“የባሕር በር ጉዳይ አሁን ባለው ትውልድ መቋጨት ያለበት ትልቅ የቤት ሥራ ነው” – ዳርእስከዳር ታዬ (ዶ/ር) በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ጀኔራል

አዲስ አበባ፡- የባሕር በር ጉዳይ አሁን ካለው ትውልድ የማያልፍ የቤት ሥራ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል ዳርእስከዳር ታዬ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ ከሱማሌላንድ ጋር የተደረገው ስምምነት ለሌሎች ሀገራት ተነሳሽነት መፍጠር እንደተቻለም ጠቁመዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል ዳርእስከዳር ታዬ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ከሱማሌላንድ ጋር የተደረገው ስምምነት ለሀገር ጥቅም ሲባል የተፈረመ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያለባትን ስር የሰደደ የባሕር በር የማጣት ችግር ለመቅረፍ የተደረገ ጥረት ነው። ጉዳዩ በዚህ ትውልድ ተዘግቶ ኢትዮጵያ የባሕር በር አግኝታ መጠቀም መጀመር ይኖርባታል።

እንደ ዳይሬክተር ጀኔራሉ ገለጻ፤ በአሁን ወቅት ጥገኝነት የፈጠራቸው የደኅንነትና የኢኮኖሚ ጫናዎች አሉ። በዚህ ምክንያት የመልክዓ ምድራዊ እስረኝነቱ መሰበር አለበት። ይህንን ለመስበር ደግሞ ኢትዮጵያ አማራጮችን በመፈለግ የባሕር በር የምታገኝበት የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ከሶማሌላንድ ጋር ተፈራርማለች።

የባሕር በር ጉዳይ አሁን ካለው ትውልድ የማያልፍ የቤት ሥራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ጀኔራሉ፤ ጉዳዩ በዚህ ትውልድ ተዘግቶ ኢትዮጵያ የባሕር በር አግኝታ መጠቀም እንዳለባት ጠቅሰዋል።

እንደ ዳርእስከዳር (ዶ/ር) ገለፃ፤ በምድር ላይ በየትኛውም ውሳኔ ለበጎ ነገር እንቅስቃሴ ሲኖር ተያይዘው የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ይኖራሉ። አሁንም ተግዳሮቶች ቢኖርም ሥራው ግን ይቀጥላል። የባሕር በር የማግኘቱ እንቅስቃሴ መንግሥት በጀመረው መንገድ ያስኬደዋል። “አንድ ሀገር ላይ ብቻ ጥገኛ መሆን የገበያ ዋጋውን ከፍ ሊያደርገው ይችላል። አማራጭ ሲኖር ግን ዋጋውም ይቀንሳል” በማለት ይህ ለኢትዮጵያ አማራጭ የሆነ አጋጣሚንም እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

ዳይሬክተር ጀኔራሉ እንዳሉት፤ ከሱማሌላንድ ጋር የሚደረገው ስምምነት ሌሎች ከደኅንነት ጋር የተያያዙ ፍላጎቶችንም ታሳቢ ያደረገ ነው። ይህ ሲሆን ከሱማሌላንድ ጋር እስካሁን ካለው የተሻለ ትስስር ይፈጥራል። በሚዘረጉት አዳዲስ መሠረተ ልማቶች የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩ እየጨመረ ይሄዳል።

ስምምነቱ ተግባራዊ ሲደረግ ሱማሌላንድ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቷም ይጨምራል ያሉት ዳይሬክተር ጄኔራሉ፤ ሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ የማድረግ ዕድል እንደሚፈጠርላቸውም ጠቁመዋል። ከአገልግሎት አንጻር ወደቡን መጠቀሙ በራሱ ሽያጭ በመሆኑ መስተጋብሩ የበለጠ ይሰፋል ሲሉም አብራርተዋል።

ስምምነቱ ከሱማሌላንድ ጋር መደረጉ እንደ ፈተና እየተነሳ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ ከሱማሊያ በኩል እየተሰማ ያለው ነገር ኢትዮጵያ ራሷን በምትገልጽበት መንገድ ካለማየት የተነሳ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የምትፈልገው የባሕር በር ማግኘት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ለደኅንነቷ አስፈላጊ የሆነ ወታደራዊ ቤዝ በመገንባት በአካባቢው ላይ ትርጉም ያለውን ሚና መጫወት ያስችላታል ሲሉ ተናግረዋል።

“ሱማሊያ እንደማንኛውም ሉዓላዊት ሀገር ስጋት ሊገባት ይችላል። መረሳት የሌለበት ግን ለሱማሌላንድ እውቅና ተሰጠም አልተሰጠም ሱማሌላንድ የሱማሊያ አካል ሳትሆን እየቀጠለች ነው” ብለዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ሱማሌላንድን መሠረት እየሠራች ቢሆንም ሌሎች አማራጮችንም ለመጠቀም ጥረቱ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

እርሳቸው እንዳሉት፤ ሱማሌላንድ አይን ገላጭ ሆነች እንጂ እንደ ጅቡቲ፣ ፑንትላንድና ኬኒያም ያሉት በተሻለ ስትራቴጂክ ጉዳዮች እንወያይ የሚል ነገር አላቸው።

ይህም ስምምነቱ ለሌሎች ሀገራት ተነሳሽነት መፍጠሩን ያሳያል ብለውም፤ በዚህም የባሕር በር ጉዳይ የሚቆም ሳይሆን ሌሎች አማራጮችም እየታዩ የሚቀጥል እንደሆነ ተናግረዋል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You