በመዲናዋ ለበዓሉ ከአንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ምርት ይቀርባል

-አንድ ኪሎ ሥጋ ከ400 እስከ 460 ብር እንዲሸጥ ተወስኗል

አዲስ አበባ፡- በመዲናዋ ለፋሲካ በዓል ከአንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርት እንደሚቀርብ የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ የሸማቾች ሥጋ ቤቶች አንድ ኪሎ ሥጋ ከ400 እስከ 460 ብር እንዲሸጡ ተወስኗል፡፡

በአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን የግብይት ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሀብተየስ ዲሮ ትናንት በሰጡት መግለጫ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ለፋሲካ በዓል የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶች እጥረት እንዳይከሰት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም በ164 መሠረታዊ የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ከአንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ምርት ለኅብረተሰቡ እንደሚቀርብ ገልጸዋል፡፡

ማኅበራቱ የሕዝቡን ዝቅተኛ ኑሮ ያማከለ የምርት ስርጭት ታሳቢ አድርገው በሥራቸው ባሉ 800 ሱቆች አማካኝነት ምርት እንደሚያደርሱ ተናግረዋል፡፡

እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ፤ የከተማው ነዋሪ በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፍና በቂ የምርት አቅርቦት እንዲኖር ከማዕከል እስከ ወረዳ ባለው መዋቅር ግብረ ኃይል ተደራጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል። በዚህም እስካሁን ጤፍ፣ ዱቄት፣ የቁም እንስሳት፣ እንቁላል፣ ሽንኩርትና መሰል ምርቶች ከተለያዩ አካባቢዎች በዩኒየኖች አማካኝነት ወደ መዲናዋ ገብተዋል፡፡

በበዓሉ ቅድመ ዝግጅት እቅድ በመውጣት ኮሚቴ አዋቅሮ ወደ ሥራ መግባት እንደተቻለ የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ የተዋቀረው ግብረ ኃይል እስከ ወረዳ ድረስ የሚከታተል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ እንደ ጤፍ፣ ዱቄት፣ የቁም እንስሳትና እንቁላል ያሉ ግብዓቶች እየገቡ እንዳለ ጠቅሰው፤ ጤፍ፣ ሽንኩርትና መሰል ምርቶች በበቂ ሁኔታ መግባታቸውን ነው የገለጹት፡፡

በተለይ የሸማቾች ሥጋ ቤቶች የአንድ ኪሎ ሥጋ ከ400 እስከ 460 ብር ብቻ እንዲሸጡ መወሰኑንም ተናግረዋል፡፡ የዋጋ ልዩነቶች እንደ በሬው አይነት የሚወሰን እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

በከተማዋ ባሉ 246 የሸማች ሥጋ ቤቶች ትስስር ፈጥረው ለከተማዋ ነዋሪዎች ሥጋ እንዲያቀርቡ ቅድመ ዝግጅት መጀመራቸውንም ተናግረዋል፡፡

በቂ ምርት ገብቶ ኅብረተሰቡ ጋር እንዲዳረስ የዝግጅት፣ የአቅርቦት፣ የገበያ ትስርና ስርጭት ላይ በትኩረት እየተሠራ እንዳለ ጠቅሰዋል፡፡

በኮሚሽኑ የሬጉላቶሪ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተጫነ አዱኛ በበኩላቸው፤ በዓሉን አስመልክቶ እየተሠሩ ካሉ የአቅርቦት ሥራዎች በተጨማሪ ኅብረተሰቡ በዓሉን በሠላም እንዲያሳልፍና የኑሮ ጫናውን ለማቅለል እየተሠራ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡

በተለይም ከምግብ ምርቶች ጋር ተያይዞ ያሉት በተገቢው ዋጋ ኅብረተሰቡ ጋር እንዲደርሱ ጠንካራ ክትትል እየተደረገ መሆን ገልጸዋል፡፡

ለሥራው የተደራጀው የሬጉላቶሪ ቡድን ምርት በትክክል ለኅብረተሰቡ መድረሱን ከማዕከል እስከ ወረዳ ድረስ ቁጥጥር እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You