በክልሉ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ኢኒሼቲቮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው

አዲስ አበባ፡– በክልሉ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥርዓትን መፍጠር የሚያስችሉ ኢኒሼቲቮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን የኦሮሚያ ሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ቶሎሳ አጀማ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ ክህሎት መር የሥራ እድል ፈጠራ ሥርዓትን መፍጠር የሚያስችሉ ኢኒሼቲቮች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ ነው፡፡

የኦሮሚያ ክልል ሦስት ትልልቅ የትኩረት አቅጣጫዎችን ተግባራዊ እያደረገ ነው ያሉት አቶ ቶሎሳ፤ ለሥራ አጦች ሰፋ ያለ የሥራ እድል መፍጠር፣ ጥራት ያለው ሥልጠና መስጠትን ጨምሮ ፈጠራና ክህሎትን ማበልጸግ ነው ብለዋል፡፡

በዘንድሮው ዓመት ለሦስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤  ባለፉት ስምንት ወራት ለአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የሥራ እድል ፈጠራ ላይ አዲስ እይታ ማምጣት መቻሉን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ክህሎት መር የሥራ እድል ፈጠራ መፈጠር አለበት የሚል አቅጣጫ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል፡፡

ሥራ አጥ ዜጎች ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት፣ ውጤታማ ሊያደርግ የሚችል ሥልጠና እንደሚወስዱ በመግለጽ ለመደራጀት፣ አስፈላጊውን ድጋፍ በማግኘት ወደ ሥራ ለማስገባትና ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል አቅጣጫ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሀገሪቱን ኢኮኖሚ መደገፍ የሚችል ዜጋ ለማፍራት ያለመ ስትራቴጂ ተነድፎ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ በዘንድሮው ዓመት በእቅድም በአፈጻጸምም የተሻለ የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በከተማና በገጠር የሥራ ፈጠራን የሚያበረታቱ  የተለያዩ ኢኒሼቲቮች ተቀርጸው ወደ ሥራ ተገብቷል ያሉት አቶ ቶሎሳ፤ በክልሉ ትላልቅ ክላስተሮች እንዲገነቡ በማድረግ ዜጎች ተደራጅተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ለሥራ አጥ ዜጎች የመሥሪያ፣ ማምረቻ፣ መሸጫ ቦታዎችን ጨምሮ የፋይናንስና ሥልጠና  ድጋፎች መመቻቸቱን ጠቅሰው፤ በማኑፋክቸር፣ ግብርና፣ እንስሳት እርባታ፣ ንግድ፣ አገልግሎት፣ በማዕድንና ኮንስትራክሽን ዘርፎች የሥራ እድል መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት እየተከተለ ባለው አቅጣጫ መሠረት በስፋት የሥራ እድል ፈጠራው በግብርና ዘርፍ የተገኘ መሆኑን በመግለጽ፤ ወጣቶች የሥራ ቦታ እና የእርሻ መሬት ቀርቦላቸው በስፋት ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አክለውም፤ በከተሞች በሥጋ፣ ወተት፣ ዶሮና ከብት እርባታ የተሰማሩ ወጣቶች ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ለኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ ብድር አቅርቦት ላይ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥሙ ገልጸው፤ በኢኒሼቲቭ መሠረት የተሰጡ ብድሮችን መሰብሰብን ጨምሮ ወላጅ ለልጆቹ እንዲቆጥብና የማምረቻ ቦታ እንዲያቀርብ መሠራቱን ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ወጣቶች ተደራጅተው የመነሻ ካፒታል እንዲያገኙ በማድረግ  የሥራ እድል ፈጣሪ እንዲሆኑ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የፋይናንስ ብድርን ለማመቻቸት ማይክሮ ፋይናንሶችን ጨምሮ የተለያዩ የውጪ ድርጅቶችን በማስተባበር ውጤታማ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን     ሰኞ ሚያዝያ 7  ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You