እንግሊዝ ከእ.ኤ.አ ከ1841በቀኝ ግዛት ስር ያስተዳደረቻት ሆንግ ኮንግ ወደ ቻይና የተመለሰችው እኤአ1997 ነው። ከዚህ ዓመት አንስቶም ቻይናና ሆንግ ኮንግ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት«አንድ ህዝብ ሁለት አስተዳደር» መርህን ሲተገብሩ ቆይተዋል።
ቻይና ሆንግ ኮንግ ምንም እንኳን የግዛቷ አካል ብትሆንም በሁሉም ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮቿ ላይ ጣልቃ እንደማትገባ አስቀድማም አረጋግጣለች፡፡ ሁለቱም ወገኖች ስምምነቶችን አክበረውና ተከባብረው ዓመታትን ቢዘልቁም ፣በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ግን የቻይና ጣልቃ ገብነት በዝቶብኛል በሚል ሆንግ ኮንግ ከቻይና ጋር እስጣ አገባ ስትገጥም ይስተዋላል።
በተለይ ከአምስት ዓመታት ቀድሞ ሆንግ ኮንግ« የዣንጥላው ተቃውሞ»የተሰኘና የቤጂንግን አስተዳደር ጣልቃ ገብነትን የሚቃወም ታላቅ ህዝባዊ ሰልፍ ያካሄደች ስትሆን፣ ይህም በታሪክ ከተከሰቱት እጅጉን ግዙፉ ተቃውሞ እስከመባልም ደርሷል።
ይህ ዓይነቱ ተቋውሞ ባሳልፈነው ሳምንትም በድጋሚ ተከስቷል። በሆንግ ኮንግ በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ተላልፈው ለቻይና እንዲሰጡ የሚፈቅድ ረቂቅ ህግ በሆንግ ኮንግ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መቅርቡም ነው ለተቃውሞው መነሻ የሆነው።
ሆንግ ኮንግ ብሪታኒያንና አሜሪካን ጨምሮ ከ20 አገራት ጋር በእስረኞች ልውውጥ ስምምነት ቢኖራትም ከቻይና መንግሥት ጋር ግን መሰል ውል አላሰረችም። ይህ በሆነበት ታዲያ ከሰሞኑ የእሰረኞች ለውውጥ ረቂቅ ህግ ይፋ መሆኑ የዓለም የፋይናንስ እንቅስቃሴና እጅግ በጣም ሀብታም ህዝብ ከሚኖርባቸው ሃገራት ውስጥ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የምትሰለፈው ሆንግ ኮንግ ዋና ጎዳናዎች ከ200 ሺ በላይ ሰዎች ለተቃውሞ እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል።
ተቃዋሚዎቹም«አዲሱ ረቂቅ ህግ በቻይና መንግሥት የተጠነሰሰና በይፋ ባይታይም የቤጂንግ እጅ ያለበት ነው፤ይህ ደግሞ በልዩ አስተዳደር የምትመራውን ሆንግ ኮንግ ኡአላዊነት የሚቀማ ነው፤ ከሁሉም በላይ የፖለቲካ እስረኞችን ለመቅጣት የተቀመረ ነው ሲሉም» ተቃውመውታል።
የሆንግ ኮንግ ፖሊስ የተቃውም ሰለፉን ለመበተን የኃይል ዕርምጃ መውሰድን ምርጫው ማድረጉና አመፁን ለማስቆም አስለቃሽ ጭስን ጨምሮ የተለያዩ የአፀፋ ምላሾችን ማድረጉ ታውቋል።
የፖለቲካ አክቲቪስትና የሆንግ ኮንግ ናሽናል ፓርቲ መስራቹን አንዲ ቻንን ጨምሮ በርካታ ወገኖች ረቂቅ ህጉ ጸድቆ የሚተገበር ከሆነ ለከተማዋ ከባድ ከባድ ቀውስ ነው ሲሉ ቢደመጡም፤የቻይና መንግሥት ድጋፍ እንዳለው የሚነገርለት የከተማዋ አስተዳደር በአንፃሩ፤ የህግ ለውጡ እጅጉን አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ ተሟግቷል። የህዝብ ደህንነት ማስጠበቅን ታሳቢ አድርጎ የተቀመረ ረቂቅ ህግ መሆኑን በመጥቀስም ከመቃወም ይልቅ መደገፍ ይገባል በሚል አስገንዝቧል።
ይህ የሆንግ ኮንግ አስተዳዳር መግለጫ ግን ለሆንግ ኮንግ ህዝብ ፈፅሞ አልተዋጠለትም። የአስተዳደሩ መግለጫ በሀገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ሳይቀር ተቃውሞ እንዲቀርብበት አስገድዷል።
የአውሮፓ ህብረትና አባል አገራቱ በተናጠል ረቂቅ ህጉን በተቃወሙት ላይ የሆንግ ኮንግ አስተዳደር እየወሰደ ያለውን የአፈና ዕርምጃ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የተጋፋና ህጉን ያማከለ አይደለም በሚል ተቃውሟቸውን አቅርበዋል። የቀድሞው የሆንግ ኮንግ ቅኝ ገዥ ብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀርሚ ሃንትም ይህን ሃሳብ ተጋርተዋል። ታይዋንም የሆንክ ኮንግ አስተዳደርን ውሳኔ ተቃውማለች።
ቤጂንግ እንድምታስበው ግዛቷ ላልሆን ሉዓላዊ አገር ነኝ የምትለው ታይዋን፤ የሆንግ ኮንግ ህዝበ ተቃውሞ ትዕይንት «አንድ ህዝብ ሁለት አስተዳደር» የሚለው መርህ እንደማይሠራ በቂ ማሳያ ነው» ስትል በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ መታለች።
የሆንግ ኮንግ አስተዳደር ይህን የማሻሻያ እቅድ በዓይነ ቁራኛ እየተከታተልኩት ነኝ ያለችው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአንፃሩ፤ ሁለቱም ጉዳያቸውን በራሳቸው መንገድ እንዲፈቱትና ይህንንም እንደሚያደርጉ እምነታቸውስለመሆኑመናገራቸው ተጠቁሟል።
ከወደ ቻይና የሚሰሙ አቋሞች ግን ረቂቁ ህጉ በእቅዱ መሠረት መሄዱን እንደሚቀጥል ማረጋገጫ የሚሰጡ ሆነዋል። በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ረቂቅ ህጉን ለመቃወም አደባባይ የወጡትም በሌላ ምክንያት ሳይሆን በውጭ ኃይሎች ግፊት ስለመሆኑም አስገንዝቧል።
ቻይና ደይሊ የተሰኘው ጋዜጣ በርዕሰ አንቀፁ «አንዳንድ የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በውጭ አጋሮቻቸው ምላስ ተታለው ረቂቅ አዋጁን ሊቃወሙ ወጥተዋል» ሲል አስገንዝቦ፤ ማንኛውም ግለሰብ፣ ቡድን ሆነም የፖለቲካ ፓርቲ ቤጂንግና ሆንግ ኮንግን ለመከፋፋል እንደማይቻለው የሚያስገነዝብ ጠንካራ አቋሙን አስነብቧል።
የተለያዩ ተቋማት አገራትና አቋም ድጋፍና ተቃውሞ የተሰነዘረበት ረቂቅ ህግ፣በተለይ በአገር ውስጥ የተነሳበት ከባድ ተቃውሞ ከዕለት ወደ ዕለት እየጋለ በመምጣቱና የተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን እስከማዘጋት መድረሱም ተዘግቧል።
ይህ ያሰጋውና የቻይና መንግሥት ድጋፍ እንዳለው የሚነገርለት የከተማዋ አስተዳደርም አዋጁን የማጽደቅ ሂደቱን ላልተወሰነ ጊዜ አራዝሟል። የከተማዋ አስተዳደር ረቂቅ ህጉን የተመለከተ የመጨረሻ ውሳኔውን ከቀናት በኋላ ያሳልፋል ተብሎ እየተጠበቀ ይገኛል።
ይህ በመሆኑም ከቀድሞው ይልቅ አሁን በሆንግ ኮንግ ጎዳናዎች አንፃራዊ የሚባል የሰላም አየር መንፈስ ጀምሯል። ይህም ሆኖ አልፎ አልፎም ጠንካራ የሚባሉ ተቋውሞዎች እየተነሱ ስለመሆናቸው የዓይን አማኞችን ዋቢ በማድረግ መገናኛ ብዙሃን ማስነበባቸውን ቀጥለዋል። በዚህ ረገድ የአሶሾየትድ ፕሬስ ዘገባ፤ አሁን ነገሮች ረገብ ያሉ እንደሚመስሉ ጠቅሶ፣ ቀን ጠብቀው ማገርሸታቸው አይቀርም ሲል አትቷል።
አሁን የመገናኛ ብዙሃኑ ዋነኛ ትኩረት የሆንግ ኮንግ ተቃውሞ በአሜሪካና በቻይና መካከል ባለው ፍጥጫ ላይ የሚያሳድረው ጫና የሚመለከት ሆኗል። ሁለቱ አገራት የንግድ ስምምነቶች ለማድረግ ቢወስኑም ውጤታማ ሳይሆን ይባስ ብሎ ተጨማሪ የቢሊየን ዶላር የንግድ ልውውጥ ማዕቀቦችን ማወጃቸው ይታወሳል።
የሲኤን ኤን ፀሐፍቶቹ ቤን ዌስት እና ኮት ስቲቨን ጂንግ እኤአ በ2012 ወደ ስልጣን የመጡት የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂን ፒንግ በስልጣን ቆይታቸው እጅግ ከባዱና ፈታኝ የቤት ሥራ ገጠማቸው ከተባለ ወቅታዊው የሆንግ ኮንግ ቀውስ ሊሆን ይችላል ሲሉ አትተዋል።
ምክንያቱ ደግሞ መሰል ተቋውሞዎች ቀጣይ ከሆኑ የሆንግ ኮንግ ኢኮኖሚ እጅጉን ይጎዳል፤ ይህም ከዋሽንግተን ጋር የንግድ ማዕቀብ ውስጥ በመግባት እየተፈተነች የምትገኘውን ቻይናን ኢኮኖሚ በተዘዋዋሪ የሚመለከት ነውም ተብሏል። ይህ እስከሆነም ፕሬዚዳንት ሺ ጂን ፒንግ ለቀውሱ አፋጣኝ እልባት ሊያስቀምጡለት እንደሚገባም ተመላክቷል።
የፕሬዚዳንቱ አስተዳደር ግን የሆንግ ኮንግ የህግ ማሻሻያ ማንም ስለተንጫጫ ሊስተጓጉል የማይችልና ተግባራዊነቱም አይቀሬ ስለመሆኑ አስርግጧል። ይህ ደግሞ «ሉአላዊነታችንን መዳፋር ነው»ለሚሉት የሆንግ ኮንግ ዜጎች ፈፅሞ የሚዋጥ አይመስልም። መሰል የየቅል ፍላጎቶች ታዲያ መጪውን ጊዜ አስጊ አድርገውታል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2011
ታምራት ተስፋዬ