‹‹በዕድሜ ጉዳይ የማያዳግም ርምጃ ሊወሰድ ይገባል›› – የአትሌቲክስ ቤተሰቦች

የኢትዮጵያ ታዳጊ ፕሮጀክቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ዘንድሮ ለ2ኛ ጊዜ በሃዋሳ ከተማ ተካሂዷል። ውድድሩ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች እና ከ18 ዓመት በታች በታዳጊ ፕሮጀክቶች የታቀፉ አትሌቶች የሚሳተፉበት ቢሆንም ከዕድሜ ማጭበርበር ጋር ተያይዞ ጥያቄ የሚነሳባቸው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች መኖራቸው ተስተውሏል። በዚህም ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ አሠልጣኞችና ታዳጊ አትሌቶች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የማያዳግም ርምጃ መወሰድ እንደሚኖርበት አሳስበዋል። ፌዴሬሽኑም በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የዕድሜ ማጭበርበር ችግር መኖሩን አምኗል።

የኢትዮጵያ ታዳጊ ፕሮጀክቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ባለፉት ቀናት በርከት ያሉ የማጣርያና የፍጻሜ ፉክክሮችን እያስመለከተ ቆይቷል። ታዳጊ አትሌቶች የውድድር ዕድልን እና ልምድን የሚቀስሙበት መድረክ ቢሆንም ከዕድሜ ማጭበርበር ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉት ችግሮች በታዳጊ አትሌቶች ዘንድ የሞራል ውድቀትን እንዳያደርስ ያሰጋል። ችግሩ መፍትሔ ያልተገኘለት ጉዳይ ሆኖ መቀጠሉን ተከትሎም ሀገርን የሚወክሉ ተተኪ አትሌቶች እንዳይፈጠሩ እንቅፋት መሆኑ አይቀርም፡፡

በአትሌቲክሱ ላይ የተጋረጠውን ይህንን ችግር ለማስቀረትም አስተማሪና የማያዳግም ርምጃ መወሰድ እንደሚኖርበት አትሌቶች፣ አሠልጣኞች እና የቴክኒክ ኃላፊዎች ገልጸዋል። በክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች እና በብሄራዊ ፌዴሬሽኑም በትኩረት ሊሠራ ይገባል። በማጭበርበር የሚገኘው ውጤት ጊዜያዊና ስፖርቱን የሚያቀጭጭ ነውና።

ታዳጊ ሞገስ ጌታሁን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን በመወከል ከ16 ዓመት በታች በ800 ሜትር 2ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ታዳጊ ነው። እድሜን በሚመለከት የምርመራው ሁኔታ መጠናከር እንደሚኖርበትና የዛሬን ውጤት ብቻ ሳይሆን በትክክለኛ ዕድሜ ለሚወዳደሩ አትሌቶች መንገድ መከፈት እንደሚኖርበት ይልጻል። ለጊዜያዊ ውጤት ተብሎ የሚደረገውን የዕድሜ ማጭበርበር ለማስቀረትም ትኩረት ሊሰጥ ያስፈልጋልም ባይ ነው።

ከትግራይ ክልል ከ18 ዓመት በታች 3 ሺ ሜትር ውድድር ሶስተኛ ደረጃን የያዘችው ህልፈይ ካህሳይ፤ ውድድሩ ጥሩ ፉክክር የተስተናገደበት ቢሆንም የዕድሜ ተገቢነት ክፍተት መኖሩን ጠቁማለች። ይህ በመሆኑም በውጤቷ ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ ሲሆን፤ በቀጣይ መስተካከል እንደሚኖርበት ገልጻለች። ሌላኛዋ የትግራይ ክልልን የወከለችው ተወዳዳሪ ማዕረግ ዓለም ከ18 ዓመት በታች 800 ሜትር ሁለተኛ ነው ያጠናቀቀችው። ፉክክር በተስተናገደበት ውድድር ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ክፍተቶች መስተካከል እንደሚኖርበት ገልጻለች። አዲስ አበባን ከ18 ዓመት በታች 800 ሜትር ወክላ አንደኛ የወጣችው ኤደን ከተማም በተመሳሳይ የዕድሜ ፍትሃዊነት ላይ እርማት እንደሚያስፈልግ ገልጻለች።

