የሠርግ ጉዳይ ሲታሰብ ሙሽሪትን በእጅጉ ከሚያስጨንቋት መካከል በእለቱ የምትለብሰው ቬሎ ጉዳይ አንዱ ነው:: በየሙሽራ አልባሳት ገበያው የምትመለከታቸው ቬሎዎች የዓይን አዋጅ ይሆኑባታል:: የሠርግ ልብሶቹ ደግሞ በሀገር ውስጥ የሚሰሩ ባለመሆናቸው ለገዥ ዋጋቸው የማይሞከር የሚሆንበት ጊዜ ብዙ ነው፤ ሌላው አማራጭ መከራየት ነው:: ኪራዩም የወዛ የማይሆንበት ሁኔታ ብዙ ነው::
በዛሬው የፋሽን ዓምዳችን ይዘን የቀረብነው መረጃ ግን ይህን ሁኔታ ለመቀየር የሚደረጉ ሙከራዎች እየተደረጉ መሆናቸውን ያመለክታል:: ደንበኞቿ የወደዱትን የሙሽራ ልብስ ወይንም ቬሎ በሀገር ውስጥ የምትሰራዋ ወጣት ፍሬወይኒ ብርሃኔ ተሞክሮም ይህንኑ ይጠቁማል::
ወጣት ፍሬወይኒ ዲዛይነር ናት:: ወጣቷ በሠርግ ወቅት ለሙሽሪት እና ለሙሽራው እንዲሁም ለሚዜዎች የሚሆኑ ልብሶችን ትሰራለች:: በተለያዩ ዲዛይኖች እና አማራጮች የደንበኞቿን ፍላጎት በመረዳት እና የራሷን ፈጠራ በማከል የሙሽራ ልብሶችን የምትሰራው ፍሬወይኒ፣ ለሥራዎቿም ‹‹ ፍሬ ሜድ ›› ወይንም ‹‹ በፍሬ የተሰራ ›› የሚል ስያሜ ሰጥታለች::
ዲዛይነር ፍሬወይኒ የሕፃናት ልብሶችን ጨምሮ ለተለያዩ በዓላትና ፕሮግራሞች የሚሆኑ ልብሶችንም ትሰራለች:: ታዋቂ ሰዎችም የሽልማት ፕሮግራም ሲኖርባቸው እና ለሙዚቃ ክሊፖቻቸው ለየት ያለ ልብስ ሲፈልጉ ምርጫቸው እንደሚያደርጓትም ታነሳለች::
ይበልጥ የምታዘነብለው ግን ለሙሽሪት እና ለሙሽራው እንዲሁም ለሚዜዎች የሚሆኑ ልብሶችን መሥራት ላይ ነው:: ይህም ከሌሎች ለየት እንደሚያደርጋት ጠቅሳ፣ ብዙ ተጋቢዎችም በሠርጋቸው ቀን ለመልበስ የሚመርጡትን ዲዛይን ይዘው ወደ እርሷ መሥሪያ ቦታ ጎራ እንደሚሉ አስታውቃለች::
ከልጅነቷ ጀምሮ የነበራት የሥዕል ፍላጎት፣ ችሎታ እንዲሁም በወረቀት ላይ የተለያዩ ልብሶች ዲዛይኖችን ትሰራ የነበረበት ሁኔታ ወደ ዲዛይነርነት ሙያ እንድታዘነብል አድርጓታል:: የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን በማኔጅመንት ብታጠናቅቅም፣ እሷ ግን ዲዛይነር የመሆን ፍላጎቷን እውን ለማድረግ ልብስ ዲዛይን ትምህርት ቤት ገብታ ተምራለች:: ማኔጅመንት መማሯ አሁን ለምትሰራው የግል ሥራዋ ግን በእጅጉ እንደጠቀማት ትናገራለች::
ትምህርቷን ከጨረሰች ከአንድ ዓመት በኋላ ትዳር እንደመሰረተች ያስታወሰችው ፍሬወይኒ፣ የሙሽራ ልብሷን የሰራችው ራሷ መሆኗን ገልጻልናለች:: ዋናውን ሥራዋን የጀመረችው ግን ልብስ እንድትሰራላት ካዘዘቻት ደንበኛዋ በተቀበለችው ቀብድ እና ባላት አንድ የስፌት ማሽን እንደነበር ታስታውሳለች::
