የፋይናንስ አቅርቦትን ማሻሻል- የግሉን ዘርፍ ለማጠናከር

በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ድርሻ ያለው የንግዱ ማህበረሰብ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የሀገሪቱን ገቢና የውጭ ምንዛሪ በማሳደግ እንዲሁም አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እንዲጨምር በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።ይህም ሚናው እየጨመረ የመጣው ሲሆን፣ አሁንም ሚናው የበለጠ እንዲጎለብት ለማድረግ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ከማድረግ አንስቶ የፋይናንስ ድጋፎችን ማድረግ ከመንግሥትና ከሚመለከታቸው አካላት እንደሚጠበቅ ይታመናል።

ይሁንና በአሁኑ ወቅት ለንግዱ ማህበረሰብ ወሳኝ ሚና ያለው የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት የዘርፉ ዋነኛ ማነቆ መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ያስጠናው ጥናት አመላክቷል።ምክር ቤቱ ከሰሞኑ “የብድር አቅርቦት ፋይዳ ለቢዝነስ” በሚል መሪ ሃሳብ ከባንክና የፋይናንስ ተቋማት፣ ከንግዱ ማህበረሰብ እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። ውይይቱም ችግሩን በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ጠቃሚ እንደሆነ ተጠቁሟል።

በውይይቱ የንግዱ ዘርፍ ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ዕድገት ያለውን ሚና አሟጦ መጫወት እንዲችል ማነቆ የሆነበትን ይህን የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት መቅረፍ የግድ መሆኑ ተገልጿል።ችግሩን በልኩ የተረዳው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የፋይናንስ አቅርቦቱን እጥረት ምክንያት ማወቅ የመፍትሔ ግማሽ ነው እንደሚባለው የንግዱ ማህበረሰብ ያለበትን ችግር ለመለየት የሚያስችል ጥናት ማስደረጉ ተጠቅሷል።ጥናቱ እንዳመላከተው፤ የንግዱ ዘርፍ ማነቆ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት 40 በመቶ ድርሻ ያለው መሆኑ አለው፡፡

በተለያዩ የንግድ ዘርፎች የተሰማሩት የንግዱ ማህበረሰቦች ካነሷቸው ችግሮች መካከል የብድር አቅርቦት ትልቁ ሆኗል።ከፋይናንስ አቅርቦት በተጨማሪ የተለያዩ ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸው አመልክተው፣ የንግድ ሥራቸውን ለማቀላጠፍ የፋይናንስ አቅርቦት ወሳኝ እንደሆነ አስታውቀዋል።የብድር አቅርቦት እጥረት ትልቁ ፈተና ነው ሲሉም ተናግረው፣ ነጋዴው ከባንክ ብድር ለማግኘት የሚወስደው ጊዜ ረዘም ያለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በንግድ ሥራው ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በመሆን በተለያየ ጊዜ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፤ በተለይም በአሁኑ ወቅት የብድር አቅርቦት እጥረት በንግዱ ማህበረሰብ ላይ እያደረሰ ያለውን ጫና ለመከላከል ምን መደረግ አለበት በሚል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ማድረጉን አበረታች ሲሉ ተናግረው፣ መድረኩ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባም እንደሆነ አስታውቀዋል።

ከ17 ሺ የሚልቁ አባላት ያሉት የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ‹‹የብድር አቅርቦት ፋይዳ ለቢዝነስ›› በሚል መሪ ሃሳብ ከሚመለከታቸው አካላትጋር ባደረገው በዚህ ውይይትም የብድር አቅርቦት ሚናን፤ የግሉ ዘርፍ የብድር ተጠቃሚነትንና የሚታዩ ችግሮችን በሚመለከት እንዲሁም የብድር አሰጣጥ ተደራሽነትና በንግድ ባንኮች የብድር አሰጣጥ ዙሪያ ያጋጠሙ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው የሚሉት ጉዳዮች ተነስተዋል።

የብሔራዊ ባንኩ ጽሑፍ አቅራቢ አቶ በለጠ አፎላ እንዳሉት፤ ብሔራዊ ባንክ በአዋጅ ከተሰጡት ተግባራት መካከል ለፋይናንስ ተቋማት ፈቃድ መስጠትና ተቋማቱን መቆጣጠር አንዱ ሥራው ነው።በመሆኑም ከብድር ፖሊሲ ጋር በተያያዘ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል።ለዚህም ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ማግኘት የሚችሉት የብድር ፖሊሲ ማውጣት ሲችሉ እንደሆነና ሕጉ አስገዳጅ ሕግ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

የባንክ ቦርድ ዳይሬክተሮች ዋና ኃላፊነት የብድር ፖሊሲን ማውጣት፣ ማሻሻልና ተቀባይነታቸው የተሟላ መሆኑን ማረጋገጥ ነው።ከዚህ ባሻገር የወጡ ፖሊሲዎችና ሕጎች ላይ በየጊዜው ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ በትግበራ ሂደት አላግባብ የሚሠሩ ሥራዎች ካሉም የማረም ኃላፊነት ያለባቸው ሲሆን፤ በዚህም ለተበዳሪዎች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርና ማመቻቸትን ይጨምራል ነው ያሉት፡፡

ከተበዳሪዎች አንጻር ብድር ከመክፈል ጋር የተያያዙ ችግሮች ሲያጋጥሙ ተጨማሪ ብድር መጠየቅ የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ ስለመኖሩ ያነሱት አቶ በለጠ፤ ተበዳሪው ብድሩን የሚከፍልበትን ጊዜ ከማራዘም ጀምሮ የብድር ዓይነቶችን በመቀያየር እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም የሚችልባቸው ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውም ገልጸዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ በተለያየ ምክንያት የብድር አቅርቦት ጉዳይ በሚበላሽበት ወቅትም እንዲሁ በተሻሻለው መመሪያ መሠረት ከአምስት እስከ ስድስት ጊዜና ተጨማሪ ብድር መጠየቅና በተለያየ የአከፋፈል ሁኔታ መክፈልና ማስታመም የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ስለመኖሩም ጠቁመዋል፡፡

ብድር ከመሰጠቱ አስቀድሞ ተበዳሪዎች በብድር አሰጣጥ ዙሪያ ስላሉ መመሪያዎችና ደንቦች በሚገባ ማወቅ አለባቸው የሚሉት አቶ በለጠ፤ መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ይህ አለመሆኑን ነው ያስታወቁት።አስገዳጅ መመሪያው ላይ በግልጽ የተቀመጡትን ሁሉ ተበዳሪዎች ማወቅና መረዳት ይኖርባቸዋል።ተበዳሪዎች ይህን መረዳት ሲችሉ ማንኛውንም ቅሬታ ይዘው መቅረብና ለችግሩ የተቀመጡ የተለያዩ የመፍትሔ አማራጮችን መጠቀምና ችግሮቻቸውን መፍታት ይችላሉ ሲሉ አስገንዝበዋል።

ባንኮችም ብድር ከመስጠት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ስለመኖራቸው የጠቀሱት አቶ በለጠ፤ ደንበኞች ብድራቸውን በራሳቸው ፍላጎትና ተነሳሽነት ለመክፈል ጥረት ሲያደርጉ አይታዩም ይላሉ።ተበዳሪዎች ብድር ከመክፈል ሳይሆን ላለመክፈል የተለያዩ ምክንያቶችን እንደሚያቀርቡ ገልጸው፣ እንዲህ ዓይነት ዝንባሌዎች በተበዳሪዎች በኩል የሚስተዋሉ ባንኮችን የሚጠቅሷቸው ቁልፍ ችግሮች እንደሆኑም አብራርተዋል።

