ምርት ገበያ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ለማገበያየት እየሠራ መሆኑን አሳወቀ

አዲስ አበባ፡- ከግብርና ምርቶች ባለፈ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ለማገበያየት እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አስታወቀ፡፡ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 19 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ምርቶችን ማገበያቱንም ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ዳዊት ሙራ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ተቋሙ አሁን ላይ እያገበያያቸው ካሉ የግብርና ምርቶች ባለፈ በቀጣይነት የኢንዱስትሪ ግብዓቶችንም ለማገበያየት እየሠራ ይገኛል፡፡

የኢንዱስትሪ ጨውን ጨምሮ ሌሎችንም ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ወደ ግብይት ሥርዓቱ ለማስገባት እየተሠራ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ሰባት ተጨማሪ ምርቶችን ወደ ግብይት ሥርዓቱ ለማስገባት የሚያስችል ከጥናት እስከ ኮንትራት ማርቀቅ የሚደርስ ሥራ ለመሥራት ታቅዶ እንደነበር አመላክተዋል።

ከዚህ ውስጥ ጨውና የቢራ ገብስ የግብይት አዋጭነታቸው ተጠንቶ የግብይት ውላቸው ተዘጋጅቶ እንዲጸድቅ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል መላኩን ጠቁመዋል። እንደጸደቀም ግብይቱ የሚጀመር ይሆናል ብለዋል፡፡

ተልባ፣ ቆዳና ሌጦ፣ ጥጥ፣ የጎመን ዘርና የጉሎ ፍሬ ግብይት ለማከናወን የሚያስችል የአዋጭነት ጥናት በመካሄድ ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ከ16 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በቆሎና ስንዴን በማገበያት ሥራ መጀመሩን አስታውሰው፤ በአሁኑ ሰዓት የሚያገበያያቸው ምርቶች 23 መድረሳቸውን ተናግረዋል።

እንደ አቶ ዳዊት ገለጻ፤ ተቋሙ በተያዘው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት 19 ነጥብ4 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 171 ሚሊዮን 639 ሺህ ኩንታል የተለያዩ የግብርና ምርቶች አገበያይቷል።

ከዚህ ውስጥ 73 ሺህ 393 ሜትሪክ ቶን ሰሊጥ ሲገበያይ፤ ቡና ደግሞ 50 ሺህ 329 ሜትሪክ ቶን ግብይት መፈጸሙን አመላክተዋል።

ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ቡና በመጠን 17 በመቶ፣ በዋጋ አምስት በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸው፤ ሰሊጥ ደግሞ በመጠን የ45 በመቶ በዋጋ ደግሞ 51 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል፡፡

ዥንጉርጉር ቦሎቄና የርግብ አተር በበጀት ዓመቱ ከ95 በመቶ በላይ የመጠንና የዋጋ ጭማሪና አፈጻጸም ያሳዩ ምርቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረው የጸጥታ ሁኔታ፣ የዓለም አቀፍ የምርቶች ዋጋ መለዋወጥ ጋራ በተያያዘ ቅንጅታዊ አሠራሮች አለመዳበራቸው፣ በድንበር አካባቢዎች ለወጪ ንግድ የሚውሉ ምርቶች በኮንትሮባንድ ንግድ መውጣት ተቋሙን እየፈተኑ ያሉ ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ችግሮቹን ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 / 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You