ሴቶችን በኢኮኖሚ ለማብቃት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፡– በመዲናዋ ሴቶችን በኢኮኖሚ ለማብቃት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ የሴቶች ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው ከሁሉም ክፍለ ከተማ ለተመለመሉ የገቢ ምንጭ ለሌላቸው 1ሺህ 51 ሴቶች ከ10 ሚሊዮን በላይ ብር ወጭ በማድረግ የተስማሚ ቴክኖሎጂ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በዚሁ ወቅት የቢሮው የሴቶች ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ነፃነት ዳባ እንደገለፁት፤ የተደረገው ድጋፍም የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ችግር በመፍታት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ያለመ ነው።

እንደ ወይዘሮ ነፃነት ገለፃ፤ ድጋፉ እናቶችንና የሚያስተዳድሯቸውን ቤተሰቦች በተለያየ መልኩ ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ የተደረገ ሲሆን፣ የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ገቢ የሚያገኙበትን እድል የሚፈጥር ነው፡፡

ባለፉት ጊዜያትም የባንክ ደብተር እንዲከፍቱ በማድረግ ለሥራ መነሻ የሚሆን ገንዘብ እንዲቆጥቡ ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰው፤ ድጋፉ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ መቆየቱንና እስካሁን ባለው ጊዜ ከ5ሺህ በላይ ሴቶች ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡

ግብዓቱ በቂ ሳይሆን ለሥራ ማስጀመሪያ እንደሚሆን ያነሱት ወይዘሮ ነፃነት፤ የዚህን ዓመት ድጋፍ ለየት የሚያደርገው በማኅበር ተደራጅቶ ለመሥራት አስቸጋሪ የሆነባቸውን ሴቶችን ያቀፈና ከአኗኗራቸው ጋር ተስማሚ መሆኑ ነው ብለዋል።

ቴክኖሎጂዎቹ የሴቶችን ልፋት የሚቀንሱና ወጪ ቆጣቢ ናቸው። በቀጣይም ሴቶቹ በማኅበር ተደራጅተው ለመሥራት የሚያስችሉ ናቸው ያሉት ኃላፊዋ፤ በተሰጡ ቁሳቁሶች ተጠቅመው በቀላሉ በመኖሪያ ቤታቸው መሥራት የሚችሉ በመሆኑ ከልጆቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው እንዳይርቁ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ድጋፉን ያገኙ ሴቶች በምን አይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል ያሉት ደግሞ በቢሮው የሴቶችን ተሳትፎ ማብቃትና ተጠቃሚነት ዳይሬክተር ወይዘሮ ስፍራሽ አልማው ናቸው፡፡

አሁን ላይ የተሰጠው ድጋፍም የተሠራውን ጥናት መነሻ በማድረግ እንደሆነ የገለጹት ወይዘሮ ስፍራሽ፤ ቢሮው እስከ ወረዳ ድረስ ባለው መዋቅር የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እንደሚሠራና ሴቶቹ ባገኙት ድጋፍም ወደሥራ የማይገቡ ከሆነ የራሱን እርምጃ እንደሚወስድ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ በቀጣይ ሴቶቹ ሥራዎቻቸውን የማስፋት ፍላጎት አላቸው። የብድር ችግር እንዳይገጥማቸው ከስኬት ባንክና ከየኛ ማይክሮ ፋይናንስ ጋር የተጀመረው የብድር ማመቻቸት ተግባር በየካ፣ በለሚኩራና በአራዳ ክፍለ ከተሞች እየተከናወነ ነው፡፡ ይህ ተግባር በቀጣይ በ12 ክፍለ ከተሞች ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

የድጋፉ ተጠቃሚ የሆኑት ወይዘሮ አለምነሽ ተሾመ በበኩላቸው፤ ድጋፉን በማግኘታቸው እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፤ በግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው እንደሚሠሩና የሚያገኙት ገቢ ሁለት ልጆቻቸውን ለማስተዳደር አነስተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮ አለምነሽ አክለውም ባገኙት ድጋፍ የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት የቤተሰባቸውን ሕይወት ለመቀየር ዝግጁ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

ድጋፉ የእንጀራ፣ የዳቦ መጋገሪያና በቀላሉ ከቦታ ወደቦታ በማንቀሳቀስ የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችሉ ማሽኖች የተካተቱበት ነው።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You