ወደ ፊት ካላሰብን ጉልበታችንን ሮቦት ይተካዋል!

ትናንት የአርበኞች ቀን ነበር:: ትናንት የትንሳኤ በዓል ስለነበር የዘንድሮው የአርበኞች ቀን የተለመደውን የሚዲያዎች ሽፋን አላገኘም:: በሌላ በኩል አራት ኪሎ ያለው የድል ሀውልት በኮሪደር ልማት ምክንያት ለዚህ ዓመት ምቹ አልነበረም:: የአርበኞች ቀን ታሪካዊ ሁነቶችን ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ላይ በዝርዝር አይተናል:: ለታሪክ ባለን አረዳድ ላይ ግን ትዝብቱን ላካፍል::

በተለያየ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚቀርቡ ብዙ ምሁራን እና ፖለቲከኞችን እንከታተላለን:: የሚቀርቡት በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ፣ ወይም በአገሪቱ ቀጣይ የዕድገትና ብልጽግና ጉዞዎች ላይ ሀሳባቸውን እንዲሰጡ ነው:: ልብ ብላችሁ ከሆነ ግን ብዙ ምሁራን እና ፖለቲከኞች ከወቅታዊ እና ከወደፊት ጉዳይ ይልቅ መቶ እና ሺህ ዓመታት ወደኋላ ተመልሰው ‹‹በዚህ ጊዜ እገሌ እንዲህ አድርጎ ነበር!›› ይላሉ:: አብዛኞቹ 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የተቸነከሩ ናቸው:: አስቂኝ በሆነ ሁኔታ ከመቶ እና ከሺህ ዘመናት በፊት የነበሩ መሪዎችንና ሥርዓቶችን እየጠቀሱ ‹‹ጨቋኝ ነበሩ›› ይላሉ:: እነዚህ ሰዎች ከመቶ እና ከሺህ ዘመናት በፊት ከነበረ ትውልድ ጋር እየተወዳደሩ ነው:: ዛሬ ላይ ‹‹አለ! የለም!›› እያከራከረ ያለውን ዴሞክራሲ ከ100 እና ከ200 ዓመት በፊት በነበረ ሥርዓት ‹‹ዴሞክራሲያዊ አልነበሩም!›› እያሉ ይወቅሳሉ:: እሺ አልነበሩም! ስለዚህ ምን ይሁን? ይከሰሱ? ማዘዣ ይውጣባቸው? ከሥልጣን እናውርዳቸው? እነዚያ ሰዎች እኮ እንኳን ሕይወታቸው አጥንታቸው ራሱ በአካል አይገኝም! በአጭሩ የሉም!

ታሪክ በታሪክነቱ ይጠቀሳል:: ከነበረው ስህተት እንማራለን፣ ከነበረው ጥንካሬም እንማራለን:: ስህተታቸው እንዳይደገም፣ ጥንካሬያቸው እንዲቀጥል ይሰራበታል:: እንዴት በ21ኛው ክፍለ ዘመን በ19ኛው ክፍለ ዘመን የነበረ ነገር ላይ ሙጭጭ ይባላል? ያ ትውልድ እና ይሄኛው ትውልድ ማለት እኮ ሌላ ዝርያ እና ሌላ ዝርያ እንደማለት ነው:: አንድ የስብሃት ገብረእግዚአብሔር አገላለጽ ትዝ አለኝ::

ስብሃት በወጣትነቱ ዘመን ወጣትነትን ሲገልጽ ስለአዛውንቶች ቀጥቃጣነትና ነዝናዛነት የተናገረው ነገር ነበረው:: እሱ አዛውንት ከሆነ በኋላ ደግሞ ስለአዛውንትነት ውበትና ፀጋ ተናገረ:: አንድ ጋዜጠኛ፤ ያኔ አዛውንቶችን እንዲህ ብለህ ነበር፤ አሁን ደግሞ አዛውንትነትን እንዲህ እያሞጋገስክ ነው አለው:: የስብሃት መልስ አፍ የሚያስይዝ ነበር:: ‹‹እየውልህ! ይሄን ጥያቄ መጠየቅ ያለብህ ያኛውን ስብሃት ነበር!›› አለው:: የስብሃት ሀሳብ፤ ያኔ በወጣትነቱ የአዛውንትነትን ቦታ ስለማያውቀው ያለበትን እያጣጣመና እየወደደ ነበር:: እሱ አዛውንት ከሆነ በኋላ ደግሞ የአዛውንትነት ውበት ታየው:: ስለዚህ ስብሃት በ30ዎቹ ዕድሜው ውስጥ እና በ60ዎቹ ዕድሜው ውስጥ ሌላ ሰው እና ሌላ ሰው ማለት ነው! ይህ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነው::

ይህ እንግዲህ 100 ዓመት እንኳን በማይሞላ የአንድ ሰው ዕድሜ ውስጥ ብቻ ያለ ለውጥ ነው:: ከመቶ እና ከሺህ ዘመናት በፊት ያለውን ትውልድ ከዚህኛው ትውልድ ጋር እያነፃፀሩ ማየት ኋላቀርነት ነው:: ለዚያውም ከእነርሱ ያልተሻለ ሁኔታ ላይ ሆነን ማለት ነው:: 21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥነውን ይቅርና እነርሱ የሰሩትን እንኳን ሳንሰራ ማለት ነው::

ይህ ያለፉ ነገሮች ላይ ብቻ መቸንከር ምን ችግር አመጣ? ከተባለ ከዓለም ጋር እንዳንራመድ ያደርገናል፤ አድርጎናል:: የሰለጠኑ አገራት እጅግ ዘግናኝ የሆኑ የእርስ በእርስና ከሌላ አገራት ጋር ጦርነት አድርገዋል:: ዛሬ ላይ ግን ያ ጉዳያቸው አይደለም:: ያ ያለፈ ታሪክ ለእነርሱ ታሪክ ብቻ ነው:: ‹‹ያኔ ለካ የሰው ልጅ እንዲህ ነበር!›› እያሉ የሚዝናኑበትና የሚገረሙበት እንጂ ዛሬ ላይ የሚገዳደሉበት አይደለም:: ይህን አልፈው ሄደዋል:: ትንታኔዎቻቸው ሁሉ ስለአሁናዊና ወደፊታዊ ሁኔታዎች እንጂ 100 ዓመት ወደኋላ እየተመለሱ አይደለም:: ዕለቱን በታሪክ የሚያስተውሱትም የዚያ ዘመን ክስተት ለዚህኛው ትውልዳቸው ስለሚያስገርም ወይም ስለሚያዝናና እንጂ ‹‹ተነስ!›› ለሚል ቅስቀሳ አይደለም:: ቢቀሰቅሱም የሚነሳላቸው የለም::

በዚህ ሁኔታ ከቀጠልን የሚኖረን የሰውነት ዋጋ ይወርዳል:: አዕምሯዊ ሥልጣኔ ከሌለን፣ ማሰብና ማሰላሰል ካልቻልን፣ አገልግሎታችን አካላዊ ብቻ ይሆናል ማለት ነው:: አካላዊ አገልግሎት ደግሞ በዚህ ዘመን በቴክኖሎጂ እየተተካ ነው:: በጉልበት ሥራ እንኳን ማገልገል አንችልም:: የጉልበትን ሥራ ማሽን እየተካው ነው:: እንኳን የጉልበትን ሥራ የአዕምሮ ሥራ የሚጠይቁ ሥራዎች ራሱ በሮቦት እየተተኩ ነው:: የሰው ልጅ ከሮቦት የተሻለ አስተሳሰብ ኖሮት የሚያገለግለው ነገር ከሌለው ከሰው ሰራሽ ማሽን በታች ሆነ ማለት ነው:: ይህ ሊቆጨን ይገባል::

ትልልቅ ፈጠራና ግኝት ይቅር! ቢያንስ ግን ስለአሁናዊና የወደፊት ጉዳዮች እንኳን ማውራት ይቸግረን? በሙያ ዘርፉ የሚመለከታቸው አካላት አሁናዊና ወደፊታዊ መላ ሲናገሩ አይሰማም:: ሐኪሙም፣ መሃንዲሱም፣ ጠበቃውም፣ የሃይማኖት አባቱም… ታዋቂ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆነው መገናኛ ብዙኃን ላይ ሲቀርቡ፤ ሮጠው ወደኋላ ነው:: ዓለም የደረሰበትን ተሞክሮ አምጥተው ከመናገር ይልቅ የጨቋኝና ተጨቋኝ ታሪክ ያመጣሉ:: የእኔ ሰባት ዘር ጨቆነም ተጨቆነም ለእኔም ሆነ ለልጆቼ ምንም ነው! ያ የእነርሱ ዘመን ባህሪ ነው፤ እኔ መኖር የምፈልገው ያለሁበት ዘመን እየኖረ ያለውን ሕይወት ነው:: ለልጆቼም ማውራት የምፈልገው ቀጣዩ ትውልድ ሊኖርበት የሚችለውን የዓለም ፍጥነት ነው:: አሁን ላይ የሚቀርቡ ትንታኔዎችና ክርክሮች ሁሉ ከዛሬ 100 ዓመት በፊት በነበሩ ነገሮች ላይ ከሆነ ግን ለቀጣዩ ትውልድ ሰነድ ሆኖ የሚቀመጠው ንትርክ ይሆናል ማለት ነው:: የዚህኛውን ዘመን ክስተቶች በበቂ ሆኔታ አያገኝም ማለት ነው:: ይህ ደግሞ የትውልድ ክፍተት ይፈጥራል::

ስለዚህ ዓለም ወደፊት ብቻ እያሰበ፣ እኛ ወደኋላ ብቻ እያሰብን የሰለጠነው ዓለም ከሚሰራው ሰው ሰራሽ ማሽን በታች እንዳንሆን ወደፊት እናስብ!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 / 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You