የቅናት ዛር

ይወዳታል ከልቡ። ፍቅር እንዲህ ከሆነ በአፍንጫዬ ይውጣ በሚባል ልክ ያፈቅራታል፡፡ ፍቅር መገለጫው ሳይገባው ግን ያፈቅራታል። ዓይኑ ስር ሆና ምን እያሰበች ይሆን ብሎ በቅናት የሚቃጠል ዓይነት ሰው ነው። በሁለቱ መካከል ያለው የእድሜ ልዩነት ግን ፍቅሩን በአግባቡ እንዳያጣጥም አድርጎታል።

አይደለም ወጣ ገባ ብላ ቤት ውስጥም ብትሆን አምሮባት ሲመለከት በቅናት እርር ድብን ይላል። የመዋደድ ሚዛኑ ግራ ገብቶት በስጦታ እያንበሸበሸ ሚስቱን የሚቀጠቅጠው አባ ወራ አሁንም ለዱላው ምክንያት አድርጎ የሚያቀረብው ይህንኑ ፍቅር ነው። ቅናት በተቃራኒ ፆታ ግንኙነት ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጠር የሚችል ቢሆንም ለእርሱ ግን የሚወደውን ሰው ከማጣት ጋር የተያያዘ የስጋት እና ሽብር ስሜት ፈጥሮበታል፡፡ ለዚህም ይመስላል እራሱ ገዝቶ አልብሶ ለብሳ ሲመለከታት ተናዶ ወደ ዱላ የሚገባው።

ፍቅር መልካም ስሜት ሊፈጥርበት ሲገባው በሽብር ስሜት ይሰቃያል። ይህ በተለያዩ ምክንያቶች ቢፈጠርበትም የፍቅሩን ጫና እያሰበ በቀላሉ ሊያልፈው ሲታገል ሰነባብቷል። በፍቅሯ የወደቀላትን ልጅ እጁ ካስገባም በኋላ ምንም ልቡ ሊያረፍለት አልቻለም።

ወዳና ፈቅዳ የትዳር አጋሩም ብትሆን ቅሉ የእርሱ ልብ ግን ትታኝ ትሄዳለች በሚል ስጋት ተወጥሮ ትኩሱን ፍቅሩን እንዳያጣጥም እግር ከወርች አስሮታል። ይህ የቅናት ስሜት በሚፈጠርበት ወቅት ስሜቱን ለመግለፅ ቃላትን ሳይሆን ጉልበትን መጠቀም እንዲጀምር አድርጎታል። በግልፅ ስለጉዳዩ ከመወያየት ይልቅ ባለቤቱ ላይ ለዱላ ሲጋበዝ መታየት የተለመደ ሆነ፡፡

ቤት ውስጥ ተቀምጣ የምትውለው የትዳር አጋሩ ‹‹ምን እያደረገች ይሆን?›› በማለት ቀኑን ሙሉ እየተብሰለሰል መዋል አልፎ ተርፎም ቀኑን ብቻ ሳይሆን ሌሊትም ኮርኒስ እየቆጠረ ነገር መብላት ሥራው ሆነ።

የእሱ የቅናት ስሜት ከፍቅር የመነጨ ሳይሆን ከእምነት ማጣት የመጣ እንደሆነ መረዳት ተስኖታል፤ እሷም ለትዳር አጋሯ ውሎዋን ለመናገር ወይም አንተ በሌለህበት ሰዓት የተፈጠሩ ነገሮችን እነዚህ ናቸው ማለት ከብዷታል።

በቅናት ምክንያት ባለቤቷ ለምግብ ያለው ፍላጎት ቀንሷል። እሷም በእርሱ ምክንያት ጭንቀት ውስጥ ከገባች ሰነባብታለች። ባለቤቷ ወደቤት ሲገባ እንደ መደሰት ፈንታ በጭንቀት የልብ ምቷ የሚጨምርበት ሁኔታ ተፈጠረ።

እሱን ስታይ በጭንቀት ከልክ በላይ ያልባት ገባ። ጭንቀቱ ነው መስል ቶሎ ቶሎ መድከምም መገለጫዋ ሆነ። በመጨረሻም ቅናት ከትዳር አጋሯ ጋር ያላት ግንኙነት ላይ ክፍተት እየተፈጠረ መጣ፡፡

አባወራው ይሄ ቅናት የዕለት ተዕለት ኑሯቸው ጋር እየተጋጨ መሆኑን ቢረዳም የሚያፈቅራትን ሴት እያሳዘነ እና እየጎዳ እንደሆነ ቢገነዘብም ቅናቱ እርሱ ራሱን ከምቆጣጠረው በላይ እሱ ተቆጣጥሮት ነበር።

የባልየው ቅናት ባለቤቴ በሥራ ብዙ ሰዓቷን የምታሳልፍ ወይንም ብዙ ጊዜዋን በማንበብ የምታሳልፈው ሆን ብላ ከእኔ ለመራቅ ብላ ነው በማለት በቅናት እርር ድብን ሲል ይታያል፡፡ በቅናቱም ምክንያት የፍቅር ግንኙነቱን እየሻከረ መምጣት ጀመረ።