ይህን ልብስ ሌሎች ሰዎች ይመለከቱታል፤ ያደንቁታልም፤ በርካቶችም ሥራዎቿን ፈልገው ወደ እርሷ መምጣት ይጀምራሉ:: ይህን ሥራ የሙሉ ጊዜ ሥራዋ አድርጋ መሥራት ከጀመረች ሁለት ዓመት ያህል ጊዜ ሆኗታል:: ፍሬወይኒ ኢንስታግራም፣ ቲክቶክና ሌሎች ማህበራዊ ገጾችን ተጠቅማ ሥራዎቿን ተጠቅማ ማስተዋወቋ ሥራዋን ለማስፋፋት በእጅጉ ጠቅሟታል::
‹‹ አንድ ደንበኛ ወደ እኔ ሲመጣ በቅድሚያ የሚፈልገውን የልብስ ዓይነት እና ምቾት የሚሰጠውን ዲዛይን እጠይቀዋለሁ›› የምትለው ፍሬወይኒ፣ በሌሎች ማህበራዊ ገጾች ላይ በተመለከተው ልብስ ዓይነት እንዲሰራለት የሚጠይቅም ካለ በቅድሚያ የአንገቱን ቅርጽ፣ የቅርጹን አወራረድ፣ የቀለም ምርጫውን ለማወቅ ጥረት ታደርጋለች:: ይህንንም መሰረት አድርጋ ልብሱን ትሰራለች::
‹‹ደንበኞቼ ይዘው የመጡትን ዲዛይን ከፈለጉም እሰራላቸዋለሁ፤ ብዙ ጊዜ ግን ደንበኞቼን የተለየና ያልተለመደ ልብስ እንዲለብሱ እጫናቸዋለሁ፤ ዲዛይኔን በወረቀት ላይ ስዬ አሳያቸዋለሁ እንጂ ያመጡትን ቀጥታ ተቀብዬ አልሰራም፤ በዚህ መልኩ ሰርቼ ሳሳያቸው ይቀበሉኛል::›› ትላለች::
ፍሬወይኒ አዲስ ዲዛይን እንደመፍጠር የሚያስደስታት የለም:: በብዙዎች ዘንድ የተለመደ የልብስ ዲዛይንና ዓይነቱን ደግማ መሥራት አትፈልግም፤ ይህ ብቻ አይደለም፤ የእሷ የፈጠራ ውጤት የሆነውን የልብስ ዲዛይንንም ደግማ መሥራት አትወድም::
በቤታቸው ሆነው እንዲሁም የራሳቸው መገኛ ኖሯቸው በማህበራዊ ገጽ ሥራቸውን እያስተዋወቁ የሚሰሩ ሰዎች በርክተዋል:: ይህ ሁኔታ አገልግሎቱን በሚፈልጉ ሰዎች ዘንድ አመኔታን ማግኘት አይከብድም ወይ ስንል ጥያቄ ያነሳንላት ፍሬወይኒ፣ ‹‹የምሰራው ከቤቴ ስለሆነ ደንበኞቼን እንደ ደንበኛ ሳይሆን እንደቤተሰብ ነው የማቀርባቸው፤ እነሱም ይረዱኛል፤ አሁን ግን የራሴን ቢሮ ለመክፈት በዝግጅት ላይ ነኝ ›› ስትል ትገልጻለች::
ፍሬወይኒ በአንድ የመገናኛ ብዙሃን ላይ ይተላለፍ በነበረ የዲዛይነሮች ውድድር መሳተፏን ታስታውሳለች:: ውድድሩ ‹‹የጥቁር ፈርጥ›› ይሰኛል:: ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ተካሂዷል:: ውድድሩንም በሁለተኛነት ማጠናቀቋን ጠቅሳ፣ ይህ መድረክ እሷን በሚገባ እንዳስተዋወቃትና በሰራዎቿም እምነት እንዲጣልባት ማድረጉን ትናገራለች::
ፍሬወይኒ ለሀገር ውስጥ የሙሽራ ልብስ ትኩረት እንዲሰጥ ትፈልጋለች:: ‹‹ለሠርግ ቀን የፈረንጅ ልብስ መልበስ እንዲቀር ፍላጎቴ ነው:: ይህን ሃሳብ ለማሸነፍ ሰዎች የሚፈልጉትን ዲዛይን ከእኔ ዲዛይን ጋር በማጣመር እሰራለሁ:: ሥራውን ብዙ ሰዎች በወረቀት ላይ ሲያዩት ይጠራጠራሉ፤ መጨረሻ ላይ አልቆ ሲያዩት ይወዱታል::›› ትላለች::
ቬሎ አሁንም ድረስ በሰዎች ልብ ውስጥ አለ የምትለው ፍሬወይኒ፣ በሠርግ ቀን የተለመደው ቬሎ ቢሆንም፣ እሷ ግን የሀገር ባህል ልብስ መሥሪያ ጨርቆችን ተጠቅማ ዘመናዊ በሆነ መልክ የሙሽራ ቀሚሶች መሥራት ምርጫዋ እንደሆነ ትናገራለች::
የተለያዩ የቬሎ ዓይነቶች እንድትሰራ ጥያቄ ሲቀርብላትም ትሰራለች:: አልባሳቱ እንዲሰሩላቸው የሚፈልጉ ሰዎች የሚያሳዩዋትን ዲዛይኖች በሀገር ውስጥ ተመሳሳይ ግብዓቶች በመጠቀም የምትሰራ ከመሆኗ በተጨማሪ ግብዓቶቹም ከውጭ ሀገሮችም አስመጥታ ትሰራለች:: ሌላ ቦታ በሚፈልጉት ዲዛይን ሳይሰራላቸው የቀሩ ሰዎች ወደ እርሷ የሚመጡበት ሁኔታ እንዳለም ጠቅሳ፣ እነዚህን ሥራዎች የሰራችባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉም ትናገራለች::
የራሳቸውን የሠርግ ልብስ ለማሰራት የሚፈልጉ ሰዎች ከሠርጋቸው ቀን እጅግ ቀድመው ቢያስቡበት መልካም መሆኑን ዲዛይነር ፍሬህይወት ትመክራለች:: ሠርግ ብዙ ወጪ እንዳለው ጠቅሳ፣ የዋጋ ጥናት አድርገው ወደ ልብስ ማሰራቱ ቢገቡ መልካም መሆኑን ገልጻ፣ ይህ ሲሆን ሠርጉን በሚፈልጉት ልብስ አምረው እንዲያሳልፉ ያስችላቸዋል ነው የምትለው::
ቬሎ በባህሪው ለሠርግ ቀን ብቻ የሚለበስ ነው:: ርግጥ ነው በፎቶ ፕሮግራም ላይም ይለበሳል፤ ይህን ማድረግ የማትመኝ ሙሽሪት የለችም:: ሙሽሮች ለአንድ ቀን ብለው ለምን ልብስ ያሰራሉ የሚል ጥያቄ ያቀርብንላት ፍሬወይኒ፣ አንዳንዶች ቬሎውን ለማስታወሻነት ወይም ለቅርስነት እንደሚያስቀምጡት ገልጻለች::
ከቬሎ ውጭ ብዙ ዓይነት የሠርግ ቀን ልብሶች እንዳሉም ፍሬወይኒ ጠቁማ፣ የሙሽራ ልብሶቹ ከቬሎ ወጣ ያሉ እና ተደጋግመው መለበስ የማይችሉ ዲዛይኖች ከሆኑ ለደንበኞቼ ሌሎች አማራጮችን አቀርብላቸዋለሁ ትላለች:: የሠርጋቸው ቀን ካለፈ በኋላ የሙሸራ ልብሱን መልሰው ለእሷ እንዲሰጧት በማድረግ ሁል ቀን መለበስ እንዲችሉ አድርጋ የምትሰራበት ሁኔታ እንዳለ ጠቁማለች::
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 / 2016 ዓ.ም