ሀገራት የዜጎቻቸው ነፀብራቅ ናቸው፤ ዜጎችም የየሀገራቸው ተምሳሌት ናቸው። የእያንዳንዱ ሀገር የኢኮኖሚ አቅም ፣ የአኗኗርና የአስተዳደር ሥርዓት፣ ወግና ባህል፣ ሥልጣኔና እድገት ሌላውም ነገር ሁሉ በአንድም ይሁን በሌላ በዜጎች ይገለጻል። በተለያዩ ሀገራት ውስጥ የተለያየ የአሠራርና የአስተሳሰብ ልዩነት ያላቸው ማህበረሰቦች የመገኘታቸው ምስጢር ይሄው ነው።
ለመማርና ለመመራመር የማይታክቱ፣ ለሥራ ጠዋት ማታ የሚተጉ፣ ለሰላምና ነፃነት ዘብ የሚቆሙ፣ ታትረው የሚያመርቱ፣ ልዩነትን የሚያከብሩ፣ ሙስናና ብልሹ አሠራርን አጥብቀው የሚፀየፉና የሚታገሉ የሀገራቸውንና የሕዝባቸውን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያስቀድሙ ስልጡን ሕዝብ ያላቸው ሀገራት፤ ኮሽታ ሳይሰማባቸው ሕዝባቸው አማን ውሎ ያድራል፤ ገበያቸው ጥጋብ ይሆናል።
እንደዚህ አይነት ማህበረሰብ የገነቡ ሀገራት በኢኮኖሚ ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የመበልጸግ እድል ስላላቸው ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ሀገራት ይተርፋሉ። በአንጻሩ ደግሞ ሠርቶ አደር ሳይሆን አውርቶ አደር ማህበረሰብን ያፈሩ፣ ደካማ የሥራ ባህል ያላቸው፤ ልዩነትን የግጭትና የጠብ አጫሪነት መሳሪያ ያደረጉ፤ ትናንት ላይ ይፈጸም፣ አይፈጸም በውል የማይታወቅ ትርክትን መነሻ አድርገው ዛሬያቸውን የሚያበላሹ አሉ።
እርስ በርስ የሚገፋፉ፤ ተምረናል ባዮች ሆነው እውቀታቸውን ለችግር መፍቻነት ከማዋል ይልቅ ለሴራና ሕዝብን ከሕዝብ ለመከፋፈል የሚጠቀሙ፤ የጦርነትን አስከፊነት ከትናንት አዳፋ ታሪካቸው መማር ተስኗቸው ዛሬም በጦርነት አዙሪት የሚዳክሩ፤ በስራ ሳይሆን በአቋራጭ መክበር የሚፈልጉ፣ ተደጋግፎ ማደግን ትተው ተጠላልፎ መውደቅን የሚመኙ፤ የሰላምን ዋጋ ያቀለሉ ዜጎች ያሏቸው ሀገራትም አሉ።
ኢትዮጵያም እንዲህ አይነት መልክ ካላቸው ሀገራት ጎራ እንዳለች የሚያሳዩ ምልክቶች ሲስተዋሉባት ኖራለች። ዛሬም ከጦርነት አዙሪት መውጣት ተስኗቸው እድገታቸው አንድ እርምጃ ወደፊት፤ ሁለት እርምጃ ወደ ኋላ ከሆነባቸው ሀገራት መሐል አንዷ ሆና ትጠቀሳለች።
በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እልፍ ወጣቶች በጦርነት እረግፈዋል፤ እየረገፉም ይገኛሉ። በሰላም እጦት ሳቢያ በተለይ ሴቶች፣ ሕፃናትና አዛውንት ህልቁ መሳፍርት የሌለው ግፍና በደል ተቀብለዋል፤ እየተቀበሉም ይገኛሉ። ገበሬው ያመረተው ምርት በሰላም ተጓጉዞ ገበያ መድረስ ባለመቻሉ፤ ለኢኮኖሚያዊ ችግር ተጋልጧል።
ሀገር የዜጎቿ የእጅ ሥራ ነች፤ በተለይም የወጣቱ ኃይል። ወጣትነት አዲስ ጉልበትና አዲስ አስተሳሰብ የታመቁበት የእድሜ ደረጃ ነው። ይህ ኃይል ሀገርን ወደ ከፍታው ማማ ለማውጣት የአንበሳን ድርሻ የሚወስድ ነው። ወጣቶች ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው። በዚያው ልክ ደግሞ በአግባቡ ካልተገሩና ካልተመሩ የሴረኞች ሃሳብ ማስፈጸሚያ መሳሪያ መሆናቸው አይቀሬ ነው።
ሊቢያን ለአብነት ብንወስድ፤ የሀገሪቱ ዜጎች ቅንጡ ሕይወት እንዲኖራቸው አድርጎ ለ42 ዓመት የመሯት ሙሃመድ ጋዳፊን ምዕራባውን ከስልጣን ለማስወገድ የተጠቀሙት የሀገሪቱን ወጣቶች ነው። ምዕራባውያን ሰውዬውን ከስልጣን ካስወገዱና ሀገሪቱ ከወደመች በኋላ ዛሬም የሀገሪቱ ዜጎች በተለያዩ ጎራዎች ተከፋፍለው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ናቸው። ሀገሪቱ የአሸባሪዎችና የወንበዴዎችም መፈንጫ ሆናለች።
አሁን በእኛ ሀገር እየታየ ያለው ሁኔታም መቋጫው ጥሩ አይሆንም። “ወጣቱ ከውስጣዊና ውጫዊ ታሪካዊ ጠላቶቻችን የሴራ ማስፈጸሚያ መሳሪያነት ምን ያህል የራቀ ነው?” የሚል ጥያቄ ከተነሳ የሊቢያ ተሞክሮ መልስ የሚሰጥ ይመስለኛል። ምክንያቱም በሀገራችን የሰላም እጦት ውስጥ በአብዛኛው እየተንቀሳቀሱ ያሉት ወጣቶች በመሆናቸው ነው። ጠብ የሚል ነገር በማያገኙበት ዓላማና ግብ በሌለው የጦርነት አዙሪት
ውስጥ ተዘፍቀው በርካታ ወጣቶች ሕይወታቸውን ገብረዋል፤ ዛሬም እየገበሩ ይገኛል። ለብዙዎች መፈናቀልና ሞትም ምክንያት ሆነዋል።
ለም አፈርና ሰፊ የሚለማ መሬት፣ ለሁሉም አይነት ምርት ተስማሚና ለኑሮ አመች የሆነ አየር ንብረት ያላት፤ የአፍሪካን 70 በመቶ የውሃ ሀብት በውስጧ የያዘች፤ በእንስሳት ሀብቷ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነች፤ ከታወቁት ባለፈ ተምርምሮ ያልተደረሰባቸው ብዙ የከበሩ ማዕድናትን በጉያዋ ያቀፈች፣ አረንጓዴና ድንግል መሬት ያላት ሀገር ይዞ ወጣቱ በሕጋዊና በሕገወጥ መንገድ ወደ ተለያዩ ሀገራት በስደት መጉረፉም ሌላው ችግር ነው።
ወጣቱ በሀገሩ ተምሮ፣ ሠርቶና ነግዶ ያልፍልኛል የሚል ሞራልና ወኔው በውስጣዊና ውጫዊ ሴረኞች ተሰልቦ፤ የሰው ሀገር ናፋቂ ሆኗል። ሀገሩን በሚጠቅምበት በወጣትነት ዘመኑ፤ እውቀትና ጉልበቱን ለሰው ሀገር እያፈሰሰ ይገኛል። በተለይ ወጣቶች በሚያደርጉት ሕገወጥ የስደት ጉዞ “እንደርስበት አለን” ካሉት የህልም እንጀራ ሳይደርሱ ብዙዎች በየበረሃው የአውሬ እራትና በባህር የአሳነባሪ ሲሳይ ሆነው ቀርተዋል።
አይናቸው እያየ የውስጥ አካላታቸው ጭምር ወጥቶ እየተሸጠ የወንበዴዎች መክበሪያና ሲሳይ ሆነዋል። በባህርና በበረሃ ይህን ሁሉ መከራ አልፈው የአሰቡበት ሀገር ሲደርሱ በድንበር ጠባቂዎች ሕይወታቸውን የሚያጡ አሉ። እንዲሁም ድንበር ላይ ተይዘው የወጣትነት ዘመናቸውን በእስር ቤት እየሟቀቁ የሚያሳልፉ ብዙዎች ናቸው።
ለአብነት ወደ ሳውዲ አረቢያ ለመግባት ሲሉ ድንበር ላይ ተይዘው ለዓመታት እስር ቤት ውስጥ ሲሰቃዩ የነበሩ 70 ሺህ የሚሆኑ ዜጎችን መንግሥት ከሳውዲ አረቢያ መንግሥት ጋር ባደረገው የተሳካ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባለፉት ተከታታይ ዓመታትም ይሁን በቅርቡ ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ተደርጓል። ይሁን እንጂ ነገሩ “ውሃ ቅዳ-ውሃ መልስ!” ሆኖ፤ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ መስዋትነት ተከፍሎና ወጪ ወጥቶ በአንድ በኩል ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሥራ ይሠራል።
በሌላ በኩል ደግሞ ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ሀገር ጥለው ይሰደዳሉ። እንደ ተባበሩት መንግሥታት የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) መረጃ ከሆነ፤ በየዓመቱ ከ200 ሺህ የሚበልጡ ስደተኞች ከጅቡቲ ተነስተው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ለመድረስ በየብስ እና በባሕር አደገኛ ጉዞ ያደርጋሉ።
በዚህ አደገኛ ጉዞ ባለፉት አምስት ዓመታት በጀልባ መስመጥ አደጋ ብቻ ከ200 በላይ ኢትዮጵያውያን ሕይወት ማለፉን መረጃዎች ያሳያሉ። ዘንድሮ ደግሞ ሚያዚያ ወር ከገባ ወዲህ ብቻ በ15 ቀን ውስጥ ሁለት ጊዜ በደረሰ የጀልባ መገልበጥ አደጋ፤ መነሻቸውን ጂቡቲ አድርገው ወደ የመን ሲጓዙ የነበሩ ስደተኞች ጀልባቸው በጂቡቲ ባሕር ዳርቻ ላይ ተገልብጣ በድምሩ 54 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ዜጎች ወደዚህ አይነት አደገኛ ጉዞ እንዲገቡና ይህ ሁሉ መከራ እንዲደርስባቸው የሚያደርጉ ብዙ ገፊ ምክንያቶች እንዳሉ ይታወቃል። ነገር ግን ወጣቱ ሀገር ጥሎ ከኮበለለ የሀገሩን ችግር ማን ያስተካክልለታል? በመሆኑም ወጣቱ ሀገር ጥሎ መሄድ መፍትሄ እንዳልሆነ አውቆ፤ ችግሮችን ተጋፍጦ፣ መስዋእትነት ከፍሎ ሀገሩን ለሥራ ምቹ፣ ለኑሮ ተስማሚ፣ የዜጎች መብት የተከበረባት፣ የበለጸገች ሀገር ከማድረግ አንጻር የአንበሳውን ድርሻ ሊወጣ ይገባል። ዛሬ ላይ በብልጽግና ማማ ላይ የሚገኙ ሀገራት ለዚህ የበቁት ትናንት በተለይ ወጣት ዜጎቻቸው በከፈሉት መራራ መስዋእትነት ነው።
ስለዚህ ወጣቱ ከውጫዊና ውስጣዊ ጠላቶች የሴራ ማስፈጸሚያነት ተቆጥቦ ለሀገሩ ሰላም ዘብ ሊቆም እና በሀገሩ ሠርቶ እራሱንና ወገኑን ሊለውጥ ይገባል። ወጣቱ ወርቃማ ዘመኑን ለሀገር ብልጽግና ልማት ሊያውለው ይገባል። ትናንት ዳር ድንበር አናስደፍርም ብለው ታሪክ ሰርተው ያለፉ የአባቶቹን ገድል፤ ዛሬ ላይ ወጣቱ በልማቱ ሊደግመው ይገባል። መንግሥትና ባለድርሻ አካላት ወጣቶች በሀገራቸው በነፃነት ሠርተው የሚለወጡበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይኖርባቸዋል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም