ከክልሉ ማዕድናት ከ213 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

– 159 የወርቅ አቅራቢዎች ፍቃድ ተሰርዟል

አዲስ አበባ፡- በተለያዩ አልሚዎች አማካኝነት ከማዕድናት ምርቶች ከ213 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኦሮሚያ ክልል ማዕድን ልማት ባለSeልጣን አስታወቀ፡፡ በሕገወጥ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ 159 የወርቅ አቅራቢዎች ፍቃድ መሰረዙ ተመላክቷል።

የባለሥልጣኑ ምክትል ኃላፊ ትዕግስት ተረፈ ለኢትዮጵያ ፕሬሰ ድርጅት እንደገለጹት፤ ባለሥልጣኑ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ሁለት ሺህ 526 ኪሎ ግራም ወርቅ ፣57 ሺህ 785 ቶን የኢንዱስትሪ ማዕድናት፣ 19 ሺህ 479 ኪሎ ግራም ጌጣጌጥ እንዲሁም 72ሺ 255 ቶን የብረት ማእድናት ለውጭ ገበያ አቅርቧል፡፡

ለውጭ ገበያ ከቀረቡት ምርቶች ከ213 ሚሊዮን 790 ህ ዶላር በላይ መገኘቱን ጠቁመው፤ በተኪ ምርቶች አማካኝነት ደግሞ ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማትረፍ መቻሉን አስረድተዋል።

ባለሥልጣኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የወጪ ንግድ ምርትን ማሳደግ ፣ ከውጭ የሚገቡ የማእድን ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካትና ሕገወጥ አሰራርን መከላከል ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ወርቅና የከበሩ ማዕድናት ገቢ ማስገኛ ብቻ ሳይሆን የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቀነስና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ታላሚ ተደርጎ እየተሰራባቸው ይገኛል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ከወጪ ንግዱ በተጨማሪ 31 ሺህ 158 የብረት ማዕድናት፣ ስድስት ሚሊዮን 956 ሺህ 487 ቶን የኢንዱስትሪ ማዕድናት እንዲሁም 23 ሚሊዮን 479 ሺህ 337 ኪሎ ግራም የግንባታ ማዕድናትን ለሀገር ውስጥ ገበያ ከቀረቡ ማቅረብ ተችሏል፡፡

ለሀገር ውስጥ ገበያ ከቀረቡ ማዕድናት ከአንድ ቢሊዮን 293 ሚሊዮን 900 ሺህ ብር በላይ መገኘቱን ምክትል ኃላፊዋ አስታውቀዋል።

በማዕድን ዘርፉ ሕገወጥነትና ብልሹ አሠራር ጎልቶ ይታያል ያሉት ምክትል ኃላፊዋ፤ ችገሮቹን ለማስተካከልም የተለያዩ የሕጋዊነት ርምጃዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም ሕገወጥ ተግባር ሲከውኑ የተገኙ 89 ማህበራት ፍቃዳቸው መሰረዙንና ለ143 አመራሮች ደግሞ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

በብዛት በወርቅ ምርት ላይ ሕገወጥነት እንደሚስተዋል አመላክተው፤ 159 የወርቅ አቅራቢዎች ፍቃድ እንዲሰረዝ መደረጉንና ሰባት የወርቅ አቅላጮችና አንድ ገዢ ከ 1506 ነጥብ 16 ግራም ወርቅ ጋር በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ ትዕግስት እንዳስታወቁት፤ በማዕድኑ ዘርፍ ያለውን ሕገወጥነት ለመከላከል እንዲሁም የወርቅ ምርትን ለማሳደግ የማዕድን ሀብትና ፈቃድ አመዘጋገብ ወደ ዲጂታል ለመቀየር እየተሰራ ይገኛል።

በተጨማሪ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ሕገወጥነት በሚስተዋልባቸው የማዕድን ምርት መገኛ አካባቢዎች ላይ ሰፊ የቁጥጥር ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 / 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You