የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከብሪክስ ጋር በመሥራት ሀገርን መጥቀም አለባቸው

አዲስ አበባ፡– የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር በቅርበት በመሥራትና በመቀናጀት ሀገርና ሕዝብን የሚጠቅም ሥራ መሥራት እንዳለባቸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

የብሪክስ አካል የሆነው የብሪክስ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጉባኤ በትናንትናው ዕለት ተካሂዷል፡፡ ከሩሲያ የመጡ የብሪክስ የሲቪል ጉባኤ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

በጉባኤው ወቅት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደገለጹት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን አስተዋፅዖ የሚፈልጉ ጉዳዮች በርካታ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ወደ  ብሪክስ ከተቀላቀለች በኋላ በሁሉም መስክ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ሥራዎችን ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር ተቀራርቦ በመሥራትና በመቀናጀት የበለጠ ሀገርንና ሕዝብን የሚጠቅም ሥራ መሥራት አለባቸው ብለዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ ሰፊ ማሻሻያ ተከናውኗል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ ቀደም የነበሩ ሕጎች መቀየራቸውን ገልጸዋል፡፡

የበለጠ ማሻሻያ በማድረግ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሥርዓትን ተከትለው ሕዝብና ሀገርን የሚጠቅም ሥራ እንዲሠሩ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የብሪክስ ጥምረት አባል መሆኗ የሲቪል ድርጅቶች ለሀገር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማድረግ እንዲችሉ ትልቅ ዕድል እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለሀገር ልማትና የዲዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አላቸው ያሉት አቶ ፋሲካው፤ በመንግሥት በኩል ጠቀሜታቸው ታምኖበት ሕጎችን የማሻሻልና ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ጥረቶች መደረጋቸውን አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለፉት ዓመታት በሚፈለገው ልክ ባይሆንም ሕዝብንና ሀገርን የሚጠቅም ሥራ አከናውነዋል ብለውም፤ በተለይ በልማት፣ በዴሞክራሲ ግንባታ፣ በግጭት አፈታትና በሰብዓዊ ድጋፎች ረገድ በርካታ ተግባራትን ስለማከናወናቸው ጠቅሰዋል፡፡

በብሪክስ የሩሲያ የባለሙያዎች ኃላፊ ዶክተር ቪክቶሪያ ፓኖቫ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ ስለ ብሪክስ ሲቪል ጉባኤ ገለጻ በማድረግ ከኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ጋር በቅርበት ይሠራል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ብሪክስን በመቀላቀሏ ለኅብረቱም ሆነ ከሩሲያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ይረዳል ያሉት ኃላፊዋ፤ የብሪክስ የሲቪል ጉባኤው በኢትዮጵያና ሩሲያ መካከል አዲስ ምዕራፍን ይከፍታል ሲሉ ገልጸዋል።

ስለ ኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምሥረታ፣ ስላሉባቸው ችግሮችና መልካም ተሞክሮዎች መረዳታቸውን በመግለጽ፤ ወደፊት በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ለማጠናከር እገዛ ይኖራል፡፡ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር ጠንካራ ትብብር እንደሚኖርም ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

ሞገስ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You