አራት ቢሊዮን ብር የወጣበት የጎባ ሆስፒታል ሕንፃ በከፊል ሥራ ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ:– አራት ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የጎባ ሪፈራልና ቲቺንግ ሆስፒታል የማስፋፊያ ሕንፃ በቀጣይ ሳምንት በከፊል ሥራ እንደሚጀምር የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስታወቁ።

በመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ የጎባ ሪፈራልና ቲቺንግ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሐመድአሚን ጣሃ (ዶ/ር) ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የሆስፒታሉ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ከምድር በላይ ባለስምንት ወለል ያለው ሕንጻንና የተለያዩ የሕክምና ቁሳቁሶች ግብዓትን ያጠቃለለ ነው።

የሕንፃ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከ600 በላይ አልጋ እንደሚኖረው አስታውቀው፤ የእራሱ የኦክሲጅን ፕላንት፣ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት የሚሰጥበትና የተለያዩ ቀዶ ሕክምናዎች የሚከናወኑባቸውን ክፍሎችን መያዙን አመላክተዋል።

የሕንፃ ግንባታው 94 በመቶ መድረሱን ዶክተር ሙሐመድአሚን ጠቁመው፤ ግንባታው ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ እንጠብቅ ካልን ጊዜ ሊወስድ ስለሚችል አመቺ ሁኔታ በመፍጠር የጤና አገልግሎቱን በተጓዳኝነት ለመስጠት ታስቧል ሲሉ አስረድተዋል።

የግንባታው ቀሪ ሥራዎች እየተከናወኑ የሲቲ ስካን ማሽን ተከላ መደረጉን ጠቅሰው፤ በተወሰኑ ማሽኖች አማካኝነት በከፊል ሥራ ለመጀመር ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ሪፈራል ሆስፒታሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለ55 ሺህ ዜጎች ተመላላሽ ሕክምና እንዲሁም ለሦስት ሺህ ሰዎች ደግሞ ከፍተኛ የቀዶ ሕክምና አገልግሎቶችን ማቅረቡን ገልጸው፤ የማስፋፊያ ሕንጻ ግንባታው በከፊል ሥራ ሲጀምር የተገልጋዮችን ቁጥር ማሳደግ ያስችላል ብለዋል።

በአጠቃላይ ሆስፒታሉ አንድ ሺህ 100 ባለሙያዎች እንዳሉት ጠቁመው፤ ከዚህ ውስጥ 11 የቀዶ ጥገና ሐኪሞች (ሰርጂን)፣ ዘጠኝ የጽንስና ማህፀን ስፔሻሊስቶች፣ አምስት የሕፃናት ስፔሻሊስቶች፣ 16 የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስቶች፣ አንድ የሰመመን መድኃኒት ስፔሻሊስትና በሌሎች ዘርፎችም የተለያዩ ባለሙያዎች በሆስፒታሉ መኖራቸውን አስታውቀዋል።

በሆስፒታሉ የቀዶ ጥገና፣ የውስጥ ደዌ ሕክምና፣ የዓይን፣ የፓቶሎጂ፣ የሕፃናትና እናቶች እንዲሁም የተለያዩ የጤና አገልግሎቶችን እየቀረቡ መሆኑን አመላክተዋል።

በአዲሱ ሕንፃ ላይ በሚገኙ የተደራጁ የሕክምና ክፍሎች አማካኝነት ደግሞ የጤና አገልግሎቱን በስፋት ለማቅረብ ተጨማሪ የሰው ኃይልን የማብቃት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

የሆስፒታሉ የማስፋፊያ ሕንፃ ግንባታ ከሰባት ዓመታት ገደማ በፊት ሲጀመር ሁለት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር የተያዘለት ቢሆንም፤ አሁን ላይ ካለው የኮንስትራክሽን ግብዓትና የተለያዩ የሕክምና ዕቃዎች የዋጋ ግሽበት አንጻር ወጪው ወደአራት ቢሊዮን ብር መዳረሱን ጠቁመዋል። የግንባታውን አጠቃላይ ሂደት መደወላቡ ዩኒቨርሲቲው እየተከታተለ መሆኑን አስረድተዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንዳስታወቁት፤ የሆስፒታሉ የጤና አገልግሎት ሽፋን ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የአካባቢውን ዜጎች ታሳቢ ያደረገ ነው።

ጌትነት ተስፋማርያም

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You