የአርበኞች ድል ሚያዝያ 27 ቀን ለ83ተኛ ጊዜ ጀግኖች አርበኞች የፖሊስ ኦርኬስትራ ማርሽ ባንድ የመከላከያ ሰራዊት የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች እና የበዓሉ ተሳታፊዎች በተገኙበት ‹‹ በሀገር ፍቅር የተገኘ የአርበኝነት ድል ›› በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ውሏል። ስለበአሉና የበአሉ ታሪክ ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ምን መሰራት አለበት? የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች አንስተን የጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ጋር ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፡፡
አዲስ ዘመን ፡- በቅድሚያ የጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማህበር እንዴት ሊቀላቀሉ ቻሉ?
ልጅ ዳንኤል፡- እኔ የተወለድኩት ኢትዮጵያን ለመውረር ድጋሚ በ1928 ዓ.ም የመጣው የጣልያን ጦር አምስት ዓመት ቆይታ ተሸንፎ የኢትዮጵያን ምድር ለቆ ከወጣ ከሁለት ዓመት በኋላ ነበር:: አባቴ ሻለቃ መስፍን ስለሺ በአምስት ዓመቱ የጦርነት ጊዜ ከማይጨው፣ በወሎ ሸዋ፣ በጎንደር፣ ኢሉባቡር እና በሌሎች በስድስት ጠቅላይ ግዛት ጦርነት ላይ ተሳትፈዋል:: ንጉሰ ነገስት አጼ ኃይለስላሴ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ከእንግሊዝ ሀገር መጥተው ሱዳን ሲደርሱ አጅበው ወደ አዲስ አበባ ይዘዋቸው መጥተዋል::
በጦርነቱ ጊዜ ከሚነግሩን ፈተናዎች ከፍተኛ የውሀ ጥም፣ ረጅም ጉዞ፣ ጸሀይ ብርድ በጦርነት ላይ ሆነው በጥይት በሚመቱበት ጊዜ ጥይቱን የሚያወጡት በሳንጃ ስለነበር ራሳቸውን የሚያክሙበት ሌላ መንገድ ባለመኖሩ ከባድ ህመም እንደነበረም ሲነግሩን አስታውሳለሁ:: ነገር ግን በነበራቸው ጽኑ እምነት፣ እናሸንፋለን የሚል ስሜት፣ አምስቱን ዓመት ታግለው ጣልያንም ተሸንፎ፤ እነርሱም ሰንደቅ ዓላማቸውን ከፍ አደረጉ ::
ስለዚህ የአርበኝነት ታሪኩን በደንብ ስለማውቅ ወደ ማህበሩ ከመቀላቀሌ በፊት አባት አርበኞች ባቋቋሙት የልማት ኮሚቴ ውስጥ እሰራ ነበር:: ማህበሩን ለማጠናከር ከተለያዩ ኤምባሲዎች ጋር እንሰራ ነበር :: ከዚያም ማህበሩ የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንትን ምርጫ በሚያደርግበት ጊዜ ጥሪ ሲቀርብልኝ ማህበሩን ልቀላቀል ችያለሁ::
አዲስ ዘመን፡- ሚያዝያ 27 ቀን የኢትዮጵያ የአርበኞች የድል ቀን ሆኖ እንዲታሰብ የተደረገበትን የታሪክ መነሻ ምን ነበር?
ልጅ ዳንኤል፡- እንደሚታወቀው የፋሽስቱ ጣልያን የሞሶሎኒ ጦር ኢትዮጵያን ለመግዛት፣ ለመውረር ከ40 ዓመት በኋላ ተመልሶ በመጣበት ጊዜ አባት እና እናት አርበኞች ተሰባስበው ከንጉሰ ነገስቱ ጋር ሆነው ወደ ማይጨው ዘመቱ:: በዘመቻው ወቅት ጠላትን ለመመከት የወጣው ጦር የጣልያን ጦር የያዘውን ዘመናዊ መሳርያ፣ የተከለከለ መርዝ እና የሰለጠነ ጦር በኢትዮጵያውያን ጦር ላይ ኃይል እያሳየ መጣ:: ይህ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ በዚህ ጊዜ ንጉሰ ነገስቱ ከክቡር ዘበኛ ወታደሮቻቸው እና ሹማምንቶቻቸው ጋር ጦርነቱን ለመቀጠል ምክር ተመከረ::
በዚህም የጣልያን ጦር ያለው አቅም በዚሁ ከቀጠለ የሚኖረውን ውድቀት በማስላት እና እንሸነፋለን ብለው በማሰብ ከከመሩ በኋላ ኢትዮጵያ የሊግ ኦፍኔሽን አባል በመሆኗ ንጉሰ ነገስቱ ያለውን ችግር ለዓለም መንግስታት እንዲያሳውቁ በምክክሩ በመወሰኑ ንጉሰነገስቱ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም ወደ እንግሊዝ ሀገር አቀኑ:: ይህ ቀን የንጉሰ ነገስቱ አገዛዝ ከተቀየረ በኋላ በመጣው አገዛዝ የሚከበርበት ቀን የተቀየረ ቢሆንም፤ አጼ ኃይለስላሴ ወደ እንግሊዝ የሄዱበት እና ከአምስት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ሀገራቸው የተመለሱት በዚሁ በሚያዝያ 27 ቀን በመሆኑ የሚከበረው የአርበኞች የድል ክብረበዓል ትክክለኛው ቀን ይህ ሆኖ ጸድቋል::
ይህም በአርበኞች ዘንድ የሚታወቀው ይህ ቀን ሲሆን፤ ተከብሮ የሚለውም የድል በዓል በመባል እንጂ የነጻነት በዓል አይደለም:: ምንም እንኳን ጣልያን ለ40 ዓመታት በእቅድ ይዛ ለበቀል ያላትን ኃይል አደራጅታ የሰለጠነ ጦር ይዞ ብትመጣም በኢትዮጵያ በኩልም ይህ ነው የማይባል ሕዝብ በጦርነቱ ተሳትፏል:: ትልልቅ አርበኞችም በጀግንነት በመዋጋት በአምስት ዓመት ውስጥም የጠላት ጦርን መውጪ መግቢያ በማሳጣት እንዲወጣ አድርገውታል::
አዲስ ዘመን፡- የአርበኞች ቀን በአደባባይ ሲከበር ከዚህ ቀደም የነበረው ሒደት ምን ይመስል ነበር? የተከበረበት አጋጣሚስ እንዴት ነበር?
ልጅ ዳንኤል፡- ጣልያን ኢትዮጵያ ውስጥ ለአምስት ዓመት በቆየችበት ጊዜ ጀግኖች አርበኞች አምስቱን ዓመት እየተዋጉና እና እየተከላከሉ ቆይተው፤ ከአምስት ዓመት በኋላ ንጉሰ ነገስቱ ወደ ኢትዮጵያ በመግባታቸው፤ ይህ ቀን መከበር ጀምሯል:: ከዚያ በፊት ግን ንጉሰ ነገስቱ በምርኮ ተይዘው የነበሩትን ጣልያናውያንም ሆነ ባንዳ የነበሩትን ከዚህ በላይ አትቅጧቸው አቅርቧቸው አብረናቸው እንሰራለን በማለት ምህረት እና ይቅርታ እንዲወርድ አድርገዋል:: ሌላኛው ያደረጉት በጦርነቱ ጊዜ በየቦታው የተሰው እና ስርዓተ ቀብራቸው በአግባቡ ያልተፈጸመላቸው ጀግኖች አርበኞችን ከያሉበት አስነስተው አጽማቸው በክብር እንዲያርፍ አድርገዋል:: በሶስተኛ ያደረጉት የአርበኞች ማህበር ከዚህ ቀደም የነበረ እና በአርበኞች የተቋቋመ ቢሆንም፤ ህጋዊ እውቅና አልነበረውም:: የአርበኞች ማህበር እውቅና እንዲኖረው እና የአርበኞች የድል በዓልም በየዓመቱ ሚያዝያ 27 ቀን እንዲከበር አደረጉ::
በንጉሱ ጊዜ የአርበኞች ቀን ሲከበር ጀግኖች አርበኞች እና ሹማምንቱ በተገኙበት በቤተመንግስቱ ግብዣ ተደርጎላቸው ጠጅ እና ጥሬ ስጋ ይቀርብላቸዋል:: ያለፈውን ጊዜ በማሰብም ይፎከራል ይሸለላል:: ከዚያ በኋላ በነበረው ስርዓት ደግሞ የጦር ሰራዊቱ ወጥቶ፣ ተማሪዎች ህዝቡ በአደባባይ በተሰበሰቡበት ይከበራል:: አሁን ላይ ደግሞ የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ከዚህ ቀደም ቀዝቅዞ የነበረውን የበዓሉን አከባበር በበለጠ እንዲከበር እየሰራ ይገኛል::
አዲስ ዘመን ፡- አሁን ያለው ወጣት በዓሉን እና ታሪኩን ከማወቅ አንፃር ምን ማድረግ አለበት ይላሉ?
