«አየር በአየር» ሥራ ምንድነው?

በሙያው ከአሥርት ዓመታት በላይ ያገለገለ አንድ ጋዜጠኛ በማህበራዊ ገጹ የጻፈውን አንድ ገጠመኝ እና ትዝብት አነበብኩ፡፡ የጋዜጠኛውን ገጠመኝና ትዝብት አጠር አድርጌ ሃሳቡን ብቻ ላስቀምጥ፡፡

ወደ ሀገረ ቻይና ሄዶ በርዕሰ መዲናዋ ቤጂንግ አድሯል፡፡ በኢትዮጵያ ዓውድ ከረፋዱ 4፡00 በሚሆንበት ሰዓት ተነስቶ ከተማዋን ሲያይ ጎዳናዎቿ ፀጥ ረጭ ብለዋል፡፡ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይኖርባታል የምትባለዋ ከተማ እንዴት እንዲህ ትሆናለች? ብሎ ተገርሟል፡፡ ወዲያውም አጠገቡ ያገኘውን ሰው ምክንያቱን ጠየቀ፡፡ የተጠያቂው ምላሽ አጭርና ተጨማሪ ማብራሪያ የማያስፈልገው ነበር፡፡ ‹‹በዚህ ሰዓት ሰው ሥራ ቦታው ላይ እንጂ ጎዳና ላይ ምን ይሠራል?›› የሚል ነበር፡፡

ጋዜጠኛው ይህን ገጠመኙን የጠቀሰው የአዲስ አበባን ሙሉቀን የመጨናነቅ ምክንያት ለመጠየቅ ነበር፡፡

የዚህን ጋዜጠኛ ትዝብት የሚያጠናክር ከሦስት ዓመታት በፊት የሰማሁት አንድ የራሴን ገጠመኝ ልጨምር፡፡ ጉዳዩ የአዲስ አበባን የትራፊክ ሁኔታ የተመለከተ ውይይት ነበር፡፡ በውይይቱ ላይ አንድ ተወያይ ያነሱት ሃሳብ በየአጋጣሚው ትዝ ይለኛል፡፡ የተወያዩ ሃሳብ በአጭሩ የሚከተለው ነበር፡፡

የመንግሥት ሠራተኛ እስከ ጠዋት 2፡30 ድረስ በሥራ ቦታው ላይ ይገኛል፡፡ የግል ተቋማት የሥራ መግቢያ ሰዓትም ከዚሁ ጋር እኩል ነው፡፡ በግል የንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ደግሞ ጭራሽ ከዚህ ሰዓት በፊት የሚገቡ ናቸው፡፡ የሚታወቁ የሥራ ዘርፎች ቢበዛ እስከ ጠዋት 3፡ 00 ድረስ በየሥራ ቦታቸው ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡

ሰውየው ይህን ካብራሩ በኋላ የጠየቁት ጥያቄ ብዙዎችን ‹‹እውነቱን እኮ ነው!›› በሚል ያስገረመ፣ አንዳንዶችንም ፈገግ ያሰኘ ነበር፡፡ ‹‹ታዲያ ከ3፡00 እስከ 11፡00 ድረስ መንገድ ዘግቶ የሚውለው ያ ሁሉ ባለመኪና በምን ሥራ ላይ የተሰማራ ነው?›› ብለው ነበር የጠየቁት፡፡

የምርምር ለብዙዎች መልስ ያልተገኘለት ጥያቄ ነበር፡፡ የሞኝ ጥያቄ ቢመስልም፤ ዳሩ ግን ትልቅ ጥናት የሚጠይቅ ነገር ነው፡፡ ለድሮው ‹‹የሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት›› የሚባል ነበር፡፡ አሁን ግን የሥራ መግቢያና መውጫውም ሆነ ከዚያ በኋላና በፊት ያለው ምንም ልዩነት የለውም፡፡ በየትኛውም ቦታ ላይ መንገዶች ይዘጋጋሉ፣ በየትኛውም ካፌና ሬስቶራንት ባዶ ወንበሮች አይኖሩም፡፡ ከረፋድ 3፡00 በኋላ ውድ የሚባሉ መኪኖች ናቸው መንገዱን ዘግተውት የሚውሉት፡፡ በየሆቴሉ እና በየካፌው በር ላይ ውድ መኪኖች ናቸው ተሰግስገው የሚውሉት፡፡ በየመዝናኛ ቦታዎች አካባቢ የእግረኛ መንገድ የሚዘጉ መኪኖች ቁጥር ሥፍር የላቸውም፡፡ እነዚህ ሰዎች በምን የሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ናቸው?

ይህንን ጥያቄ አጠገቤ ለሚገኙ ሰዎች ጠይቄ አውቃለሁ፡፡ የሚሰጠኝ መልስ ግን ተለምዷዊ እና የግምት መልስ ነው፡፡ በርግጥ ይህ ከፍተኛ ጥናት የሚጠይቅ ውስብስብ ጉዳይ እንጂ ዝም ብሎ በግምት የሚገኝ አይደለም፡፡ ብዙ ሰው ሲለው የምሰማው መልስ ግን ‹‹አየር በአየር›› የሚባል ምንነቱን የማላውቀው ሥራ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎችም ‹‹ምንድነው የምትሠራ?›› ሲባሉ ‹‹ዝም ብሎ አየር በአየር ነው›› ሲሉ ይሰማል፡፡ ስለአንዳንድ ሰዎች ሲያወሩም ‹‹እሱ እኮ ዝም ብሎ አየር በአየር ነው የሚሰራ›› ሲባል ይሰማል፡፡

ለመሆኑ ይህ አየር በአየር የሚባል ሥራ ምን ይሆን? ቋሚ ቅጥር ያልሆነ ማለት ይሆን? ቋሚ መገኛ የሌለው ተንቀሳቃሽ ሥራ ማለት ይሆን? የአገልግሎት ዓይነት ይሆን ወይስ የዕቃ (goods) ዓይነት ይሆን?

እዚህ ላይ ከማስተውለው ነገር ተነስቼ ትንንሽ የሽያጭ ዓይነቶችን ልጥስ፡፡ በተቀምጥኩበት ካፌ ወይም ምግብ ቤት የተለያዩ ምርቶችን የሚይዙ ሰዎች ይመጣሉ፡፡ ይህ ራሱን የቻለ ሥራ ነው፤ ይህ ምንነቱ የማይታወቀው ‹‹አየር በአየር›› የሚባለው ሥራ የሚገልጸው አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ተጨባጭ የሆነ ነገር አለው፡፡ ሲቀጥል እነዚህ ሰዎች በአነስተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ እንጂ በውድ መኪኖች አስፋልትና የእግረኛ መንገድ ዘግተው የሚውሉ አይደሉም፡፡

ሌላው ሊገመት የሚችለው ነገር ድለላ ነው፡፡ ድለላ ደግሞ የራሱ ቢሮና ቦታ ያለው ነው፡፡ በርግጥ ድለላ ዓይነቱ ብዙ ነው፡፡ በተለይም ሕገ ወጥ የድለላ ዓይነቶች ቋሚ ቢሮና ቦታ አይኖራቸውም፤ ሥራቸውም በግልጽ አይነገርም፣ አይታወቅም፡፡ የሚደልሉትም እንደ ቤት እና መኪና ያሉ በግልጽ የሚታወቁ ነገሮችን ሳይሆን ብዙ ነውር የሆኑ ነገሮችን ሁሉ እንደሚሆን በሀሜት ደረጃ ሲወራ እንሰማለን፡፡ ‹‹አየር በአየር›› የሚባለው ሥራ ከዚህ ውስጥ የሚካተት ይሆን?

አንዳንድ ሰዎች አሉ፤ ምን እንደሚሰሩ የት እንደሚሰሩ የማይታወቅ፤ ብቻ ግን በሥራ ሲለፉ ከሚውሉ ሰዎች የተሻለ ኑሮ ሲኖሩ የሚታይ፤ ውድ መኪና ይዘው የሚታይ፤ ‹‹አየር በአየር›› ማለት የሆነ በአስማት የሚገኝ ገንዘብ ማለት ይሆን?

አንዳንድ ወገኖች ምናልባት በውጭ ሀገር ጥሩ ኑሮ ያለው ቤተሰብ ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ምንም ሥራ ላይሰሩ ይችላሉ፡፡ ከውጭ በሚላክላቸው ገንዘብ ብቻ ሲዝናኑ ሊውሉ ይችላሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት እንደሚኖር ቢታወቅም ቢያንስ ግን ይህ ሁሉ ሰው በዚህ ሁኔታ የሚኖር ሊሆን ይችላል? ጥያቄው ለአንዳንድ የሰዎች የሞኝ ጥያቄ እንደሚመስል አምናለሁ!

ከረፋድ ጀምሮ እስከ ሥራ መውጫ ሰዓት ድረስ ሲርመሰመስ የሚውለው ሁሉ ከሥራ ውጭ ነው ማለት አይደለም፤ ይህን አምናለሁ፡፡ የአንዳንድ ሰዎች ሥራ በባህሪው በዚያን ሰዓት መንቀሳቀስን የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በግል ጉዳዮች ምክንያት በዚያን ሰዓት መንቀሳቀስ የግድ ሊሆን ይችላል፡፡ ዳሩ ግን፤ እነዚህ አጋጣሚዎች ይህን ሁሉ መርመስመስ ይፈጥራሉ?

የመንገዱ ነገር ከመሠረተ ልማት ዕድገት ደረጃችን ጋር የሚያያዝ ስለሆነ በጥቂት መኪኖች ብቻ ይዘጋጋል ብለን እንያዘው፡፡ ዳሩ ግን በነጩ የሥራ ቀን ካፌዎችና ሆቴሎች፣ መዝናኛዎች ከአፍ እስከ ገደፋቸው ሞልተው የሚውሉት ሥራ ጥለው በሚሄዱ ሰዎች ነው? ለሆቴሎችና ካፌዎች ጥሩ የሥራ ሰዓት ነው፤ በረንዳ ላይ ሳይቀር አንድ ጠረጴዛ ላይ አራት አምስት ሆኖ የሚታየው ያ ሁሉ ሰው ግን በምን የሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማራ ይሆን? የሚል የጅል ጥያቄ ይመጣብኛል፡፡

የሥራ ዘርፍ ማለት የግድ እኔ የምሠራው፣ ወይም እኔ የማውቃቸው ሰዎች የሚሰሩት ብቻ ማለት እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ዳሩ ግን የእረፍት ቀናት ከሆኑት በላይ በሥራ ቀን የምግብና መጠጥ ቤቶች የበለጠ ሞልተው ሲታይ ‹‹በመብላትና መጠጣት ገቢ የሚገኝበት የሥራ ዘርፍ አለ እንዴ?›› የሚል ጥያቄ ያጭራል፡፡ እሁድ ወይም ሌላ ካላንደር በሚዘጋበት ቀን እንዲያውም በተቃራኒው ካፌዎች ሰው የማይበዛባቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ በሥራ ቀን፣ በሥራ ሰዓት የበለጠ የሚሆንበት ምክንያት ምን ይሆን? ‹‹አየር በአየር›› የሚባለው ሥራ በእንዲህ ዓይነት ቦታዎች የሚሰራ ይሆን?

ለመሆኑ ‹‹አየር በአየር›› ሥራ ምንድነው?

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You