ቅድሚያ ለሴት ወይስ ቅድሚያ ለቆንጆ?

ብዙ ጊዜ የምታዘበው ቢሆንም የቅርብ አጋጣሚ ብቻ ልጥቀስ። ባለፈው ሐሙስ ላምበረት አደባባዩ አካባቢ አንዲት ከክፍለ ሀገር እንደመጣች የምታስታውቅ ልጅ መንገድ ልታቋርጥ ሻገር ማለት ስትጀምር አንድ በወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኝ አሽከርካሪ ልትሻገር በምትችልበት ርቀት ላይ እያለ አካባቢውን የሚያናውጥ ‹‹ክላክስ›› አደረገ። ልጅቷ ተደናግጣ ወደኋላ ተመለሰች። ይህ ብቻ አይደለም! ሲያልፍ አንገቱን አሾልኮ የስድብ መዓት አወረደባት። ‹‹ክላክስ›› ከማጮሁ ጀምሮ በቁጣና በትዝብት ሲያዩት የነበሩ ሰዎችን አላያቸውም።

እንዲህ አይነት ማደነባበር እንኳን እንግዳ ነው ተብሎ ለሚታሰብ ሰው ለከተማው ነዋሪም ያስደነግጣል። ጭራሽ ልጅቷ ተደናብራ አደጋ ላይ እንድትወድቅ የሚያደርግ ነው። ደግሞስ በዚያ ልክ አካባቢውን በሚያናውጥ ሁኔታ ባይሆን ምን ችግር ነበረው? ማስጠንቀቁ ትክክል ሆኖ ሳለ ያንን ሁሉ ቁጣ እና እልህ ምን አመጣው? የማይናገሩና የሚፈሩ ሴቶችን ሲያዩ ለምን ደማቸው ይፈላል? ይህን የምልበት ምክንያት ብዙ ጊዜ ስለታዘብኩት ነው። ምናልባት አለባበሷ እና ገጽታዋ እነርሱ ማየት የሚፈልጉት አይነት ስላልሆነ ይሆን?

‹‹ዘናጭ›› የሚባል አይነት የተራቆተ አለባበስ የለበሰች፣ በሹል ጫማ የተንጠለጠለች ሴት ሲያዩ ግን ገና ከብዙ ሜትር ርቀት ላይ እጃቸውን አውጥተው እንድታልፍ ይማጸናሉ። ይህ ተገቢ እና መሆን ያለበት ነው፤ ዳሩ ግን ነገርየው የሰብዓዊነት ከሆነ ለምን ለተጎሳቆሉት አይሰራም?

እዚህ ላይ ግን ‹‹ዘናጭ›› የሚባሉትን አይሳደቡም፣ አይገላምጡም ማለቴ አይደለም፤ ይህንንም ብዙ ቀን ታዝቤ አውቃለሁ። የሚሳደቡበትና የሚናገሩበት ዓውድ ግን ይለያያል። ‹‹ዘናጭ›› የተባለችዋ በተለምዶ ‹‹መላከፍ›› የሚባለውን አይነት ነው። መጨቃጨቁንም ሆነ መሳደቡን እንደ አንድ የመግባቢያ መንገድ በማየት ወይም ‹‹ይሄውም ተስፋ ነው›› በሚል ነው። ከተናገሩም ‹‹ምን ትመስላለች! ሂጂ ወደዚያ!›› አይነት ጭቅጭቆች ናቸው። ያም ሆነ ይህ ይህም ቢሆን የኋላቀርነት መገለጫ የሆነ ነውር ነው። ከዚህም በላይ የከፋው ግን የተጎሳቆሉና ‹‹ዘናጭ›› የማይባሉትን የሚሳደቡበት ቋንቋ በጣም የከፋ መሆኑ ነው። ከልባቸው ተናደው፣ የደም ሥራቸው እየጠወጣጠረ ነው የሚሳደቡ፤ ይህ ከምን የመጣ ይሆን? ለምን እኔ በምፈልገው ልክ አልዘነጠችም ነው? አንደኛው ምክንያት ይህ ሲሆን ሌላኛው ምክንያት ግን ወዲህ ነው፡፡

‹‹ዘናጭ›› የሚባሉት ትንሽም ቢሆን ነቃ ያሉ ናቸው ተብሎ ይታሰባል። መብታቸውን ያስከብራሉ፣ ለነፃነታቸው ይሟገታሉ ተብሎ ይታመናል። ያም ሆኖ ግን እነርሱም ቢሆን ከስድብ ያለፈ ትህትና ያለው ነገር ማየት እምብዛም ነው። እንዲህ አይነቶቹን እናገራለሁ ቢል እጥፍ ስድብ ይጠብቀዋል። እንዲያውም አንዳንዶቹ አስቀድመው የዱቤ የሚሳደቡም አሉ። ‹‹ምናባቱ ይመስላል!›› በማለት በያዘው መኪና አይነትም ሊሳደቡ ይችላሉ። ይህ የስድብ አቻነት ያመጣው ጫና ነው መሰለኝ ዘናጮቹ ላይ ቁጣውና ስድቡ ያን ያህልም ነው፡፡

በአለባበሷ፣ በተክለ ሰውነቷም ሆነ በአጠቃላይ ነገረ ሁኔታዋ ከገጠር የመጣች የመሰለቻቸውን ግን እንደማትሳደብ ያውቃሉ። ስለዚህ የስድብ አምሮታቸውን ሁሉ የሚወጡ እንደዚች አይነቷ ላይ ነው። ‹‹ምናባሽ! እያየሽ አትሄጂም?›› ሲላት ተደናግጣ ዝም ነው የምትለው። የአብዛኞቻችን ችግር ደግሞ ፈሪ ላይ መበርታት ነው። የማይናገሩት ላይ መደንፋት ነው። ይናገሩኛል ተብሎ የሚጠረጠሩት ላይ የማሽቃበጥ ቀብዲ ነው የሚሰጠው። ይህንን በብዙ ሁኔታዎች ልብ ብሎ መታዘብ ይቻላል፡፡

ለምሳሌ፤ አለቃውን ቀና ብሎ የሚናገር ሠራተኛ አይኖርም፤ ወይም እጅግ በጣም ጥቂት ነው። የበታቹን ቁም ስቅል የሚያሳይ ግን መዓት ነው። የታክሲ ረዳት ላይ የሚደነፋው ብዙ ነው፤ ለአንድ የቀበሌ የሥራ ኃላፊን ግን ጠንከር ያለ አስተያየት እንኳን አይሰጥም። አስተናጋጅ ላይ የሚጮኸው ብዙ ነው፤ ባለቤቱ ሲመጣ ግን እየተሽቆጠቆጠ ያስተባብላል፤ ወይም በጣም ተለሳልሶ ይናገራል። እንዲህ አይነት ልማድ ባህላችን የሆነ ሁሉ ይመስላል፡፡

በብዙ የአገልግሎት ቦታዎች ላይ በግርምት አስተውየ አውቃለሁ። በአካላዊ ቁመናም ይሁን በአለባበስ ‹‹ቆንጆ›› የምትባል ሴት ስትመጣ ቦታ ለመስጠት፣ ቅድሚያ ለመስጠት፣ ለሚያስፈልጋት ነገር ለመተባበር የሚረባረበው ብዙ ነው። በዚያው አገልግሎት ቦታ ላይ ግን ጎስቆል ያለች ሴት ካለች ማንም ልብ አይላትም። ምናልባት በዕድሜ የገፋች ወይም የአካል ጉዳት ከሌለባት በስተቀር ቅድሚያ የሚሰጣት የለም። ሲጀመር በዕድሜ የገፋች ካልሆነችና የአካል ጉዳት ከሌለባት ለምን ቅድሚያ ይሰጣታል? ይባል ይሆናል። ‹‹ዘናጭ›› የምትባለዋን ታዲያ ለምን ይረባረቡባታል? ቅድሚያ ለሴት ከተባለ አገልግሎቱን ማግኘት ያለባት የትኛዋም ሴት ናት። የተጎሳቆለች የምትመስለዋን ማንም ልብ ካላላት ግን ነገርየው የሰዋዊነት ሳይሆን የግል ስሜትና ፍላጎት ነው። በእርግጥ ትብብር የሚደረገው በግል ስሜትና ፍላጎት ነው። ቆንጆ ቆንጆዎችን ብቻ እየለዩ ማድረጉ ግን ከሰብዓዊነት ያርቃል። ይህ ነገር ግን ተፈጥሯዊ ይሆን ወይስ በልማድ የመጣ?

ለምሳሌ፤ አንድ በሀሜት የሚነገር ነገር አለ። የሥራ ቅጥር ወይም ሌላ ውድድር ላይ ቆንጆ ሴት ካለች ‹‹ውይ! በቃ ይቺ ናት የምታልፍ!›› እየተባለ በቀልድም በቁም ነገርም ይነገራል። ከዚህ ሁኔታ በመነሳት ይህ ሀሜት እውነትነት ይኖረዋል ብሎ ለመገመት ያስገድዳል። ፈታኙ ወይም አወዳዳሪው አካል ቢያገኛትም ባያገኛትም መጓጓቱ አይቀርም ተብሎ ይገመታል። ይህ ደግሞ ከሕግና መርህ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሰብዓዊነትም ጋር ይጣረሳል ማለት ነው። ሰዎችን እኩል ማድረግ ሕግ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊነትም ነው።

እንዲያውም በዚህ ሀሜት ምክንያት አንድ የተዛባ ልማድ ተፈጥሯል። ለምሳሌ፤ አንዲት ቆንጆ የምትባል ሴት (‹‹ውበት እንደ ተመልካቹ ነው›› የሚለውን እንያዝና) አንድ ውድድር ብታልፍ በብቃቷ አይደለም ሊባል ነው ማለት ነው። በብቃቷ መመስገን ሲገባት በሌላ ነገር ነው የሚል ሀሜት ለወርድባት ነው ማለት ነው። ስለዚህ ይህ ሀሜት መቅረት አለበት፣ ይህ ሀሜት ይቀር ዘንድ ደግሞ አካላዊ ገጽታን መሠረት ያደረጉ ግልጽ ልዩነቶች ሊቀሩ ይገባል። የአሠራር ሕግና ደንብ ባላቸው በትልልቅ ቦታዎች ብቻ ሳይሆን እንደ ወረፋ ባሉ ጥቃቅን ነገሮችም ጭምር ማለቴ ነው።

መነሻዎቼ አሽከርካሪዎች ነበሩና ቅድሚያ ለቆንጆ ብቻ ሳይሆን ቅድሚያ ለሰው ስጡ!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You