ዳንኤል፡– አሁን ላይ ያለው ወጣት እንደቀደሙት አባቶች ጋሻና ጦር ይዞ ወደ ጦር ሜዳ በመግባት ሳይሆን ዘመኑ የሚጠይቀውን እውቀት በመያዝ ባላቸው እውቀትና ችሎታ የሀገራቸውን ሰላም የሚያስጠብቁ፣ የነበረውን አብሮነት የሚያስከብሩ እና የሚያከብሩ ታሪክን እና ባህልን ጠብቀው የሚያቆዩ መሆን አለባቸው:: በአሁን ጊዜ በሀገራችን ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ ወጣት ነው:: በመሆኑም እነዚህ ወጣቶች ራሳቸውን ከማይወክሉ እና ከማይገልጹ ቦታዎች በመጠበቅ ቁምነገር የሚሰሩ መሆን አለባቸው::
አዲስ ዘመን፡- ማህበሩ ይህንን የአርበኞች የድል በዓል ከዓመት ዓመት ተጠብቆ እንዲቆይ እና ታሪኩ ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ ምን ስራዎችን እየሰራ ነው?
ልጅ ዳንኤል ፡– የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ለተወሰኑ ዓመታት ተቀዛቅዞ የነበረውን የአርበኞች የድል በዓል የሚከበርበትን መንገድ በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲከበር፣ የኢትዮጵያ የቆየ ታሪክ እንዳይጠፋ፣ ጀግኖች አርበኞች እንዳይረሱ፣ በተለያዩ የጦር ግንባሮች የተፈጸሙ የጦርነት ጀብዶች ተመዝግበው እንዲቆዩ እየሠራ ነው::
የተለያዩ መጽሄቶች ላይ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የመገናኛ ብዙሃኖችን በመጠቀም እና ከሚዲያው ጋር ግንኙነት በመፍጠር ስለአርበኞች ብዙዎች ጋር እንዲደርስ እያደረግን ነው:: ከዚህ ቀደም ይነገሩ የነበሩ የተዛቡ ታሪኮችን በማረም ትክክለኛውን ታሪክ በማንጸባረቅ፣ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች እየሄድን ተማሪዎች እንዲያውቁት የማድረግ ሥራም በመሠራት ላይ ይገኛል::
የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ በአጠቃላይ ግንዛቤ የሚፈጥሩ የጥያቄና መልስ ውድድሮችን እናዘጋጃለን:: በተጨማሪም ተማሪዎች ጣልያን ኢትዮጵያን ለምን መውረር እንደፈለገች፣ የዓለም መንግስታት አፍሪካን ለመቀራመት የፈለጉበትን ምክንያት፣ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ አጀማመሩ ምን ይመስል እንደነበር እና ወደፊት በሀገራችን ሰላም ፈጥረን ራሳችንን እንዴት ማሳደግ እና በኢኮኖሚ ጠንካራ ማድረግ እንደሚገባን ከተማሪዎች ጋር ውይይት እናደርጋለን::
አዲስ ዘመን፡- የቀድሞ ጀግኖች ቤተሰቦችን ከማስታወስ እና ከማገዝ አንፃር ማህበሩ ምን ስራዎችን ይሰራል?
ልጅ ዳንኤል፡- ማህበሩ በየጊዜው በሚያወጣቸው ታሪክን የሚያሳዩ መጽሄቶች ላይ እነዚህ አርበኞችን በማካተት ታሪካቸው እንዲታወቅ እና እንዲታወስ ያደርጋል:: በቀድሞው የአጼ ኃይለስላሴ ዘመን ከተመለከትን ጋሻ መሬት ይሰጣቸው ነበር:: ከዚያ በኋላ በነበረው ስርዓት ንብረታቸው ተወርሶ ችግር ላይ ወድቀው እነዚያ አባቶችም በየመስጊዱ እና በየቤተክርስቲያኑ ኒሻናቸውን አውጥተው መለመናቸው የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ነው:: አሁን ላይ ማህበሩ ከመንግስት ጋር በመነጋገር ይሰጣቸው የነበረው ድጎማ እንዲያድግ እያደረግን ነው::
ጣልያን በኢትዮጵያ በቆየችበት ጊዜ የጣልያንን ጦር ለመመከት የወጣው ሰራዊት ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ሰው እንደተዋጋ ይነገራል:: እነዚህ አርበኞች በእድሜቸው መግፋት አንዳንዶቹም በህመም ምክንያት የአልጋ ቁራኛ ሆነው ይገኛሉ:: በህይወት የሌሉም ይኖራሉ:: ነገር ግን ማህበሩ የአርበኞች ልጆችን በመቀበል የማህበሩ አባል እንዲሆኑ በማህበሩ ውስጥም እስከ ፕሬዚዳንት ድረስ የመመረጥ እድልን ሰጥቷቸዋል:: በእድሜ ባለጸጋ ሆነው የሚረዳቸው የሌለ ህክምና የሚስፈልጋቸውንም ድጋፍ እንዲደረግላቸው እናደርጋለን:: የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አበቤም የነጻ ህክምና እንዲያገኙ አድርገዋል::
ወደ ፊት ካቀድናቸው ሥራዎች መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተሰንዶ የሚገኘውን የአርበኞችን ታሪክ የሚገልጸውን ሰነድ መረጃ ዲጂታላይዝ የማድረግ ስራ አንደኛው ነው:: ይህንን ለማድረግ ከአንዳንድ ኤምባሲዎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ለመስራት አቅደናል:: ከዚህም ውጪ ለአርበኞች መሰብሰቢያ መጦርያ የሚሆን ማዕከል የመገንባት እቅድም ይዘናል::
አዲስ ዘመን፡- በእርሶ እይታ ሀገራችን ባለውለታዎቿን የምታከብርበትን መንገድ እንዴት ይገልፁታል?
ልጅ ዳንኤል፡– እውነቱን ለመናገር እኛ ሀገር ጀግና እና አርበኛ እንደተዋረደ ነው:: በንጉሰ ነገስቱ ጊዜ እንደ አውሮፓውያን ሀገራት ባይሆንም የተለያዩ ሹመቶች እየተሰጣቸው በአስተዳደር ስራዎች ላይ እንዲሰሩ ይመደባሉ:: ሀገሪቱ በጊዜው አቅምም ስላልነበራት ሁሉንም ማዳረስ አይቻልም:: ሆኖም ግን በዚያን ወቅት የበዓል ወቅት ሲሆን፣ በቤተመንግስት ሰንጋ ይታረዳል፣ ጠጅ ይጣላል፣ ይፎከራል፣ ይሸለላል:: እነዚህን በማድረግ ያለፈ ጊዜያቸውን አስታውሰው፤ በደስታ ወደቤታቸው ይሄዱ ነበር::
በሌላ በኩል በተለያዩ ጊዜያት አርበኞችን ለማክበር ፍላጎቱ ቢኖርም፤ በሀገሪቱ ስርዓቶች በተለዋወጡ ቁጥር እነዚህ አርበኞች እንደ ጥፋተኛ እየተቆጠሩ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲውሉ ለእንግልት፣ ለእስር ከዚያም በላይ ለሞት ተዳርገዋል:: በመንግስቱ ነዋይ ጊዜ እነ ራስ አበበ አረጋይ፣ እነ ደጃዝማች ለጥ ይበሉ፣ ራስ መስፍን ስለሺ፣ በሌላውም ጊዜ ብዙ ለሀገር ውለታ የዋሉ አርበኞች ተገድለዋል:: በእኔ አመለካከት ጥንታዊ የኢትዮጵያ አርበኞች የሚገባቸውን አላገኙም::
አዲስ ዘመን፡- የጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማህበር የአርበኞችን ዋጋ ከማሰብ እና ታሪክን ከማስተላለፍ አንጻር ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለው ያስባሉ ?
ልጅ ዳልንኤ፡-ከሞላ ጎደል አዎ! ፍጹም የሆነ ምንም ነገር የለም:: በተቻለን መጠን የገባንበትን መሃላና ኃላፊነት እየተወጣን ነው:: ነገር ግን እንቅፋቶች የሉም ማለት አይደለም፤ ብዙ ችግሮች ይኖራሉ:: አንዳንዴ ዘግየት ልንል እንችላለን፤ ነገር ግን እንደገና ወደ ቦታችን እንመለሳለን:: አሁን ካለንበት የበለጠ መስራት እንችላለን:: ነገር ግን ይህን ሁሉ ለማድረግ በሀገር ሰላም እንዲኖር ያስፈልጋል:: በውስጣችንም ሰላም ይገባል:: በመሆኑም ማህበሩ እነዚህን በማመዛዘን እየሰራ ይገኛል::
አዲስ ዘመን ፡- በሀገራችን በአሁን ሰዓት በተለያዩ ቦታዎች ላይ ግጭቶች ይከሰታሉ:: እነዚህ ግጭቶች መንስኤያቸው ምንድነው ብለው ያምናሉ መፍትሄውስ?
