ሕዝቡ የሰላሙ ባለቤት ሆኖ ከፍ ባለ ቁርጠኝነት ሊንቀሳቀስ ይገባል!

የሰላም እና የልማት ጥያቄ በየትኛውም ጫፍ ያለው ሕዝባችን የዛሬ ሳይሆን ዘመናት ያስቆጠረ ጥያቄ ነው። ይህንን ጥያቄ ታሳቢ ያደረጉ የለውጥ ንቅናቄዎችም በተለያዩ ወቅቶች ተከናውነዋል። የተፈለገውን ያህል ውጤታማ መሆን ባይችሉም፤ ከሁሉም በላይ የመላው ሕዝባችን ፍላጎት ሰላምና ልማት መሆኑን በተጨባጭ አሳይተዋል።

በርግጥም ኢትዮጵውያን እንደ አንድ ትልቅ ማኅበረሰብ፤ ረጅም ዓመታት የሀገረ መንግሥት ምስረታ ታሪክ እንዳለው ሕዝብ፤ ከዛም በላይ በተለያዩ ወቅቶች ገንነው የወጡ ስልጣኔዎች ባለቤት እንደሆነ ማኅበረሰብ ዛሬ ላይ ካለንበት ማኅበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እውነታ አኳያ ስለ ሰላማቸው እና ልማታቸው አብዝተው ማሰባቸው የሚጠበቅ ነው።

ለዚህም ነው በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች በብዙ ቁጭት ሀገርን እንደ ሀገር ከፍ ሊያደርግ የሚችል አስተሳሰብ ሰንቀው፤ ለተግባራዊነቱ የሚጠበቀውን መስዋዕትነት ለመክፈል ልበ ሙሉ ሆነው በተለያዩ የለውጥ እሳቤዎች መገለጥ የቻሉት፤ ብዙ መስዋዕትነት በመክፈልም ለዓላማቸው ስኬት ያላቸውን ቁርጠኝነት በተጨባጭ በአደባባይ ማሳየት የቻሉትም።

ይህ የትውልዱ ከቁጭት የመነጨ ቅናት የፈጠረው የለውጥ ተነሳሽነት፤ በየወቅቱ በተፈጠሩ የሰላም እጦቶች በብዙ መንገጫገጮች ውስጥ ለማለፍ ተገድዷል ፤መንገጫገጮቹ በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች በብዙ የተመኙትን ከሰላም የሚመነጭ ሀገራዊ ብልጽግና እውን ማድረግ እንዳይቻላቸው አድርገዋል።

ይህ በእያንዳንዷ ሀገራዊ የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ የሚከሰት የሰላም እጦት፤ ዛሬም እንደሀገር ለጀመርነው የለውጥ ጉዞ ዋነኛ ፈተና ከሆነ ውሎ አድሯል። ከቀደሙት ዘመናት ባለፈም ሀገርን እንደ ሀገር የመቆም ስጋት ውስጥ የከተተበት ሁኔታም ባለፉት ሁለት ዓመታት በተጨባጭ ታይቷል። ያስከፈለንም ዋጋ በአንድም ይሁን በሌላ የእያንዳንዱን ዜጋ ጓዳ አንኳኩቷል።

ያለ ሰላም ትውልድ የተሻለ እና ቀና ነገር ማሰብ አይችልም፤ ያለ ሰላም ነገን ተስፋ ማድረግ፤ በተስፋ ህይወትን ማለምለምም አይቻልም። ያለ ሰላም ገብቶ መውጣት፤ አርሶ መብላት እና ነግዶ ማግኘት አይቻልም። ያለ ሰላም ሀገራዊ ብልጽግናን ቀርቶ የተለመደውን የድህነት ሕይወት መኖር አይታሰብም። ያለ ሰላም ስለ ብሔራዊ ጥቅምም ሆነ ስለብሄራዊ ክብር ማሰብ የሚቻል አይደለም።

ይህንን ባለፉት ሦስት ዓመታት እንደ ሀገር ከነበርንበት እውነታ ለመረዳት የሚከብደን፤ አስረጂ የሚያስፈልገን አይደለም። ከፍ ያለው የለውጥ መነቃቃታችን በሰላም እጦት ተቀዛቅዞ በብዙ መስዋዕትነት ከጫንቃችን ያራገፍናቸውን ትናንቶች እስከ ምናፍቀው የደረስንባቸው ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፤ ለትናንቶች የልብ ልብ እስከመሆን ደረስን እራሳችንን ታዝበነዋል።

ይህ ሁሉ የደረሰብን እንደ አንድ ትልቅ ማህበረሰብ የሰላም እጦት በየዘመኑ ምን ያህል ብዙ ዋጋ እንዳስከፈለው፤ ተስፋችንን እንደተናጠቀን በአግባቡ ተረድተን ስለሰላማችን በአንድነት ዘብ መቆም ስላልቻልን ነው። ለዚህ የሚሆን ማኅበረሳባዊ መነቃቃት መፍጠር ባለመቻላችን ነው። ለሰላማችን ከኛ በላይ ዘብ ሊቆም የሚችል አካል እንዳለ አምነን በመዘናጋታችን ነው።

ሀገራዊ ሰላም ከእያንዳንዱ ዜጋ ማንነት የሚቀዳ ነው። ሀገራዊ ሰላም በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ ነፍስ ፣መንፈስ እና አእምሮ ላይ በጻፍናቸው ባህላዊ ፣ መንፈሳዊ /ሃይማኖታዊ እና ምሁራዊ የሰላም እውቀት የሚሰላ ነው ። ለዚህ ደግሞ በዋነኛነት ሰላማዊ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የቤተሰብ እና የማኅበረሰብ፣የሃይማኖት እና የትምህርት ተቋማት ኃላፊነት ከሁሉም በላይ የላቀ ነው።

እንደ ሀገር በዘመናት መካከል ለተፈጠሩ የሰላም እጦቶች የተወሰኑ ግለሰቦች እና ቡድኖች ተጠያቂ የሚሆኑበት እውነታ ሊኖር ቢችልም፣ እውነቱ ግን ከዚህ ባለፈ ስለሰላም ያለንን የተዛባ አመለካከት የሚመለከት ነው። ስለሰላም ያለን እውቀት የምንፈልገውን ሰላም መፍጠር የሚያስችል አቅም ማጣቱ ነው።

ለዚህ ደግሞ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እየፈተነን ያለው የሰላም እጦት የተገዛበት አስተሳሰብ መሰረት ፣ እንደሀገር ከምንፈልገው ሀገራዊ ብልጽግና አኳያ ምን እና ምን ነው ? በሰላም እጦት የከፈልነው እና እየከፈልነው ያለው ዋጋስ ለለውጥ ከተነሳንበት መነቃቃት አኳያ ምን ትርጉም አለው? ይህንን በአግባቡ ማጤን የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ነው።

ዜጎች ከማንም በላይ የሰላማቸው ባለቤት ናቸው። ስለ ዛሬ ይሁን ቀጣይ ሰላማቸው ትውልድ ተሻጋሪ ለሆኑ የሰላም እሴቶች ትኩረት ሰጥተው መሥራትም ይኖርባቸዋል። በእጃቸው ያለው ሰላም ፣ ከየትኛውም አይነት ሰላም ከሚሰጠው ጥፋት የበለጠ የተስፋቸው አልፋ እና ኦሜጋ መሆኑን የሕይወት እውቀት አድርገው ሊወስዱት ይገባል።

አሁን ያለው ትውልድም ሆነ የቀደሙት ትውልዶች በብዙ የሚሹትን ሀገራዊ ብልጽግና እውን ማድረግ የሚቻለው ስለ ሰላም ያለን አመለካከት በተጨባጭ እውቀት ሲቃኝ እና በተረዳነው መጠን ስለ ሰላም ዋጋ ለመክፈል ቁርጠኛ ስንሆን ብቻ ነው።

አሁን ላይ እንደ ሀገር በሁለንተናዊ መልኩ ሰላም በማስፈን የሕዝቡን የልማት ፍላጎት ተጨባጭ ለማድረግ እየተደረገ ያለው ጥረት ተስፋ ሰጪ እየሆነ ነው። በዚህም አብዛኞቹ የግጭት አካባቢዎች ሰላም ሰፍኖባቸዋል። ለዚህ ደግሞ የማኅበረሰቡ አስተዋጽኦ ከፍያለ ነው። ሰላሙን ለዘለቄታው ለማስቀጠልም በተመሳሳይ መልኩ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነ ይታመናል።

በተለይም በወለጋ ዞን ለዓመታት የነበረው የሰላም እጦት የአካባቢውን ሕዝብ ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለ የአደባባይ ምስጢር ነው። ችግሩን በመቀልበስ ሂደትም የአካባቢው ማኅበረሰብ የነበረው አስተዋጽኦም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ሕዝቡ ስለሰላሙ፣ ሰላሙ የሚፈልገውን ያህል መስዋዕትነት ከፍሏል።

ዛሬ ያለበት አንጻራዊ ሰላም ለራሱ ፣ ለልጆቹ እና ለልጅ ልጆቹ የተሻሉ ነገዎችን ለመፍጠር የሚያስችለው ፣ እንደ አንድ ትልቅ ማኅበረሰብ በለውጡ ውስጥ የነበረውን መነቃቃት በመመለስ የራሱን ዕጣ ፈንታ በራሱ እጅ የሚቀረጽበትን ዕድል የሚያጎናጽፈው ነው። የለውጥ ወቅት ህልሙን በእጁ የሚያስጨብጠው ዋነኛ አቅሙም ነው። ከዚህ የተነሳ ሰላሙ ዳግም ከእጁ እንዳይወጣ የሰላሙ ባለቤት ሆኖ ከፍ ባለ ቁርጠኝነት ሊንቀሳቀስ ይገባል!

አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You