12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናና የተማሪዎች ዝግጅት

የባለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል አጠቃላይ መልቀቂያ ፈተና ውጤት አስደሳችነቱ ሲጠበቅ አስደንጋጭነቱ ታውጆ በወቅቱ ፈጥሮት የነበረው አሳዛኝ ስሜት የሚረሳ አይደለም። ጉዳዩ ወደፊትም ቢሆን፣ በተለይም በትምህርት ምሁራን ዘንድ፣ ሳይጠቀሱ ከማይታለፉት ትምህርታዊ ጉዳዮች (መጥፎ ገጠመኞች) መካከል ፊት መሪው እንደሚሆን ይጠበቃል። ወደፊት የሚመጡት የትምህርት ዓለም ሰዎች እንዳይደግሙት በአስተማሪነቱ ሁሌም ቢሆን የሚጠቀስ እንጂ በይሁነኝ ሊታለፍ የሚችል ተራ ጉዳይ አይሆንም።

በተለይ በወቅቱ እንደ አጠቃላይ በማህበረሰቡ፤ እንዲሁም ከራሱ ከተፈታኝ ተማሪው ጀምሮ ቤተሰብ፣ መምህራን፤ እንዲሁም ከአካባቢና የትምህርት ባለሙያዎች ጀምሮ መላው ህብረተሰብን ያሳዘነ፤ ቆም ብሎም እንዲያስብ እድል የሰጠ፤ ከፖሊሲ ጀምሮ በርካታ ነገሮች ዳግም እንዲፈተሹና አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ይሻሻሉ ዘንድ የሚያስገድድ ውጤት ነበር ባለፈው ዓመት የተመዘገበው ያለፉ ተፈታኞች በመቶኛ 3ነጥብ2 ሆኖ የተመዘገበበት።

በወቅቱ የሚመለከታቸው፣ “ከፈረሱ አፍ” እንዲሉ የጉዳዩ ባለቤት የሆኑ ተቋማት እና የየተቋማቱ አስተዳዳሪዎች ሲናገሩት እንደነበረው፤ የተገኘው ውጤት “እጅግ አስደንጋጭ” ብቻ ሳይሆን እጅግም አሳፋሪ ነበር። የዚህ ደግሞ መነሻው ከዛ በፊት በነበሩት ዓመታት በትምህርት ላይ የተሠራው አሻጥር ሲሆን፤ ይህ አሻጥር ከስሩ ተመንግሎ እስካልተጣለ ድረስ ችግሩ የመጨረሻ እልባት ሊያገኝ አይችልም።

በወቅቱ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ሰጥተውት በነበረው መግለጫ እንዳሉት “በ2015 ዓ.ም 845ሺህ ተማሪዎች ፈተናው ላይ ተቀምጠው የማለፊያ፣ ወይም ከግማሽ በላይ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች 27ሺህ 267 (3ነጥብ2 በመቶ) ሲሆኑ፤ (19ሺህ 17 ከተፈጥሮ ሳይንስ፤ 8ሺህ 250 ተማሪዎች ደግሞ ከማህበራዊ ሳይንስ) ብቻ” ነበሩ። ዘንድሮ ይህ ሁሉ ወደኋላ መቅረት፤ ይህ ሁሉ ጉዳትና ሀገራዊ ኪሳራ… ተወግዶ አዲስ ውጤት ይመዘገባል የሚል የብዙዎች ተስፋ ከወዲሁ በስፋት እየሄደ ይገኛል።

ባለፈው ዓመት 649 የተፈጥሮ ሳይንስ ከፍተኛው ውጤት ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፤ በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 533 ሆኖ መመዝገቡ ይታወሳል። ይህም ዘንድሮ፣ የፀጥታ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ሳይጨምር ከ670ሺህ በላይ ተፈታኝ ተማሪዎች ለፈተና ተመዝግበው እየተጠባበቁ ባሉበት ሁኔታ፣ የአምናው ውጤት በከፍተኛ የተፈታኝ ተማሪዎች ጥረት ይቀየራል፤ ተቃራኒ በሆነ መልኩም ይለወጣል ብለው ሃሳባቸውን ከወዲሁ በመሰንዘር ላይ ያሉ ወገኖች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።

በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከተፈተኑት ተማሪዎች መካከል ደግሞ 3ነጥብ2 በመቶ (ወንድ 18ሺህ 383፤ ሴት 8884) የሆኑት ብቻ ከ50 በመቶ በላይ ማምጣታቸውን ተከትሎ በወቅቱ፣ በተለይ የጉዳዩ ባለቤት በሆነው፣ በትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት አስደንጋጭ ተብሎ ሲነገር፤ “አስደንጋጭ” የተባለው ውጤት እንደሚያሳየው ለፈተና ከተቀመጡት ከ980ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል 30ሺህ ገደማ ብቻ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ማግኘት የቻሉ መሆኑ ሲታወጅ ያልተከዘ፤ ቆም ብሎ ወደ ኋላ እና ወደፊት ያላሰበ፤ “ችግሩ ምንድን ነው?” በማለት ራሱንም ሆነ ሌላውን ያልጠየቀ አልነበረም። “ከ50 በመቶ በታች ያመጡ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ መቀላቀል” እንደማይችሉ ሲገለፅም እንደዛው።

ኢዜአ “ዘንድሮ በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ የቅድመ ዝግጅት ሥራ በትኩረት እየሠሩ መሆናቸውን አስተያየታቸውን የሰጡ የአፋርና አማራ ክልል ትምህርት ቢሮዎች ገለፁ።” (ኅዳር 13/2016) በማለት የዘገበውም ሆነ ሌሎች እዚህ ያልጠቀስናቸው የአምናውን 3ነጥብ2 በመቶ ለመቀልበስና የተሻለ ውጤት ለማምጣት ቀን ከሌት በመሥራት ላይ እንደሚሆኑ ከወዲሁ መገመት ይቻላልና ከአምናው ዘንድሩ ጥሩ ውጤት ይጠበቃል።

“ባለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱት 5ሺህ 300 የክልሉ ተማሪዎች መካከል ከ50 በመቶ በላይ ያመጡት 19 ተማሪዎች ብቻ” መሆናቸውን፣ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ “ዓመታትን ያስቆጠረ የትምህርት ጥራት ችግር” መሆኑን ለጣቢያው የተናገሩት የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱ ሀሰን ይህንን ውጤት ለመቀልበስና ከአምናው የተሻለ ውጤት ለማምጣት “ይህን ውጤት ለማሻሻል በክልሉ ያሉ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ከመደበኛ ክፍለ ጊዜ ውጭ የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ” ይገኛል፤ በተጨማሪም “በክልሉ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውና በትምህርታቸው የተሻሉ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የ’አፋር ታለንት አካዳሚ’ ተቋቁሞ ወደ መማር-ማስተማር ስራ ገብቷል”።

ትምህርት ሚኒስቴር ከተፈታኞች ውስጥ 96 በመቶዎቹ ከግማሽ በታች ውጤት ማምጣታቸውን መግለፁን ተከትሎ፣ “ችግሩን ለመፍታት ከመምህራን፣ ከርዕሰ መምህራን፣ ከተማሪ ወላጆችና ከተማሪዎች ጋር ሰፊ ውይይት መደረጉንና ከችግሩ ለመውጣት በአብሮነት መሠራት እንደሚያስፈልግ መግባባት ላይ“ መደረሱን ከላይ የተጠቀሱት የዘርፉ ኃላፊዎች የተናገሩ ሲሆን፣ በሌሎችም ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች ተደርገው ከሆነ የባለፈው ዓመት የ3ነጥብ2 ከመቶ ውጤት ተቀልብሶ የዘንድሮው የዚህን ግልባጭ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መገመት ይቻላል። “ከትምህርት ቤቶችና ተማሪዎች ጀምሮ ሁሉም ያለበትን ሃላፊነት በየደረጃው እንዲወጣ አቅጣጫ አስቀምጠን በቅድመ ዝግጅት ላይ እየሰራን ነው” የተባለውንም ለሌሎች ተሞክሮ ሊሆን የሚችል ከመሆኑ አኳያ እዚህ መጥቀሱ ተገቢ ይሆናል።

በያዝነው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ይሰጣል ተብሎ የጊዜ ሰሌዳ የተጣለለት ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ከሌሎቹ ዓመታት ለየት የሚያደርጉት በርካታ ጉዳዮች ያሉ ሲሆን፤ እንደ ፈተናዎች ድርጅት ከሆነ የፈተና ዝግጅት ሥራው የሀገሪቱን ሥርዓተ ትምህርት የተከተለ እና ተማሪዎቹን በአግባቡ መመዘን በሚያስችል መልኩ መዘጋጀቱ፤ ተማሪዎች በሥነ-ልቦና እራሳቸውን እንዲያዘጋጁ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸው፤ ተማሪዎች የሚፈተኗቸውን የትምህርት ዓይነቶች አውቀው ዝግጅት እንዲያደርጉ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር መከናወኑ፤ ብሔራዊ ፈተናው ለ3ኛ ጊዜ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚሰጥ መሆኑ፤ ትምህርት ሚኒስቴር ለተፈጥሮ ሳይንስ እና ማኅበራዊ ሳይንስ የትምህርት መስኮች፣ ለእያንዳንዳቸው በስድስት የትምህርት ዓይነቶች እንዲሰጥ በወሰነው መሠረት የሚከናወን መሆኑ፤ ባለፈው ዓመት በአማካይ “1 ሺህ 326 ትምህርት ቤቶች ደግሞ አንድም ተማሪ” ያላሳለፉበት ሁኔታ መኖሩና ዘንድሮ ያ ዳግም ይከሰታል ተብሎ የሚጠበቅ አለመሆኑ ወዘተ የሚጠቀሱ ናቸው።

ይህንኑ ፈተና በተመለከተ፣ ምንም እንኳን የብሔራዊ ፈተናዎች ድርጅት “ፀጥታ በሌለባቸው አንዳንድ አካባቢዎች” በሚል ቢያልፈውም፣ በሀገሪቱ ፀጥታ ያለ መኖሩ ጉዳይ ከፍተኛ ችግር ስለመሆኑ አመላካች አካባቢዎች መኖራቸው አልቀረም።

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ተተኪ ኃላፊ አቶ ፀጋ ተሰማ ሰሞኑን እንደገለፁት በብሔረሰብ አስተዳደሩ ስር የሚገኙ 43 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 12ኛ ክፍል ያሏቸው ቢሆንም፣ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ሳቢያ መማር-ማስተማር በሚከናወንባቸው 20 ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ብቻ ያሉ ተማሪዎች ናቸው ሀገራዊ መልቀቂያ ፈተናውን የሚወስዱት። ይህ፣ ከግማሽ በላይ ትምህርት ቤቶችን ከፈተና ውጭ ያደረገው በቂ ማሳያ ነውና የሰላም ማጣት ትርጉሙ ምን እንደሆነ፤ የጉዳቱ ወሰን የት ድረስ እንደሆነ በእግረ መንገድ ሳይሆን በቀጥታ የሚለው አለና ልብ ያለው ሁሉ ልብ ሊል ይገባዋል።

የባለፈው ዓመት 3ነጥብ2 በመቶ ውጤትን በተመለከተ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ ውጤቱን ይፋ ባደረጉበት ወቅት “የመግቢያ ፈተናዎቹ ውጤት ማሽቆልቆል ትምህርት ቤቶች፣ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የተማሪዎች ወላጆች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለትምህርት ጥራት ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጡ ማንቃቱ”ን መግለፃቸው የሚታወስ ነው። በዚሁ የሚኒስትሩ መግለጫ መሠረት አስፈላጊው ሥራ ሁሉ ተሰርቷል ተብሎ ይገመታል ብቻ ሳይሆን ይጠበቃል። በመሆኑም ከባለፈው ዓመት በተሻለ ከዘንድሮው የተሻለ ውጤት ይገኛል ተብሎም ይታሰባል። አምና “አምስት ትምህርት ቤቶች ሁሉንም ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች” እንዳሳለፉ የተመሰከረላቸው ሲሆን፤ ዘንድሮ ይህ ቁጥር በሁለት ዲጂት ያድጋል የሚሉ ወገኖችም አሉ።

ወደ ተፈታኝ ተማሪዎች እንምጣ፤ ዝግጅታቸው ምን እንደሚመስልም እንመልከት። ጨዋታችንንም አላማውን “በተግባር የተደገፈ ትምህርት በመስጠት የላቁ ተመራማሪዎችን ማፍራት” ካደረገው፤ ለየት ያለ የማስተማር ሥነ-ዘዴን በመጠቀም፣ ከመደበኛው ትምህርት አሰጣጥ የተለየ መንገድን በመከተል ላይ ከሚገኘው፤ በአንድ የውጭ ዜጋ በሆኑ መምህር፣ በከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ እና በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ማፍራትን አላማው አድርጎ ወደ ሥራ ከገባው፤ በአጭር ጊዜም ስሙን ከገነባው፤ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ስር ከሚተዳደረው፤ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ምኒልክ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ እንጀምር።

በካምፓሱ ተገኝተን በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚመ ራውን የመማር-ማስተማር ተግባር ከተመለከትን በኋላ ተማሪዎች ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እያደረጉ ያሉትን ዝግጅት በተመለከተ አስተያየት ለመውሰድ በካምፓሱ አግኝተን ያነጋገርናቸው ሊያ ገብሩ እና ናሆም መስፍን የሚከተለውን ብለውናል።

እንደ 12ኛ ክፍሏ ተማሪ ሊያ ገብሩ አስተያየት ከሆነ ፈተና ማለት ምንም ማለት አይደለም። ከሌሎች ፈተናዎችም ተለይቶ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ አይደለም። በፕሮግራም እስከ ተመራን ድረስ፤ በአግባቡ ትምህርታችንን እስከ ተከታተልን ድረስ፤ እስካጠናን እና የቤተሰቦቻችንን እና የመምህራኖቻችን ምክር እና አስተያየት እስከ ሰማን ድረስ ማትሪክ ፈተና ምንም ሊያሳስበን የሚችል የፈተና ዓይነት አይደለም። በቀላሉ ልናልፈው የምንችለው ፈተና ነው።

ሌላው እንግዳችንና የዚሁ ክፍል እና ትምህርት ቤት ተማሪ ናሆም መስፍንም በዚሁ በሊያ አስተያየት ይስማማል። እሱ እንደሚለው ከሆነ ለተማሪ ፕሮግራም ማለት ቁልፍ ጉዳይ ነው። በፕሮግራም መመራት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ ነው። በፕሮግራም ማጥናት፣ በፕሮግራም መጫወት፣ በፕሮግራም መተኛት ወዘተ ለተማሪ መሠረታዊ የሕይወት መርሆች መሆን አለባቸው። ካልሆነ ብዙ ነገሮች ይበላሻሉ።

መኖሪያዋ ገርጂ አካባቢ የሆነው ሊያ ገብሩ እንደምትመሰክረው ከሆነ ለውጤታማነቷ የመምህ ሮቿና የአጠቃላይ የካምፓሱ አስተዳደር ድርሻ እንዲህ በቀላሉ የሚታለፍ ወይም የሚታይ ጉዳይ አይደለም። ባለውለታዎች ናቸው። ያለ እነሱ መልካም እና ቤተሰባዊ ተግባር ስለ ጥሩ ውጤት መናገር አይቻልም። ይመክሯቸዋል። ያግዟቸዋል። በተለይ ከማትሪክ ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ እንዲለማመዱ የሚያደርጉላቸው ከፍተኛ ጥረት ቀላል አይደለም።

ከሰሚት አካባቢ የመጣው ናሆም እንደነገረን ከሆነ እሱ ለጥናት የሚፈልገው አካባቢ በፀጥታ የተሞላ ሲሆን፤ ጊዜውም ሌሊት ቢሆን ይመርጣል።

ከኬጂ እስከ 8ኛ ክፍል በሁለት ትምህርት ቤቶች (ሀርመኒ እና ሳፋሪ አካዳሚ) ትምህርቱን የተከታተለውና ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ወደ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ምኒልክ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ የገባው ተማሪ ናሆም ከትምህርት ቤት ይገባል፤ ካስፈለገ ትንሽ ዘና ይላል፤ በጊዜ ይተኛል፤ ሰዎች ከተኙ በኋላ በመነሳት ያጠናል፤ ካስፈለገም ያነጋል።

እንደ ናሆም አስተያየት ዘንድሮ 12ኛ ክፍሎች ስድስት ስድስት የትምህርት ዓይነቶችን ይፈተናሉ። እንደ የአንድ ትምህርት ተቋም ተፈተኞች (ባች) ሁሉም በሁሉም ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የትምህርት ቤቱን የውጤት የበላይነት ማስጠበቅ ይፈልጋሉ። በዚሁ መሠረትም እየተዘጋጁ ይገኛሉ። በመምህራን በኩልም እየተደረገላቸው ያለው እገዛ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ነው።

ትምህርቷን እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ በቪዥን አካዳሚ በመከታተል፤ ከፍተኛ የሚኒስትሪ ውጤት በማውጣት ወደ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ምኒልክ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ የመጣችው ሊያም እንደ ትምህርት ተቋም ሁሉም ከፍተኛ ውጤት ማምጣትን ታሳቢ አድርገው ነው እየተዘጋጁ ያሉት። መምህራኖችም የማትሪክ ጥያቄዎችን ከማለማመድ ጀምሮ በቅርብ በመከታተልና በመርዳት እያደረጉ ያሉት ይህንኑ እነሱን የማብቃት ሥራ ነው።

የግል ዝግጅቷን በተመለከተም እንደምትናገረው ማትሪክ ነው ብላ ምንም የምታካብደው ነገር የለም፤ ከመማሪያ-ማስተማሪያ መጻሕፍት ጀምሮ፤ አጋዥ መጻሕፍትን አካትቶ የማታነባቸው ተያያዥ ጽሁፎች የሉም። በመምህራን በኩል የሚቀርቡ ገለፃዎችንም ሆነ የላቦራቶሪ ሙከራዎችን በጉጉትና በፍቅር ነው የምትከታተለው። ወለም ዘለምን አታውቅም።

የሊያ እና የኖሆም የመጨረሻ አስተያየትና የአቻ ምክር የዘንድሮ ተፈታኞች በሙሉ በርትተው ማጥናት፣ ማጥናት፣ ማጥናት ያለባቸው መሆኑ፤ ገና ለገና ብሔራዊ ፈተና ነው ብሎ ማካበድና ከባድ አድርጎ ማየት የማያስፈልግ መሆኑ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፤ በራስ የአጠናን ስልትና ፍላጎት መሠረት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ላይ ያተኮረ ነው። እኛም የእነዚህኑ ጎበዛዝት ምክርና አስተያየት በማጋራት አበቃን።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You