የትግራይን ክልል አትሌቲክስ ለመደገፍ ጥረት እየተደረገ ነው

የትግራይ ክልል በአትሌቲክስ ስፖርት ሀገርን በዓለም አቀፍ ደረጃ በመወከል ውጤታማ የሆኑና ሰንደቅ ዓላማዋን ማውለብለብ የቻሉ አትሌቶችን ከሚያፈሩ ክልሎች አንዱ ነው:: ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት በኮቪድ 19 ቫይረስ እና በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተከስቶ በነበረው ጦርነት ምክንያት ከእንቅስቃሴ ርቆ ቆይቷል:: የክልሉን የስፖርት እንቅስቃሴ ወደ ቀድሞ ውጤታማነቱ ለመመለስ ጥረቶች ቢኖሩም አስከፊው ጦርነት ባስከተለው የሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ሁኔታውን አስቸጋሪ ሊያደርገው ችሏል::

ለአራት ዓመታት በነበረው አለመረጋጋት ከውድድር ርቆ የቆየው ክልል ከፕሪቶሪያው ስምምነት ወዲህ ወደ ስፖርታዊ እንቅስቃሴና ውድድር ለመመለስ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል:: አትሌቲክስም ልክ እንደሌሎች ስፖርቶች ሁሉ በጦርነቱ ብዙ ችግሮች የገጠሙት ቢሆንም ይህንኑ ተቋቁሞ ወደ እንቅስቃሴ ለመግባት የተለያዩ የመፍትሄ አማራጮችን ለመጠቀም ጥረት እያደረገ ነው:: የውስጥ ውድድሮችን በማድረግ እንዲሁም ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ በሚያዘጋጀው ውድድሮች እየተሳተፈ ወደ እንቅስቃሴ ተመልሷል:: ካለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ቻምፒዮና እና በቅርቡ በተካሄደው የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይም ተሳታፊ ነበር::

በሀዋሳ በተካሄደው የፕሮጀክቶች ውድድር ታዳጊ አትሌቶችን ለመምረጥ በጥር ወር በአዲግራት ከተማ በተደረገው ማጣሪያ አትሌቶችን በመለየት ተስፋ ሰጪ ተሳትፎ ማድረግ ችሏል:: 15 ሴት እና 12 ወንድ በድምሩ 27 አትሌቶችን በማካፈልም የተሻለ እንቅስቃሴን በማድረግ ተጠናቋል:: በክልሉ የሚገኙ ስድስት ክለቦችም ተደራጅተው ወደ ነበራቸው ቁመና ለመመለስ ከፕሮጀክቶች አትሌቶችን በመመልመል ወደ እንቅስቃሴ ለመግባት እየሰሩ ነው:: በርካታ የንብረት ውድመት የደረሰባቸው ክለቦቹ በጥናት ለይተው በመቐለ ከተማ በተካሄደው የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፤ ባላቸው ቁሳቁስም እንቅስቃሴ ጀምረዋል::

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሚያውቃቸውና ድጋፍ የሚያደርግላቸው ስምንት ፕሮጀክቶች በክልሉ ሲገኙ በየዓመቱ የሚደረገውን የአቅም መፈተሻ ውድድር በማድረግ የትጥቅ ድጋፍ ተደርጎላቸው በተሻለ እንቅስቃሴ ውስጥ ይገኛሉ:: በክልሉ ስፖርት ቢሮ ለሁሉም ስፖርቶች የተመደበ በጀት ባለመኖሩ አትሌቲክስም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ከሆኑት ስፖርቶች ተርታ ይሰለፋል:: በቁስና በሰው ሕይወት መጥፋት ከፍተኛ ጉዳትን በማስተናገዱ የሁሉም አካላትን ርብርብ የሚፈልግ በመሆኑ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል:: ለዚህም የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶችን በመጠቀም ስፖርቱን ወደ ቀድሞ ቁመናው ለመመለስ በእቅድ እየተሰራ ይገኛል::

የበጀት እጥረቱን ለመፍታት የሚያስችለውን እቅድ ለማስፈጸም ከብሄራዊ ፌዴሬሽን ጋር በትብብር ለመስራትና የሩጫ ውድድርን በክልሉ በማካሄድ የገቢ ማሰባሰቢያ ለማድረግ ታስቧል:: በተጨማሪም ከክልሉ የወጡና ውጤታማ አትሌቶች ስፖርቱን የሚደግፉበትን ሁኔታ በመፍጠር አስፈላጊውን ገቢ ለመሰብሰብና ክልሉ በሀገር አቀፍ ውድድሮች ለመሳተፍ ታቅዷል:: የገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶቹ ስኬታማ እንዲሆኑም ቅድመ ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው::

የክልሉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ኢንስትራክተር ቢንያም ሕይወት፣ በተገኘው ሰላም ምክንያት ስፖርተኞችን በማሰባሰብ ወደ እንቅስቃሴና ውድድር እንዲመጡ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል:: ስፖርት ሊቆም ስለማይገባና ከክልሉ የወጡ አትሌቶች የሚያደርጉትን ውጤታማነት ለማስቀጠል ስፖርቱን በሚደግፉ አካላት ባለው አቅም እየተሰራ ይገኛል:: በክለቦች የነበሩት አትሌቶች በአብዛኛው አዲስ አበባ ወደሚገኙ ክለቦች በመፍለሳቸው በክልሉ የሚገኙ ክለቦች ከፕሮጀክቶችና ከተለያዩ ቦታዎች አትሌቶችን እያሰባሰቡ በመሆናቸው ውጤታማ ለመሆን ከሁለት እስከ ሶስት ዓመት መስራት ይጠበቅባቸዋል::

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለፕሮጀክቶቹ የትጥቅ ድጋፍን ያደረገ ቢሆንም ለስምንት ፕሮጀክቶች ሲሰጥ የነበረው የትጥቅ ድጋፍ አሁን ወደ ስድስት ፕሮጀክቶች ቀንሷል:: በዚህም መሰረት የተሰጠውን ትጥቅ ለስምንት ፕሮጀክቶች ለማከፋፈል መገደዳቸውን የቴክኒክ ኃላፊው ተናግረዋል:: ካለፈው ዓመት አጋማሽ አንስቶም አትሌቶቹ በስልጠና ላይ ይገኛሉ:: ከጉዳቱ ስፋት አንጻር የተደረገው ድጋፍ አናሳ በመሆኑም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል:: የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከትጥቅ በተጨማሪ የ2 ሚሊየን ብር ድጋፍን ቢያደርግም በቂ ባለመሆኑና ክልሉም የገንዘብ ችግር ስላለበት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል::

በአሁኑ ወቅት በየክልሉ ከስፖርት እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ ችግሮች በመኖራቸው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ወርዶ በቅርበት በመስራት ስፖርቱ በውጤታማነቱ እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚኖርበትም ኃላፊው ያስገነዝባሉ:: ክልሉ በገንዘብና በቁሳቁስ ከፍተኛ ችግርን እየተጋፈጠ በመሆኑ በምን መልኩ ይፈታ በሚለው ላይም አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ እገዛውን ቢያደርግ ስፖርቱን ወደ ቀደመ ቁመናው መመለስ እንደሚቻልም እምነታቸው ነው::

ዓለማሁ ግዛው

 አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2016 ዓ.ም

Recommended For You