የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት በዘጠኝ ወራት 2 ነጥብ 84 ቢሊዮን ብር አገኘ

አዲስ አበባ፡- ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሁለት ነጥብ 84 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር አስታወቀ፡፡

በኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ቺፍ ኮርፖሬት ስትራቴጂ ኦፊሰር አቶ አሚኑ ጁሀር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አክሲዮን ማህበሩ በበጀት ዓመቱ ከባቡር አገልግሎቶች 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 2 ነጥብ 84 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ችሏል፡፡

የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ67 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው አቶ አሚኑ አመላክተዋል።
ማህበሩ በዘጠኝ ወራት ውስጥ መንገደኞችን የማጓጓዝ አቅሙን 155 ሺህ ለማድረስ አቅዶ 148 ሺህ 664 መንገደኞችን ማጓጓዙን ጠቁመው፤ አፈጻጸሙ 95 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ መሆኑን ገልጸዋል።
በዘጠኝ ወሩ የተጓጓዘው መንገደኛ ብዛት ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተጓጓዘው ጋር ሲነጻጸር የ19 ሺህ 664 ልዩነት ያለው ሲሆን የ15 በመቶ እድገት አሳይቷል ብለዋል፡፡

በዘጠኝ ወሩ ሁለት ነጥብ 01 ሚሊዮን ቶን የገቢና ወጪ ጭነት ለማጓጓዝ ታቅዶ አንድ ነጥብ 442 ሚሊዮን ቶን ጭነት ማጓጓዝ መቻሉን አመላክተው፤ ይህም የእቅዱን 71 ነጥብ ስድስት በመቶ የሚሸፍን መሆኑን አስረድተዋል። በዘጠኝ ወሩ የተጓጓዘው ጭነት መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የሰባት በመቶ ቅናሽ እንዳሳየ ጠቁመዋል።
የባቡር ትራንስፖርት መለዋወጫዎች ላይ ባጋጠሙ ብልሽቶች፣ በጭነት ማንቀሳቀሻ ክሬን መስተጓጎል ምክንያት እንዲሁም በቀይ ባህር ባጋጠመ የጸጥታ ችግር ምክንያት የጭነት መጠን መቀነሱን አንስተው፤ በተጨማሪ በጅቡቲ ወደብ በደረሰ የጎርፍ አደጋ ምክንያት ለተወሰኑ ቀናት ኦፕሬሽን መቋረጡ ለጭነት መጠኑ መቀነስ ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል።

የደህንነት እና ጸጥታ ችግሮች፣ ስርቆት እና ውድመት፣በሰውና በእንስሳት ላይ የሚደርስ አደጋ እና የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ባለፉት ዘጠኝ ወራት አክሲዮን ማህበሩ ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል መሆናቸውን አስታውሰው፤ ችግሮችን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በቅርበት እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር የባቡር የመጫንና የማውረድ ቅልጥፍናን ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሰባት ነጥብ አምስት በመቶ ለማሻሻል አቅዶ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው፤ የአገልግሎት ማሻሻያው አፈጻጸም በጥናት ላይ እንደሚገኝና ውጤቱ ሲታወቅ ይፋ እንደሚደረግ አቶ አሚኑ ጨምረው ገልጸዋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You