በኮሪደር ልማቱ ለተነሱ 4 ሺህ ዜጎች ተገቢው ካሳ፣ ቤትና ቦታ ተሰጥቷል

– ለ1 ሺህ 117 ባለይዞታዎች 30 ሄክታር ምትክ መሬት ተዘጋጅቷል

– ለ307 የግል ይዞታ ተነሺዎች ሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ካሳ ጸድቋል

አዲስ አበባ፡በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው የኮሪደር ልማት ለአራት ሺህ ዜጎች ተገቢው ካሳ፣ ቤትና ቦታ መሰጠቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡ ለ1 ሺህ 117 ባለይዞታዎች 30 ሄክታር ምትክ መሬት መዘጋጀቱን እና ለ307 የግል ይዞታ ተነሺዎች ሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ካሳ መጽደቁንም ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን ትናንት አካሂዷል፡፡

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኮሪደር ልማቱን የአንድ ወር ከ15 ቀን የአፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ ለኮሪደር ልማቱ አምስት ሺህ 135 ዜጎች የተነሱ ሲሆን፤ እስካሁን ለአራት ሺህ የልማት ተነሺዎች ተገቢው ካሳ፣ ቤትና ምትክ ቦታ ተሰጥቷል።

ለአንድ ሺህ 117 የግልና የመንግሥት ባለይዞታዎች 30 ሄክታር ምትክ መሬት ተዘጋጅቶ እየተስተናገዱ መሆኑን ገልጸው፤ የቀበሌና የኪራይ ቤት ተከራይ ነጋዴዎች ወደ ባለይዞታነት ተሸጋግረዋል ብለዋል፡፡

ለ307 የግል ይዞታ ተነሺዎች ሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ካሳ ለመስጠት ጸድቋል ያሉት ከንቲባዋ፤ እስካሁን አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ካሳ የተከፈለ ሲሆን፤ ቀሪው በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራን በተመለከተ በኮሪደር ልማት፣ በመልሶ ማልማትና በአረንጓዴ ልማት ዘርፎች ለ15 ሺህ 269 ዜጎች በቋሚነትና በጊዜያዊ የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ሲሆን፤ ኮሪደር ልማቱ ሲጠናቀቅ የሥራ ዕድሉን በ51 በመቶ ከፍ ያደርገዋል ሲሉ አስታውቀዋል።

የኮሪደር ልማቱን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ፣ ለልማት ተነሺዎች ተገቢውን ካሳ ለመክፈል እና ሥራዎችን በፍጥነትና በጥራት ለማጠናቀቅ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማት ሥራው ከተማዋ ካለባት የመሠረተ ልማት እጥረት እና የሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ እንዲሁም ዘመናት ያስቆጠሩ መሠረተ ልማቶችን ለማዘመን፣ ለማደስ እና የነዋሪዎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ኮሪደር ልማቱ በመጀመሩ የመሠረተ ልማት ጉድለቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ሲኖሩ የነበሩ በርካታ ነዋሪዎች ምቹ የመኖሪያ ቤት አግኝተዋል ያሉት ከንቲባዋ፤ ይህም የከተማዋን ገቢና የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ይጨምራል፤ ለስማርት ሲቲ አገልግሎትም መሠረት ይጥላል ሲሉ አንስተዋል፡፡

እንደ ከንቲባዋ ገለጻ፣ የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ከድንገተኛ፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ለመታደግ ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ነው፡፡ እንዲሁም ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ፣ ቴሌኮም እና ኤሌክትሪክ በተቀናጀ መንገድ በመሬት ውስጥ እየተሠሩ በመሆኑ የከተማ ሥርዓትን የሚያሳልጥ ነው፡፡

የኮሪደር ልማቱ የትራፊክ ፍሰቱን የሚያቃልሉ የአውቶቡስና ታክሲ ተርሚናሎች፣ ምቹ የታክሲ ማውረጃና መጫኛ ተርሚናሎች፣ የመሮጫ ትራኮች፣ የእግረኛ መንገዶች፣ የሳይክል መንገድ፣ የእግረኛ መሸጋገሪያ ድልድዮች ያካተተ ነው፡፡ ይህም የትራንስፖርት አገልግሎቱን በከፍተኛ ሁኔታ ያሻሽላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ ብቁ የሰው ኃይል ስምሪት፣ የማሽነሪ፣ የፋይናንስ አቅርቦትና የፕሮጀክት አመራር ክህሎት እና የብዙ ባለድርሻ አካላትን እገዛ የሚጠይቅ በመሆኑ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ 48 ነጥብ ሰባት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን፤ መሰረታዊ የሆኑ የመንገድ የኮሪደር ልማቶች በሦስት ወር ተጠናቀው ለሕዝብ ክፍት እንዲሆኑ 24 ሰዓት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ ከኮሪደር ልማቱ ተያያዥ የሆኑ ሌሎች የመልሶ ማልማት ሥራዎችን በሚቀጥለው በጀት ዓመትና በቀጣይ ጊዜያት ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You