ግብርና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለውና 120 ሚሊዮን የሚጠጋውን ሕዝብ የሚመግብ ዘርፍ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ 96 ሚሊዮን ወይም 80 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ኑሮው ቀጥታ ከግብርና ሥራ ጋር የተያያዘ ነው። ከውጭ ምንዛሪ አንጻርም ብንመለከተው አብዛኛው ድርሻ የሚገኘው ከዚሁ ዘርፍ ነው።
ይህንኑ ሐቅ በመገንዘብ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት አበረታች ውጤቶች መመዝገብ ጀምረዋል። የሀገሪቱን መልክዓ ምድርና የአየር ፀባይን መሠረት ያደረጉ ሥራዎች በመሠራታቸው ጤፍን የመሳሰሉ ምርቶች ምርታማነት ከመጨመሩም ባሻገር ኢትዮጵያ በታሪኳ አምርታቸው የማታቃቸው የበጋ ስንዴና ሩዝን የመሳሰሉ ሰብሎች ከራስ ፍጆታ አልፈው ለውጭ ገበያም ለመቅረብ ችለዋል። በፍራፍሬ ዘርፍም አበረታች ተግባራት ተከናውነዋል።
ሆኖም የግብርና ምርታማነቱ ዘላቂነት ላይ ጥላ የሚያጠሉና በአፋጣኝም መፍትሔ የሚፈልጉ ችግሮችም ተደቅነዋል። ከእነዚህ ተግዳሮቶች ውስጥ የአፈር አሲዳማነት መጨመር በዋነኝነት የሚጠቀስ ነው።
የአፈርን ኬሚካዊ ይዘት አማካይ ሊያደርጉ የሚችሉ እንደ ማግኒዢየም፣ ፖታሺየም፣ ካልሺየም ያሉ ንጥረ ነገሮች ታጥቦ መሄድና ለተክሎች የሚሆኑ ንጥረ ነገሮች ሲመናመኑ የአፈር አሲዳማነት ይፈጠራል። የእርሻ ድግግሞሽ መብዛትና የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎችን በአግባቡ አለመሠራትና የተዛባ የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ አጠቃቀም ለአሲዳማ አፈር መፈጠር መንስኤ ሲሆኑ በእነዚህ ምክንያቶችም በኢትዮጵያ የአፈር አሲዳማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው በኢትዮጵያ እየታረሰ ካለው የመሬት ሽፋን 43 በመቶው በአሲዳማነት የተጠቃ ነው። ከዚህ ውስጥም 28 በመቶ በጠንካራ አሲዳማነት የተጠቃ ሲሆን ይህም አጠቃላይ ከሚታረሰው መሬት ሦስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር ይሸፍናል ።
ይህም ማለት በኢትዮጵያ እየታረሰ ካለው 15ሚሊዮን ሄክታር ውስጥ ወደ 7ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በአሲዳማ አፈር የተጠቃ ነው ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያለው መሬት ምንም አይነት ምርት መስጠት ከማይችልበት ደረጃ ደርሷል ማለት ነው።
ችግሩ ጎልቶ የሚታይባቸው ክልሎች አማራ፤ ኦሮሚያ፤ ሲዳማ፤ ቤኒሻንጉልና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሲሆኑ እነዚህ አካባቢዎች ደግሞ ቀደም ሲል በምርታማነታቸው የሚታወቁና አብዛኛውም የግብርና ምርት የሚገኝባቸው አካባቢዎች ከመሆናቸው አንጻር ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል።
ስለዚህም ከ80 በመቶ በላይ ሕዝብ የሚተዳደርበትና የሀገሪቱ ሕልውና ተደርጎ የሚወሰደው የግብርና ሥራ በአሲዳማ አፈር መጨመር ምክንያት ችግር እየገጠመው መጥቷል። መንግሥት የግብርና ምርታማነት እንዲጨምር እያደረጋቸው ያሉ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ውጤት እያመጡ ቢሆንም የአሲዳማ አፈር መጨመር ግን አፋጣኝ መፍትሔ ካልተሰጠው የሚደረጉ ጥረቶች የሚፈለግባቸውን ውጤት እንዳያመጡ እንቅፋት መሆኑ አይቀሬ ነው።
ስለዚህም የግብርና ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት የአፈር አሲዳማነትን ሊቀንሱ የሚችሉ ተግባራትን በአፋጣኝ ወደ መሬት ማውረድ ይጠበቅባቸዋል። ዘላቂ በሆነ መልኩ የአፈርና የአካባቢ እንክብካቤ ሥራዎችን ከማከናወን ጎን ለጎን የአፈር አሲዳማነትን ለማከም በካልሽየም ካርቦኔት ወይም “በግብርና ኖራ” ማከም ፍቱን መፍትሔ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣሉ።
ሆኖም በየጊዜው እየጨመረ ካለው የአፈር አሲዳማነት መጨመርና ከጉዳዩ ኣሳቢነት አንጻር እየተወሰደ ያለው እርምጃ አዝጋሚ ነው። እንደ ዕድል ሆኖ የግብርና ኖራ በኢትዮጵያ በቀላሉ እና በብዛት የሚገኝ ከመሆኑም በላይ ዋጋውም ርካሽ የሚባል ቢሆንም በትኩረት ማነስ የተነሳ ይህንን ዕድል መጠቀም አልተቻለም።
ስለሆነም የሀገሪቱ የጀርባ አጥንት የሆነውን ግብርና እየጎዳ የሚገኘውን የአሲዳማ አፈር መስፋፋት ለመግታትና የተጀመረውን ምርትና ምርታማነትን ዘላቂ በሆነ መልኩ ለማሳደግ የግብርና ኖራ መጠቀም ዋነኛ መፍትሔ መሆኑን ከመረዳት ባሻገር ወደ ተግባርም ማሸጋገር ጊዜ ሊሰጠው አይገባም!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም