ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ እንደመሆኗ መጠን የበርካታ ባሕልና ሀገር በቀል ዕውቀቶች ባለጸጋም ናት። ሀገራችን ከምትታወቅባቸው ሀገር በቀል ዕውቀቶች መካከል የባሕል ሕክምና፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ ቁጠባ፣ ባሕላዊ የአስተዳደር ሥርዓት፣ የዘመን አቆጣጠር፣ ዕደጥበብና የእርቅ ሥርዓት ተጠቃሽ ናቸው። ለሀገር ግንባታ ጎልህ ሚና ያላቸው ሀገር በቀል ዕውቀቶች ትኩረት ባለማግኘታቸው ተገቢውን ጥቅም ሳናገኝባቸው ቆይተናል። [በመሆኑም] ሀገር በቀል ዕውቀት ለሀገራዊ ችግሮች መፍትሔ በመሆናቸው ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል (“ሀገረሰባዊ ዕውቀቶች ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማት”፣ ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር)።
የሀገር በቀል ዕውቀት አስፈላጊነት የቅንጦት አይደለም። አንዳንድ ሀገሮች ለሀገር በቀል ዕውቀት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የዕውቀት ዘርፉ ለሀገር ዕድገትና ብልፅግና የሚያበረክተውን አስተዋፅዖ ለማሳደግ በሕገ መንግሥታቸው ውስጥ የሀገር በቀል ዕውቀትን የሚመለከት አንቀጽ አካትተዋል። በሀገራችን ስለሀገር በቀል ዕውቀት ጉዳይ በሕገ መንግሥታችን የተቀመጠ አንቀጽ ባይኖርም እንኳ በአዋጅ ቁጥር 482/2006 የተጠቀሰ ሐሳብ አለ። በተጨማሪም ሀገራችን የፈረመችውን ዓለም አቀፍ የብዝኃ ሕይወት ስምምነት (Biodiversity Convention, 1992) መሠረት በማድረግ በተዘጋጀው ብሔራዊ የብዝኃ ሕይወት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ስለሀገር በቀል ዕውቀት ጉዳይ ተጠቅሷል። («የኢትዮጵያ ሀር በቀል ዕውቀት ዳሰሳ ለሠላም፣ ለዴሞክራሲና ለልማት ማሳለጫ አማራጭ ሥልት»፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ፤ ከጥቅምት 8 እስከ 9 ቀን 2012 ዓ.ም፣ አምስተኛው ዓለም አቀፍ ዓውደ ጥናት) በመሆኑም ለእነዚህ ሕግጋት በመገዛት የሀገር በቀል እውቀቶቻችንን መንከባከብ፣ ማልማት፣ መጠቀም ይኖርብናል።
“ሀገር በቀል ሪፎርም አገር በቀል ዕውቀት ይፈልጋል″ (አቶ እንዳልካቸው ስሜ፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ፣ ሪፖርተር ጋዜጣ)። በሀገር በቀል እውቀት ያልታሸ ሪፎርም (ለውጥ) ምንም የሚጠበቀውን ፍሬ ሊያፈራ አይቻለውም።
የሀገር በቀል ዕውቀት የአንድ ማኅበረሰብ መለያ የሆነ፣ የተካበተ የነገሮችና ሁኔታዎች ዕይታ፣ የአስተሳሰብና የግንዛቤ ችሎታ ዘርፈ ብዙ የባሕላዊ አሠራር ሥርዓትና ልማድ ተመጣጣኝ ቴክኖሎጂና ክሂሎትን ሁሉ ይመለከታል። የሀገር በቀል ዕውቀት በሁለት ምድቦች ይመደባል። አንደኛው ምድብ የሀገር በቀል ዕውቀት ተቋማዊ የማኅበረሰብ ዕውቀት (Tacit) ይባላል። ይህ የሀገር በቀል ዕውቀት ከማኅበረሰቡ ትዕይንተ ዓለም (World View) የሚመነጭ፣ በማኅበረሰቡ የእርስ በርስ ግንኙነትና ከተፈጥሮ ጋር ባለው መስተጋብር ውጤት ላይ የተመሠረተ፣ የማኅበረሰቡን የጋራ ማንነት ገላጭ የሆነና ማንኛውም ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ዘመን ተሻጋሪ እሴቶች ሁሉ ያቀፈ ነው። ሃይማኖት፣ ሥነ ቃል፣ ወግ፣ ትውፊት፣ አፈ ታሪክ፣ ተረት፣ ተረትና ምሳሌ፣ ሞራል፣ ዘርፈ ብዙ የማይዳሰስ ባሕል፣ የአሠራር ሥርዓታት (የቅራኔ አፈታት፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና ልማት፣ የምግብ አዘገጃጀት፣ የአለባበስ፣ የዳኝነት፣ የባሕላዊ አስተዳደር መዋቅር፣ ወዘተ) ሁሉ በዚህ የሀገር በቀል ዕውቀት ምድብ ይካተታል። ይህ የሀገር በቀል ዕውቀት ዘርፍ ከማኅበረሰቡ የጋራ ሥነ ልቦናና ታሪክ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ በመሆኑ የዕውቀቱ መጥፋት ወይም መዳከም የማኅበረሰቡ ማንነት መዳከም ወይም መጥፋት አመልካች ነው። ዕውቀቱ እንደ ማኅበረሰቡ የዕድገት ደረጃ በሥነ ቃል ወይም በሥነ ጽሑፍ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊተላለፍ ይችላል።
ሁለተኛው ምድብ የሀገር በቀል ዕውቀት በጠበብት ወይም የአካባቢ ባለሙያዎች የተያዘ ዕውቀት (Explicit) ሲሆን፣ የዕውቀቱ ባለቤቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ታቅፈው የሚኖሩ በመሆኑ በግል የያዙት ዕውቀት የማኅበረሰብ ዕውቀት አካል ነው። ይህ ዕውቀት የአካባቢውን ማኅበረሰብ፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፣ አያያዝና ጥበቃ ሥርዓት የሚጠቁም ሲሆን፣ ዕውቀቱ በብዙኃኑ ሲሰርፅና ሲስፋፋ ወደ ተቋማዊ የማኅበረሰብ ዕውቀት የመሸጋገር ዕድል አለው። ማኅበረሰቡ ዕውቀቱን ቀስ በቀስ የጋራ ዕውቀት (Common knowledge) ስለሚያደርገው በአንድ የአካባቢ ጠበብት ብቻ የተያዘ ዕውቀት ሆኖ አይቀርም። የሀገር በቀል ዕውቀት የይዞታ ባለቤትነት (Patent Right) የሌለው በዚህ ምክንያት ነው። እያንዳንዱ የጠበብት ዕውቀት ማለትም የሥር ማሽ ሕክምና፣ ሽመና፣ ሸክላ ሥራ፣ አናጢነት፣ ግንበኝነት፣ አንጥረኝነት፣ ፋቂነት፣ የአካባቢ ባሕላዊ ግብርና ዘዴ (ጥምር ግብርና፣ ቅይጥ ግብርና) ወዘተ ልዩ ዕውቀት ባካበቱ የማኅበረሰቡ አባላት መንጭቶ ቀስ በቀስ በመዳበር ወደ ሌላው የማኅበረሰቡ አባል በልምድ ቅስሞሽ ሲተላለፍና በስፋት ሲሠራጭ ተቋማዊ ዕውቀት ሊሆን የሚችል የአካባቢ ማኅበረሰብ ዕውቀት ይሆናል። (ዘኒከማሁ)
ስለ ሀገር በቀል ዕውቀት ይህንን ያህል ካልን ወደ ዛሬው ጉዳያችን እንምጣ።
