አሜሪካ ለዩክሬን የ61 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ አፀደቀች

የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከወራት ክርክር በኋላ ለዩክሬን በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች ወታደራዊ እርዳታ ለማድረግ ውሳኔ አሳልፏል።

በኮንግረሱ ብዙ ተቃውሞ ገጥሞት የነበረው ይህ የ61 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ ዩክሬን ራሷን ከሩሲያ ወረራ ለመመከት ያግዛታል ተብሏል።

አሁን ድጋፉ ‘መቼ’ ነው ለዩክሬን የሚደርሰው የሚለው ጥያቄ መነጋገሪያ ሆኗል። ምናልባትም በቀናት ውስጥ እርዳታው ለዩክሬን መድረስ እንደሚጀምር መላ ምቶች አሉ።

የሩሲያ ጥቃትን ለመከላከል እጅግ ወሳኝ ለሆነው ወታደራዊ ድጋፍ ምስጋናቸውን የገለጡት የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዜሌንስኪ፤ “ዴሞክራሲ እና ነፃነት ሁሌም ዓለም አቀፍ ጠቀሜታ አላቸው፤ አሜሪካ ድጋፍ ማድረግ ከቀጠለች ደግሞ መቼም ቢሆን አይከስምም” ብለዋል።

አክለው ድጋፉ ጦርነቱ እንዳይስፋፋ ከማድረጉም በላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ይታደጋል ሲሉ ተደምጠዋል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ በበኩላቸው እርዳታው “አሜሪካን የበለጠ ሀብታም ያደርጋታል፤ ዩክሬንን ደግሞ የበለጠ ያላሽቃታል አልፎም ለበርካታ ዩክሬናውያን ሞት ምክንያት ይሆናል” ብለዋል።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በአውሮፓውያኑ የካቲት 2022 ነው ሁሉን አቀፍ ጦርነት ዩክሬን ላይ ያወጁት። በጦርነቱ ከሁለቱም ወገኖች በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች እና ሠላማዊ ዜጎች ሲገደሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዩክሬናውያን ደግሞ ተሰደዋል።

ያለፈው ቅዳሜ ዕለት የፀደቀው እርዳታ ከዩክሬን ባለፈ 26 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ለእስራኤል፤ 9 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ለጋዛ ሰብዓዊ እርዳታ፤ 8 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ ራሳቸውን “ከኮሚዩኒስት ቻይና እንዲጠብቁ” እንደ ታይዋን ላሉ የእስያ ፓሲፊክ ግዛቶች እና ሀገራት ተሰጥቷል።

ምክር ቤቱ ከገንዘብ እርዳታው ባለፈ የቲክ ቶክ ባለቤት የሆነው የቻይናው ኩባንያ ማኅበራዊ ሚዲያውን እንዲሸጥ አሊያም እንዲታገድ የሚለውን ረቂቅ አፅድቋል።

አዋጁ በ311 ድጋፍ እና በ112 ተቃውሞ ሲፀድቅ ምክር ቤቱ በጭብጨባ የቀለጠ ሲሆን አንዳንደ ተወካዮች የዩክሬንን ባንዲራ ሲያውለበልቡ ታይተዋል።

አዋጁ ቀጥሎ ወደ ሴኔት የሚሄድ ሲሆን ሴኔቱ በጥቂት ቀናት ውስጥ ያፀድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል። ቀጥሎ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ይፈርሙበታል።

ፕሬዚዳንት ባይደን የምክር ቤቱን ውሳኔ አወድሰው “ፈርማዬን በፍጥነት አኑሬ ሕግ ከሆነ በኋላ የጦር መሣሪያ እና ሌሎች ቁሳቁሶች ወደ ዩክሬን መላክ አለብን” በማለት ሴኔቱም በፍጥነት እንዲያፀድቀው ጠይቀዋል።

የኔቶ ዋና ፀሐፊ ጄነስ ስቶልተንበርግ ይህ እርዳታ ከአውሮፓ አጋሮች እየተደረገ ያለውን ድጋፍ ያጠናክረዋል ብለዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ኃላፊዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ ደግሞ “ዩክሬን ራሷን ከሩሲያ ለመጠበቅ የሚደርግላት ሁሉ እርዳታ ይገባታል” ሲሉ ተደምጠዋል።

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ኃላፊ ኦሌክሳንደር ሜሬዥኮ ውሳኔውን “ታሪካዊ” ካሉት በኋላ “በእርግጠኝነት የሠላማዊ ዜጎችና ወታደሮችን ሕይወት ይታደጋል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በምዕራባውያን እርዳታ ላይ ጥገኛ የሆነችው ዩክሬን በተለይ በቅርብ ሳምንታት እየገፋ ከመጣው የሩሲያ ጦር ራሷን ለመከላከል ከውጭ የሚመጣ እርዳታ ትሻለች።

የጦር መሣሪያ እጥረት የገጠማቸው የዩክሬን ወታደሮች በጦርነት ቀለሀና ቁሳቁስ እየቆጠቡ እየተጠቀሙ እንደሆነ ተዘግቧል።

ዜሌንስኪ እና የሲአይኤ ኃላፊ ዊሊያም በርንስ ዩክሬን ከአሜሪካ እርዳታ ካልደረሳት በቀር ጦርነቱን መሸነፏ የማይቀር ነው ብለው ነበር።

ባለፉት ስድስት ወራት ሩሲያ በርካታ ግዛቶችን በቁጥጥሯ ሥር ያዋለች ሲሆን ሌሎች ምዕራባውያን የዩክሬን አጋሮች ከአሜሪካ የሚመጣው እርዳታ በመጓተቱ ተፈትነው ነበር።

ምንም እንኳ እርዳታው ዩክሬን ጦርነቱ እንድትረታ ያግዛል ተብሎ ባይጠበቅም ለመዋጋትና ምናልባትም ድርድር ለማድረግ የሚሆን ኃይል እንዲኖራት ያግዛል ተብሏል።

እርዳታው በምክር ቤቱ የተጓተተው አንዳንድ ሪፐብሊካን ፖለቲከኞች ገንዘቡን ለዩክሬን ከምናውለው ይልቅ በአሜሪካ-ሜክሲኮ ላለው የስደተኞች ፍልሰት ልናውለው ይገባል ብለው በመቃወማቸው ነው።

በሚቀጥለው ምርጫ ሪፐብሊካኖች ድምፅ አግኝተው ኮንግረስ መግባት የሚችሉ ከሆነ ለዩክሬን የሚደረገው ድጋፍ ሊቋረጥ ይችላል የሚል ስጋት አለ።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You