የአፈር አሲዳማነት መጨመርና የግብርናው ዘርፍ ተግዳሮት

የኢትዮጵያ የአፈር ሀብት መረጃ ፕሮጀክት ጥናት መሰረት እየታረሰ ካለው የመሬት ሽፋን 43 በመቶው በአሲዳማነት የተጠቃ ነው። ከዚህ ውስጥም 28 በመቶ ጠንካራ አሲዳማ ሲሆን ይህም አጠቃላይ ከሚታረሰው መሬት ሦስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር ይሸፍናል።

በሀገራችን ዋነኛው የኢኮኖሚ ምንጭ ግብርና መሆኑ ይታወቃል። ይህን ዋና የሀገር ኢኮኖሚ ምሶሶ የሆነውን ግብርና ለማስፋፋት ብሎም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የአፈር ጤናን መጠበቅ የህልውና ጉዳይ ተደርጎ መታየት እንዳለበት የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ታዲያ ይህን የኢኮኖሚ ዋልታ የሆነ የግብርና ዘርፍ በአፈር አሲዳማነት የተነሳ እየተጎዳ ከሆነ ኢኮኖሚው ላይ የሚኖረው ተፅእኖ ምን ሊሆን ይቻላል? ይህን የአፈር ለምነትን መቀነስ እና የሚያስከተለው ችግር በምን መልኩ ይቀረፋል ? እና ሌለች ጥያቄዎችን ይዘን የዘርፉን ባለሙያዎች አነጋግረናል። ከምላሻቸው ጋር መልካም ቆይታ።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) እንደሚያብራሩት ፤ የአፈር ኬሚካዊ ይዘት (ፒኤች) ከሚጠበቀው በታች ሲሆንና የአልሙኒየም ንጠረ ነገሮች በሚበዙበት ጊዜ የአፈር አሲዳማነት ይከሰታል። የአፈርን ኬሚካዊ ይዘት አማካይ ሊያደርጉ የሚችሉ እንደ ማግኒዢየም፣ ፖታሺየም፣ ካልሺየም ያሉ ንጥረ ነገሮች በተለይ ከፍተኛ ዝናብ በሚዘንብባቸው አካባቢዎች በዝናብ ታጥበው መጠናቸው ስለሚቀንስ ለአሲዳማ አፈር መፈጠር ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ ይጠቁማሉ። የእርሻ ድግግሞሽ መብዛትና፤የአፍርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎችን በአግባቡ አለመስራትና የተዛባ የሰው ሰራሽ ማዳበሪያ አጠቃቀም ለአሲዳማ አፈር መፈጠር መንስዔ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ክፍል የተክሎች ባይሎጂ እና ባዮ ዳይቨርስቲ መምህር የሆኑት ዶክተር የወንደሰን ጠና በበኩላቸው የአፈር አሲዳማነት ማለት አሲዳማ አፈር የአፈሩ ኬሚካላዊ ይዘት ወይም ፒ ኤች (pH) መጠን ከሰባት በታች የሆነ እና የሃይድሮጅን (H+) እና አልሙኒየም (Al+3) ንጥረ- ነገሮች የሚበዙበት አፈር ማለት ነው።

በአፈር ሳይንስ እና ፕላንት ኒውትሬሽን ላይ በርካታ ጥናቶች ያደረጉት ዶክተር ጠና የአፈር አሲዳማነት በሀገራችን በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ የሚገኝ የአፈር ለምነት ችግር ሲሆን፤ ከፍተኛ ዝናብ የሚያገኙና በምርታማነታቸው የተሻሉ ናቸው የሚባሉትን የሀገሪቱን አካባቢዎች ጭምር እየጎዳ መሆኑንም ነው የሚጠቁሙት።

የአፈር ጤንነት ችግሮች በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ይገለፃሉ። ይኸውም አሲዳማነት፣ የጨዋማነት ችግር የሚነሳበትና ኮትቻማ/ጥቁር ወይም መረሬ አፈር/ ብሎ ማስቀመጥ እንደሚቻል ዶክተር የወንደወሰን ይናገራሉ። በኢትዮጵያ ከ15 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሚታረስ መሬት ሲኖር ወደ 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት በአሲዳማነት የተጠቃ እንደሆነ ነው የጠቀሱት።

አፈር ሰብሎች የሚፈልጓቸውን ንጥረ-ነገሮች በተሟላና በተመጣጠነ መልኩ ሳይዝ ሲቀር ምርታማነት ጥያቄ ውስጥ እንደሚወድቅ የሚናገሩት ዶክተሩ፤ ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ከ1 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በአፈር አሲዳማነት ክፉኛ የተጎዳ በመሆኑ ምርታማነቱ ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ የሚቀመጥ መሆኑን ይጠቁማሉ። እፅዋት ከአየር፣ ውሃና የፀሐይ ብርሃን በተጨማሪ 18 ዓይነት ንጥረ-ነገሮችን ከአፈር ውስጥ ሊያገኙ እንደሚችሉ የሚናገሩት ዶክተር የወንደወሰን የአፈርን ደህንነት መጠበቀ የግድ የሚል ተግባር መሆኑ ይናገራሉ።

የአፈር አሲዳማነት መንስኤዎች የሚባሉ በዋነኝነት የዝናብ መብዛት፣ የአፈር መሸርሸር፣ የሰብል ተረፈ-ምርት ሙሉ በሙሉ ከማሳ ማንሳት እና ፍግ አለመጠቀም፣ እንዲሁም አሲዳማ ዝናብ የመሳሰሉት አፈር ውስጥ ያሉ ለተክሉ እድገት ጠቃሚ ንጥረ-ነገሮች እንዲሟጠጡ እንደሚያደርግ በመንስኤነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ይናገራሉ።

እንደ ዶክተር የወንድወሰን ገለፃ የአፈር አሲዳማነት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋል ሲሆን በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ተጠቃሽ ናቸው።

ይህን ችግር የሚያሰከትለውን የአፈር አሲዳማነት ለማከም ኖራ ዋናው መፍትሄ መሆኑን የተናገሩት ዶክተሩ አሲዳማ አፈርን ለመከላከል በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ መንገዶች ከሚወሰዱ እርምጃዎች ባሻገር አፈሩን በኖራ የማከም ሥራ በዋናነት ተመራጭ ነው ይላሉ።

የተለያዩ አፈርን የማከሚያ ግብአቶች ያሉ ቢሆንም በቀላሉ ከመገኘትና ከዋጋው ርካሽነት አንፃር ካልሽየም ካርቦኔት ወይም “የግብርና ኖራ” እየተባለ የሚጠራው በስፋት አገልግሎት ላይ እንደሚውል ገልጸዋል።

ወደ 15 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር የሚታረስ መሬት ሲኖር፤ ከዚህ ውስጥ 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር ወይም ከ43 በመቶ የማያንሰው በአሲዳማ አፈር የተጠቃ መሆኑን ጠቅሰው፤ ወደ 4 ሚሊየን ሄክታር የሚሆነው በጠንካራ አሲዳማነት የተጠቃ እንደሆነና በኖራ መታከም ያለበት መሆኑን አስረድተዋል።

ጠንካራ አሲዳማ አፈር ስንል የአፈሩ ኬሚካላዊ ይዘት ወይም ፒ ኤች (pH) መጠን ከ 5 ነጥብ 5 በታች የሆነ እና የሃይድሮጅን (H+) እና አልሙኒየም (Al3+) ካታዮኖች የሚበዙበት አፈር ሲሆን፤ የእነዚህ ካታዮኖች መብዛት የሰብሎችን ሥር በመመረዝ በዕድገታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖን እንደሚፈጥር ባለሙያው ይናገራሉ።

ፒ ኤች መጠኑ ከሰባት ወደ ዜሮ እየቀነሰ ሲሄድ የአሲድነቱ ጥንካሬ የሚጨምር ሲሆን ከሰባት ወደ 14 ሲጨምር የጨዋማነቱ ባህሪ እንደሚጨምር ነው የሚያስረዱት። በአገራችን ሁኔታ አሲዳማ አፈርን ለማከም ኖራ መጠቀም የሚያስፈልገው የአፈሩ ፒ ኤች መጠን ከ5 ነጥብ 5 በታች ሲሆን ነዉ። ኖራ በተፈጥሮ የሚገኝ የካልሲየም እና የማግኒዚየም ካርቦኔት ሃይድሮኦክሳይድ ውህድ ሲሆን፤ አሲዳማ አፈር ውስጥ በሚጨመርበት ወቅት አሲዳማ አፈር ውስጥ የሚገኙትን አልሙኒየም እና ሃይድሮጂን አሉታዊ እንቅስቃሴዎችን በመግታት የአፈሩን ፒ ኤች መጠን ከፍ በማድረግ ለእፅዋት እድገት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

በአማካይ በአፈር አሲዳማነት የተጎዳ መሬትን ለማከም በሄክታር 30 ኩንታል የግብርና ኖራ እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት ዶክተር የወንድወሰን በአሲዳማነት የተጠቃ መሬት አሲዳማነትን የሚቋቋሙ ሰብሎች ካልተዘሩበት ወይም አፈሩን በኖራ የማከም ሥራ ካልተሰራ የሚሰጠውን የአፈር ማዳበሪያ ከጥቅም ውጭ በማድረግ ለኪሳራ ይዳርገናል ነው ያሉት።

ከዚህም በተጨማሪ የሰብልን ተረፈ ምርቶች ማሳው ላይ በመተው፤ የተፈጥሮ መዳበሪያዎችን በመጠቀም ቀይጥ ማዳበሪያዎችን መጠቀም የአፈርን አሲዳማነት ለመቀነስ መፍትሄ መሆኑን አስቀምጠዋል። ከዚህም በተጨማሪ አሲዳማ አፈር የሚስማማቸውን ሰብሎች አሲዳማ አፈር ያለበት አካባቢ መትከል ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

ይህም ሲባል ቡና አሲድ ያለባቸው አካባቢዎች ቢዘራ ምርታማነቱን አይጎዳውም። ከዚህም በተጨማሪ ሻይ ቅጠልም በአሲዳማ አፈር ላይ ጥሩ ምርት የሚሰጥ ሲሆን፤ ድንችም እንደዚሁ የአሲድ መሬት ላይ ቢተከል የተሻለ ምርት ይሰጣል ብለዋል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኽ ተስፋ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ሀሳብ የአሲዳማነት መጨመር ምክንያቶች ወይም የአፈርን አሲድነት የሚጨምሩ አራቱ ዋና ዋና ምክንያቶች እንዳሉ ይዘረዝራሉ። እነዚህም ከእርሻ ማስወገድ፤ ናይትሮጅንን እና ናይትሬት ከዕፅዋት በታች ማፍሰስ፤ የናይትሮጅን ማዳበሪያዎች ተገቢ ያልሆነ አጠቃቀም፤ የኦርጋኒክ ቁስ መገንባት ናቸው ብለዋል።

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ እንደሚሉት የአሲድነት አካላዊ መገኘት የኢኮኖሚ ችግር ምልክት መሆኑን ለማወቅ፣ አሲዳማነት የሚጠይቀውን ወጪ፣ እና የአሲድ አፈርን ለመከላከል እና/ወይም ወደ ነበረበት ለመመለስ ወጪዎችን መለየት እና መጠኑን ማወቅ አስፈላጊ ነው።

ከአሲድነት ጋር የተያያዙ ወጪዎች በሁለት ትላልቅ ቡድኖች ሊከፋፈሉ ይችላሉ የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በእርሻ ላይ ወጪዎች እና ከእርሻ ውጭ ያሉ ወጪዎች መሆናቸውን ያብራራሉ።

በእርሻ ላይ የአፈር አሲዳማነት ወጪዎች ዝቅተኛ የሰብል ምርት እና ምርታማ ማስመዝገብ ማለት ነው። በአንዳንድ የአሲዳማነት ሁኔታዎች ይህ ማለት ከአሲዳማነት በፊት በጣም ትርፋማ የሆነው ኢንተርፕራይዝ አነስተኛ ትርፋማ በሆነ የመሬት አጠቃቀም ተተክቷል ማለት ነው።

ምንም እንኳን በአሲድነት ላይ የተደረገው የኢኮኖሚ ጥናት በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ብቻ ቢሆንም በግርድፉ ቢሆንም እነዚህ ወጪዎች እንደ ኢኮኖሚ ጉዳትነት ሊቆጠሩ ይችላሉ ብለዋል።

እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለፃ የአሲዳማነት ችግርን ለማቃለል በእርሻ ላይ ያሉ አንዳንድ ወጪዎች የበለጠ በእርግጠኝነት እና ትክክለኛነት ሊገለጹ ይገባል። ለምሳሌ፣ በአርሻ መሬት ላይ ያለውን አሲድ ለመቀነስ የኖራ አጠቃቀም ተጨማሪ ወጪ ተሳቢ በማድረግ የኢኮኖሚ ጉዳትን መረዳት ይቻላል ብለዋል።

የአፈር አሲዳማነት የመሬት ሽፋን መቀነስ፤ የውሃ ፍሳሽ እና የአፈር መሸርሸር እድልን ይጨምራል፤ ይህም ደግሞ ግድቦችን ደለልን በመሙላት ጉዳት ሊያደርስ የችላል። ከዚህም በተጨማሪ በመንገዶች ላይ በሚደርስ ጉዳት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የራሱን ጫና ማሰከተሉ አይቀሬ ነው ይላሉ።

በተጨማሪም ከአሲድነት ጋር የተያያዘውን የናይትሮጅን መለቀቅ የጅረቶች ብክለትን ያስከትላል፤ በዚህም የአካባቢ ወጪዎችን ያስከትላል፤ ከሁሉም በላይ ግን ምርትና ምርታማነት በመቀነሱ ምክኒያት የሚደርሰውነ ያህል ኢኮኖሚያዊ ጫና መለካት ከባድ ነው ይላሉ።

ምሁራኑ ምርታማ መሬትን አክሞ ወደ ምርት በማስገባት ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና መቀነስ ተገቢ ነው ያሉ ሲሆን በዚሁ ምክንያት ሀገር ከግብርና ማግኘት የሚገባትን ምርት ከማጣቷም ባሻገር በአሲዳማ አፈር ምክንያት የምታወጣውን ያልተገባ ወጪ ለመቀነስ ማህበረሰቡ የአፈር አንክብካቤና ጥበቃ ስራ ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

የተሻለ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ምርት ከለም መሬታችን ይታፈስ ዘንድ የአፈር አስዳማነትን የሚጨምሩ ተግባራትን ከመፈፀም መቆጠብ ይገባል። ከዚህም በላይ ወጪ ቀናሽ የሆኑ የአፈር ማከሚያ ዘዴዎችን በመጠቀመም በአሲዳማ አፈር ምክንያት እየታጣ ያለውን ምርት እንዲጨምር ማድረግ ያስፈልጋል።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2016 ዓ.ም

Recommended For You