ፕሮጀክቱ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርጓል

ኮይሻ፡– የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሥራ ከተጀመረ አንስቶ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት የሚያስችሉ ሥራዎች ማከናወኑን ገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የአካባቢያዊና ማኅበራዊ ፕላኒንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛቸው ደሳለኝ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የግንባታ ምዕራፍ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ አካባቢያዊና ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት የሚያስችሉ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ሥራዎቹ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስተባባሪነትና በኮንትራክተሩ ዊ ቢውልድ ድጋፍ አድራጊነት የተከናወኑ ናቸው፡፡

ፕሮጀክቱ ዋና ተልዕኮው የኤሌክትሪክ ኃይል አምርቶ የሕዝቦችን እና የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ግዛቸው፤ የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንጻርም አቅሙ የፈቀደውን ድጋፍ አድርጓል፤ እያደረገም ነው ብለዋል፡፡

በፕሮጀክቱ አዋሳኝ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የመንገድ፣ የድልድይ፣ የንጹሕ መጠጥ ውኃ፣ የጤና እና የትምህርት ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ በተጨማሪም የትራንፎርመር ድጋፍ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ሥራ፣ የመስተዳድር ቢሮዎች ግንባታ እና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ሥራ እንዲሁም ሌሎች ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል፡፡

ከመንገድ መሠረተ ልማት እጥረት ጋር ተያይዞ የአካባቢው ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንዳልነበር የጠቀሱት አቶ ግዛቸው፤ በኦሞ ወንዝ ምክንያት ለዘመናት የቅርብ ሩቅ ሆነው የኖሩት የዳውሮና የጎፋ ሕዝቦች በተሠራው ድልድይ አማካኝነት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብራቸው መሳለጡን ለአብነት አንስተዋል፡፡

ወረዳን ከወረዳ ቀበሌን ከቀበሌ የሚያገናኙ መንገዶች መሠራታቸው በወሊድ ወቅት በእናቶች ላይ የሚያጋጥምን አደጋ ያቃለለ መሆኑንም አክለዋል፡፡

በኮንታ ዞን የኮይሻ ወረዳን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ጥያቄ ለመመለስም በየደረጃው ካሉ አካላት ጋር ንግግር መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በደቡብ ኦሞ ዞን የታችኛው ተፋሰስ አካባቢ የሚያጋጥሙ ውስን አሉታዊ ተፅዕኖዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የበርካታ ተቋማት እንቅስቃሴ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ግዛቸው፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልም በዘላቂነት ምላሽ ለመስጠት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ ዘላቂ የልማት ሥራዎችን ለመሥራት እንቅስቃሴ መጀመሩን እና ከባለድርሻ አካላትም ጋር አዎንታዊ የትብብር መንፈስ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

በአረንጓዴ ልማት ዘርፍም የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የራሱን ችግኝ ጣቢያ በማዘጋጀት የተራቆቱ ቦታዎችን መልሶ የማልማትና በካምፕ አካባቢዎችም ለምግብነት የሚውሉ ፍራፍሬዎችን የመትከል ሥራ መሥራቱን ገልጸዋል፡፡

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን  ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You