ልጅ ዳንኤል፡- ግጭት የሌለበት ሀገር የለም:: በኢትዮጵያም የመጀመርያውም አይደለም የመጨረሻውም ላይሆን ይችላል:: በአሁን ሰዓት እንኳን በራሺያ እና በዩክሬን፣ በእስራኤል እና በፍልስጤም መሀል ጦርነት አለ:: ወደ ሀገራችን ስንመለስ የግጭቶቹ መንስኤ ማጥናትና ማወቅ ያስፈልጋል:: በራሳችን ዜጎች በውስጣችን የተፈጠረ ከሆነ በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት ስልጣን ለመያዝ ከመፈለግ፤ ሌላኛው ከውስጥም ሆነ ከውጭ በህዝብ መካከል መቃረን እንዲፈጠር ህዝብ እርስ በራሱ እንዲጋጭ ያልተፈጠሩ ነገሮች እንደተፈጠሩ አድርጎ ማሰራጨት፣ ሀይማኖትን መሰረት አድርጎ ሌላ አቅጣጫ እንዲይዙ በማድረግ ህዝብ ስለ ጉዳዩ መረጃ ሳይኖረው ወደ ጸብ እንዲገባ ማድረግ ህዝብ የኔ በሚላቸው በሚያምንባቸው እሴት፣ ባህልና እምነት ላይ ያሉ ጥቂት ልዩነቶች ላይ መሰረት እያደረጉ ግጭቶችን ለመፍጠር የሚፈልጉ አሉ::
እንደ ድሮ አባቶቻችን ቢሆን በአንድ አካባቢ ግጭት ሲከሰት ገና ከጅምሩ በሽማግሌዎች በታሪክ አዋቂዎች ዘንድ ውይይት ተደርጎ ችግሩ እንዲፈታ ያደርጉታል:: የተፈጠረውን እሳት ከመነሻው ያጠፉታል እንጂ አያዳፍኑትም:: በመሆኑም አሁን ላይ ያሉትን ችግሮች በአንድ ህዝብ ስሜት በሆደ ሰፊነት ነገሩን ከስሩ መርምሮ መነጋገር እና ችግሩን መፍታት ያስፈልጋል:: ጦርነት ሴቶችን፣ ህጻናትን፣ አረጋውያንን ይጎዳል የሀገር ኢኮኖሚን ያዳክማል፤ ይህ ደግሞ በምዕራባውያን ስር ሆነን በሌላ መልኩ ተገዢዎች እንሆናለን:: ይህ እንዳይሆን ደግሞ ሰላም የሰፈነባት ሀገር እንድትኖረን ሁሉም የራሱን ኃላፊነት መወጣት አለበት::
አዲስ ዘመን፡- በሀገራችን የሚገኙ የተለያየ ሀሳብ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገር ሰላም እና መረጋጋት ምን አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ?
ልጅ ዳንኤል፡– በሀገራችን በአብዛኛው የስልጣን ሽግግር የተደረገው ምናልባትም ሁሉም በአፈሙዝ ነው ማለት ይቻላል:: አሁን ላይ የተደረገው ለውጥም ምንም ረብሻ ሳይኖር የመንግስት ሽግግር ተደርጓል:: በዓለም ላይ ብዙ አይነት የፖለቲካ ሀሳብና ርዕዮተ ዓለም ሊኖር ይችላል:: ለሌላው ሀገር የሠራ የፖለቲካ ሀሳብ እና አካሄድ ለእኛ ሊሠራ ይችላል ማለት አይደለም:: የሌላው አገር ተሞክሮ ሊሠራም ላይሠራም ይችላል:: በመሆኑም እነዚህን የፖለቲካ ሀሳቦችን ይዘን በብዙ መልኩ ፋይዳ የሌለው ክርክር ውስጥ ከመዋኘት ይልቅ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰሩት ለሀገራቸው ለአንድ ኢትዮጵያ እስከሆነ ድረስ ከሌሎች ጋር ቁጭ ብሎ በመነጋገር የትኛው ሀሳብ እና አካሄድ ለእኛ ሀገር ይሆናል የሚለውን መነጋገር ይገባል:: ምንም አይነት የፖለቲካ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች እርስ በእርስ በመነጋጋር ሀሳባቸውን አቋማቸውን መግለጽ ይችላሉ::
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ ተቋቁሞ በሥራ ላይ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ውጤታማ እንዲሆን በምን መልኩ መካሄድ አለበት:: ከኮሚሽኑ ምን ይጠበቃል ?
ልጅ ዳንኤል፡- ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ ትልቅ እድል ነው ብዬ አምናለሁ:: በሀገራችን ጥያቄ የሚነሳባቸውን የሀይማኖት፣ የብሄር ልዩነት፣ የሰንደቅ ዓላማ እና ሌሎች የሀሳብ ልዩነቶች አሉ:: ሁሉም የራሳቸውን ሀሳብ ሊያንጸባርቁ ይችላል:: ለሁሉም ችግር መፍትሄው ግን ልብን ከፍቶ ሌላ የተደበቀ አጀንዳን ሳይዙ ቀና በሆነ ስሜት በእርጋታ እና ተጨባጭ መረጃዎች ላይ በመመርኮዝ መወያየት ነው::
ኮሚሽኑ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በእኩል በማስተናገድ ከጀርባው ምንም ነገር ሳይኖር ማስተናገድ ይገባዋል:: ተቆጥቶ የመጣውንም ቢሆን መጀመርያ በማረጋጋት ሰከን እንዲል በማድረግ ሀሳብን መጋራት ያስፈልጋል:: ከሁሉም በላይ በውይይታቸው ላይ የሚነጋጋሩባቸው ታሪኮች ጥራዝ ነጠቅ እንዳይሆኑ ታሪክን ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው:: ስኬታማ መሆን እንዲቻል በውይይቱ ላይ የሚኖሩ ተሳታፊዎችም ሀሳባቸውን ለማስረዳት በሚሞክሩበት ጊዜ ከንግግራቸው ጀምረው ሌሎችን የሚያስከፋ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል::
አሁን ላይ በብዙ የመገናኛ ብዙሃኖች በሚያቀርቧቸው፣ በሚያስተላልፏቸው፣ በሚያ ዘጋጇቸው የውይይት መድረኮች ላይ ሰፊ ሀሳብን የያዙ ምሁራንን ተመልክቻለሁ:: በመሆኑም ታሪክ አዋቂዎችን በዚህ ውይይት ላይ ማካተት ያስፈልጋል:: በሁሉም አካላት ዘንድ መቻቻል፣ መግባባት፣ ሀሳቦችን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ መመልከት ያስፈልጋል:: ለውይይት እድል የሚሰጣቸው ምሁራንም ሆኑ ባለሙያዎች የሚያነሱት ሀሳብ ለይስሙላ ሳይሆን ከልባቸው እና እንደ ሀገር እንደ ህዝብ ላሉብን ችግሮች እውነተኛ መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ ሀሳቦችን ማንሳት እና አንዱ የሌላኛውን መልዕክትም ሆነ ሀሳብ ከንቀት በጸዳ መልኩ መደማመጥ ሊኖር ይገባል:: ይህ የሀገር ጉዳይ የ120 ሚሊዮን ህዝብ ሰላም ጉዳይ በመሆኑ፤ የሚደረገው ውይይት ንጹህ እና ሌላ ዓላማ የሌለው መሆን አለበት::
አዲስ ዘመን፡- ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ ቢገልፁልን?
ልጅ ዳንኤል፡- የዘንድሮው የአርበኞች የድል በዓል መሪ ቃል ‹‹ በሀገር ፍቅር አርበኝነት የተገኘ ድል ›› የሚል ነው:: ሀገራችን በከፍተኛ የሀገር ፍቅር በብዙ መስዋዕትነት የተገኘች ሀገር እንደመሆኗ በየትኛው ቦታ ላይ ያለ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንደ ቀደመው ጊዜ እንደ አያቶቹ በአጼ ቴዎድሮስ፣ በአጼ ዮሀንስ ጊዜም ሆነ በአጼ ምኒሊክ ጊዜ በሌሎቹም ነገስታት ጊዜ የነበራቸውን የሀገር ፍቅር እጥፍ ድርብ አድርጎ ሀገሩን መጠበቅ ይገባዋል:: የተቸገሩትን በመርዳት እድሜያቸው የገፋ አረጋውያንን በማገዝ እና እርስ በእርስ በመደጋገፍ ሀገራቸውን ኢትዮጵያን ዘብ ሆነው እንዲጠብቁ እላለሁ ::
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ::
ልጅ ዳንኤል ፡- እኔም አመሰግናለሁ::
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 / 2016 ዓ.ም