አንድ ዩኒቨርሲቲ ሲቋቋም ከመማር ማስተማሩ በተጨማሪ በአካባቢው ያለውን የመልማት ጸጋ ታሳቢ ያደረገ የምርምር ሥራዎችን በመሥራት የማህበረሰቡን የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል ማድረግ ነው።ከተመሠረተ ገና የስድስት ዓመት ዕድሜ የሆነው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሚገኘው የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመበት ዓላማና ግብ አንጻር ምን ሠራ? በተለይ ክልሉ ከፍተኛ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት ያለው ከመሆኑ አኳያ እድሉን ከመጠቀም አንጻር ምን አከናወነ? በተለይም አካባቢው ከሚታወቅበት በቡና ልማት ዙሪያ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ችግር ፈች ምርምሮችን ከመሥራት አንጻር ምን አከናወነ? ሲል በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የመልካም አስተዳደርና የምርምራ ቡድን የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክስ ምርምር ቴክኖሎጂ ሽግግርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ከለላው አዲሱ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርጓል።እንደሚከተለው አቅርቦታል።
አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው ሲመሰረት እንደማንኛውም ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የራሱ የሆነ ሀገራዊ ተልዕኮ አለው።ከዚህ አንጻር ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ሲቋቋም ዋና ተልእኮው ምን ነበር?
ዶክተር ከለላው፡- ማንኛውም የከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሲመሰረት መማር ማስተማር፣ ምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት የሚሉትን ሶስት ዋና ዋና ተልዕኮዎች ይዞ ነው። ቦንጋ ዩኒቨርሲቲም የተመሰረተው እነዚህን ተልዕኮዎች ታሳቢ አድርጎ ነው።ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሥራ ከጀመረ ስድስት ዓመቱ ነው። በእነዚህ ዓመታት ሶስቱን ዋና ዋና ተልዕኮዎች በማስተሳሰር እቅዱን ማሳካት የሚችልበትን ስትራቴጂ በመንደፍ ወደ ሥራ ገብቷል።
ከመማር ማስተማር ተልእኮ አኳያ የዩኒቨርሲቲው ተማሪ የመቀበል አቅምና ውስጣዊ አደረጃጀቱ እየሰፋ መጥቷል። በ14 ፕሮግራሞች የመማር ማስተማር ሥራውን የጀመረው ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታና የመልማት ጸጋ በመገንዘብ የማህበረሰቡን ፍላጎት መሠረት ባደረገ መንገድ፣ ተገቢ በሆኑ የትምህርት ፕሮግራሞች ላይ የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ አሁን ላይ 40 በሚደርሱ የቅድመ ምረቃ እና ሰባት የድህረ ምረቃ የትምህርት ፕሮግራሞችን እያስተማረ ይገኛል።እስካሁን በሶስት ዙር ተማሪዎችን አሰልጥኖ አስመርቋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የመማር ማስተማርና ሌሎች ማህበረሰብ አቀፍ ሥራዎችን በቴክኖሎጂ አስደግፎ ከመሥራት አንጻር ዩኒቨርሲቲው ምን ያህል ዘምኗል?
ዶክተር ከለላው፡- የትምህርትና ስልጠና ሥራዎችን የበለጠ ለማቀላጠፍ ፤ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችንና መሠረተ ልማቶችን ከማስፋት አንጻር ሰፊ ሥራዎችን ሰርተናል፤ አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱም ማንዋል ከሆነው አሰራር ወደ ዲጂታል አሰራር ተለውጧል። የተማሪ ምገባ ሥርዓት፤ የላይብረሪና የሪጂስትራል አገልግሎቶችን እንዲሁም የሠራተኛ የሰዓት መቆጣጠሪያ ጨምሮ በርካታ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ ሆኗል።
የትምህርት አሰጣጡ ዓለማቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል ተማሪዎች በቀጥታ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ሀገራት ከሚገኙ ፕሮፌሰሮች ትምህርት የሚያገኙበት እና በሴሚናሮች መሳተፍ የሚችሉበት ዘመናዊ የኦንላይን ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ ሆነዋል። ለዚህ ዓላማ ስምንት ስማርት የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተዋል፤ አሁንም እየተገነቡ ያሉ ክፍሎች አሉ።
ተማሪዎች ያለምንም የኢንተርኔት ግንኙነት ስማርት ስልኮቻቸውን ተጠቅመው በሶስት ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ የማጣቀሻ መጻሕፍቶችን በቀላሉ ማግኘት የሚያስችላቸው የቴክኖሎጂ ሥርዓት ተመቻችቷል። ምግብ ቤት ለመመገብ ሲሄዱ በወረቀት ሳይሆን በፊት ምልከታ ብቻ ራሳቸውን እያሳዩ እንዲገቡ ተደርጓል። አስተማማኝ የሆነ የኢንተርኔት አገልግሎት በግቢው ውስጥ አለ። ተማሪዎች እና መምህሮቻቸው ማንኛውም ሥራ በኦንላይን ለመተግበር አይቸገሩም።
አዲስ ዘመን፡- አካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ያገናዘበ ምርምሮችን ከማከናወን አንጻር ዩኒቨርሲቲው ምን እየሰራ ነው?
ዶክተር ከለላው፡- ከመማር ማስተማር ሥራዎች በተጓዳኝ የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት አንዱ የዩኒቨርሲቲው ተልእኮ ነው። ስለዚህ በተለይ ከመማር ማስተማር ጋር ተያይዞ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ጊዚያቶች የምርምርና የማህበረሰብ አቀፍ ሥራዎችን በተሳለጠ መንገድ ለማስኬድ በመጀመሪያ ደረጃ ችግሮች መለየት ነበረባቸው። ከዚህ አኳያ አካባቢው ላይ ምን ችግር አለ? የሚለውን ለመለየት የምርምር ባለሙያዎች ችግሮችን በጥናት እንዲለዩ ስምሪት ተደርጎ እንዲጠና ተደርጓል።በ12 ወረዳዎች ላይ ጥልቅ የሆነ የችግር ልየታ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ችግሮችን የመለየት ሥራዎች ተከናውነዋል።
80 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ማህበረሰብ የሚተዳደረው በግብርና ነው። በመሆኑም ችግሮቹ እንደ ሀገር ዘርፈ ብዙ ናቸው። ከዚህ አንጻር በክልሉ ያሉ ችግሮች መነሻቸው ምንድን ነው? በሚለው ላይ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊውን ሁኔታ ሁሉ የሚያስተሳስር የልየታ ጥናት በማድረግ የመተንተን ሥራዎች ተሰርተዋል።በተለይ በዘጠኝ የዋና ዋና የትኩረት መስኮቸ ላይ ችግሮችን ለይቶ ለማስቀመጥ ተሞክሯል። ችግሮች በጣም ዘርፈ ብዙ ስለሆኑ ዘጠኙን በአራት ዋና ዋና መስኮች በመለየት በቅደም ተከተል በማስቀመጥ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸውን ችግሮችን መለየት ተችሏል።
አዲስ ዘመን፡- በአካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ጸጋ ወደ ልማት ለመቀየር ምን እየሰራችሁ ነው ?
ዶክተር ከለላው፡- በምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት የአካባቢውን የተፈጥሮ ጸጋ ከሀገራዊ አቅጣጫ ጋር በማስተሳሰር ወደ ልማት ለመቀየር የሚያስችሉ የትኩረት መስኮችን የመለየት ሥራዎች ተሰርተዋል።እንደሚታወቀው አካባቢው በተፈጥሮ ሀብት በጣም የታደለ ነው። በደን እና በእንስሳት እንዲሁም ከግርብና ጋር በተገናኙ ሀብቶች በጣም የበለጸገ ነው፡፡
ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ ባለመዋላቸው የማህበረሰቡ ኑሮ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።ይህን ሀብት በሚገባ አልምቶ መጠቀም ቢቻል የተሻለ ኑሮ መኖር የሚችልበት ሰፊ እድልና አጋጣሚ አለ።ለምሳሌ ‹‹ከአግሮ ኢኮሎጂ›› አንጻር በዚህ አካባቢ ሁሉም ዓይነት አግሮ ኢኮሎጂ አለ። ስለዚህ ከግብርና አንጻር የተለያዩ የሰብል ዓይነቶችን ለማምረት ምቹ እድል አለ። ይህም ክልሉን በጣም ሰፊ የግብርና አቅም እንዲኖረው አድርጎታል።በነገራችን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ የተመዘገበው ዓለም አቀፍ ‹‹ባዮስፌሪ›› ዘርፍ በዚህ ክልል የሚገኝ ነው። በዩኒቨርሲቲው ወደ አካባቢው ሲመጣ እነዚህን ሁሉ ዕድሎች በመጠቀም በአግባቡ የማህበረሰቡን ሕይወት ለማሳደግ አስቦ ነው።
ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያ ትኩረት አድርጎ የሠራው ትምህርት ላይ ነው።ስለሆነም እንደ ሀገር በትምህርቱ ዘርፍ መንግሥትን ከመደገፍ እና የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ከመዝጋት አኳያ በተለይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራት ላይ በርካታ ሥራዎች ተሰርቷል። የትምህርት አሰጣጡ በጥራትና በተግባር ተደግፎ የሚሰጥበትን አግባብ ከተለያዩ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ውጤት ተኮር የሆነ ሥራዎችን አከናውነናል።
‹‹ካማራ ኢዱኬሽን›› ከሚባል ድርጅት ጋር በመተባበር 42 ለሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ለእያንዳንዳቸው 25 ኮምፒውተሮችን ሰጥተናል። ኮምፒውተሮቹ በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶች የተጫኑባቸው ናቸው።በዚህም ተማሪዎችን ለመደገፍ ጥረት ተደርጓል።ከከፋ ዞን ውጭ ሸካ፤ ኮንታና ቤንች ሸኮ እና ምዕራብ ኦሞ ድረስ ዲጂታል ቤተመጽሐፍ ተደራሽ ሆኗል።
በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ የክልሉ ተማሪዎችን ወደ ዩኒቨርሲቲው በመጥራት በየዓመቱ የማበረታቻ እውቅና ይሰጣል።ይህም ለሌሎች ተማሪዎች የሞራል መነሳሳት ከመፍጠር ባሻገር ዘርፈ ብዙ ትርጉም ያለው ነው ።
አዲስ ዘመን፡- በትምህርት ዘርፉ ሆነ በአጠቃላይ ከተልእኮው አኳያ በተጨባጭ ምን ውጤት እየተገኘ ነው ?
ዶክተር ከለላው፡– ለምሳሌ ቀድሞ በነበረው የትምህርት ሥርዓት በክልሉ ባሉ ዞኖችና ወረዳዎች በብሔራዊ ፈተና ምንም ዓይነት ተማሪ የማያልፍባቸው ትምህርት ቤቶች ነበሩ።ዩኒቨርሲቲው ድጋፍ ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ግን በጣም የተሻለ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ማትሪክን ማለፍ ችለዋል።
ከትምህርት ዘርፉ ባሻገር ዩኒቨርሲቲው ከምርምር አንጻር ዋናው የትኩረት መስኩ ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ላይ ነው። በተጨማሪም ጤና እና ማህበራዊና መሰል ዘርፎች የሚያከናውናቸው ሥራዎች አሉ።በዋናነት ምርትና ምርታማነት ማሻሻል አለብን በሚል ማህበረሰቡን የማስተማርና የመለወጥ ሥራዎችን ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው። በዚህ ዘርፍ ምርምሮች ተጀምረዋል። ምርምሮቹ ተግባራዊ ምርምሮች ናቸው።
ምርምሮችን ለመሥራት የመጀመሪያው ሥራ ምርምር የሚከናወንበትን ቦታ መለየት ነው። የመጀመሪያው አመራጭ የዩኒቨርሲቲውን ግቢ ማየትና መጠቀም ነው። ዩኒቨርሲቲው ወደ 2 መቶ ሺ ካሬ ሜትር መሬት አለው።የግቢውን የመሬት አቀማመጥ መሰረት ያደረገ ሥራዎች ተሰርተዋል። ግብርና ላይ የሚሰራው የግብርና የምርምር አንዱ እና ግንባር ቀደሙ ነው። በዩኒቨርሲቲው ካለን መሬት በተጨማሪ ከወረዳ አስተዳደሮች ጋር በመነጋገር በተለያዩ ወረዳዎች ላይ መሬቶችን የማግኘትና ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት የምርምር ሥራዎን በመሥራት ማህበረሰቡን በተግባር እያስተማርን እንገኛለን።
ግቢው ውስጥ ያሉ ቦታዎችን መጠቀም ስለሚያስፈልግ ምን ምን ጉዳዮችን እንስራ በሚል ሃሳብ በተለይም አካባቢው በሚታወቅባቸው እንደ ቡና፤ ማር፤ ቅመማ ቅመም፤ ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን ብለን፣ በሳይንሳዊ መንገድ ሥራዎችን በመሥራት እውቀት የማሸጋገር ተግባራትን አከናውነናል።
አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው በተጨባጭ ወደ ውጤት የተቀየሩ የምርምር ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋልናል፣ ዋና ፋይዳቸው ምንድን ነው?
ዶክተር ከለላው፡- በዋናነት አራት ፋይዳዎች አሉት። እነዚህም ምርምር አንዱ ሲሆን ተመራማሪዎች የትም መሄድ ሳያስፈልጋቸው በግቢው ውስጥ በቀላሉ ተግባራዊ ምርምር ማድረግ የሚችሉበት አውድ ተፈጥሯል። ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው እየኖሩ የሚመራመሩበት (living laboratory) አላቸው። በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን በተግባር እያዩት፤ እየነኩና እየዳሰሱ የሚማሩበት ተቋም ነው። ለምሳሌ የእንስሳት ሀብት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች በወተት ሀብት ልማት ሥራ፤ የበግ እርባታ፤ የከብት ድለባና ሌሎች ተያያዥ መስኮች ላይ ከዩኒቨርሲቲው መውጣት ሳይጠበቅባቸው እዚሁ በተግባር ይማራሉ፡፡
በተመሳሳይ አካባቢው የቡና መገኛ እንደመሆኑ መጠን ማህበረሰቡም ሕይወቱን ከመሰረተባቸው ዘርፎች ቡና አንዱ ነው። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው የቡና አመራረት ዘዴዎችን ለማዘመን በቡና ላይ የምርምር ተግባራትን ከማከናወን ባለፈ፣ በትምህርት ዘርፉም በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ በቡና ዙሪያ ትምህርት የሚሰጥ የቡና የትምህርት ክፍል ከፍቷል። በዚህ ዓመት 37 የሚሆኑ ተማሪዎችን በመጀመሪያ እና 10 የሚሆኑ ደግሞ በሁለተኛ ዲግሪ ለመጀመሪያ ጊዜ በቡና ሳይንስ የትምህርት ክፍል ያስመርቃል፡፡
ቡና እንደ ሀገር ያለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የሚታወቅ ነው።ነገር ግን የቡና መገኛ ሆነን እያለ ከምርትና ምርታማነት አንጻር ሌሎች ብዙ ሀገራት ኢትዮጵያን የቀደሙበት አግባብ አለ። የቡና መነሻ ኢትዮጵያ ሆና እያለች ከእኛ በተሻለ በጥራት በማምረት ለዓለም ገበያ እያቀረቡ ያሉ ሀገራት አሉ። ይህ ደግሞ ዘርፉ ሳይንሳዊ በመሆኑ አሰራር ባለመታገዙ ነው።
በተገቢው መንገድ እንደ ሀገር በቡና ዘርፉ በካበተ እውቀት ያዳበሩና የተካኑ ባለሙያዎች ሊኖሩ ይገባል። ቡና የማያመርቱ እንደ ጣሊያን ያሉ ሀገሮች ሳይቀር በቡና ዙሪያ ሳይንሳዊ ትምህርት ይሰጣሉ። ይህንን እውን ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ በቂ ባለሙያ እንዲኖሩ ለማስቻል ከፍተኛ ሥራዎችን እየሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በቡና ሳይንስ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በዘርፉ ከተሰማሩ ድርጅቶችን ጋር ለማስተሳሰር ምን እየሰራችሁ ነው?
ዶክተር ከለላው፡– የቡና መገኛ ሀገር እንደመሆናችን መጠን ዘርፉን በሚገባ አውቆና ተረድቶ የተሻለ ሀገራዊ ተጠቃሚነትን ለመፍጠር እየሰራን ነው።ለዚህም በቡና መስክ ስፔሻላይዝ ያደረገ ባለሙያ ማፍራት ወሳኝ ነው።ይህንን እውን ለማድረግ ወደ ሥራ ገብተናል። አሁን ላይም በርካታ የቡና ድርጅቶች የቡና ሳይንስ ተማሪዎችን ለመቅጠር ጥያቄ እያቀረቡ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው በራሱ ገቢን ከማመንጨት አንጻር ምን እየሰራ ነው?
ዶክተር ከለላው፡– ዩኒቨርሲቲው በከፍተኛ ደረጃ እየሰራባቸው ካሉ መሰኮች ገቢ ማመንጨት አንዱ ነው። እንደ ሀገር ከከፍተኛ ተቋማት ጋር ተያይዞ የሪፎርም ሥራዎች እየተሰሩ ነው። ከእነዚህ የሪፎርም ሥራዎች ደግሞ አንደኛው ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆን አለባቸው የሚል ነው። ራስ ገዝ ለመሆን ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች የራሳቸውን ሀብት ማፍራትም አለባቸው።ራስ ገዝነት ደግሞ ብዙ እድሎች ያሉት፣ ይህም በብዙ መንገድ የሚታይ ነው። ከእነዚህ መካከል አንዱ ፋይናንስ በማመንጨት የፋይናንስ ነፃነትና አቅም መፍጠር ነው።
አሁን እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተቀመጠው አቅጣጫ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ቢያንስ ግማሽ ያህሉን ዓመታዊ ገቢያቸውን በራሳቸው መሸፈን አለባቸው የሚል ነው። ይህን ለማሳካት ከወዲሁ መሥራት ካልተቻለ ስኬታማ መሆን ፈታኝ መሆኑ አይቀርም። ከዚህ አኳያ አሁን ላይ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በራሱ እያስገኘ ያለው ገቢ ቀላል አይደለም። ወተት እናመርታለን፣ የተከልነው ቡና ምርት መስጠት ጀምሯል፤ ፍራፍሬ ላይ በተለይም ከአናናስ እና ከሙዝ ላይ ከፍተኛ ገቢ እያገኘን ነው።
እዚህ ላይ መረዳት የሚገባን ከዚህ ቀደም ሙዝ እና አናናስ በአካባቢው አያታወቁም ነበር። ነገር ግን እነዚህ ፍራፍሬዎችን በማምረት ገቢ ማስገባት ተችሏል። ይህም ከዩኒቨርሲቲው ገቢው ባሻገር ለአርሶ አደሮች ተሞክሮ መስጠት የቻለ ነው። ዩኒቨርሲቲው የተሻሻለ የሙዝ ዝርያ ማህበረሰቡ የሚያገኝበትን መንገድ ፈጥሯል። ሙዝ ላይ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማምጣት በመትከል፤ ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ የተሻለ ውጤት ተገኝቷል። ይህንን ምርት ወደ ውጭ እያወጣን ለማህበረሰቡ ተደራሽ እያደረግን ነው።ወተትም እና አናናስም እንደዚያው ነው።
አዲስ ዘመን ፡- የዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ተልእኮ የማህበረሰብ አቀፍ ሥራዎችን ማከናወን ነው፤ ከዚህ አኳያ ምን ተሰርቷል ?
