የውሃና ኢነርጂ ተደራሽነትን ለማሳደግ ለሚሰማሩ ድርጅቶች ድጋፍ ይደረጋል

– 71 ሚሊዮን ዜጎች ንጹሕ የመጠጥ ውሃ እያገኙ ነው

አዲስ አበባ፡- መንግሥት የውሃ ኢነርጂ ተደራሽነትን ለማሳደግ ለግልና ልማታዊ ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በአሁኑ ጊዜ 71 ሚሊዮን ዜጎች ንጹሕ የመጠጥ ውሃ እያገኙ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ሚኒስቴሩ በዘርፉ ከተሠማሩ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ልማታዊ ድርጅቶች ጋር ትናንት ተወያይቷል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ መንግሥት የውሃና ኢነርጂ ተደራሽነትን ለማሳደግ ለሚሠማሩ ለግልና ልማታዊ ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል፡፡

መንግስት የመጠጥ ውሃና የገጠር ኢነርጂን ተደራሽነት ለማሳደግ ከልማታዊ ድርጅቶች ጋር እየሠራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የሰብዓዊ ጉዳዮች ድጋፍን ጨምሮ በመጠጥ ውሃና ኢነርጂን አቅርቦት በጋራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዓለም ባንክ የመጠጥ ውሃና ኢነርጂ ተደራሽነት ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅሰው፤ ዩኒሴፍም በልማታዊ ድርጅቶቹ በኩል ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ልማታዊ ድርጅቶች የመጠጥ ውሃና ኢነርጂ ተደራሽነትን ለማሳደግ እንደሚረዱ በመግለጽ፤ መንግሥት ከድርጅቶቹ ጋር የሀብት ብክነት ሳይኖር በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አመላክተዋል።

የሀገሪቱ የመጠጥ ውሃና ኢነርጂ ሽፋን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ በተለይም ዓለም ባንክ፣ ዩኒሴፍ፣ የኔዘርላንድ፣ ዴንማርክ፣ ኤምባሲዎችን ጨምሮ የአፍሪካ ልማት ባንክና የተለያዩ የልማት ድርጅቶች አጋር መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በአንዳንድ ልማታዊ ድርጅቶች የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ ክትትል በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የልማታዊ ድርጅቶች ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በከርሰ ምድር ውሃ ላይ ኢንቨስት ለሚያደርጉ ባለሀብቶች መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ያሉት ኢንጂነር ሀብታሙ፤ በሪል ስቴቶች፣ ሆቴልና ሪዞርት የተሰማሩ ባለሀብቶች የጉድጓድ ውሃን ቆፍረው ለማኅበረሰቡ እንዲያቀርቡ ማበረታቻ ይደረግላቸዋል ብለዋል፡፡

የጉድጓድ ውሃን ለማውጣት የሚጠቅሙ ማሽኖች ላይ ባለሀብቶች ሊሳተፉ እንደሚገባቸው ጠቅሰው፤ ባለሀብቶች ፍቃድ አውጥተው በዘርፉ ሊሠማሩ እንደሚችሉ አመላክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከ71 ሚሊዮን ዜጎች ንጹሕ መጠጥ ውሃ እያገኙ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህም በአማካኝ 68 በመቶ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ግጭት ባለባቸው፣ ድርቅና የተፈጥሮ አደጋ ችግር ያለባቸው አካባቢዎችን መልሰው እንዲያገግሙ የማድረግ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በተለይም አማራ ክልል፣ ትግራይ፣ የተወሰኑ የኦሮሚያ አካባቢዎች ላይ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የኢነርጂ አቅርቦትን ለማሳደግ ሰዎች በአካባቢያቸው ላይ ኃይል ማግኘት የሚችሉበትን አማራጮች እየቀረቡ እንደሚገኙ በመግለጽ፤ በተለይም የፀሐይ ኃይል አቅርቦት፣ ባዮጋዝ፣ ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተሰሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You