ሩሲያ ፈረንሳይና ብሪታኒያ በዩክሬን ጦርነት ጉዳይ የሰጡትን አስተያየት “አደገኛ” አለች

የፈረንሳይ ፕሬዝዳንትና የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስለ ዩክሬን ጦርነት አስተያየት ሰጥተዋል። የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት እና የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዩክሬን ጦርነት ዙሪያ የሰጡትን አስተያየት ሩሲያ “አደገኛ ነው” በማለት ፈርጃለች።

ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን በዩክሬን ጦርነት ላይ የሰጡት አስተያየት በግጭቱ ዙሪያ ያለውን ዓለም አቀፍ ውጥረት የሚያባብስ መሆኑን ክሬምሊን አስታውቋል።

የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ባሳለፍነው ሃሙስ በሰጡት አስተያየት ላይ ወታደሮችን ወደ ዩክሬን የመላኩን ጉዳይ አሁንም በድጋሚ ማንሳታቸው ተነግሯል።

የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን በተመሳሳይ ቀን ኪቭን በጎበኙበት ወቅት፤ ዩክሬን ሩሲያን ለማጥቃት የብሪታኒያ የረጅም ርቀት መሳሪያዎችን መጠቀም ትችላለች ማለታቸው ተሰምቷል።

የሩሲያ ቤተ መንግሥት ክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ በዚህ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ የፕሬዝዳንት ኢማኑል ማክሮንን ንግግር “በጣም ወሳኝ እና በጣም አደገኛ መግለጫ” በማለት ገልጸውታል።

በጦርነቱ ውስጥ የፈረንሳይ ቀጥተኛ ተሳትፎን በተመለከተ የማክሮን አስተያየት “በጣም አደገኛ አዝማሚያ” ነው ሲሉም ቃል ዘቀባዩ ገልጸዋል።

የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ዩክሬን በሩሲያ ውስጥ የሚገኙ መሰረተ ልማቶችን ለማጥቃት የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የረጅም ርቀት መሳሪያዎችን መጠቀም እንደምትችል መግለጻቸውም “ሌላኛው አደገኛ መግለጫ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

አስተያየቶቹ በዩክሬን ግጭት ዙሪያ ቀጥተኛ ውጥረቶችን የሚያባብስ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ይህም የአውሮፓን ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችልና መላውን የአውሮፓ የደህንነት መዋቅር የሚያናጋ ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የፈረንሳይ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ እንደዘገበው የሀገሪቱ ብሄራዊ የስለላ ተቋም ስለ ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የተሳሳተ ትንታኔ ሰርቶ ፕሬዝዳንት ማክሮን በተሳሳተ መንገድ እንዲጓዙ ማድረጉን ገልጿል።

ይሄንን ተከትሎም የሀገሪቱ የወታደራዊ ስለላ ተቋም ኃላፊ ኤሪክ ቪዳውድ ስልጣናቸውን በራሳቸው ፈቃድ መልቀቃቸው የሚታወስ ነው።

ፈረንሳይ መከላከያ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን የተረዳበት እና ምላሽ እየሰጠ ያለበት አካሄድ ትልቅ ስህተት ያለበት የሚል የትንታኔ ሪፖርት አውጥቷል።

ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጦርነቱን ተከትሎ ጉዳዩን በዲፕሎማሲ ለመፍታት ከሩሲያ አቻቸው ጋር ወደ ሞስኮ የተጓዙት በዚህ የተሳሳተ ትንታኔ መሰረት እንደሆነም በወቅቱ ተገልጿል።

የፈረንሳይ ወታደራዊ የስለላ ተቋም ሩሲያ በኔቶ ላይ ያሳየችው ስጋት ምክንያታዊ መሆኑን እና ዩክሬንን ሙሉ ለሙሉ ላታጠቃ ትችላለች የሚል አቋም መያዙ ተገልጿል።

ይሁንና የአሜሪካ እና ብሪታኒያ የስለላ ተቋማት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ ጥቃት እንደምትሰነዝር ከጦርነቱ በፊት አስጠንቅቀው ነበር።

በተያያዘ ዜና ሩሲያ በጦር ግንባር ድልን እየቀዳጀች መሆኑን እና በርካታ ስፍራዎችን ከዩክሬን በማስለቀቅ እየተቆጣጠረች መሆኑን የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ስርጌ ሼይጉ በሰጡት መግለጫ፤ የፈረንጆቹ 2024 ከተጀመረ ወዲህ ባሉ የመጀመሪያ ወራት የሩሲያ ጦር 500 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፍራን ከዩክሬን ጦር በማስለቀቅ መቆጣጠሩን ተናግረዋል።

የዩክሬን ጦር ዋና አዛዥ ጄነራል ኦሌክሳንደር ሰርሰይኪ በቅርቡ በሰጡት አስተያየት፤ የዩክሬን ጦር ከምስራቃዊ ዶኔስክ አካባቢ ለቀው በመውጣት ላይ እንደሚገኝ መግለጻቸው ይታወሳል።

ጄነራል ኦሌክሳንደር ሰርሰይኪ አክለውም ዩክሬን ጦር የሚያስፈለገውን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ከአሜሪካ ከማግኘቱ በፊት ሩሲያ ያላትን የወታደርና የጦር መሳሪያ ቁጥር ብላጫ በመጠቀም ቦታዎችን እየተቆጣጠረች መሆኑን አስታውቀዋል።

አሜሪካ ባሳለፍነው ሳምንት ለዩክሬን የ61 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ወታደራዊ ድጋፍ ለማቅረብ መወሰኗ ይታወቃል። ሆኖም ግን የአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፎች የዩክሬን ወታደሮች በጦር መሳሪያ እጥረት እየተቸገሩ ያሉበት የጦር ግንባሮች ለመድረስ ገና ጊዜ ይወስድባቸዋል ነው የተባለው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2016 ዓ.ም

Recommended For You