የሬሚዲያል ፈተና ከሰኔ ወር መጀመሪያ ጀምሮ ይሰጣል

– ከ78 ሺህ በላይ ተማሪዎች የሬሚዲያል ትምህርት እየወሰዱ ነው

አዲስ አበባ፡- የሬሚዲያል ፈተና ከሰኔ ወር መጀመሪያ እስከ 15 ባሉት ቀናት በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ተማሪዎች ልማት ዴስክ ኃላፊ አቶ በየነ ተዘራ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የዘንድሮውን የሬሚዲያል ፈተና ከሰኔ ወር መጀመሪያ እስከ 15 ባሉት ቀናት በሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ለመስጠት እየተሠራ ነው፡፡

ባለፈው ዓመት የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ ፈተናውን በሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ለመስጠት እየተሠራ ነው ያሉት አቶ በየነ፤ ፈተናው በኦንላይን፣ በኦንላይንና በወረቀት አልያም በጥብቅ ቁጥጥር በወረቀት ለመስጠት ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ከነበሩ ክፍተቶች ትምህርት በመውሰድ ዘንድሮ ፈተናው በጥብቅ ቁጥጥር በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን በመግለጽ፤ ፈተናው በማዕከል ደረጃ በጥብቅ ቁጥጥር ተዘጋጅቶ የሚሰጥና የሚመራ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

የሬሚዲያል ትምህርት ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመወያየት ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰው፤ ከ70 በመቶ የሚዘጋጀውን ፈተና ከሰኔ ወር መጀመሪያ እስከ 15 ለመስጠት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮው ዓመት 32 ሺህ 500 ተማሪዎች 50 በመቶ በላይ በማምጣት በቀጥታ ዩኒቨርሲቲ ገብተው መደበኛ ትምህርት እየተከታተሉ እንደሚገኝ አስታውሰው፤ ከ78 ሺህ በላይ ተማሪዎች በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ሬሚዲያል ትምህርት እየወሰዱ ይገኛል ብለዋል፡፡

የሬሚዲያል ትምህርት ከታኅሣሥ ጀምሮ እስከ ሰኔ መጨረሻ እየተሰጠ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ውጤታቸው 30 በመቶ በዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ሂደትና 70 በመቶ በማዕከል እንደሚዘጋጅ አስረድተዋል፡፡

የሬሚዲያል ትምህርት ተማሪዎች እራሳቸውን አሻሽለው ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ ዕድል ፈጥሯል ያሉት አቶ በየነ፤ በተማሪዎች የትምህርት ዝግጅትና ውጤት ላይ መሻሻል ማምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

የሬሚዲያል ትምህርት የዩኒቨርሲቲዎችን ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ውጤታማ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተማሪዎች በቁጭት አንባቢና ጠያቂ እንዲሆኑ የሚያስችሉ የስብዕና፣ የሥነ ልቦና ማነቃቂያ ትምህርት እየተሰጣቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You