ዶክተር ከለላው፡- ከማህበረሰብ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ሥራዎችን እየሰራ ነው። ዩኒቨርሲቲው ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት ፍራፍሬ ፣ አሳ ፣ እንቁላል እና ሌሎች ምርቶችን ያመርታል። አሁን ከ2000 በላይ ዶሮዎች አሉት። በቀን እስከ 1900 እንቁላል ይመረታል።እነዚህን ምርቶች አንድም ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በተመጣኝ ዋጋ ይሸጣል።ከዛም ባለፈ ሥራ የሌላቸው ሴቶች አንድ ላይ በማደራጀት የሽያጭ ማዕከላትን በመገንባት ሸጠው እንዲጠቀሙ ያደርጋል።
እነዚህ የተደራጁ ሴቶች ወተቱንም፤ እንቁላሉንም፤ አናናሱንም በተመጣጣኝ ዋጋ ይወስዱና የተወሰነ ዋጋ ጨምረው ለማህበረሰቡ ይሸጣሉ። በዚህ ውስጥ ሁለት ነገሮችን አሳክተናል። አንደኛው የሥራ እድል ፈጥረናል። ሁለተኛው ደግሞ ማህበረሰቡ ከዚያ በፊት በቀላሉ የማያገኛቸውን ምርቶች በቀላሉ በአቅራቢያው እንዲያገኝ አድርገናል።
ከዚህ ውጭ ጎባ በሚባል ቆላማና ለም አፈር በሚበዛበት አካበቢ የሰሊጥ፤ ጤፍ፤ ማሾ የሚባሉ ዝርያዎችን በስፋት አምርተናል። ሞሪንጋ፤ ካሳቫ የመሳሰሉትንም በስፋት እንዲለሙ አድርገናል።ያመረጥነውን ሰሊጥ “በኢሲኤክስ” አንድ ዙር ሸጠናል። የተመረተው ሰሊጥ ሳይንሳዊ ዘዴን የተከተለ ስለነበር ምርት ገበያ ላይ አንደኛ ደረጃ መውጣት የቻለ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው “ሌትስ ፊድ አፍሪካ” የሚል ፕሮጀክት አስጀምሮ ነበር ። ይህ ፕሮጀክት ምን ላይ ደረሰ?
ዶክተር ከለላው፡– እንሰት በደቡብ አካባቢ በስፋት የሚታወቅ እና የሚመረት ነው። በትንሽ ቦታ ላይ ብዙ ምርት ያስገኛል። አንድ እንሰት በጣም ብዙ ሰው ይመግባል ፤ ድርቅንም ይቋቋማል። ስለዚህ እንሰትን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ቢመረት እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አኳያ በጣም ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል። ዩኒቨርሲቲውም ይህን ታሳቢ አድርጎ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር እየሰራ ነው።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማህበረሰባችን ቡና እና መሰል ተክሎችን በስፋት በመትክል እንሰትን ማምረት ላይ የመቀዛቀዝ አዝማሚ እያሳየ ነው።ይህ ልክ አይደለም። ምክንያቱም የምግብ ዋስትና ጉዳይ በጣም ትኩረት የሚሻው ነው። ከዚያ አንጻር ፋይዳው የጎላ ስለሆነ ይህንን ለማህበረሰባችን ማስተማር እና ወደ እንሰት አምራችነቱ መመለስ ያስፈልጋል።
የእንሰት እርሻን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ወደ አፍሪካ ሀገራት ለማስፋፋት እየሰራን ነው።በዚህም ከኢትዮጵያዊን ባለፈ አፍሪካዊያንን በቀላሉ መመገብ እንደምንችል በጥናት አረጋግጠናል። በዚህ ረገድ እኛ ጋር የተሻሻሉ የእንሰት ችግኞችን በስፋት በግቢ ውስጥ እና ከግቢው ውጭ ባሉ ቦታዎች ላይ የማፍላት ሥራ ተሰርቷል።
እነዚያን ችግኞች ለማህበረሰቡ እያስተላለፍን ነው።ጌሻ በተባለ ወረዳ ላይ ወደ 20 ሄክታር መሬት በእንሰት ለመሸፍን ታቅዶ እየተሰራ ነው።ሥራውን እንደ ፋኦ (Food and Agriculture Organization) ካሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራን ነው።ፋኦ በዚህ ጉዳይ ላይ መግባቱ ጥሩ ነው።ምክንያቱም ወደ አፍሪካ ሀገራት የማስፋፋት ስትራቴጂክ እቅዳችንን ቀላል ያደርገዋል።
አዲስ ዘመን፡- በአካባቢያችሁ ሰፋፊ የእርሻ ድርጅቶች ይገኛሉ።ከእነሱ ጋር ተባብሮ ከመሥራት አኳያ ምን እያደረጋችሁ ነው?
ዶክተር ከለላው፡- በአካባቢያችን በርካታ ሰፋፊ የእርሻ ሥራዎችን የሚያከናወኑ ድርጅቶች አሉ።ለምሳሌ አንዱ ውሽ ውሽ የሻይ ቅጠል ነው። ከውሽ ውሸ ሻይ ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል።ሻይ ላይ እኛ ላይ እየሞከረነው ያለው ነገር አለ።
ሌላው ተማሪዎቻችን ኢንትርን ሺፕ እዚያ ሂደው ይማራሉ። ምሩቃኖቻችን እዛ ሄደው ይሰራሉ።ለምሳሌ በዘንድሮው ዓመት 15 የሚሆኑ ምሩቃን እዚያ እንዲቀጠሩ ተደርጓል። ጉመሮ እና ጨዋቃ የሚባሉ አሉ። በእነዚህ ተቋማት ተመራቂዎቻችን ሄደው እንዲሰሩ ማድረግ ተችሏል።ይህ ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው ከሚገኙ የእርሻ ተቋማት ጋር የሚያደርገው ትስስር ነው።
አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው ለሚያደርጋቸው የምርምር ሥራዎች የሚያስፈልገውን ወጪ የሚሸፍነው እንዴት ነው ?
ዶክተር ከለላው፡- እኛ በመጣንበት አጭር እድሜ አኳያ የምርምር ሥራዎችን በተፈለገው ልክ መሥራት የቻልነው ከመንግሥት በምናገኘው በጀት ብቻ ነው። አሁን ላይ ምርምርን በውስጥ ገቢ ብቻ ማከናወን ከባድ ነው።የውጭ የገንዘብ ድጋፍ ያስፈልጋል። ይህ ምናልባትም ከዩኒቨርሲቲው ዕድሜ ጋር የሚገናኝ ሊሆን ይችላል።
በነገራችን ላይ ከመንግሥት የሚገኘውን በጀት በትክክል ምንም ሳይባክን ሥራ ላይ ከዋለ ብዙ ሥራዎችን መሥራት ይቻላል።ይህን ከማድረግ አንጻር የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ውጤታማ ነው ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- አካባቢው በተለያዩ እጽዋት የተሞላ እንደመሆኑ መጠን ባህላዊ የመድኃኒት ቅመማን በምርምር በማስደገፍ ዘመናዊ ከማድረግ አንጻር ምን እየሰራችሁ ነው?
ዶክተር ከለላው፡– ይህ ዩኒቨርሲቲው እያከናወናቸው ከሚገኙት 17 ፕሮጀክቶች መካከል ሀገር በቀል የመድኃኒት እውቀቶችን ማዘመን የሚለው አንዱ ነው። በዚህ ላይ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። ከባህል መድኃኒትነት ጋር ተያይዞ ሀገር በቀል እውቀቶች አሉ። ከዚህ አንጻር የመጀመሪያው ያለው ሀብት ምንድን ነው? የሚለውን መለየት ነው።
አካባቢው በእጽዋት የታደለ ስለሆነ መድኃኒትነት ያላቸው እጽዋቶች በብዛት ይገኛሉ። እነዚህ ተጠቅመው ደግሞ በባሕላዊ መንገድ በሽታን የሚያድኑ የሀገር በቀል እውቀት ባለቤት የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ።እነዚህ ሰዎች እያንዳንዱ እጽዋት ለየትኛው በሽታ እንደሚውል ያውቃሉ።ከ350 በላይ የሚሆኑ እጽዋት ተለይተው በአንድ ማዕከል ውስጥ እንዲበዙ እና እንዲቀመጡ በማድረግ የምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን፡፡
ዶክተር ከለላው፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ሙሉቀን ታደገና ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም