የመንግሥት አገልግሎት ዘርፍን ውጤታማ ለማድረግ ምን መደረግ አለበት?

የአንድን ሀገር ምጣኔ ሃብት ለማሳደግ እንዲሁም በርካታ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር የሥራ ፈጠራ (ኢንተርፕርነርሺፕ) አዋጭ መንገድ መሆኑ ይነገራል። በስፋት የሚታወቅውም በግለሰብ ደረጃ በሚከናወኑ ተግባራት አዳዲስ ምርቶች፤ የምርት ሂደቶችንና አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ሰፊ የገበያ ድርሻን ለማግኘት መሥራት ነው። በአንጻሩ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪውም አገልግሎቱን በተሻለ ጥራትና ቅልጥፍና ተደራሽ ለማድረግ የኢንተርፕርነርሽፕ ክህሎት ሊኖረው እንደሚገባ ይገለጻል። ፐብሊክ ኢንተርፕርነርሽፕ በኢትዮጵያ እምብዛም የሚታወቅ ባይሆንም ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየተተገበረና ውጤት እያስመዘገበ መሆኑ ይነገራል።

የኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሀሰን ሁሴን(ዶ/ር) እንደሚያብራሩት ኢንተርፕርነርሽፕ የሚጀምረው የተለመደውን ትክክል ነው የተባለውን አሠራርና አካሄድ ጥያቄ ውስጥ በማስገባት ነው። በግለሰብ ደረጃ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ለዓመታት የተሠራው ሥራ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ አስችሏል። ነገር ግን ይህ ለውጥ ሀገራዊ ፋይዳ ሊኖረው የሚችለው በመንግሥትም በኩል ፐብሊክ ኢንተርፕርነርሽፕ መተግበር ሲችል ነው። በአሁኑ ወቅት በስፋት እንደሚስተዋለው የመንግሥት ትኩረት ሌብነትና ሙስና ላይ ነው። ነገር ግን አገልግሎት ላይ የማይውሉ በርካታ የሚባክኑ ሀብቶች አሉ።

በመንግሥት ተቋማት ኃላፊነትን በመውሰድ ሥራን ላለመሥራት፤ አይቻልም፤ ኃላፊው ቢሮ የለም፣ መመሪያው አይፈቅድም፣ ወዘተ የሚሉ የተለመዱ መልሶች ዛሬም አሉ የሚሉት ሀሰን (ዶ/ር)፣ በአንጻሩ በየተቋማቱ ከፍተኛ ብቃትና ችግሮችን ቶሎ የመፍታት አቅም ያላቸው ባለሙያዎች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡

ነገር ግን ለእነዚህ ሰዎች ምቹ ሁኔታ ባለመፈጠሩ በአካባቢያቸው ያለውን ችግር መፍታት እየቻሉ ሳይተገብሩት ይቀራሉ። በኮሮና ወቅት ሥራ በቢሮ መከናወን አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም ብዙ አዳዲስ ነገሮች ተፈጥረው እንደ ሀገር በርካታ ሥራዎች መከናወናቸው ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆናል።

በተጨማሪም በበርካታ ተቋማት በርካታ ቁሳቁሶች ዎርክ ሾፖች በራስ አቅም ብዙ ሊሠሩ እየቻሉ በትንንሽ ምክንያቶች ቆመዋል። በርካታ ስታርት አፖች ደግሞ እነዚህን አጋጣሚዎች በማጣታቸው ሀሳቡ እያላቸው ተቀምጠዋል። የፐብሊክ ኢንተርፕርነርሽፕ መተግበር እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል ይሆናል ይላሉ።

«የፐብሊክ ሰርቪስ ሪፎርም ፐብሊክ ኢንተርፕርነርሽፕን ያካትታል» ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪሰ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ናቸው ። መኩሪያ (ዶ/ር) እንደሚያብራሩት፤ በኢትዮጵያ ያለው ሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት ከመቶ አስራ አምስት ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም ዛሬም በርካታ ተግዳሮቶች ያሉበት ነው። ወቅቱ ከሚጠይቀው አኳያ ለውጥ የሚያስፈልግ በመሆኑም በመንግሥት በኩል ዝርዝር

ጥናት ተከናውኖ ዘመኑን የሚዋጅ ሥርዓት ለመዘርጋት የመንግሥት አስተዳደርና አገልግሎት ፖሊሲ ተዘጋጅቷል። በዚህ ፖሊሲ እንዲተገበሩ በቀዳሚነት ከተመላከቱት ጉዳዮች መካከል አገልግሎቱ ፐብሊክ ኢንተርፕርነርሽፕ ባሕሪ እንዲኖረው ማስቻል አንዱ ነው። ይህ አሁን ያለውን ሁኔታ ለማስተካከል ብቻ ሳይሆን በቀጣይም ከጊዜ ጋር ለመራመድ የሚያስችለው ይሆናል።

ፐብሊክ ኢንተርፕርነርሽፕ በዋናነት ጊዜንና ቴክኖሎጂን በየወቅቱና በየሁኔታው የሚፈጠሩ አጋጣሚዎችን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ነው ያሉት መኩሪያ (ዶ/ር)፣ በተለመደው አካሄድና በትምህርት አንድ ተቋም ትልቅ የበቃ ነው ሊባል የሚችለው ብዙ ሀብት፤ ትልቅ ሕንጻና በርካታ በጀት ሲኖረው ነው። አሁን ባለው ዘመን እውቀት፣ አሠራርና ብቁ ኤክስፐርት እንደ ሀብት የሚወሰዱበትና ግዑዝ የሆነው ነገር ጠቀሜታው እየቀነሰ መጥቷል ብለዋል።

በመንግሥት በኩል በዚህ ዓመት ለአገልግሎትና ለእቃ ስምንት መቶ ቢሊዮን ብር በጀት ይዟል። ይህ በጀት ውጤታማ እንዲሆንና የዜጎችን ሕይወት እንዲቀይር ከተፈለገ በመንግሥት መዋቅር ፍጥነትና ጥራት የሚያሟላ

የኢንተርፕርነር ሥራ የሚያድግበት ምቹ ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል። በተጨማሪም የመንግሥትና የግል ኢንተርፕርነሮችም በቅንጅት ተናበው ሊሠሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል። የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) በበኩላቸው ተቋማቸው ፐብሊክ ኢንተርፕርነርሽፕ በመተግበሩ የሚታይ ለውጥ ማስመዝገቡን ይናገራሉ።

አብዲ (ዶ/ር) “ፐብሊክ ኢንተርፕርነር ሊተገበር የሚችለው በጋራ ነው። በተቋማችን አራት ሺ የሚደርሱ ያሉ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ሰማኒያ በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች ናቸው። ፐብሊክ ኢንተርፕርነርሽፕ ወደ ትግበራ የገባውም እነዚህን ሁሉ በማካተት ሲሆን ሥራውንም የጀመርንው በማኔጅመንት ደረጃ ራስን ከመለወጥ ጀምረን ነው” ብለዋል።

ለረጅም ግዜ በብልሽት ቆመው የነበሩ ማሽኖችን ወደ ሥራ ከማስገባትም ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል ያሉት አብዲ (ዶ/ር)፣ በዚህም ከሌሎች ለውጦች በተጓዳኝ ባለፉት ሁለት ዓመታትም ገቢውንም ከነበረበት አንድ ነጥብ 78 ቢሊዮን ብር ወደ አምስት ቢሊዮን ማሳደግ ተችሏል። ይህንንም ለማከናወን ያስቻለን ከኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር ሥልጠና በመውሰድና በጋራ መሥራት በመቻላችን ነው ሲሉም አብራርተዋል።

በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ሊኖር የሚገባው ፐብሊክ ኢንተርፕርነርሽፕ በቀዳሚነት ሕዝብንና ሀገርን የማገልገል ጠንካራ ፍላጎት መኖርን ይጠይቃል። ለዚህም በተሠማሩበት የሥራ መስክ ችግሮችን በነቂስ መለየት፤ እነዚህ ችግሮች የሚቀረፉባቸውን መንገዶችና አሠራሮችን በመዘርጋትና ሁኔታዎችን በማመቻቸት ለሥራ ምቹ ከባቢን መፍጠርም ይጠበቃል ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ በዚህ ሂደት የአስተሳሰብና የመዋቅር ለውጦችም ሊደረጉ ይችላሉ ብለዋል፡፡

ራስወርቅ ሙሉጌታ

 አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You