አዲስ አበባ፡- ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን አጋርነት፣ በፌደራሊዝም ሥርዓት ትግበራ ላይ ጠቃሚ ምክረሃሳቦችን በመስጠት፣ የልምድ ልውውጥ በማድረግና ጥናቶችን በማካሄድ ወዳጅነታቸውን እንደሚያጠናከሩ መቀመጫቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ የቤልጂየም እና ብራዚል አምባሳደሮች አስታወቁ፡፡
በኢትዮጵያ የቤልጂየም አምባሳደር የሆኑት ሚስተር ፍራንሲስ ዱሞንት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ ቤልጂየም በአገራቱ መካከል ያለው የምክክር ልምድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየሠራች ነው፡፡
ኢትዮጵያ የቤልጅየም ዋነኛ አጋር አገር መሆኗን ጠቁመው፤ ኢንተር ዩኒቨርሲቲ ኮርፖሬሽን ፎር ዴቭሎፕመንት በሚል ከፍሊሚሽ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል ጋር ወዳጅነት ተፈጥሯል፤ ይህም በቤልጂየም የልማት አጋርነት የሚደገፍ ነው፡፡ በዚህም የልምድ ልውውጥ የኢትዮ-ቤልጂየም ፌዴራሊዝም ጥናት መርሐ ግብር ተመስርቷል፡፡ በመርሐ ግብሩም በፌዴራሊዝም ሥርዓት ፅንሰ ሃሳብ መሰረት የኢትዮጵያን ፌዴራሊዝም መመዘንና በሁለቱ አገራት መካከል ግንኙነትን ማጠናከርን ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ ሚስተር ፍራንሲስ ዱሞንት ገለፃ፤ በቤልጅየም ክልሎች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩና የየራሳቸው ፓርላማ እንዲኖራቸው እውቅና ተሰጥቷል፡፡ ይህም ክልሎቹ ውስጣዊ እና ውጫዊ ግንኙነቶችን ለማድረግ መብት የሚኖራቸው ሲሆን፤ የፌዴራል መንግስቱን ህግ ማክበር ግዴታቸው እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ ይህም ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ የብራዚል ምክትል አምባሳደር ሚስተር ዦ ማርሴሎ ሞንቴኔግሮ በበኩላቸው፤ ሁለቱ አገራት እንደየአገራቸው ነባራዊ ሁኔታ በፌዴራሊዝም ባለሙያዎች የተደገፈ ምክክር የሚያካሂዱ ሲሆን፤ የየአገራቱን ልምዶች ለመለዋወጥም በጋራ እየሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ፌዴራሊዝም በውይይቶች በታገዘ ሃሳብ የሚያድግ መሆኑን ገልጸው፤ብራዚል ከኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ሥርዓት፤ስኬቶችና ተላምዶዎች መቅሠም የምትፈልጋቸው ጉዳዮች መኖራቸውንም አስገንዝበዋል፡፡ ሁለቱ አገራት በፌዴራል ሥርዓት እንደመተዳደራቸው መጠን አንዳቸው ከሌላኛው ልምድ እንደሚቀስሙ ተናግረዋል፡፡
«በብራዚል ከሚገኘው ገቢ ከ60 እስከ 70 ከመቶ የሚሆነው ለፌዴራል መንግስት ገቢ ይደረጋል» ያሉት ዦ ማርሴሎ ሞንቴኔግሮ፤ ቀሪው ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የሚጠቀሙበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በብራዚል የፌዴራሊዝም ሥርዓት በመልክአምድራዊ አቀማመጥ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ ከዋና የአገሪቱ ክፍል መገንጠልን ባይፈቅድም እያንዳንዱ ግዛት ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር