‹‹49ሺህ ለሚሆኑ ከስደት ተመላሾች በሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል›› – አቶ ደረጀ ተግይበሉ-ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከልና የተመላሽ ዜጎች ድጋፍና ክትትል መሪ ሥራ አስፈጻሚ

ሰዎች የመኖሪያ አካባቢያቸውን ቀይረው ኑሮአቸውን በሌላ አካባቢ የሚያደርጉት፣ ሀገራቸውንም ለቀው ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገር የሚሰደዱት በአብዛኛው የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ነው፡፡ የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመለከተው በተለይም ወደመካከለኛው ምሥራቅ ሀገሮች የሚሄዱ በቤት ሠራተኝነት ጭምር የሚሄዱ ዜጎች ዋነኛ ዓላማቸው ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን በኢኮኖሚ ለማገዝ በማለም ነው፡፡

ሆኖም ወደመካከለኛው ምሥራቅ የሚሄዱ ዜጎች የአብዛኞቹ የጉዞ ሰነድ ታሪክ የሚያሳየው ከመነሻ እስከ መድረሻቸው ድረስ ያለው ጉዞ ሕጋዊነትን የተከተለ አይደለም፡፡ ሕጋዊ ሆነው እንዲሄዱ በመንግሥት በኩል ምቹ ሁኔታዎች ቢኖሩም ሕጋዊ የመሆን ፍቃደኝነት በብዙዎች ዘንድ አለመኖሩ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ተቋማት ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡

በሚያደርጉት ሕገወጥ ጉዞ ምክንያትም በበረሃ ላይ መቅረት፣ በባህር ውስጥ መስመጥ፣ ላላስፈላጊ የገንዘብ ወጪ መዳረግ፣ ለአካላዊና ሥነልቦናዊ ጥቃት መጋለጥ እንዲሁም ለአስገድዶ መደፈር ሰለባ እና ለመሳሰሉት ችግሮች ይዳረጋሉ፡፡

ከሰሞኑ በተሰማው መረጃ እንኳን በጀልባ መስመጥ ሕይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ እውነታዎች እየታዩ እንኳን ሰዎች ሕገወጥ ስደትን መምረጣቸው የሚያስገርም ነው፡፡

በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፈው በለስ ቀንቷቸው ለሥራ የሚሄዱባቸው ሀገሮች ቢደርሱ እንኳን ለተለያዩ የሠብዓዊ መብት ጥሰቶች መዳረጋቸው አይቀርም፡፡ መብታቸውን እንኳን ለማስከበር ሕገወጥ መሆናቸው እንቅፋት ሆኖባቸው ለከፋ ችግር እንደሚዳረጉ በተለያየ ጊዜ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እጅግ ዘግናኝና አሰቃቀቂ የሆኑ ድርጊቶች ቢፈጸምባቸውም ሕጋዊ መፍትሄ ለማግኘት ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለም፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ወደ ሀገራቸው የሚመለሱ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣት የመብት ጥሰቱ መበራከት አንዱ ማሳያ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ ይህ ሁሉ እያለ ግን አሁንም ሕገወጥ ስደት አልቆመም፡፡

ዜጎች ሕጋዊ መንገደዱ እያለ ለምን ሕገወጥ ስደትን ይመርጣሉ የሚለው አሁንም መልስ የሚያሻው ጥያቄ ነው፡፡ በተለይም ሞትን ጨምሮ በርካታ አሰቃቂ ተግባራት እየደረሰባቸውም ቢሆን ዜጎች ከጉዞ ጀምሮ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለማለፍ ለምን መረጡ? በአሰሪዎች የሚደርሰውን ስቃይና በደል ከተበዳዮች አንደበት እየሰሙ ለምን ትምህርት ሊወስዱበት አልቻሉም? መንግሥትስ ከዚህ አስከፊ ነገር ዜጎችን ለመታደግ ምን ሠራ? የሚለው የብዙ ሰዎች ጥያቄ ነው፡፡

እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን ይዘን ጉዳዩ በዋነኝነት ወደሚመለከተው ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አቅንተናል፡፡ በሚኒስቴሩ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከልና የተመላሽ ዜጎች ድጋፍና ክትትል መሪ ሥራ አስፈጻሚ ከአቶ ደረጀ ተግይበሉ ጋርም ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪትን በተመለከተ ያለውን የሕግ ጽንሰ ሃሳብ ቢያብራሩልን?

አቶ ደረጀ፡- የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት በሕግ የተደገፈ አሠራሮችን የሚከተል ሲሆን፤ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪትን የሚመለከት አዋጅም አለው:: በአዋጁ ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ነው:: ሥራ የሚለው በራሱ ከሥራና ክህሎት ጋር ይያያዛል:: የሥራ ዕድሎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚፈጠሩ ናቸው:: በተለይም የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪቱ መደበኛ የሆነ ፍልሰትን የሚከተል ነው::

ዜጎች ሥራውን በግላቸውም የሚያመጡት ሊሆን ይችላል:: በሌሎችም በሚገኝ የሥራ ዕድል፣ ወይንም መንግሥት ከሀገራት ጋር በሚኖረው ግንኙነት በሚመቻች ዜጎች በውጭ ሀገር ሄደው ለመሥራት ፍላጎት ሲኖራቸው ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሠራር ነው ያለው:: ዜጎች ውጭ ሀገር ሄደው ለመሥራት የሚያስችላቸው መስፈርቶች በመኖራቸው መስፈርቶቹን አሟልተው ሲገኙ የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ::

በተለይ ደግሞ ወደ ተለያዩ የአረብ ሀገራት የሥራ ዕድል አግኝተው የሚሄዱ ዜጎች ለጉዞ ዝግጅት ከማድረጋቸው በፊት መሠልጠን ይጠበቅባቸዋል:: ቀደም ሲል የነበሩ አንዳንድ መስፈርቶች ላይም ማሻሻያ ተደርጓል:: ቀደም ሲል ወደ አረብ ሀገራት ለመሄድ አንዱ መስፈርት ስምንተኛ ክፍል ማጠናቀቅ የሚል ነበር:: አሁን ላይ አስፈላጊ ሆኖ ባለመገኘቱ መስፈርቱ ቀርቷል:: ከትምህርት ደረጃ ይልቅ የሚሰጠውን ሥልጠና ተከታትለው፣ አልፈው ወደ ሥራ የሚሄዱበት ሁኔታ ነው የተመቻቸው::

በመደበኛው አሠራር መሠረት፤ ግለሰቡ ለተቀጠረበት የሥራ ዘርፍ ብቁ ሆኖ ነው መሄድ የሚጠበቅበት:: ለእያንዳንዱ የሥራ ዘርፍ የተቀመጡ መሥፈርቶችን ማሟላት ይጠበቃል ማለት ነው:: ሕጋዊው መሥመርም በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በኩል ነው የሚፈፀመው:: መንግሥት ለሥራ ወደ ውጭ ለሚሄዱ ዜጎች ለሚሰጠው አገልግሎትም የሚጠይቀው ክፍያ የለም::

ዜጎችን ለማነሳሳት ሆን ብለው የተዘጋጁ አንዳንድ ሕገወጥ ኤጀንሲዎች በመኖራቸው በነዚህ የሚጭበረበሩ መኖራቸውን መዘንጋት የለበትም:: ከእነዚህ በተጨማሪም በደላሎችም ይጭበረበራሉ::

እነዚህ አካላት ከፍተኛ ገንዘብ በመጠየቅ ተጓዦች ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራሉ:: ገንዘቡንም የሚጠይቁት ሩቅ ሳይሄዱ እዛው ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ደጃፍ ላይ ነው:: ብዙ ገንዘብ ከፍለው የሀሰት ሰነድ እየሰጧቸው ብዙዎች ሲያለቅሱ እናያለን::

ስለዚህም ማንኛውም ወደ ውጭ ለመሄድ የሚፈልግ ዜጋ እራሱን ከእነዚህ ሕገወጥ ደላሎች መጠበቅ አለበት::

አሁን ባለው አሠራር፤ ቀደም ሲል በፌዴራል መሥሪያቤቶች ብቻ ይፈጸሙ የነበሩ አሠራሮች ቀርተው አገልግሎቱ በክልሎችም የሚፈጸምበት አሠራር ተፈጥሯል:: በጣም ጥቂት ካልሆነ በስተቀር ጉዳያቸው በያሉበት አካባቢ ያልቅላቸዋል:: ስለዚህም ወደ ሕገወጥ ደላላ የሚያስኬዳቸው ነገር የለም::

አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ዜጎች ጉዞአቸውን ሕጋዊ ሆነው መፈጸም እየቻሉ ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተውና ተንገላትተው ሕገወጥ ሆነው ለመጓዝ የሚመርጡት ለምንድነው? በመንግሥት በኩል ያልተሠራ ሥራ ይኖር ይሆን?

አቶ ደረጀ፡- ሕጋዊ ሆነው መሄዳቸው ጥቅሙ ሰፊ ነው:: ለጉዞ ከሚያወጡት ወጪ ጀምሮ ባለው ሂደት ውስጥ የሚገጥማቸው ችግር አይኖርም:: ቅጥር ፈጽመው ለመሄድ ሲዘጋጁም ደመወዛቸውንና ሌሎች ጥቅማጥቅሞቻቸውን ቀድመው ያውቃሉ:: ውልም ይገባሉ:: የሠሩበትንም የሚከለክላቸው አካል አይኖርም:: አሠሪያቸው ቢከለክላቸው እንኳን ከመሄዳቸው በፊት ዋስትና የገባላቸው አካል ወይንም ኤጀንሲ ስላለ ከዋስትናው ላይ ሊከፍል ይገደዳል:: የማስፈጸም ኃላፊነትም አለበት::

ሠራተኛው የመብት ጥሰት ቢደርስበት መከላከልም ሆነ፣ ጥብቅና መቆም የሚቻለው በሕጋዊ መንገድ መሄድ ሲቻል ነው:: በውላቸው ላይ ግዴታቸውና መብቶቻቸው በመቀመጣቸው፤ በሕግ ማስፈጸም ይቻላል:: የሚመከረውም ሕጋዊ መንገድን ተከትለው እንዲሄዱ ነው::

ዜጎች እነዚህን ሁሉ ጥቅማጥቅም የሚያስገኝላቸውን ሕግ ትተው በሕገወጥ ለመሄድ ጥረት የሚያደርጉት በተለያዩ ምክንያቶች ነው:: አንዱ ከግንዛቤ እጥረት ነው:: ምክንያቱም ቀድመው የሚያገኟቸው በሕገወጥ ተግባር ላይ የተሠማሩትን በመሆኑ ሕጋዊ መንገድ መኖሩን አያውቁም:: በዚህ ችግር ውስጥ የሚወድቁት በአብዛኛው በሀገሪቱ በገጠር የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው:: የመገናኛ ብዙሃን ተደራሽነትና የመረጃ ክፍተት መኖር ያመጣው ችግር እንደሆነ ይታሰባል::

በችግር ውስጥ አልፈው ተሳክቶላቸው ሠርተው ለቤተሰብ አንዳንድ ነገር ማድረግ የቻሉትን እንደ ናሙና በማየት ለመሄድ መነሳሳት ሌላው ገፊ ምክንያት ነው:: ከአቻ ግፊት በተጨማሪ ልጆቻቸው እንዲሄዱ የሚያነሳሱ ቤተሰቦችም አሉ:: ደላሎችም የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ከፍተኛ ሚና አላቸው:: ደላሎች ተአማኒ መስሎ ለመታየት ከሚጠቀሟቸው ዘዴዎች ሕጋዊው አካሄድ ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ እየዋሹ የማሳመን ሥራ ይሠራሉ::

ነገር ግን ሰዎች ያልተገነዘቡት ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች የቅብብሎሽ ሥራ ስለሚሠሩ ችግሩም በዚያው ልክ የሰፋ ነው:: በሕገወጥ መንገድ መሄድ እያስከተለ ያለው ችግር የብዙዎችን ቤት አንኳኩቷል:: ምንም እንኳን ግንዛቤ መፍጠር ላይ ሰፊ ሥራ መሥራት ቢያስፍልግም በተጨባጭ እየታየ ያለው ችግር ብቻውን አስተማሪ ይመስለኛል::

የኢትዮጵያ ድንበር ሰፊ ነው:: በየድንበሩ ሰዎች አቋርጠው ለመሄድ ይሞክራሉ::በድንበር አካባቢ ላይም ግንዛቤ ለመፍጠር ጥረት ሲደረግ በፍጹም ሃሳባቸውን ለመቀየር ፈቃደኛ አይሆኑም:: የሞት አደጋ እንኳን

ለመቀበል ዝግጁ ነው የሚሆኑት:: አንዴ ድንበር ላይ ከደረሱ ወደኋላ አይሉም:: ይሄንን በቦታው ተገኝተን ያየነውና የሞከርነው ነው:: ይሄ ሁኔታ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ምን ያህል አእምሮአቸውን እንደለወጧቸው የሚያሳይ ነው::

በዚህ አይነት ጉዞ ውስጥ እድሜያቸው 14 የሆኑ ታዳጊዎች ይገኙበታል:: በትምህርታቸው ስምንተኛ ክፍል ከደረሱ በኋላ ህልማቸው ሁሉ ስደት ነው:: የወደፊት እቅዳቸውን ሲጠየቁ እንኳን ምላሻቸው አረብ ሀገር መሄድ የሚል ነው:: የተሳሳተ አመለካከት የብዙ ወጣቶችን አስተሳሰብ መርዟል ማለት ይቻላል::

ሁሉም ሰው መገንዘብ ያለበት ግን በምንም አይነት መመዘኛ መደበኛ የሆነና መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት አንድ አይነት ይዘት የላቸውም:: የጅቡቲ ኤምባሲ በቅርቡ በሰጠው መረጃ 38 ሰዎች በጀልባ በመስመጥ ሕይወታቸውን አጥተዋል:: ይሄን ለአብነት አነሳሁት እንጂ በጀልባ ለማቋረጥ ሲሞክሩ ሰምጠው ሕይወታቸው ያለፈ ዜጎች ጥቂት የሚባል አይደለም::

ችግሩን አልፈው አቋርጠው የሚፈልጉበት ሀገር ከደረሱ በኋላም ቢሆን በጥይት የሚመቱና ሌላም ችግር ደርሶባቸው ሕይወታቸውን የሚያጡ መኖራቸው በተለያየ ጊዜ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ::

በሕገወጥ መንገድ ለመሸጋገር ጅቡቲ ውስጥ ተይዘው ያገኘናቸው ዜጎች ቤተሰቦቻቸው ከ90 ሺህ ብር እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር ገንዘብ ሰጥተዋቸው እንደላኳቸው ነው የነገሩን:: ቤተሰብ ይህን ያህል ገንዘብ ማውጣት ከቻለ በአካባቢያቸው ላይ የሥራ እድል ሊያመቻቹላቸው አይችሉም ነበር ወይ ? የሚል ጥያቄ ይፈጥራል:: ይሄን ጥያቄ ለልጆቹም አቅርበን:: ከሀገር ወጥተው ለመሥራት ካልሆነ በስተቀር ገንዘቡን እንደማይሰጧቸው ነው የነገሩን:: ስደትን አማራጭ አድርጎ የማየት ሁኔታ ቤተሰብ ድረስም የዘለቀ በመሆኑ ሰፊ ሥራ እንደሚጠይቅ ነው የተገነዘብነው:: ችግሩ ደግሞ በሁሉም ክልሎች መኖሩ ደግሞ አሳሳቢ ነው ::

በምሥራቅ ኢትዮጵያ በኩል በድንበር ለመውጣት የሚደረግ እንቅስቃሴን ለአብነት አነሳን እንጂ በደቡብ ኢትዮጵያ በኬንያ፣ በታንዛኒያ፣ ሞዛቢክ በኩል አቋርጠው ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት የሚሞክሩ ብዙዎች ናቸው:: በሕገወጥ መንገድ የሚጓዙ ልጆቻቸውን መርቀው የሚልኩ ወላጆች እና የኃይማኖት አባቶች በርካታ ናቸው:: በሕገወጥ የሚደረግ ጉዞን ሁሉም ህብረተሰብ የተቀበለውና በበጎም ያየው ይመስላል::

አዲስዘመን ፡- ሕገወጥነትን ለመከላከል የማያስችሉ የተለያዩ ተግዳሮች እንዳሉ ቢታወቅም ችግሮቹ ግን ከመንግሥት አቅም በላይ ናቸው ?

አቶ ደረጀ፡- በአንድ አካል ብቻ ችግሮችን ማስወገድ ስለማይቻል የተለያዩ አካላትን ትብብር ይጠይቃል:: በሕገወጥ መንገድ የሚሄዱ ዜጎች ድንበርን አቋርጠው ስለሆነ የሚሄዱት፤ በየድንበሩ ጠንካራ ቁጥጥርን ይጠይቃል:: በዚህ ላይ በሕገወጥ አዘዋዋሪነት ላይ የሚሰማሩት ኢትዮጵያውያን ብቻ አይደሉም:: የሌሎች ሀገሮች ዜጎችም የሚሳተፉበት በመሆኑ ቁጥጥሩ የተጠናከረ እንዲሆን ከሀገራት ጋር አብሮ መሥራት ይጠይቃል:: ኢንተር ፖልን የመሳሰሉ የፀጥታ አካላት ጭምር ነው መተባበር አለባቸው::

ሕገወጥ ስደተኞች አውሮፓ እስኪደርሱ ድረስ በርካታ ሀገራትን ያልፋሉ:: በዚህ ሂደት በርካታ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ናቸው የሚሳተፉት:: ስለዚህ የአህጉራዊ ድርጅቶች ትብብርና ተሳትፎ ወሳኝ ነው:: አልፎም የመንግሥታትን ትብብር ይጠይቃል:: በአሁኑ ጊዜ የሰዎች ሕገወጥ ዝውውር ጉዳይ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ የብዙ ሀገሮች እራስ ምታት በመሆኑ የጋራ ትብብር ሥራ ይጠይቃል::

ከሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርና የአደንዛዥ እጽ ዝውውር ቀጥሎ በአስቸጋሪ ሁኔታ እየተነሳ ያለው የሰዎች ሕገወጥ ዝውውር ነው:: በዚህ የሰዎች ሕገወጥ ዝውውር ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ የሚዘዋወርበት ወንጀል ነው:: ይሄ መንግሥትን የሚፈትን ነው:: ስለዚህም ሁሉን ያቀፈ አሠራር ያስፈልጋል::

ለአብነት በጅቡቲ ያየነውን ማንሳት እፈልጋለሁ:: በሕገወጥ ድንበር አቋርጠው የገቡ ሰዎች ያለማንም ከልካይ በከተማዋ ውስጥ ሲዘዋወሩ ነው ለመታዘብ የቻልነው:: በሕጉ መሠረት አንድ ሀገር በተለያየ መንገድ ሀገሩ የገቡትን የሌላ ሀገር ዜጎች መዝግቦ መጠለያ ወይንም በካምፕ ውስጥ ነው ማቆየት ያለበት እንጂ በቀጥታ ከሀገሩ ነዋሪ ጋር እንዲቀላቀሉ ማድረግም፤ መፍቀድም የለበትም:: ነገር ግን ጅቡቲ ውስጥ ይህ አልተደረገም::

በመቀጠልም ወደሀገራቸው የሚሄዱበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው የሚጠበቅበት:: በተመሳሳይ አዘዋዋሪዎችም፣ በዝውውር ውስጥ የተሳተፉ ዜጎችም ጭምር ላይ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ የግድ ይል ነበር:: የማጣራት ሥራንም ማጠናከር ከአንድ ሀገር የሚጠበቅ ተግባር ነው መሆን ያለበት:: በነበረን ቆይታም መገንዘብ የቻልነው በከፍተኛ ሁኔታ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ ደላሎች መኖራቸውን ነው:: ይሄ ችግሩ ምን ያህል ሥር እንደሰደደ ነው የተረዳነው:: ስለዚህ ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት የጋራ ትብብርን ይጠይቃል ማለት ነው::

አንድ ግንዛቤ መያዝ ያለበት ነገር ሰዎች ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር የሚንቀሳቀሱት በደላላ ወይንም በሌላ አካል በሚደረግ ግፊት ብቻ አይደለም:: ተፈጥሮአዊ ጭምር ነው:: አንዳንዴ የድርቅ፣ የጎርፍ አደጋ በአካባቢያቸው ላይ ሲከሰት፣ እርስበርስ ግጭት ሲፈጠር አካባቢያቸውን ጥለው ለመሰደድ ይገደዳሉ:: አማራጭ አጥተናል ብለው በሚያስቡበት ጊዜ አማራጭ የሚያደርጉት መሰደድን ነው::

በዚህ ሁኔታ ስደት ሊስፋፋ ይችላል:: ይህ ሁኔታ ከአቅም በላይ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ስለሚፈጠር ፍልሰትን ለማቆም የሚደረግ ጥረትን ሙሉ ለሙሉ ላያስቆመው ይችላል:: ይህ ሲባል ግን ፍልሰትን ለመከላከል የሚደርግ እንቅስቃሴ ይቀራል ማለት አይደለም::

የኢትዮጵያ መንግሥት ሕገወጥ ስደትን ለማስቀረት ከሚያደርጋቸው ሥራዎች በተጓዳኝ ሕገወጥ ደላሎችን እንዲቀጡ በማድረግ ላይ ይገኛል :: በተለይም በሰው መነገድና በሕገወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከል የወጣ አዋጅ ቁጥር 11/ 78/ 2012 አለ:: ይህን አዋጅ የማስፈጸም ኃላፊነት የተሰጠው ለፍትህ ሚኒስቴር ነው:: ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ የራሱን አደረጃጀት ፈጥሯል:: በአደረጃጀቱ ውስጥም ሴክሬታሪያት አለው:: ሴክሬታሪያቱ በአዋጁ ተቋማትን የማስተባበር ሥልጣን ተሰጥቶታል:: በዚህም አንዱ የመከላከል ሥራ ነው የሚሠራው::

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርም ሕገወጥ ስደትን የመከላከል ሥራ ይሠራል :: በዚህ ቡድን ውስጥ ዓለምአቀፍ ተቋማትን ጨምሮ ወደ 17 የሚሆኑ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የተካተቱ በመሆናቸው የመከላከሉን ሥራ በጋራ እየሠራን እንገኛለን::

አዲስ ዘመን፡- ሕገወጥ ስደት በሀገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ እያሳደረ ያለው ተጽእኖ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ደረጀ፡- እንደሀገር ጉዳቱ በተለያየ መንገድ ነው የሚገለፀው:: ለሥራ የደረሱ ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውን ልንጠቀምባቸው የምንችላቸው ወጣቶች ናቸው በዚህ የሕገወጥ የሰው ዝውውር ውስጥ በስፋት የሚሳተፉት:: ባለፈው ዓመት ከስደት እንዲመለሱ ከተደረጉት ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ከ14 እስከ 35 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው:: ሀገራችን እነዚህን ዜጎች ማጣቷ በራሱ ክፍተኛ የሆነ ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያሳጣታል::

ሀገራዊ ገጽታ ላይም የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ አለው:: ወጣቶቹ ለሥራ በሚሄዱባቸው ሀገራት በሚደርስባቸው የተለያዩ ጉዳቶችና ተጽእኖዎች የችግሩ ገፈት ቀማሽ እነርሱ ቢሆኑም የሀገር ገጽታን ያበላሻል:: ህብረተሰቡም ይሄን መገንዘብ አለበት:: ይሄን ሁሉ ለመከላከል ዜጎች በሀገር ውስጥ ሠርተው መለወጥ የሚችሉብትን ሁኔታ ማመቻቸት የግድ ይላል:: የሚሻለውም በሀገር ውስጥ ሠርቶ መበልጸግ ነው::

አዲስ ዘመን፡- በሕገወጥ ስደት ለችግር ተጋልጠዋል የሚባሉ ዜጎች ምን ያህል እንደሆኑና የደረሰባቸውንም ጉዳት የሚያሳይ ጥናት አለ?

አቶ ደረጀ፡- ችግሩን ለመለየት ራሱን የቻለ የጥናት ሥራ ባይካሄድም፤ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች በተለያየ ሥራ መንግሥትን ስለሚደግፉ ከነዚሁ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በተደጋጋሚ የጥናት ሥራዎች ተሠርተዋል:: የጥናት ውጤቱ ከሚያሳየው በላይ ጉዳቶቹ በግልጽ የሚታዩ ናቸው:: እኛም ተመላሾቹን ስንቀበል በተግባር የምናያቸው ነገሮች አሉ::

ከሚመጡት ዜጎች መካከል ከፎቅ ተወርውረው፣ በጥይት ተመትተው፣ ተደብድበው፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ይገኙባቸዋል:: በቀዶ ጥገና ከሰውነት ክፍላቸው ውስጥ የተወሰነ አካላቸው በስርቆት የተወሰደባቸው በርካታ ናቸው:: የሚገርመው ደግሞ እነዚህ ዜጎች የትኛው የሰውነት ክፍላቸው በምን ሁኔታ እንኳን እንደተወሰደባቸው አያውቁም:: በደረሰባቸው የሥነልቦና ችግር ለአእምሮ ጤና ችግር የተጋለጡም ይገኙባቸዋል::

በተለይም ለጤና ችግር የተጋለጡት አካባቢያቸውንና ቤተሰባቸውን ለይተው ማወቅ ባለመቻላቸው ከቤተሰባቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ለማድረግ እንኳን የተቸገርንበት ሁኔታ ብዙ ነው:: እንደ ሳምባ፣ የቆዳ በሽታ ያሉ ተላላፊ ለሆኑ በሽታዎች የተጋለጡም በርካቶች ናቸው::

አዲስ ዘመን፡- ዜጎች በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ እስካሁን በተሠሩ ሥራዎች የተገኙ ውጤቶች ካሉ ቢገልጹልን

አቶ ደረጀ፡- መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየወሰደ ያለው ርምጃ ዜጋ ተኮር ፖሊሲን መሠረት ያደረገ ነው:: ይህንኑ መነሻ በማድረግም ዜጎችን ከሄዱበት የማስመለስ ሥራ እየሠራ ነው::

ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት ዜጎችን በተገቢው ሁኔታ እንዲመለሱ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ተመልሰው እንዳይሰደዱ በሀገር ውስጥ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና ቅድሚያም በመስጠት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል:: ባለፈው ዓመት ከመጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ መጋቢ አጋማሽ 2015 ዓ.ም 133ሺ 102 ዜጎች ተመልሰዋል:: እነዚህ ዜጎች ማህበራዊና ሌሎች ድጋፎችን እንዲያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ ባሉ የሥራ አማራጮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማረግ መንግሥት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል:: በተለይም በሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከዓለምባንክ ጋር በመተባበር ሰፊ ሥራ ሠርቷል::

ከ2015ዓ.ም እስከ 2016 ዓ.ም ታህሳስ ወር ባለው ጊዜ ወደ 49 ሺህ ለሚሆኑ ከስደት ተመላሽ ዜጎች በሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል:: ለእነዚህ ዜጎች ከሥልጠና ባሻገር ለሥራ መነሻ የሚሆን ብድርና የመሥሪያ ቦታም ይመቻችላቸዋል:: ሆኖም ካለው ቁጥር አንጻር ገና ብዙ መሥራት ይገባል::

አዲስ ዘመን፡- ዜጎች እንዳይሰደዱ ቀድሞ በመከላከል ላይ የተሠሩ ሥራዎችስ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው ማለት ይቻላል?

አቶ ደረጀ፡- የመከላከሉን ሥራ የሚሠራ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ ወደ 17 የሚሆኑ ተቋማት የተካተቱበት ብሄራዊ ኮሚቴም ተዋቅሯል:: በተለይም በ2015 ዓ.ም በህብረተሰብ ውስጥ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ተሰሚነት ያላቸውን አካላት፣ ዜጎች የሚሄዱባቸው ሀገሮች አምባሳደሮች የተካፈሉበት ሆሳእና ላይ መድረክ ተዘጋጅቶ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል:: መደበኛ ያልሆ ፍልሰትን ለመከላከል የመግባቢያ ሰነድ ተፈርሟል:: ውጤት ያስገኘ እንቅስቃሴ ማድረግ ተችሏል:: በተለይም ክልሎች አቅድ አውጥተው የመከላከሉን ሥራ ወደታች አውርድው እንዲሠሩ ያስቻለ ነው:: በዚህ ቢያንስ ዜጎች መረጃ እንዲኖራቸው ያስቻለ ነው::

አዲስ ዘመን፡- በተሠሩት ሥራዎች ሕገወጥ ስደት ቀንሷል ማለት ይቻላል?

አቶ ደረጀ፡- ጥናት ይፈልጋል:: ሆኖም ግን ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽን ተከስቶ በነበረበት ወቅት ሀገራት ድንበሮቻቸውን ዘግተው ስለነበር ስደት ቀንሶ ነበር:: ይሄ የሚያሳየው ሀገሮች ድንበሮቻቸው ላይ የተጠናከረ ሥራ መሥራት ከቻሉ ስደትን መቀነስ ይቻላል::

አዲስ ዘመን፡- መንግሥት በስፋት ዜጎችን ከውጭ ሀገራት በመመለስ ላይ ይገኛል:: ዜጎችን እንዲመለሱ እየተደረገ ያለው ከየትኞቹ ሀገራት ናቸው ?

አቶ ደረጀ፡- ባለፈው ዓመት ከሳውዲአረቢያ ብቻ ነበር:: ዘንድሮ ዜጎችን እየመለስን ያለነው ከበርካታ ሀገሮች ነው:: ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ሄደው ከተያዙና ለችግር ከተጋለጡ መንግሥት ከሀገራቱ ጋር በሚያደርገው ስምምነት መሠረት ዜጎችን የማስመልስ ሥራ ይሠራል:: በዚህ ዓመት ከኦማን፣ ከየመን፣ ከሳውዳረቢያ፣ ዜጎችን በመመለስ ላይ ይገኛል:: የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከምትገኘው ሱዳንም ዜጎች ለችግር እንዳይጋለጡ ረጅም ዓመት በሀገሪቱ ውስጥ የቆዩ ዜጎችን እንዲመለሱ እያደረግን ነው::

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን

አቶ ደረጀ፡- እኔም አመሰግናለሁ::

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You