በግሉ ዘርፍ የብድር ተጠቃሚነት እና ተግዳሮቶች ላይ ጽሑፍ ያቀረቡት የዘርፉ ባለሙያና ከንግድ ምክር ቤቱ ጋር ለረጅም ጊዜ የሠሩት አቶ ጌታቸው ተክለማርያም ለሀገሪቱ የግል ዘርፍ የሚደረግ የብድር አቅርቦት ከምጣኔ አንጻር እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

የፋይናንስ አቅርቦቱን ከማሻሻል አንጻር ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለ መሆኑንም ጠቁመዋል።የሀገሪቷን ኢኮኖሚ ለማሳደግ፣ የተሻለ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የግሉ ዘርፍ ያለበትን ችግር ቀርፎ የተሻለ አቅም ያለው የግል ዘርፍ ለመፍጠር ውስን የሆነውን ሀብት በአግባቡ መጠቀም የግድ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በኢኮኖሚው ውስጥ ሁለት መሠረታዊ ለውጦች ተመዝግበዋል ያሉት አቶ ጌታቸው፣ አንደኛው ከዚህ ቀደም የመንግሥት ፕሮጀክቶች እንደሚበዙና የግሉ ዘርፍ ቁጥር የተመናመነበት ጊዜ እንደነበር አስታውሰዋል።ተገቢነት የሌለው የካፒታል ክፍፍል እንደነበረም ገልጸው፤ በወቅቱ የነበረው መንግሥትም ይህን ያምን ስለነበር ተግባራዊ ሆኗል ብለዋል።

አሁን እንደ ፖሊሲ ተሻሽሎ ለግሉ ዘርፍ የተሻለ ዕድል ሊሰጠው እንደሚገባ ታምኖበት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።የግሉ ዘርፍ የተሻለ ኢኮኖሚውን ማንቀሳቀስ የሚችል አቅም እንዳለው በማመን መንግሥት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ በመሆኑ ይህ ትልቅ ለውጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መሬት ላይ ያለውን እውነታ ስንመለከት አሁን ያለው አጠቃላይ የፋይናንስ አቅርቦት በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ይገኛል ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ይህን ከማሻሻል አንጻር ብዙ ሥራ ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል።አጠቃላይ በሀገሪቱ ያለው የፋይናንስ አቅርቦት ዝቅተኛ ቢሆንም፣ የፋይናንስ አቅርቦት ለግሉ ዘርፍ ቀዳሚ ጉዳዩ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።አብዛኛው የግሉ ዘርፍ ቀዳሚ ችግር የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት መሆኑ በጥናት መለየቱን አስረድተው፣ ይህም ከሌሎች ችግሮች በበለጠ ጎልቶ እንደሚታይ ነው ያመለከቱት።

ቀደም ሲል ያለው የብድር አቅርቦትም ቢሆን ከተማ ተኮር መሆኑን ያነሱት አቶ ጌታቸው፤ በተወሰነ መልኩ አሁን አሁን መሻሻሎች መታየታቸውን ጠቅሰዋል።ለአብነትም በተለያዩ የገጠር ከተሞች የባንክ ቅርንጫፎች መስፋፋትና መሻሻሎች እየታዩ እንደሆነ ገልጸው፣ ባጠቃላይ የመንግሥት ብድር እየቀነሰ የግሉ ዘርፍ ብድር ደግሞ እየጨመረ መምጣቱን ነው ያስረዱት።ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት / ከጂዲፒ/ ጋር ሲነጻጸር መሻሻሉ ብዙም እንዳልሆነ አመላክተዋል።‹‹ከፍተኛ የሆነ የብድር ፍላጎት አለ፤ አቅርቦቱ በጣም ዝቅተኛ ነው፣ ይህም በብድር አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ሰፊ ክፍተት ያለ ስለመሆኑ ያስማማል›› ብለዋል።

ካለው ፍላጎት አንፃር አቅርቦቱ በቂ አለመሆኑን ጠቅሰው፣ ችግሩን ለመፍታት የፋይናንስ ዘርፉን ዲጂታላይዝድ ማድረግና መንግሥት መውሰድ የጀመራቸው ማሻሻያዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከተደረገ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው ጽሑፍ አቅራቢ አቶ ቴዎድሮስ ኃይሉ በበኩላቸው በሀገሪቱ የንግድ ባንኮች የሚሰጠው የብድር አቅርቦት እያደገ መምጣቱን አስታውቀው፣ በተያዘው ዓመት በአንዳንድ ባንኮች ካልተሰበሰበ ብድር (ሊኩዲቲ) ጋር በተያያዘና በሌሎች ምክንያቶች አቅርቦቱ ቅናሽ ማሳየቱን ተናግረዋል። የግሉ ዘርፍ ተወዳዳሪና ለምጣኔ ሀብታዊ እድገት አስተዋጽኦ ጉልህ ሚና የሚያበረክት እንደመሆኑ ጠንካራ የንግድ ዘርፍ ለመፍጠር የብድር አቅርቦትን ማሻሻል የግድ መሆኑን አመላክተዋል።ለዚህም በመንግሥት በኩል የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነና መሻሻሎች እንዳሉ ነው ያመላከቱት።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጥ፤ በበኩላቸው ምክር ቤቱ የግሉን ዘርፍ መብት ፍላጎትና ጥቅምን እንደሚያስጠብቅ ገልጸዋል።በሀገሪቱ ንግድና የኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ያለ የግሉ ዘርፍ ድምጽ መሆኑን አመልክተው፤ ምክር ቤቱ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው ብሎ ከለያቸው ዘርፎች መካከል የፋይናንስ ጉዳይ ቀዳሚ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በአዲስ አበባ ከተማም ሆነ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች የተሰማሩና በተለያየ የንግድ ደረጃ ያሉ አባላቱ በብድር አቅርቦት ዙሪያ ቅሬታ እንዳላቸውም ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል።ምክር ቤቱም የአባላቱን ቅሬታ ተቀብሎ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማድረግ በጉዳዩ ላይ የማስተማር ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።ችግሩ አሁንም እንዳልተፈታ ጠቅሰዋል።

ፕሬዚዳንቷ፤ በሀገሪቱ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ የንግድ ዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።የንግዱ ዘርፍ ተወዳዳሪ እንዲሆንና ለምጣኔ ሀብታዊ እድገት አስተዋፅኦ እንዲያበረክት በጥናት የተደገፈ የብድር አቅርቦት ማመቻቸት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ የብድር አቅርቦቱን በአግባቡ ተደራሽ ማድረግ ከተቻለ ዜጎች በማኑፋክቸሪንግ፣ ኢንዱስትሪ፣ በግብርናና በአገልግሎት ዘርፍ በመሰማራት ለኢኮኖሚ ዕድገቱ የድርሻቸውን መወጣት ያስችላቸዋል።ይሁን እንጂ በቂ ያልሆነ የብድር አቅርቦት፣ የብድር መክፈያ ጊዜ ማጠር፣ የብድር ማስያዣ መስፈርት ግልፅ አለመሆንና፣ የብድር መክፈያ ምጣኔ ከፍተኛ መሆን ለንግድ ሥራው ትልቁ ማነቆ ሆኗል።ብድር ለማግኘትና ለማስፈቀድ የሚወስደው ጊዜ ረዥም መሆንና የብድር ዓይነቶች አለመስፋት ተጨማሪ ችግሮች ናቸው፡፡

ይሁንና ምክር ቤቱ የግሉን ዘርፍ በማጠናከር በሀገሪቱ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ የበኩሉን ሚና እየተወጣ እንደሆነ ገልጸው፤ ምክር ቤቱ በእነዚህ ችግሮች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመምከር የመፍትሔ ሃሳብ ለመንግሥት ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል። እነዚህን ችግሮች በመፍታት በባንኮችና ማይክሮ ፋይናንሶች ፖሊሲና መመሪያን መሠረት ያደረገ የብድር አቅርቦት እንዲፈጠር መንግሥት በትኩረት መሥራት እንዳለበትም አመላክተዋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You