በብድር የስኬት መንገዷን የጠረገችው ሴት

አዲስ አበባ ሸጎሌ ሩፋኤል አካባቢ በ1986 ዓ.ም ነበር የተወለደችው። ገና የስድስት ዓመት ሕፃን እያለች ነበር ወላጅ እናቷን በሞት ያጣችው። የእናት እቅፍን ሳትጠግብ እናቷን ብታጣም አባትም እናትም ሆነው ምንም እንዳይጎድልባት አድርገው አባቷ እንዳሳደጓት ትናገራለች። ለእናትና ለአባቷ ብቸኛ ብርቅ ሴት ልጅ የነበረችው ይህቺ ልጅ በብቸኝነት ማደጓን፤ እሷን ለማሳደግ የተከፈልው የአባቷን ድካም ለመመለስ ስትል ባጠራቀመችው ጥንካሬ ነገን የተሻለ ለማድረግ የምትታትር ውጤታማ ሴት ለመሆን በቃች። አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው የሃያ ዘጠኝ ዓመቷ ወጣት አሁን ላይ የበርካታ ንብረቶች ባለቤት ሆናለች።

በልጅነቷ እንደ ማንኛውም ልጅ በቀበሌ ቤት ውስጥ በመካከለኛ ኑሮ ያደገች ልጅ ናት። አባቷ የጁቡቲ ሹፌር የነበሩ ሲሆን፤ እሷ ሠራተኛ ተቀጥሮላት በአባቷ ድካምና ፍቅር ማደጓን ታስታውሳለች። አባት ብቸኛ ልጃቸው ልጅነቷን የተሻለ ለማድረግ ሁልጊዜ ጥረት ያደረጉ ሲሆን እድሜዋ ለትምህርት እንደደረሰ በቅድስት ማሪያም ካቶሊክ ትምህርት ቤት ገብታ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍለ ድረስ እዛው እንደ ተማረች ታስታውሳለች።

የኢኮኖሚ አቅማቸው አነስ ከሚል፤ በአስተሳሰባቸው የላቁ ቤተስቦች ውስጥ አድጋ በመውጣቷ የተነሳ ታላቅ ህልምን የሰነቀችውን ወጣት ለስኬት መንገድ ማሳያ ትሆናለች ስንል ለዛሬው በሴቶች ዓምድ እንግዳ ልናደርጋት ወደናል። መልካም ቆይታ።

የዛሬ እንግዳችን ወይዘሮ ሜላት ደምሰው ትባላለች፡፡ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች። በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ ፕሮግራም በሲቪል ኢንጂነሪንግ የተመረቀች ሲሆን፤ በማታ የትምህርት መርሀ ግብር ከሼባ ዩኒቨርሲቲ ማኔጅመንት ተምራ ሁለት የመጀመሪያ ዲግሪ በተመሳሳይ ዓመት ይዛ እንደወጣች ትናገራለች።

መጀመሪያ ተማሪ እያለች በቀን ዲግሪ ፕሮግራም በምሽት ደግሞ ማኔጅመንት ተምራ ተመርቃለች። ይህን ጥንካሬ በአፍላው የወጣትነት እድሜ ላይ ልትላበስ የቻለችው ብቸኛ ልጃቸው ተንቀባራ እንድታድግላቸው ሲሉ በበረሃ እየተጓዙ ላሳደጓት አባቷ ስትል እንደሆነ ትናገራለች። ጠንካራ ልጅ ማሳደጋቸውን በተግባር እንዲያዩላት ያሰበችው ወጣትም ትምህርቱን ጠንክራ በመማር ተመረቀች።

እድል መግቢያ በሯን ወለል አድርጋ የከፈተችላት ወጣት እንደተመረቀች አንድ ወር እንኳን ሳትቆይ ነበር ፍያብ ሪል እስቴት ውሰጥ ጁኒየር ፕሮጀክት ማናጀር ሆና የተቀጠረችው። ሥራ የጀመረችው ከአራት ዓመታት በፊት እንደሆነ የምትናገርው ወጣት ሜላት በድርጅቱ ተቀጥራ መሥራት በጀመረችበት ወቅት ነበር ድርጅቱ ከሚያገኙት ደመወዝ አስር በመቶ አሚጎስ በተባለ የብድርና ቁጠባ ተቋም እንዲቆጥቡ አስገዳጅ ሁኔታን አስቀምጦ የነበረው።

ሥራ እንደተቀጠረች መጀመሪያ ታገኝ የነበረው ደመወዝ ሁለት ሺ ብር ሲሆን ለአንድ ዓመት ከሠራች በኋላ ነበር ደሞዟ ከፍ ያለው። በወቅቱ ድርጅቱ ከጀማሪነት ተነስቶ ከፍ ሲል በከፍታው ልክ ሠራተኞቹን ለማሳደግ በማሰብ ደመወዙን ወደ 25 ሺ ብር አሳደጉላቸው። የደመወዝ ጭማሪው ትልቅ አቅም የፈጠረላት ወጣት ህልሟ ጥግ ለመድረስ የተለያዩ ሃሳቦችን ማሰብ ጀመረች።

መጀመሪያ ማስተርሰ ዲግሪዋን ለመማር በማስብ ስትቆጥብ የቆየችው ወጣት ለማስተርስ መማሪያ የሚሆን ገንዘብ ሲጠራቀም ያንን ተበድራ ትምህርቷን አጠናቀቀች። ለማስተርስ የሚሆን አርባ ሺ ብር ስትበደር የደሞዟ እኩሌታ የነበረ አንድ ሺ ብር እየተቆረጠ የከፈለች መሆኑን ታስታውሳለች። ከሁለት ሺ ብር ደመወዝ አንድ ሺውን ለማስተርሷ እያጠራቀመች በተጨማሪ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ የአምስት መቶ ብር እቁብ እየጣለችም ነበር። እቁቡን ስታጠናቅቅ ብድሯን ዘግታ ጨረሰች።

ከማስትሬት ትምህርቷ በኋላ ደሞዟ ከፍ ሲል በተለያዩ የትርፍ ጊዜ ሥራዎች ገቢ ማግኘት ስትጀምር ቁጠባዋን ከፍ አድርጋ መኪና ለመግዛት አቀደች። እቅድ ጥረት ሰኬትን የምታከታትለው ወጣት ምንም ነገር ስታቀድ አይሳካም የሚል እምነት ውስጧ እንደማታስቀምጥ ታስረዳለች።

መኪና የመግዛት ህልሟን ለማሳካት ከቁጠባው በተጨማሪ እቁብ በመግባት ወደ ሶሰት መቶ ሺ ብር ታገኛለች። ከዛም ባለቤቷ ሶስት መቶ ሺ ብር ተጨማሪ ገቢ በማድረግ የቁጠባ መጠን ጨምረው ከፍ ያለ ብድር ለማግኘት ቻሉ። የቀደመ በቁጠባ የተጠራቀመው ገንዘብ ላይ በመጨመር ያላትን የቁጠባ ገንዘብ ከፍ በማለቱ ከተቀመጠው ሶስት አጥፍ መበደር ቻለች። በዚህም ለስኬት የሚያንደረድራትን መንገድ በአግባቡ የተረዳቸው ይች ወጣት ገንዘቡ ተበድራ የጀቡቲ የጭነት መኪና ገዛች።

በወቅቱ የጁቡቲ መኪና ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ የነበረ ሲሆን በወር ከመቶ ሺ ብር በላይ ትርፍ በመያዝ ለብድሩ ስልሳ ሺ ብር እየከፈለች፤ ተጨማሪ ገቢ ስታገኝ ቁጠባው ላይ በመጨመር ገንዘብ ስትይዝ ቆየች። ከዛም የተወሰነ ትርፍ ስታገኝበት መኪናውን ሸጣ ቤት እንዲኖራት ለማድረግ ተጨማሪ ገንዘብ ማጠራቀም ጀመረች።

የነበረባትን ብድር በሙሉ ዘግታ፤ ድጋሚ ቁጠባዋን አሳድጋ መበደር አቅዳ ለመንቀሳቀስ ስትሞክር ባሰበችው ፍጥነት ሊሄድ ባለመቻሉ ለተወሰነ ጊዜ ብድር የመበደር ሀሳቧን ትታ ብድራን ዘግታ እየቆጠበች ብቻ መቆየትን ምርጫዋ አደረገች። ከዛ ባለቤቷ ይሰራው ከነበረው ገንዘብ ጋር በመደመር በመተጋገዝ ቁጠባ ጀመሩ።

መጀመሪያ ኮንዶሚኒየም ገዝተው በስድስት ወር ሸጠው ያለውን ገንዘብ ጨማምረው የተወሰነውን ገንዘብ ለሪልእስቴት ሼር ሲገቡ በገሚሱ ደግሞ ሁለት መቶ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ቤት ገዝተው ማከራየት ጀመሩ። ቤቱ በወር እስከ ሰባ ሺ ብር ስለሚያስገኝ ብድሩን እየከፈለ ሲቆይ ጎን ለጎን የሪልእስቴት ድርሻዋን ከፍ እያደረገች በመሄድ የሀብት መጠኗን ማሳደግ ጀመረች።

በአርባ ሺ ብር የተጀመረ ብድር ባጠቃላይ እስካሁን ድረስ አስር ሚሊየን ብር በመውሰድ እየዘጉ መቆየታቸውን ትናገራለች። በትንሹ ደፍራ ታላቅ ባለሀብት ለመሆን መንገድ የጠረገላትን ብድር መጀመሪያ እስክትጀምር ድረስ ለቀናት እንቅልፍ አጥታ እንደነበር ትናገራለች።

“መጀመሪያ ብድር ለመበደር ማሰብ በራሱ ሞት የሚሆንብኝ ዓይነት ሴት ነበርኩ” የምትለው ሜላት “የመጀመሪያዋ ማስተርስ ዲግሪዬን ለማመር ስል የተበደርካት አርባ ሺ ብር ግን የብድር ዓይነ ጥላዬን ገፎልኛል” ትላለች። በወቅቱ ለመበደር ስታስብ እንቅልፍ አጥታ የነበረ ሲሆን ትምህርቷንም ተምራ ብድሯን መልሳ መኖር እንደሚቻል በመገንዘብ ሃሳቧ ወደፊት ማድረግ ችላለች።

ባለቤቷና አባቷ ለእያንዳንዱ ስኬቷ ቀኝ እጅ እንደነበሩ የምትናገረው ሜላት ባለቤቷ ሰው ተበድሮ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራቱ ጥንካሬ እንጂ ውድቀት አለመሆኑን እየነገረ ያበረታት እንደነበር ትናገራለች።

“ሰው መጀመሪያ የሚሠራው ሥራ ያዋጣል ወይም አያዋጣም የሚለውን ጉዳይ ጥናት ማድረግ አለበት፤ ብድር ተበደሬ ምን ሥራ ላይ ባውለው ስኬታማ እሆናለሁ የሚለውን ነገር ማቀድ እጅግ አስፈላጊ ነው። የሚጀመረውም ሥራ ምን ያህል ትርፍ ያስገኛል፤ ትርፉስ ብድሩን እየከፈለ ተጨማሪ ገቢ ሊሆን ይችላል ወይ የሚለውን ግምት ውስጥ ማስገባት ተገቢ ነው” ትላለች። መኪናው በወር ከመቶ ሺ ብር በላይ የሚያስገባ ሲሆን ከዛ ላይ ብድር ስልሳ ሺ ብር እየተከፈለ ትርፍ የነበረው መሆኑ ውጤታማ እንዳደረጋት ትናገራልች።

መጀመሪያ ሰው ከትንሽ ተነስቶ ትልቅ ደረጃ ይደርሳል ሲባል እውነት የማይመስላት እንደነበረ የምትናገረው ሜላት የቅጥር ሥራ ላይ ሆና በምን መልኩ ስኬት ላይ ልትደርስ እንደምትችል ትኩረት አድርጋ ታስብ እንደነበር ታስረዳለች። ሰው በብድር ሥራ ሠርቶ ይለወጣል ሲባል ህልም እየመሰላት የኖረችው ወጣት ህልሟ እውን እንደሆነ በራሷ አይታ ማረጋገጧን ትናገራለች።

ባለቤቷና አባቷ የሚያደርጉላት ድጋፍ ከፍ አድርጎኛል የምትለው ወጣት ከዛም በተጨማሪ በቅጥር ሥራ ላይ መቆየት እርግጠኛ የሆነ ገቢ ይዞ ተጫማሪ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል መሆኑን ትናገራለች። በቅጥር ሥራ መቆየት በቢዝነስ ኪሳራ ቢገጥም ምን ይውጠኛል ያለ ገቢ ልቀር ነው ወይ ከሚል ስጋት የሚያፀዳ መሆኑን ታብራራለች።

ከዩኒቨርሲቲ በተመረቀች በዓመቷ ወደ ትዳር ዓለም እንደገባች የምትናገረው ሜላት ትዳር ውስጥ በዚህ ፍጥነት እገባለሁ ብላ ባታስብም ትዳር ውስጥ መግባቷ የበለጠ ብርታት የበለጠ አቅም እንደፈጠረላት ትናገራለች። የትዳር አጋሯ የሥራ ሰው መሆኑ ወድቀትን የማይፈራ ከስህተቱ ተምሮ ለተሻለ ስኬት የሚተጋ መሆኑ ለስኬቷ ጉልበት እንደሆናት ታስረዳለች።

አባቷ በቁጥብነትና በትጋት ሲያሳድጓት ባለቤቷ ደግሞ ሳይሞክሩ ሥራን ከመሸሽ ይልቅ ሞክሮ መሳሳትን፤ ሞክሮ ማየትን እንድትለምድ አድርጎ ነገ የተሻለ ህልም ያላት ባለ ራእይ ሴት እንድትሆን እንዳደረጋት ትናገራለች። “ከስኬታም ሰዎች ጀርባ ጠንካራ ሰዎች መኖራቸው የማይካድ ሀቅ ነው ” የምትለው ሜላት የራሷን ድርጅት የምታስተዳደር ሴት የመሆን ህልም የሰነቀች፤ ነገ አንድ በሴት የሚመራ ተቋም እንዲኖራት አልማ ለህልሟ የምትተጋ ሴት መሆኗን ትናገራለች።

አሁን የሁለት ዓመት ሕፃን ልጅ ያላት እናት፤ እንደ አባትም እንደ እናትም ያሳደጋት አባት ልጅ፤ ለባሏ መልካም ሚስት፤ በሥራዋ ጠንካራ ሠራተኛ የሆነች ሴት ሆናለች ወይዘሮ ሜላት ደምሰው። ሜላት “ለዚህ ደረጃ እንድበቃ ላደረገው ለአባቴ፤ በሁሉም ርምጃ ላይ ውጤታማ እንድሆን ከጎኔ ለነበረው ጠንካራው ለባለቤቴ ለፍፁም አብርሃ፤ ሕይወትን በአዲስ ዓይን እንዳይ ያረገችኝን ልጄን ማመስገን እፈልጋለሁ” ትላለች።

ህልም ጥረት የገንዘብ አቅም አንድ ላይ ተደምረው፤ የቤተሰብ ድጋፍ ታክሎበት ውጤታማ ያደረጋትን ሴት ተሞክሮ ስንመለክት በሷ መንገድ ለመጓዝ ድፍረትን እናገኝ ዘንድ ነውና ለመሥራት አቅዳችሁ ህልም እያላችሁ በገንዘብ እጦት የታሰራችሁ ሜላት ገንዘቡ የሚያረፍበት ቦታ ትክክል መሆኑን ማረጋገጥ ብቻ በቂ ነው፤ ጠንካራ ሥራና የተሳካ እቅድ ለስኬት በር ቁልፉ ነው ትላለች። እኛም ለስኬት ቀን ከሌሊት መጣር እና ያሉትን አማራጮች ሁሉ መጠቀም መልካም መሆኑን ተናግረን የዛሬውን አበቅተናል። ቸር ይግጠመን።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You