የደቡብ ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ኃላፊ አቶ መንግስቱ ጋልቹ በበኩላቸው፤ የታዳጊ ወጣቶች ውድድር ታዳጊ አትሌቶችን ለማፍራት የሚደረግ እንደሆነና የሚሻሻሉ ነገሮች ቢኖሩም ጅማሮው መልካም መሆኑን ይገልጻሉ። ሀገርን የሚወክሉ አትሌቶችን እየተመለከቱ የሚያድጉ ሠልጣኞች እንደመሆናቸው ክልሎች፣ ፕሮጀክቶችና አሠልጣኞች መሥራት ያለባቸው የእድሜ ጣራ ላይ ሊሆን ይገባል። ፌዴሬሽኑም መታረም የሚገባውን አርሞ ማለፍ ይኖርበታል። ባለፈው ዓመት ከነበረው ሁኔታ መሻሻል ቢኖርም አሁንም ግን ክልሎች በዕድሜ ጉዳይ ኃላፊነትን መወጣትና ፌዴሬሽኑም የጠበቀና የማይቆራረጥ ርምጃ መውሰድ አለበት።

የትግራይ ክልል አትሌቲክስ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ሰለሞን ጸጋይ፤ ውድድሩ ጥሩ ቢሆንም ከዕድሜ ተገቢነት ጋር ተያይዞ ተገቢነት እንደሌለ ይጠቁማሉ። ትክክለኛውን የዕድሜ እርከን ጠብቀው የሚወዳደሩ እንዳሉ ሁሉ ከተፈቀደው ዕድሜ በላይ የሆኑ አትሌቶችን ያሰለፉ በመኖራቸው ፌዴሬሽኑ የማስተካከያ ርምጃ መውሰድ ይኖርበታል። በዕድሜ ማጭበርበር ምክንያት ወደ ፊት ኢትዮጵያ የምትኮራበት ውጤት ሊጠፋ ይችላል። በፌዴሬሽኑ በኩል ለበርካታ ዓመታት ችግሩ ሲፈጠር ርምጃ ይወሰዳል ቢባልም አስተማሪ አለመሆኑንና ክልሎች ተገቢውን አትሌት የማያሰልፉ ከሆነ ተቀጥቶ ለሌሎች ማስተማርያ ማድረግ እንደሚኖርበትም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሳትፎና ውድድር ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ፣ ውድድሩ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ እየተካሄደ ቢሆንም ከዕድሜ አንጻር እንደተጠበቀው አለመሆኑን አስረድተዋል። ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አትሌቶችን ሕጋዊ ከሆነ የህክምና ተቋም አስመርምረው በትክክለኛ የዕድሜ ደረጃ የሚገኙትን እንዲያሳትፉ መልዕክቱን አስተላልፏል። ነገር ግን አሠልጣኞችና የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ሁኔታው ቀጥሏል።

በእርግጥም በሁሉም የውድድሩ ተካፋይ ክልልና ከተማ አስተዳደር የዕድሜ ችግሮች ይስተዋላሉ። በተወዳዳሪ አትሌቶች ምትክ በትክክለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሠልጣኞች መቅረታቸውንም ይገልጻሉ። ጉዳዩ ስህተትም ወንጀልም በመሆኑ የአሠልጣኞች፣ ቡድን መሪዎችና የቴክኒክ ኃላፊዎች የቤት ሥራ መሆን ይኖርበታል። ለተከሰተው ጥፋትም በሚቀርበው ሪፖርት መሠረት ውሳኔው በቀጣይ እንደሚገለጽም አስረግጠዋል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You