።
አዳዲስ ምርትና አገልግሎቶችን ለዜጎች ለማቅረብ፣ የላቀ የደንበኞች አገልግሎት ተሞክሮን እውን ለማድረግ፣ የሥራ ፈጠራን ለማበረታታት፣ የኢኮሜርስ ግብይትን ለማሳለጥ፣ የፋይናንስ አካታችነትን የሚጨምሩ የአነስተኛ ብድር አገልግሎቶችን ያለ ዋስትና ለማቅረብ፣ የክሬዲት ግብይት ለማስፋፋት፣ የብድር ምጣኔን ለማሻሻል እንዲሁም የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ የሚያዘምኑ እና ቢዝነስን የሚያቀላጥፉ የዲጂታል አገልግሎቶችን ለማቅረብ ያስችላል። በሀገሪቱ የተማከለ ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ዳታቤዝ ለመገንባት ለቢዝነስ እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፈጣን እና አስተማማኝ የማንነት ማረጋገጫ በመስጠት የተሻለ አሠራርን እንዲተገብሩ ይጠቅማል።
ይህ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ለዜጎች ተደራሽ እንዲሆን ለማስቻል በብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮጀክት አማካኝነት ብዙ እየተሠራ ነው። በቅርቡም በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ዲጂታል መታወቂያ ተደራሽ እንዲሆን እና ሁሉም ዜጋ በፍጥነት አገልግሎት ማግኘት እንዲችል ኢትዮ ቴሌኮም ከብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮጀክት ጋራ ለመሠራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ፈርሟል።
በስምምነቱ ወቅትም ኢትዮ ቴሌኮም በሀገር አቀፍ ደረጃ በ29 ከተሞች የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባን አስጀምሯል። በኩባንያው 32 ሚሊዮን ዜጎችን የዲጂታል ተደራሽ በማድረግ ሀገራዊ እቅዱን 36 በመቶ ያህል ለማሳካት አቅዶ ሥራ ጀምሯል።
ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አስቻይ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ተዓማኒነት ያለው የማንነት መለያ ዲጂታል መታወቂያ መሆኑን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ አስታውቀዋል። ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ አካታች ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባትና ዜጎች በኢኮኖሚው እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እድል ይፈጥራል ሲሉ አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የዲጂታል እድሎችን መጠቀም ፈጠራ የታከለበትና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት ወሳኝ ነው። ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን እውን ለማድረግ በርካታ መሠረተ ልማቶች እየገነባ ይገኛል። ስትራቴጂውም አራት ዋና ዋና አስቻይ ሚና ይጫወታሉ ተብለው የተለዩ ጉዳዮች አሉት። የመጀመሪያው ኮኔክቲቪቲ (የሞባይል የኢንተርኔት እና የመሳሳሉት) ሲሆን፤ አገልግሎቶችን በሰፊው ተደራሽ ማድረግን ይመለከታል። ሁለተኛው አስቻይ ሁኔታዎችን /ኢነበሊንግ ሲስተም/ ሲሆን፣ አስቻይ ሲስተሞች ከሚባሉት መካከልም አንደኛው ዲጂታል መታወቂያ ነው።
ዲጂታል መታወቂያ ዜጎች በየትኛውም ስፍራ፣ በማንኛውም ሰዓት ማንነታቸውን የሚገልጽ ተዓማኒነት ያለው መለያ እንዲኖራቸው ያስችላል። ይህ ሲሆን ደግሞ በመንግሥትና በዜጎች መካከል በቀላሉ መረጃ መለዋወጥ ብቻ ሳይሆን፣ የአገልግሎት ተደራሽነት የሚረጋገጥበት እድል ይፈጠራል። ይህም አስቻይ ሁኔታ ዲጂታል መታወቂያን ብቻ ሳይሆን እንደ ቴሌብር ያሉ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶችንም ይዟል።
ሦስተኛው ምህዳሩን ደህንነቱ የተጠበቀ ማድረግ ነው። ይህም በቀላሉ የመንግሥት አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ ዜጎች ካሉበት ሆነው በተቀላጠፈና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ አገልግሎትን እንዲያገኙ ያስችላል። አገልግሎቶችን በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ እድል ይፈጥራል።
አራተኛውና የመጨረሻው ምህዳሩ /ኢኮ ሲስተም/ እንዲኖር ያስፈልጋል። የዲጂታል ምህዳሩ የሚፈልገውን እውቀት ለማምጣት ሰዎች ላይ መሥራት ይጠይቃል። ምቹ የሆኑ አስቻይ የፖሊሲና ሪጉሌሽን ሥርዓቶችን መዘርጋትንም እንዲሁ ይጠይቃል።
ዲጂታል መታወቂያ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ረገድ በርካታ አስቻይ ሁኔታዎች መፍጠር ይችላል የሚሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ፤ ከዲጂታል ኢትዮጵያና ከዲጂታል ኢኮኖሚ አንጻር ሲታይ አካታች ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመፍጠር ትልቅ እድል እንደሚፈጥር አስታውቀዋል። ዲጂታል ኢኮኖሚ እየገነባን ተደራሽና አካታች ካልሆነ ትርጉም አልባ ይሆናል ሲሉ ያስረዳሉ።
ዲጂታል መታወቂያ ለአካታች ኢኮኖሚ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሁሌም ዜጎች በኢኮኖሚ ግንባታ የሚሳተፉበት እድል የሚፈጠርበትና ከዲጂታል ኢኮኖሚ የሚገኙ ቱሩፋቶችን ተጠቃሚ መሆን የሚችልበትም እንደሚሆን አመልክተዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ሀገራት ለዜጎቻቸው ተአማኒነት ያለው መለያ የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው። ዜጎች በየትኛውም ቦታ ሆነው ማንነታቸውን ማረጋገጥ የሚችሉበት ተአማኒነት እና እውቅና ያለው መለያ ሊኖራቸው ይገባል። አንድ ዜጋ ይህ ዲጂታል መታወቂያ ሲኖረው ደግሞ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ራሱን ማሳተፍ እንዲችል ትልቅ እድል ይፈጥርለታል። የሕዝብና የመንግሥት አገልግሎት የሚባሉትን በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ ያስችላል።
ለአብነት ለዜጎች የጤና እንክብካቤ ለመስጠት ሲፈለግ በዲጂታል መታወቂያ ማንነቱን በማረጋገጥ ካለበት ስፍራ ሆኖ አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ ይቻላል። በአገልግሎት ሰጪውም ሆነ በተቀባዩ መካከል ተአማኒነት ይፈጥራል። ይህ ሲሆን ደግሞ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን ለማሳለጥ፣ ኢ ኮሜርስና አዳዲስ አገልግሎቶች ተደራሽ ለማድረግ መደላደል ይፈጥራል። አካታች የሆነ አስተዳደር እንዲኖር ስለሚያደርግ ዜጎች ካሉበት ሆነው መደበኛ የሚባሉ የመንግሥት እና ሌሎች አገልግሎቶች በእኩል ማግኘት የሚችሉበትን እድል ለመፍጠር ያስችላል።
‹‹ዲጀታል መታወቂያ በመረጃ የሚመራ ኢኮኖሚን ለመገንባት ያስችላል፤ እንዲህ ዓይነት ኢኮኖሚ ስንገነባ ደግሞ በመረጃ ላይ የተመሠረተ የፖሊሲ ማሻሻያ ለማድረግ እንችላለን›› የሚሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ኢኮኖሚውን ለመገንባትም ሆነ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት መረጃ ላይ የተመረኮዘ ማሻሻያ እንዲደረግ በእጅጉ እድል ይፈጥርልናል ይላሉ።
በዲጂታል ዓለም ሊከሰቱ የሚችሉ የተለያዩ ወንጀሎች ለመከላከል ያግዛል። የዲጂታል መታወቂያ መኖር ጊዜና ወጪ በመቆጠብ ዜጎችንም ሆነ አገልግሎት ሰጪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ዲጂታል መታወቂያ እንዲኖር የሚያስችል መሠረተ ልማት መገንባት የሚያስፈልገው በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች መሆኑን አብራርተዋል።
ብዙ ጊዜ ገንዘብና ጊዜ የሚባክነው ማንነትን ለማወቅና ለማጣራት በሚደረግ ሂደት እንደሆነ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ጠቅሰው፤ ለዚህም ዜጎች በጣም ቀላል የሚባሉ አገልግሎቶችን ባሉበት ሆነው ማግኘት መቻላቸውን በአካል ቀርቦ እስከሚረጋገጥ ድረስ ረጅም ጊዜ ይፈጃል። ዲጂታል መታወቂያ መኖሩ ግን ለሰው ልጅ ዘመናዊ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ እንዲኖር እድል ይፈጥራል፤ ጊዜና ገንዘብንም ይቆጥባል ሲሉ አብራርተዋል።
የዲጂታል መታወቂያ መኖር ዜጎች ካሉበት ቦታ ሆነው ራሳቸውን በመግለጽ በቀላሉ አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚያስችል ጠቅሰው ፤ የንግድ ተቋማት ያላቸውም አዳዲስ ምርትና አገልግሎቶችን ለገበያ ማቅረብ እንደሚያስችላቸው አመላክተዋል፡
ዲጂታል መታወቂያ ተግባራዊ ያደረጉ ሀገራት ኢኮኖሚያቸውን በማሳደግ ዜጎችና መንግሥት ያላቸውን ግንኙነት በማሻሻል አገልግሎቶች እንዲፋጠኑ ትልቅ እድል ፈጥሮላቸዋል የሚሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ በእኛ ሀገር ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በፍጥነት ለሁሉም ዜጋ ተደራሽ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ባለፉት ጊዜያት እንደ ሀገር በተሠሩ ሥራዎች አራት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዜጎች ብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸው የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ካለው ሕዝብ ቁጥር አኳያ በዚህ አካሄድ ሁሉንም ተደራሽ ለማድረግ እንደማይቻል ተናግረዋል። ኢትዮ ቴሌኮም ይህን ክፍተት በመሙላት መታወቂያው በፍጥነት ተደራሽ እንዲሆን አልሞ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ እንዳብራሩት፤ ብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያ ምዝገባው አዲስ አበባን ጨምሮ በ29 ከተሞች በይፋ የተጀመረ ሲሆን፣ ኢትዮ ቴሌኮም ዜጎች ተደራሽ ለመሆን በአገልግሎት መስጫ ማዕከላት አገልግሎቱን መስጠት ጀምሯል። በተጨማሪም ዜጎች ባሉበት ቦታ ሆነው በቴሌ ብር ሱፐርአፕ ምዝገባውን ማከናወን ይችላሉ። በቀጣይም ከአጋሮች ጋር በመሆን አገልግሎቱን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ በተለያዩ ከተሞች የማስፋፊያ ሥራ ይሰራል።
በሀገር ደረጃ 2018 ዓ.ም 90 ሚሊዮን ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ እንዲያገኙ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በወር በአማካኝ አንድ ሚሊዮን ዜጎችን ለመመዝገብ ታቅዷል ይላሉ። ከ90 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም 32 ሚሊዮን የሚሆኑትን እንደሚመዘገብ አስታውቀዋል።
‹‹ዲጂታል ኢኮኖሚው እየፈጠነ ዲጂታል መታወቂያ ወደኋላ የሚቀር ከሆነ ተደራሽ መሆን የሚቻለው ለጥቂቶች ብቻ ነው›› የሚሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ጤናማና ዘላቂነት ያለው፣ ሁሉም የዲጂታል ኢኮኖሚ ከሚያመጣው መልካም አጋጣሚ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችልበት አሠራር መዘርጋት ወሳኝና አስፈላጊ ነው ብለው እንደሚያሰቡ ተናግረዋል።
እሳቸው እንደተናገሩት፤ የብሔራዊ መታወቂያ አንደኛው ጠቀሜታ አካታችነት ማምጣት ስለሆነ ይህን ለማሳካት አንድ ሺ ሁለት መቶ የመመዘገቢያ ኪቶችን በመግዛት ሥራው ተጀምሯል። ይህን እቅድ ለማሳካት በአገልግሎት ማዕከሉ ብቻ ሳይሆን የሞባይል ቲም/ቡድን/ እንዲኖር ይደረጋል። ሞባይል ቲም እንዲኖር ያስፈለገበት ምክንያት አንዳንድ ተቋማትና ስደተኞች ወደ አገልግሎት ማዕከላት መጥተው ለመመዝገብ ስለሚቸገሩ ነው፤ እነዚህ ወገኖች ባሉበት ሆነው ምዝገባውን ማከናወን እንዲችሉ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
በአዋጁ መሠረት ዲጂታል መታወቂያውን የማግኘት መብት ያላቸው ከአምስት ዓመትና ከአምስት ዓመት በላይ የሆኑ ዜጎች ሲሆኑ፤ ከኢትዮጵያውያን ውጭ ደግሞ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሕጋዊ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ ያላቸው የውጭ ሀገር ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ እንዲወሰዱ ይፈቅዳል።
ዲጂታል መታወቂያውን ለመወሰድ የሚያስፈልገውን ማንነት የሚገልጽ የቀበሌ መታወቂያ፣ አልያም መንጃ ፈቃድ ያስፈልጋል፤ ከዚህ ውጭም የትኛውንም ዓይነት ሰነድ በመያዝ በአገልግሎት መስጫ በማቅረብ በፍጥነት አገልግሎት ማግኘት ይቻላል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ከከተማ እና የገጠር ነዋሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲ፣ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ እና የብሔራዊ ሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ተፈታኝ ተማሪዎች፣ በተፈናቃዮች ጣቢያ የሚገኙ፣ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚዎች እና ሕጋዊ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ ያላቸው የውጭ ሀገር ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ማከናወን ይችላሉ። ዲጂታል የክፍያ አገልግሎቶችን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ ወሳኝ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም