ከአምስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ የወባ ሕሙማንን ማከም የሚያስችል መድኃኒት ተሰራጭቷል

አዲስ አበባ፡- በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከአምስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ የወባ ሕሙማንን ማከም የሚያስችል መድኃኒት ማሰራጨት መቻሉን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። ከአስር ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች የወባ በሽታ ምርመራ ማድረጋቸውን ሚኒስቴሩ ጨምሮ ገልጿል።

የዘንድሮ የዓለም የወባ ቀን በሃገር አቀፍ ደረጃ “ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የወባ ማስወገድ ትግበራን እናፋጥን” በሚል መሪ ሃሳብ ከሚያዚያ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት አምስት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ ተግባራት ታስቦ ይውላል፡፡

የጤና ሚኒስቴር በየዓመቱ ሚያዚያ 17 ቀን የሚከበረውን የዓለም የወባ ወረርሽኝ መከላከል ቀን ምክንያት በማድረግ ትናንት በሰጠው መግለጫ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ደረጄ ዱጉማ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከአምስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ ሕሙማንን ማከም የሚያስችል መድኃኒት ተሰራጭቷል፡፡

ከዚህ ቀደም የነበሩት የወባ መመርመሪያ መሣሪያዎች የማያገኙት የወባ አስተላላፊ ትንኝ በመኖሩ በዚህ በጀት ዓመት መለየት የሚችል አዲስ የወባ መመርመሪያ መሣሪያ ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ ምርመራ ካደረጉ ዜጎች ውስጥ ሦስት ነጥብ አራት ሚሊዮን የሚሆኑት የወባ በሽታ እንዳለባቸው በሕክምና ተረጋግጧል ያሉት ዶክተር ደረጄ፤ በተለይ ተፈናቃይና ግጭት ባሉባቸው አካባቢዎች የወረርሽኝ መከላከሉ ሥራ ይበልጥ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።

ደረጄ (ዶ/ር) አክለውም፤ የመመርመሪያ ኪቶችን ከሰባት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ለማከፋፈል መቻሉን ጠቁመዋል።

እንደ ደረጄ (ዶ/ር) ገለጻ የወባ በሽታ የሚከሰትባቸው ወቅቶች በተለይ የመኸር መሰብሰቢያና የበልግ ወቅቶች በመሆናቸው ከሚያስከትለው ከፍተኛ የጤና ችግር በተጨማሪ ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳት አለው፡፡ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በ380 ወረዳ ሰባት ሺህ 600 ቀበሌዎች ላይ የወባ ወረርሽኝ መከላከል የማኅበረሰብ ንቅናቄ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

በሀገሪቱ የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል በ2015 በጀት ዓመት 19 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን የአልጋ አጎበር ማሰራጨት መቻሉን ደረጄ (ዶ/ር) አንስተዋል፡፡

የተሰጠው አጎበር ለሦስት ዓመት የሚያገለግል በመሆኑ በዚህ ዓመት አጠቃቀሙን የመከታተልና የማጠናከር ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ክፍተት ባለባቸውና ተፈናቃይ ዜጎች ባሉባቸው አካባቢዎች ከሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ የአልጋ አጎበሮች ተገዝተው ለማሰራጨት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡

ደረጄ (ዶ/ር)፤ የኬሚካል ርጭት የሚያስፈልግባቸው አካባቢዎች ላይ ከአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ ቤቶች አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል፤ በቀጣይም እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ እስከ ሁለት ሚሊዮን በላይ ቤቶች የኬሚካል ርጭት እንዲያገኙ ኬሚካሎቹ ተጓጉዘው በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል፡፡

የዓለም ወባ ቀንን በየዓመቱ ማክበር አንዱና ዋና ዓላማው የኅብረተሰብ የጤና ችግር የሆነው የወባ በሽታ ላይ የሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ለማጠናከርና በበሽታው ዙሪያ ያለው ግንዛቤ ማጎልበት እንዲቻል መሆኑን ደረጄ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም የወባ በሽታ ወረርሽኝ ካለበት የስርጭት መጠን ለመግታት ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሚያገለግል እስትራቴጂክ ዕቅድ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You