እንደሚታወቀው፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (በወቅቱ አጠራር ILS ፋኩልቲ) እሩቅ በማይባል ወቅት የአንድ ዓመት የቋንቋ ተመራቂ ተማሪዎቹን በሙሉ በአዲስ አበባ የንግድ ቤት ስያሜዎች አሰያየም ላይ እንዲያጠኑ አድርጎ ብዙዎቻችንን ያስደመመ ግኝት ይፋ አድርጎ ነበር።
እንደ ተማሪዎቹ ጥናት ከሆነ፣ በአሁኑ ዘመን በከተማዋ የሚገኙ የንግድ ተቋማት በአብዛኛዎቹ ስያሜዎች ብሔርና ወንዜ ተኮር (ልክ እንደ ፖለቲካ ፓርቲዎቻችን ስምና ስያሜ ማለት ነው) ናቸው። እነዚህም ሕዝብን እንደ ሕዝብ ወደ አንድ የማምጣት አቅማቸው ቀጫጫ ነው።
ሌሎችና ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉት ደግሞ ስያሜያቸው ከሀገሩ የተጣላና መጤ ነው። ዋሽንግተን ካፌና የመሳሰሉት ሁሉ ሀገራዊ ባለ መሆናቸው ሀገራዊ መግባባትም ሆነ በቀላሉ ለመያዝ የሚያበቃቸው ምንም አይነት ኢትዮጵያዊ ንጥረ ነገር የላቸውም። አሁን አሁን፣ ጭራሽ “ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተቋማት” ናቸው ወደ ሚባሉትም ባንኮች ሁሉ ሳይቀር እየተዛመተ የመሆኑ ጉዳይ ነገሩን አሳሳቢ ያደርገዋልና ቢታሰብበት አይከፋም።
ምንም እንኳን፣ ከላይ እንደ ተመከለከትነው የሀገር በቀል ዕውቀታችን ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ቢደርስም እያንሰራራ (“ዳግም እውቅና አገኘ” እንደ ተባለው የእነ እንቶኔ ኮሌጅ) ስለ መገኘቱ አንዳንድ ምልክቶች እየታዩ ነውና እነሱን ለማበረታታት፤ ከማንነታቸው ያፈነገጡትንም ወደ ራሳቸው ይመለሱ ዘንድ በማሰብ እንመልከታቸው።
በአሁኑ ሰዓት ጎልተው ከሚሰሙት የንግድና የመንግሥታዊ ፕሮግራሞች ስያሜ መካከል አንዱ “ሌማት” ነው፤ “የሌማት ትሩፋት”። “ሙዳይ”፣ “አገልግል”፣ “አኮ” (ኦሮምኛ ሲሆን በአማርኛ “አያት″ ማለት ነው)፣ “ዓባይ”፤ “ጤና አዳም” እና ሌሎች በርካታ ሀገር በቀል ስያሜዎች ወደ አደባባይ እየመጡና በቀላሉም እየተለመዱና እየተወደዱ ይገኛሉ።
ባጠቃላይ፣ የንግድ ስም አሰያየም ዘፈቀዳዊ ሳይሆን ሳይንሳዊ ነው። በደመነፍስ የሚመራ ሳይሆን በእውቀት የሚተዳደር ነው። ከነፈሰው ጋር የሚነፍስ ሳይሆን ራሱን ችሎ የሚቆም ዘርፍ ነው። ባለሙያዎች እንደሚመክሩት፣ የንግድ ስም (ድርጅት) ስያሜ “ንግዴን በትክክል ይወክላል?”፤ የእኔን የምርት እሴቶች፣ ተልዕኮ እና ራዕይ በትክክል ይገልፃል?”፤ “ንግዴን ምን ማለት እንደሆነ እና ለደንበኞቼ የማቀርበው ነገር ቀጥተኛ ነጸብራቅ ነውን?”፤ “ከተፎካካሪዎቼ ጎልቶ የመውጣት ዕድሉ ምን ያህል ነው?” “ደንበኞቼ እኔን እንዲመርጡ፣ ከእኔም ጋር እንዲቆዩ ምን ያህል ያግዛል?”፤ “ሁሉን አካታች ነው፣ አግላይ አይደለም?” “በደንበኞች ለመፃፍ እና ለመታወስ ቀላል ነውን?”፤ “ውስብስብ ወይም ግራ የሚያጋቡ ቃላት፣ ጽንሰ ሀሳቦች አሉበት?”፤ እና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በትክክል መመለስ ይጠበቅበታል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም