የምግብ ቱሪዝምን ምን ያህል ተጠቅመንበታል?

ሰዎች የአንድን ሀገርና አካባቢ የምግብ ጣዕም ለመቅመስና ለማጣጣም የሚያደርጉት ጉዞ የምግብ ቱሪዝም ይሰኛል፡፡ የዓለም ቱሪዝም ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው ሰዎች ለማንኛውም አይነት የቱሪዝም ተግባራት ከሚያወጡት አጠቃላይ ወጪ 15 በመቶ ያህሉ በምግብና መጠጥ ላይ የሚውል ነው፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሰፊ ባህልና የምግብ አሰራር ባለባቸው ሀገራት ደግሞ የምግብ ቱሪዝምን ለማስፋፋት የሚያስችል ዕምቅ ሀብት አለ፤ ይሁንና ይህንን የቱሪዝም ዘርፍ ምን ያክል ጥቅም ላይ ውሏል ተብሎ ሲጠየቅ መልሱ እምብዛም ነው የሚሉ ምሁራን በርካታ ናቸው።

የሆቴል ማኔጅመንት ኢንስትራክተርና ተመራማሪ የሆኑት አቶ ሀብቱ ተካ እንደሚሉት፤ የምግብ ቱሪዝም ኢትዮጵያ ያልተጠቀመችበት ዕምቅ ሀብት ነው፡፡

የምግብ ቱሪዝም በየዓመቱ ከሰባት እስከ 12 በመቶ እድገት እያሳየ ትልቅ ትኩረት እየተሰጠው ያለ የቱሪዝም ዘርፍ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሀብቱ፣ ሀገራት ከዘርፉ ከፍተኛ ጥቅም እያገኙ ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ኢትዮጵያን የጎበኙ ቱሪስቶች ስለባህላዊ ምግቦቻችን ብዙ ነገር እንደሚሉ ጠቁመው፣ በተለይም የቡና ሥርዓታችን፣ ዶሮ ወጥ፣ ክትፎ፣ ሽሮ እና እንጀራ ያሉ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ ባህላዊ ምግቦቻችን ላይ ጥሩ ዳሰሳዎችን መጻፋቸውን ያነሳሉ፡፡

ኢትዮጵያ ሰፊ ናት፤ በየአካባቢው በርካታ ባህላዊ ምግቦች አሉ፡፡ ምግቦቹ የያዙት ንጥረ ነገር፣ ተፈጥሯዊ (ኦርጋኒክ) ግብዓቶችን መጠቀማችን፣ በጣዕማቸው ቶሎ የሚወደዱ መሆናቸው፣ በባህላዊ ቁሳቁሶች መቅረባቸውና ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆኑትን እንደ መሶብና ሰፌድ ያሉ ከሳር የሚበጁ የምግብ ማኖሪያና ማቅረቢያዎች መጠቀማችን ለምግብ ቱሪዝም ተመራጭ ያደርገናል ይላሉ፡፡

በሆቴሎች የባህላዊ ምግቦች አቀራረብና እነርሱን ለማስተዋወቅ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን መሠረት ባደረገ የዳሰሳ ጥናት ላይ መሳተፋቸውን የሚገልጹት አቶ ሀብቱ፤ በዓለም አቀፍ ብሎጎችና ድረገጾች ላይ ባህላዊ ምግቦቻችንን በሰፊው የማስተዋወቅ ስራ እንዳልተሰራ ይናገራሉ፡፡

የምግብ አሰራርን የሚያሳዩ ወርክሾፖች፣ ፌስቲቫሎችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች ከማዘጋጀት አንጻርም ብዙ ይቀረናል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች በከፍተኛ ደረጃ መጠቀም የምንችልበትን እድል እያባከንን ነው ሲሉ ሃሳብ ይሰጣሉ፡፡

ቱሪስቶች የምግብ ጣዕሞችን ለመቅመስ ብቻ ብለው ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ እንደሚጓዙ አመላክተው፣ አሁንም ቢሆን ሳይረፍድ ባህላዊ ምግቦቻችን ምን እንደሚመስሉ በስፋት የማስተዋወቅ ስራ ከሰራን፣ ኢትዮጵያ ከዘርፉ ጉልህ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ማግኘት ትችላለች ይላሉ፡፡

በቀጣይ በተለያዩ የሼፎች ማህበራት በኩል ምርምሮች በማድረግና የባህላዊ ምግቦቹን የንጥረ ነገር ይዘታቸው ምን እንደሚመስል ሰንደን ማስቀመጥ ይጠበቅብናል ሲሉ ይናገራሉ። ባህላዊ ምግቦችን እንደ መድኃኒት በመጠቀም ሰዎች የጤና ጥቅም ከማድረግ አንጻርም ብዙ ስራ መስራት እንደሚገባና ቱሪስቶች በባህላዊ ምግብ አሰራር ሂደቶች ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ።

በሰሜን ተራሮች አካባቢ ጎብኚዎች እንጀራ እንዲጋግሩ ይደረጋል፤ ወደ አርባ ምንጭ አካባቢ የሚያቀኑ ሰዎችም ከሀገሬው ሰዎች ጋር በቆጮ ዝግጅት ይሳተፋሉ፤ እንደዚህ ያሉ ቱሪስቶችን አሳታፊ እንቅስቃሴዎች ቆይታቸው ያማረና የሚታወስ እንዲሆንና ወደ መጡበት ሀገር ሲመለሱ ሌሎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ማበረታታት እንደሚችሉ ይጠቁማሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ ምግቦች መረጃ ማግኘት ባለመቻላቸው ካሉበት ሀገር ምግብ ይዘው የሚመጡ ቱሪስቶች አጋጥመውኛል የሚሉት አቶ ሀብቱ፤ አስጎብኚ ድርጅቶቻችንም ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ቅንጡ የሚባሉ ዘመናዊ ሬስቶራንቶችን ማስጎብኘት ብቻ ሳይሆን ባህላዊ ምግቦቻችን የሚገኙባቸውን አካባቢዎችም ጥቅል ውስጥ አካተው ምግቦቹን የመቅመስ ዕድል ሊፈጥሩላቸው ይገባል ሲሉ ይመክራሉ፡፡

የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ መውሰድ መልካም ነው ያሉት አቶ ሀብቱ፤ ስፔን በየትኛው የሀገሪቱ አካባቢ ምን አይነት ምግቦች እንደሚገኙ የሚያሳይ የምግብ ቱሪዝም ካርታ ሰርታ በዘርፉ ብዙ መጠቀም እንደቻለች ነው ያስረዱት። ቻይናዎች የሻይ ባህላቸውን የሚያስተዋውቁበት ሙዚየም አላቸው፡፡ በሙዚየሙ የሻይን ታሪካዊ አመጣጥና የሻይ አይነቶችን በማስጎብኘት ቱሪስቶች እንዲሸምቱ ያደርጋሉ፡፡ አሁን ለምግብ የሚጓጓ ትውልድ እየተፈጠረ ነው፡፡ ኢትዮጵያም የምግብ ሙዚየም በማቋቋም የቱሪዝም ዘርፉን ማሳደግ ይቻላል ይላሉ፡፡

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቱቲዩት የስልጠና ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ክብረት በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች አሉ፡፡ እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆነ ባህላዊ ምግብ ዝግጅት አላቸው፡፡ ነገር ግን በሀገራችን ለሀገር በቀል እውቀቶች ትኩረት ስለማይሰጥ ተጠንተው ለገበያና ለቱሪዝም መስህብነት እየቀረቡ አይደሉም፡፡

ባህላዊ ምግቦቻችን ጥንተ ተፈጥሯቸውን እንደያዙ ሳይበረዙና ሳይከለሱ ከትውልድ ትውልድ እዲተላለፉ ተጠንተው ተሰንደው መቀመጥ አለባቸው የሚሉት ሀብታሙ፤ ወደ ገበያ እንዲገቡ በማድረግ ቱሪስቶች እነዚህን ባህላዊ ምግቦች ሰርተው እየተመገቡ በመዝናናት የቆይታ ጊዜያቸው እንዲራዝሙ በማድረግ ገቢ ማግኛ መሆን አለባቸው ሲሉም ያክላሉ፡፡

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቱቲዩት በሲዳማ፣ በስልጤ፣ በሐረሪ፣ በጋሞ እና በድሬዳዋ አካባቢ የሚገኙ ባህላዊ ምግቦች አጥንቶ መሰነዱን የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፤ ይህ በኢኮ ቱሪዝም ቱሪስቶች በአካባቢዎቹ ባህል መሰረት ምግቦችን እየሰሩ በመመገብ የሚዝናኑባቸው የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲሆኑ ማድረግ የሚያስችል ነው ይላሉ፡፡ የጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል፣ አፋርና ሶማሌ ባህላዊ ምግቦችንም ለመሰነድ እየተሠራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 / 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You