– ኢፕድ በሥልጠና ማዕከሉ ለሰባት ተቋማት ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፦ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሥልጠና ማዕከል ያገኘነው ሥልጠና ሥራችንን በብቃት ለመፈጸም ትልቅ ስንቅ ያገኘንበት ነው ሲሉ ሥልጠናውን የተከታተሉ ሠልጣኞች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሥልጠና ማዕከሉ ከመጋቢት 26 እስከ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በፎቶ ጋዜጠኝነት፣ በግራፊክስ አርት እና በብራንዲንግ ንድፈ ሃሳብና ቴክኒክ የሥልጠና ዘርፎች ለሰባት ተቋማት ባለሙያዎች ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ትናንት ተጠናቋል።
የፎቶ ጋዜጠኝነት ሠልጣኝ እና ከአዲስ አበባ አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ሠራተኛ አቶ ተስፋዬ ዘውዱ እንደገለጹት፤ በተለያዩ ጊዜያት የፎቶ ጋዜጠኝነትን ንድፈ ሃሳብ የመማር እድሉ ገጥሞኛል። ነገር ግን ተግባር ተኮር ሥልጠና ያገኘሁት በኢፕድ ሥልጠና ማዕከል ነው።
“ይህ ሥልጠና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሥራ የሚያግዝ እውቀት እንድጨብጥ አድርጎኛል” ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ በኢፕድ ሥልጠና ማዕከል ያገኙት ሥልጠና ለሥራቸው ትልቅ ግብዓት ያገኙበት እንደሆነ ገልጸዋል።
ኢፕድ ለረጅም ዓመታት ያካበተውን ልምድ ለሌሎች ተቋማት ለማካፈል የሥልጠና ማዕከል መክፈቱ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
የግራፊክስ አርት ሠልጣኝ እና የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ሠራተኛ አቶ ሙላቱ ሙጨ በበኩላቸው፤ በተሰጣቸው ሥልጠና ትልቅ እውቀት እንዳገኙበት ገልጸው፤ በቀጣይ ያገኙትን እውቀት በመደበኛ ሥራቸው እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል።
በአሠልጣኞቹ ብቃት መደሰታቸውን የገለጹት አቶ ሙላቱ፤ የሥልጠናው ጊዜ ቢራዘም ለሥራቸው እንደሚያግዛቸው እና በተለያዩ የሥልጠና ዓይነቶች በኢፕድ ሥልጠና ማዕከል መውሰድ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድም ተክሉ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ኢፕድ በየዘመኑ እያካበተ የመጣውን ልምድ ለሌሎች ተቋማት ማካፈል አለበት በሚል በአሥር ዓመት ስትራቴጂክ እቅዱ ውስጥ አካትቶ እየሠራ ነው።
ለፌዴራልና ለክልል አመራሮችና ባለሙያዎች ያለባቸውን ክፍተት ለመሙላት የሥልጠና ማዕከል አቋቁሞ እየሠራ ነው ያሉት አቶ ወንድም፤ በሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ተቋማት ውጤታማ እንዲሆኑ የተለያዩ የሥልጠና ዓይነቶችን አዘጋጅቶ እያሠለጠነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በተለይም የተቋማት ውስንነቶችን በማረም ወደ ሥራ ከማስገባት አንጻር ውስንነቶች አሉ ያሉት አቶ ወንድም፤ ኢፕድ በሥልጠና ማዕከሉ የሚሰጠው ሥልጠና በተቋማት የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ለማረም ይረዳል። ይህም የተቋምን ገጽታ በስፋት በማስተዋወቅ እና የሚሰነዘሩ ትችቶች እንዲታረሙ በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ ሠልጣኞች ባሉበት የሥራ ቦታ የተሰጣቸውን ሥልጠና ውጤታማ እንዲያደርጉ የሚያስችል ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸው፤ ኢፕድ በሥልጠና ማዕከል በተያዘው በጀት ዓመት ማለትም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ60 በላይ የሚሆኑ ተቋማት ሙያተኞችን ማሠልጠኑን ተናግረዋል።
ሥልጠናቸውን ያጠናቀቁት ሠልጣኞች የሥልጠና ማዕከሉ 25ኛ ዙር ሠልጣኞች ሲሆኑ፤ ከዚህ በፊት የኢፕድ ሥልጠና ማዕከል በ24 ዙሮች የፌዴራልና የክልል ተቋማትን ሠራተኞችና አመራሮችን በተለያዩ የሥልጠና ፕሮግራሞች አሠልጥኗል።
ከዳግማዊ ምኒልክ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን ድርጅት፣ ከፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት፣ ከ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ፣ ከአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕፃናት እና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ፣ ከአዲስ አበባ አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን እና ከግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር የተውጣጡ 25 ሠልጣኞች ሥልጠናውን ተከታትለዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም