በአባቶቻችን የድል በዓሎች ፊት የመቆም የቅስም ልዕልና አለን ?

በአባቶቻችንና በእናቶቻችን መስዋዕትነት የተገኙ ድሎችን ስናከብር፤ እኛ ኢትዮጵያውያን እንደሌሎች ሀገራት የነፃነት ቀን ሳይሆን የድል ቀን ነው የምናከብረው ብለን ስንጎርር አፍራለሁ። ገና ነፃ ወጥተን የምናከብራቸው ደርዘን የነፃነት ቀን በዓላት ስለማኖሩን። በዚህ ጉዳይ ላይ ስለምመለስበት ወደ ገደለው። ድሎቻችንን በቁመታችንና በወርዳችን ልክ አሳንሰን ስንመለከት እሸማቀቃለሁ። የነፃነትን ሳይሆን የድል ቀንን በማክበራችን ስንታበይ ጀግኖች አባቶቻችን ከሰማዕትነታቸው አንድ አፍታ ቀና ብለው ቢያዩን ምን ይሉን ይሆን ብዬ እቆዝማለሁ።

በበኩሌ ድላችን ነፃነታችንና ሉዓላዊነታችን አባቶቻችን ካወጁበት አደባባይ ወይም ፌርማታ እንዳልተንቀሳቀሰ ሳስብ፤ ድሎ የጀግኖች አባቶቻችን ብቻ እንደሆነ ይሰማኛል። እነሱ ባስቀመጡበት ባቆሙበት እንዳለ ነውና። ዛሬም 1888 እና 1933 ዓ.ም እንደቆመ ነው። እንዲሁም ደረቴን ነፍቼ፣ ቀና ብዬ የድሉ ባለቤቱ እንደሆንሁ ማሰብ እንደ ቋጥኝ ይከብደኛል። ያሸማቅቀኛል። የእኔ ትውልድም ሆነ የእኔ አስተዋጽኦ ወይም አበርክቶ የለማ። አዎ ! የዓድዋውም ሆነ የሚያዝያ 27ቱ የድል በዓል ከፌርማታው አልተንቀሳቀሰም።

ዛሬም አባቶቻችንና እናቶቻችን ባቆሙበት ቦታና ጊዜ እንዳለ ነው። እኛ በዓመት አንድ ጊዜ ወደኋላ በታሪክ ሰረገላ እየተመለስን እንሳለመዋለን፣ እንዘክረዋለን እንጂ፤ ወደዛሬ አላመጣነውም። በሀገረ እና በሕዝበ ነገር አልተረጎምነውም። እሴት አልጨመርንበትም። ከውጭ ወራሪ ከቅኝ ግዛት ነፃ ካወጡን አባቶች በኋላ የጨመርነው አንዳች ነገር ወላ ሀንቲ የለም። እንዲያውም በጀግናና በድል ሽሚያ አዋርደናቸዋል። ማቅ አልብሰናቸዋል።

በሀሰተኛ ትርክትና በታሪክ እስረኝነት አባዜ ሀውልታቸውን በማፍረስና ለማፍረስ በመገልገል ያዙኝ ልቀቁኝ በማለት አዋረድናቸዋል። ትርፉ ትዝብት ነው። ከፍታቸው ዘመን፣ ድንበር፣ ዘር፣ ሃይማኖትና የቆዳ ቀለም የተሻገረ ነው። በልካችን ልንቀደውም ልንሰፋውም አይቻለንም። ልናዋርዳቸው አይቻለንም። አባቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ከቅኝ ግዛት ነፃ ቢያወጡንም፤ እኛ ዛሬም በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ በባርነት ቀንበር ስር ነን።

ከጭቆናና ከአፈና ቀንበር፣ ከተመጽዋችነት፣ ከድህነት፣ ከኋላቀርነት፣ ከጥላቻ፣ ከልዩነት፣ ከቂም በቀል፣ ከጦርነት፣ ከሙስና፣ ከብልሹ አሠራር፣ ወዘተረፈ ባርነት ነፃ አልወጣንም። እነዚያ የድል ቀንን ሳይሆን የነፃነት ቀንን ነው የሚያከብሩ ብለን ካናናቅናቸው ሀገራት በታች ነን። ትላንት ነፃ ከወጡት ከእነ ደቡብ አፍሪካ፣ ቦትስዋና፣ ናይጄሪያ፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ሞሮኮ፣ ወዘተረፈ በታች ነን። ለዚህ ነው ድሎቻችንን ከፌርማታቸው አላቀሳቅስናቸውም የምለው።

ከቅኝ ግዛት እንጂ ከሌላ ሌላው ባርነት ገና ነፃ አልወጣንም። ነፃነታችን ሙሉኡ አይደለም። እየተመጸወትን ሉዓላዊነታችንና ነፃነታችን ተከብሯል ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር አንችልም። የድል ቀን በዓልን እንጂ የነፃነት ቀንን አናከብርም ብለን ብንኩራራም ሀቁ ይሄ ነው። የድል ቀንን ማክበር በራሱ ግብ አይደለም። ደርዘን ነፃነቶችን ማለትም ከድህነት፣ ከተረጂነት፣ ከድንቁርና፣ ወዘተረፈ ነፃ ወጥተን የድል በዓላትን ካላጀብናቸው፤ በድል በዓሎቻችን ፊት የመቆም የቅስም ወይም የሞራል ልዕልና የለንም። እስኪ እናንተም ተወያዩበት፣ ተከራከሩበት። ለመንደርደሪያ ያህል ይህን ካልሁ ለዛሬው መጣጥፌ መነሻ ወደሆነኝ የሚያዝያ 27 የአርበኞች ቀን ወይም የድል በዓል ላምራ።

ኢትዮጵያ በወራሪው የፋሺስት ጣሊያን ሠራዊት ላይ ድል የተቀዳጀችበት 83ኛ ዓመት እሁድ ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አራት ኪሎ በሚገኘው የሚያዝያ 27 ቀን አደባባይና የድል ሐውልት ሥር ተከብሯል። የድል ቀኑ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባላት፣ የተለያዩ ሀገሮች ኤምባሲዎች ሚሊቴሪ አታሼዎችና የከተማው ነዋሪዎች በተገኙበት ተከብሯል።

ከሰማንያ ሦስት ዓመት በፊት የተገኘው የሚያዝያ 27ቱ ድል ለመላው ለአፍሪካ አህጉር ነፃ አወጣጥ መንገድ ጠራጊ መሆኑንም ‹‹ትንሣኤና ሕይወት ሚያዝያ ፳፯ት›› እንዲህ ያመሳጥራል። ለኢትዮጵያ ድጋፍ በሰጠችው የእንግሊዝ ጦር ሠራዊት ውስጥ ከቅኝ ግዛቶቿ የአፍሪካ ሀገሮች የተካተቱት አፍሪካውያን ወታደሮች ኅሊና ውስጥ ‹‹እኛም ነፃ መውጣት አለብን!›› የሚለው መነሳሳት የታየው በሚያዝያው የኢትዮጵያ ድልና ስኬት መሆኑም ያወሳል።

እንደ ታሪካዊው ድርሳን አዘጋገብ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ከ1928 ዓ.ም. ከሚያዝያ 27 ቀን (አዲስ አበባ በፋሺስት ኢጣሊያ የተያዘችበት) እስከ 1933 ሚያዝያ 27 ቀን (አዲስ አበባ በድል የተያዘችበት) ድረስ የጠላት ኰቴ በመስኮቿ ላይ ቢረግጥም ገዢነቱን አላወቀችለትም። ጫካው ሁሉ የጃርት ወስፌ ስለሆነበትና ሜዳውም ቢሆን አቃቅማ ብቻ ሆኖ ስላስቸገረው ምን ያህል ጭንቀት እንዳደረበት አምስት ዓመት ያልሞላው የስቃዩ ዘመን ምስክር ነው።››

ፋሺስት ኢጣሊያ በመስከረም 1928 ዓ.ም. በወልወል በኩል የጀመረችው ወረራ አጠናክራ ለአምስት ዓመታት ሀገሪቱ በወረራ ከያዘችበት በኢትዮጵያውያን ተጋድሎና እርመኛ አርበኝነት በድል የተጠናቀቀበት መሆኑ ነበር። የወቅቱ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (1923-1967) በስደትና በዲፕሎማሲያዊ ትግል ከቆዩበት የእንግሊዟ ባዝ ከተማ በሱዳን በኩል በምዕራብ ኢትዮጵያ ኦሜድላ ላይ ጥር 12 ቀን 1933 ዓ.ም. የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ያውለበለቡበት፣ ከወራት ቆይታ በኋላም ከአርበኞች ጋር የዘለቁበትና በዕለተ ቀኑ ሚያዝያ 27 አዲስ አበባ የደረሱበት ነበር።

የፋሽስቶች ወረራና ለጊዜውም ቢሆን ኢትዮጵያን መያዛቸው፣ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተጀመረው በአውሮፓ ውስጥ ነው ከሚለው አተያይ በተቃራኒው፣ በአፍሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ መስከረም 22 ቀን 1928 ዓ.ም. በተፈጸመው ወረራ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመሩን የሚሞግቱ ምሁራን (ፕሮፌሰሮቹ ንጉሤ አየለ፣ ዓለሜ እሸቴ፣ ሪቻርድ ፓንክረስት) አሉ። እንዲያውም የአፍሪካ ቀንድ ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም. የዘለቀ የጦርነት ጎራ ሆኖ መዝለቁም ታውቆለታል። ከድል ሐውልት ማዕቀፍ ውስጥ በተናጠል ኪነ ቅርፆች ላይ ከተጻፉት መታሰቢያዎች መካከል ቀዳሚው፣ ለሀገራቸው ነፃነት አምስት ዓመት ሙሉ በዱር በገደል እየተንከራተቱ ደማቸውን ላፈሰሱና አጽማቸውን ለከሰከሱ ለስመ ጥሩ አርበኞች የቆመ የዘላለም መታሰቢያ ነው።

ሌሎቹ አምስት ዓመት ሙሉ በጠላት የጭቆና ቀንበር ውስጥ ተቀምጠው የሞት ጥላ በራሳቸው ላይ እያንዣበበ ሃሳባቸውን ከአርበኞችና ከስደተኞች ሳይለቁ ሀገራቸውን በስውር ላገለገሉ የውስጥ አርበኞች የቆመ መታሰቢያ። ያለ ሀገር ክብርና ነፃነት አለመኖሩን ተረድተውት የጠላት መሣሪያ ከመሆን መከራና ስደትን መርጠው አምስት ዓመት ሙሉ ተስፋ ባለመቁረጥ ሲንገላቱና ሲንከራተቱ ለኖሩ ስደተኞች የቆመ መታሰቢያ የሚሉ ናቸው። አፍሪካዊ አውሮፓዊን ድል ለማድረግ የቻለበት ከዓድዋው ድል ቀጥሎ ሁለተኛው የድል ቀን ሚያዝያ 27 መሆኑ በአፍሪካውያንም ሆነ በሌላው ዓለም እንደሚታወቅ ይወሳል።

ከስድስት አስርታት በፊት፣ በታተመ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የታሪክ ድርሳን ላይ እንደተመለከተው፣ በነገሥታቱ መሪነት ኢትዮጵያን የድል አክሊል እንደተቀዳጀች እንድትኖር ያደረጓት ሕይወታቸውን ስለሰውላትና የማትናድ ሕንፃና የማትፈርስ ግንብ አድርገው ስለገነቧት ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ምርምር በማድረግ ብዙ ድርሳናት የጻፉት የቴልአቪቭ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የታሪክ ምሁሩ ሀጋይ ኤርሊህ (ፕሮፌሰር) እንደጻፉት፣ የአርበኞች ድል በዘመኑ የነበሩ የዓለም ኃያላን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ተቀብለው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች አባል እንድትሆን አድርጓል።

በጦርነቱ መባቻ በፋሽስት መሪ ሙሶሎኒ ትዕዛዝ ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም. የጣሊያን ጦር በወረራ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን፣ ከአምስት ዓመታት በኋላ በአርበኞች ትግል በተገኘው ድል በዚሁ ቀን ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ተመልሰው አዲስ አበባ በመግባታቸው በዓሉ ለኢትዮጵያ ሁለተኛ የድል በዓል ሆኗል። የጣሊያን ጦር ዓድዋ ላይ በኢትዮጵያ ጀግኖች ከተሸነፈ ከአርባ ዓመታት በኋላ እንደገና ለበቀል ሲመጣ በተደራጀ የጦር መሣሪያ በአየር ኃይል መርዛማ ኬሚካል በመጠቀም ንፁሃን ዜጎችን ቢፈጅም፣ የኢትዮጵያ አርበኞች ለወራሪው ኃይል ሳይበገሩ ለአምስት ዓመታት ታግለው ማሸነፋቸው ይወሳል።

እንደ ሀጋይ ኤርሊህ ማብራሪያ፣ በወረራው መጀመሪያ ንጉሠ ነገሥቱ ከጣሊያን ጋር ውጊያ መግጠማቸው፣ ፍልሚያው እየተጠናከረ ሲሄድ ጣሊያን በናፓል የመርዝ ጋዝ ሕዝቡን ፈጅቷል። አፄ ኃይለ ሥላሴ ወደ መንግሥታቱ ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) መሄዳቸውን፣ አርበኞቹ ውስጥ ለውስጥ እየተገናኙ በዱር በገደሉ የሽምቅ ጦርነት ከፍተው የትጥቅ ትግላቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን፣ ከአምስት ዓመታት ፍልሚያ በኋላ ለድል መብቃታቸውን ጠቅሰዋል ይለናል የአማርኛው ሪፖርተር ጋዜጣ።

በዘንድሮው የድል በዓል አከባበር ላይ፤ በቀደምት አርበኞቻችን ለተፈጸሙ ታላላቅ የድል ታሪኮች የአሁኑ ትውልድ ተገቢውን እውቅናና ክብር መስጠት ይኖርበታል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ። 83ኛው የአርበኞች የድል በዓል “በሀገር ፍቅር አርበኝነት የተገኘ ድል” በሚል መሪ ሃሳብ በአራት ኪሎ የድል ሐውልት በተለያዩ ሁነቶች ባለፈው እሁድ ተከብሯል ይለናል “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ በዘገባው። የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በቀደምት እናትና አባት አርበኞቻችን ለተፈጸሙ ታላላቅ ጀብድና የድል ታሪኮች የአሁኑ ትውልድ ተገቢውን እውቅናና ክብር መስጠት ይኖርበታል።

ጥንታዊ አርበኞች በዱር በገደል ፋሽስቱን ተዋግተው በሕይወት መስዋዕትነት የሀገራችንን ሉዓላዊነት አስከብረዋል ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ አርበኞች ደማቸውን አፍሰው አጥንታቸውን ከሰክሰው ያስገኙት ድል በመሆኑ መጪው ትውልድ ታሪኩን በልኩ እንዲያውቅ ማድረግ ይገባል። አርበኞች በአንድነትና በሀገር ፍቅር ስሜት ወራሪው ኃይል ዳግም በውርደት እንዲመለስ በማድረጋቸው ውለታን የምናውቅ፣ የምናከብርና የምንዘከር ሰዎች በመሆን ድሉን ሕያው ማድረግ ያስፈልጋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ እንዳመለከቱት፤ የድል ታሪኩ ይበልጥ የሚጎላው ሕዝቡ የጋራ ታሪኩን በሚገባው ልክ ሲያውቅ፣ ሲስማማበትና ለታሪክ ተመራማሪዎች እንዲሁም ባለሙያዎች ተገቢው እውቅና ሲሰጥ ነው። ታሪክን ከማክበር ባለፈ የሁሉ መሠረት የሆነውን ሰላም መገንባት መንከባከብና ሰላምን ሊያሳጡ የሚችሉ ነገሮች ሲታዩ ለመፍታት መረባረብ ሁሉም ሊተገብረው የሚገባ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል። ሰላም መተኪያ የሌለው ካመለጠ ደግሞ ለመመለስ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ ሁላችን ለሰላም መፈጠር መሥራት ይጠበቃል።

በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ የሰላም እጦቶች እንቅልፍ ሊነሱን ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንቷ ፤ ለሀገርና ለሕዝቦች ሰላም ሁሉም አካል ቅድሚያ መስጠት። የድል ታሪኩን ስናስብ ኢትዮጵያ የጦርነት ታሪክ የሚነገርባት ሀገር ብቻ ሳትሆን ሊወር የመጣን ጠላት በድል የምናሸንፍበትና እድገታችንን የምናፋጥንበት ሊሆን ይገባል ብለዋል። የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በበኩላቸው፤ የድል በዓሉን ስናስብ በሀገር ፍቅር መስዋዕትነት የተገነባውን ሰላምና ነፃነት በመንከባከብ መሆን አለበት ሲሉ ተናግረዋል። ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ እንዲሉ አበው እማው የጣሊያንን ነገረ ወረራ በወፍ በረር እንቃኝ።

በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት ስምምነት ላይ የደረሱበት ወቅት ነበር። በዚህ ወቅትም ጣሊያኖች ሀገራቸውን ወደ ጥንቱ የሮማ አገዛዝ ለመመለስ ተነሱ። ኢጣሊያ ህልሟን ለማሳካት የተሻለ እና ምቹ ኾኖ ያገኘችው ደግሞ ከቀይ ባሕር – ሕንድ ውቅያኖስ እስከ ዛንዚባር ድረስ ያለው አካባቢ ነው። በአያቶቻቸው ያልተሳካውን ኢትዮጵያን የማስገበር ሕልም ለማሳካት በሃይማኖት ሰበብ በአባ ጁሴፔ ሳፔቴ አማካይነት ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ከአሰብ ባላባቶች ጋር ተወዳጁ። በ1862 ዓ.ም ከባላባቶቹ “ለማረፊያ” በሚል መሬት በመግዛት “ሩባቲኖ” የሚባል የኢጣሊያ የመርከብ ኩባንያ ወደብ እንዲመሠርት አደረጉ። በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉስ የነበሩት አፄ ተክለጊዮርጊስ ከአፄ ቴዎድሮስ ያልተረጋጋች ሀገር ተረክበው ስለነበር ጉዳዩን ያሰቡበት አይመስልም።

ኩባንያው አሰብን ለ12 ዓመታት ከተጠቀመበት በኋላ በ1874 ዓ.ም (በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት) ለኢጣሊያ መንግሥት ሸጠው። በዚሁ ዓመት የኢጣሊያ መንግሥት አሰብ የኢጣሊያ ግዛት መኾኑን በአዋጅ አሳወቀ። ከዚህም ባለፈ በምጽዋ ጦር በማስፈር ወደ መሃል ሀገር መስፋፋቱን ቀጠለ። በሁለቱ ሀገራት መካከል መካረሩ እየጠነከረ ሂዶ ዶጋሌ ላይ ድል ተመቱ። በ1888 የሀገሪቱን ድንበር ጥሶ በድጋሚ ወረራ ፈጸመ። ኢትዮጵያውያንም በጀግንነት በመፋለም በድል አጠናቀቁ። ድሉ ከኢጣሊያ መንግሥት ባለፈ የአውሮፓ መንግሥታትን ጭምር ጭንቀት ውስጥ ከተተ። ሽንፈቱ የነጭ ሽንፈት እንደኾነ ተገነዘቡ።

ድሉን ተከትሎ “ኢትዮጵያ የግዛት ማስፋፋት ልታስብ ትችላለች” በሚል የብዙ ቅኝ ገዥ ሀገራትን ትኩረት መሳብ ቻለ። በሰሜን እና በደቡብ ምስራቅ ጣሊያን፣ በደቡብ ምዕራብ እንግሊዝ እንዲሁም በምስራቅ ፈረንሳይ ከበባ ማድረጉን ቀጠሉ። በተለይም ደግሞ ጣሊያን በዓድዋ የገጠማትን የሽንፈትን ቁስል በድል ለመሻር ሀገሪቱን ለመምራት ወደ ስልጣን የመጡት ሁሉ እንቅልፍ ነሳቸው። በ1922 ወደ ስልጣን የመጣው ፋሽስቱ ሞሶሎኒ እረፍት አልነበረውም።

በ1927 ዓ.ም ኢጣሊያ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1908 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገውን የወሰን ስምምነት በማፍረስ 96 ኪሎ ሜትር የኢትዮጵያ ግዛት ላይ በሚገኘው ዋርዴር እና ወልወል ላይ ጦሯን አሰፈረች። ሳትውል ሳታድር በአካባቢው በነበረው በኢትዮጵያ ጦር ላይ ጦርነት ከፈተች። ከዚህም ባለፈ የጣሊያን ጦር መስከረም/1928 የመረብን ወንዝ ተሻግሮ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ጭምር ወረራ ፈጸመ። የኢትዮጵያውያን አርበኞች ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የጣሊያን ጦር እረፍት አሳጡት።

ትግሉ ከአምስት ዓመታት ቆይታ በኋላ የኢትዮጵያ አርበኞች በከፈሉት መስዋዕትነት በድጋሚ ድል ማድረግ ተችሏል። ቀኑ የኢትዮጵያ አርበኞች በአንድነት በፋሽስቱ ጣሊያን ዳግም ወረራ ወቅት የከፈሉትን መስዋዕትነት እና ያስገኙትን ድል ለማሰብ በየዓመቱ ሚያዝያ 27 ቀን ይከበራል። ለዛሬው የኢጣሊያንን ተደጋጋሚ ወረራ አነሳን እንጂ ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ቱርኮች፣ ግብጾች፣ ማህዲስቶች፣ በጎረቤቶቿ ጭምር የተቃጣባትን ትንኮሶ በተባበረ የኢትዮጵያውያን ክንድ ድል በማድረግ ነፃነቷን ያስጠበቀች ቀደምት ሀገር ያደርጋታል ይለናል አሚኮ።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You