ሰውየው ‹‹እርር ድብን ማለት አንገሽግሾኛል፤ ጨጓራዬን ልተፋው ነው፤ አንድ በሉኝ›› በማለት ወዳጅ ዘመዱን ቢያማክርም ምንም ዓይነት መፍትሔ ሊያገኝ አልቻለም። ውስጥ ውስጡን እየበላ ከቁጥጥር ውጭ ያደረገው ቅናትን ፈፅሞ ልያጠፋው አለመቻሉ ከብዶታል።

የሚገርመው የአስራ አምስት ዓመት ሴት ልጁም ውጭ ቆይታ ከመጣች ከእናቷ ባልተናነሰ ሁኔታ ይቀጠቅጣታል። ከሁሉ በላይ ̋እንደ እናትሽ መሆን ፈለግሽ ? ̋ እያለ የሚያወጣው የስድብ ቃል አፍላዋ ልጁ ጀርባዋን እንድትሰጠው ካደረጋት ሰነባብቷል። የልጅና የእናትዬው በሁኔታው መሰላቸትና ውጭ ውጭ ማለት ይበልጥ እያሳበደው ራሱን መቆጣጠር የማይችልበት ደረጃ አደረሰው።

አስከፊው ቀን

በትዳር በርካታ ዓመታትን አሳልፈዋል። የባልዬው አመል ከሠርጉ ቀን አንስቶ የነበረ ቢሆንም እለት እለት ተግተው ለፍተው ያፈሩት ጥሪት ሲበረክት ቤታቸው በሀብት ሲሞላ አናኗራቸው ሲቀየር ቅናቱ ተባብሶ ቀጠለ። ዘይኑ ፈረጃ ምራ ይባላል። ይህ ሰው ሚስቴ ትታኝ ልትሄድ ነው በሚል ምክንያት ጥቅምት 6 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ በኮልፌ ቀራንዬ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ቤቴል ወይራ ሰፈር አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በር ላይ የትዳር አጋሩ ጋር ፀብ ውስጥ ይገባል።

ይህች የትዳር አጋሩ የሆነችውን ወይዘሮ ጀሚላ ሰኢድ መኪና ውስጥ ተቀምጣ እያለ ነበር ባል ሌላ ባል አግብተሽ ልጆቹን ይዘሽ ወደ ውጭ ልትሄጂ ነው እያለ መጮህ የጀመረው። በኃይለ ቃል ሲናገር የቆየው ባልም በእጁ ይዞት የነበረውን የምንጣፍ መቁረጫ እያሳየ በዚህ ቆራርጬ ነው የምጥልሽ እያለ ይጮህ ነበር።

በመቀጠል እጁን ወደ መኪናው ጋቢና በማስገባት እንዳትጮህ አፏን ካፈናት በኋላ ከተር እየተባለ በሚጠራ ስለታማ የምንጣፍ መቁረጫ የተለያዩ የሰውነት አካሏን በመውጋት ከፍተኛ ጉዳት አደረሰባት። ከዛ በኋላ ከመኪና ውስጥ ጎትቶ በማውረድ መሬት ላይ ጥሏት በወደቀችበት በያዘው ስለት ጀርባዋን እና ትከሻዋን ደጋግሞ በመውጋት የግድያ ሙከራ በማድረስ ሊያመልጥ ሙከራ አደረገ።

የአባትና ልጅ ጦርነት

አባትዬው ከእናቷ ጋር በተጣላ ቁጥር ልጁን የንዴት ማብረጃ ማድረግ ከጀመረ ሰነባብታል። ልጅቷን በሰብበ አስባቡ የሚቀጠቀጣትም ቢሆን እናት ገበናዋን ለመሸፈን በሚል ልጇን እያባበለች ነገሩ ከቤታቸው ውጭ እንዳይሰማ ስታደርግ ቆይታለች።

የትዳሯ ህልውና እንዳይናጋ በተቻላት መጠን መልካም ነገሮችን በጥንቃቄና በትእግስት እያደረገች ብትቆይም ምንም ዓይነት የባህሪ መሻሻል ባለቤቷ ላይ መመልከት አልቻለቸም ነበር። ከሁሉ በላይ ገና ሮጣ ያልጠገበች ሴት ልጃቸው ላይ የሚያደርገው ነገር ትእግስቷን እያስጨረሳት ነው።

በታኅሣሥ 14 ቀን 2014 ዓ.ም ቀኑን ሙሉ ሚስቱን እየተከተለ በነገር ሲሸነቁጣት የዋለው ባል በግምት ከቀኑ 9፡30 አካባቢ ሲሆን መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የ15 ዓመት ልጅ የሆነችው ልጃቸውን ከትምህርት ቤት ስትመለስ አርፍደሻል በሚል ምክንያት በመጥረጊያ እንጨት እና በመጋረጃ መስቀያ ብረት ደጋግሞ በመምታት እጇ፣ ጭንቅላቷ እና እግሯ እንዲያብጥ አድርጓት የነበረ ቢሆንም የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው በሰላም መኖር ጀምረው ነበር።

በተመሳሳይም በነሐሴ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት አካባቢም ይህች የ15 ዓመት የሆነችው ልጁ ያለምንም ምክንያት በኤሌክትሪክ ገመድ ጀርባዋ እና እግሮቿን ደጋግሞ በመምታት ጀርባዋ እና እግሮቿ እንዲቆስሉና እንዲያብጡ አድርጓትም ነበር።

እናትና ልጅን በየተራ ሲያሰቃይ የቆየው ባልና አባት ለቤተሰባቸው ደህንነት ሲሉ በዝምታ የሚያልፉትን ሚስትና ልጁን መቀጥቀጥ መብቱ እንደሆነ በማድረግ ሲያደርስ የነበረው ድብደባ አልበቃ ብሎት ባለቤቱን ክፉኛ በማቁሰል ከአካባቢው ይሰወራል።

የፖሊስ ምርመራ

ወይዘሮ ጀሚላ ክፉኛ ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውን የሰማው ፖሊስ በመኖሪያ ቤታቸውና ወይዘሮዋ በተኙበት ሆስፒታል ባደረገው ምርመራ መሠረት የገዛ ባለቤታቸው ጉዳቱን በማድረግ የተሰወረ መሆኑን ይረዳል። ፖሊስ ወንጀለኛው መሰወሩን ከሰማ በኋላ በክትትል ተይዞ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ተጣርቶበት እንዲቀርብ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።

ተጠርጣሪው በሕዝብና በፀጥታ ኃይሎች ርብርብ በቁጥጥር ሲል ቢውልም ̋የተፈጠረው ተራ ግጭት እንጂ በዚህ ልክ እኔ ጉዳት አላደረስኩም ̋ በማለት የእምነት ክህደት ቃል ቢሰጡም፤ የዓይን አማኞች ምስክርነት፤ የተበዳዮች ቃልን በመቀበል ሰውዬው ለፈፀመው ወንጀል ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ለማድረግ ፖሊስ መረጃውን አጠናቀረ።

መረጃውንና ማስረጃውን በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በማቅረብም ወንጀለኛው ክስ እንዲመሰረትበት አደረገ።

የዐቃቤ ሕግ ክስ ዝርዘር

በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወ/ሕ/አ በ27/1/ እና 539/1/ሀ/ እንዲሁም በወ/ሕ/አ 556/2/ሀ እና /ሐ/ ላይ በተደነገገው መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ያቀረበው የክስ ዝርዝር።

ዘይኑ ፈረጃ ምራ የተባለ ተከሳሽ ጥቅምት 6 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ሲሆን በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ቤቴል ወይራ ሰፈር አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በር ላይ የትዳር አጋሩ የሆነችውን የግል ተበዳይ ጀሚላ ሰኢድ መኪና ውስጥ ተቀምጣ እያለ ሌላ ባል አግብተሽ ልጆቹን ይዘሽ ወደ ውጭ ልትሄጂ ነው በሚል ምክንያት ቆራርጬ ነው የምጥልሽ እያለ እጁን ወደ መኪናው ጋቢና በማስገባት እንዳትጮህ አፏን ካፈናት በኋላ ከተር እየተባለ በሚጠራ ስለታማ የምንጣፍ መቁረጫ የተለያዩ የሰውነት አካሏን በመውጋት ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰ በኋላ ከመኪና ውስጥ ጎትቶ በማውረድ መሬት ላይ ጥሏት በወደቀችበት በያዘው ስለት ጀርባዋን እና ትከሻዋን ደጋግሞ በመውጋት የግድያ ሙከራ በማድረስ ወንጀል፤

በተጨማሪም በታኅሣሥ 14 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 9፡30 ከላይ በተጠቀሰው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የ15 ዓመት የሆነችው ልጁ ከት/ቤት ስትመለስ አርፍደሻል በሚል ምክንያት በመጥረጊያ እንጨት እና በመጋረጃ መስቀያ ብረት ደጋግሞ በመምታት እጇ፣ ጭንቅላቷ እና እግሯ እንዲያብጥ በማድረግ እንዲሁም በነሐሴ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት አካባቢም ይህች የ15 ዓመት የሆነችው ልጁ ያለምንም ምክንያት በኤሌክትሪክ ገመድ ጀርባዋ እና እግሮቿን ደጋግሞ በመምታት ጀርባዋ እና እግሮቿ እንዲቆስሉና እንዲያብጡ በማድረግ ከተሰወረ በኋላ በክትትል ተይዞ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ተጣርቶበት በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወ/ ሕ/አ በ27/1/ እና 539/1/ሀ/ እንዲሁም በወ/ሕ/አ 556/2/ሀ እና /ሐ/ ላይ በተደነገገው መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ውሳኔ

በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክሮች አቅርቦ ያሰማ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበውን ክስ መከላከል ባለመቻሉ ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት 11 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኗል፡፡

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You